ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ እንኳ ብንጀምር አፄ ቴዎድሮስ አፄ ዮሐንስ አፄ ምኒሊክ ልጅ እያሱ አፄ ኃይለሥላሴ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ዛሬ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገራቸውን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ጦር ግንባር ዘምተዋል። ከፊት ሆኖ ስለአገር መዝመትንም ሆነ መዋጋትን ባነሳን ቁጥር ጥሩ ስምና ታሪክ የሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብቻ ነው።
በግንባር ተገኝቶ ተዋግቶ አያውቅም። መቼም ወያኔ ከፍጥርጥሯ ጀምሮ ሌብነት ዘረፋና ክህደት መለያዋ ነው፤ መለስ እርሙን አንድ ጊዜ አጋሮቹን እየመራ ባንክ እንዲዘርፍ “ተልዕኮ” ተሰጥቶት እነሱን ማግዶና አጋፍጦ ጥሎ በመመለሱ ግምገማና እስር ገጥሞት ነበር። ይሄን ፍርሀቱን ነው እንግዲህ ለሕወሓት አጋብቶባት ዘመኗን ሁሉ ጨካኝና አረመኔ የሆነችው። ጀግናማ ሩህሩህና ደግ ነው። ፈሪ ግን ጭካኔው ልክ የለውም። ሕወሓት ባለፉት 30/47 ዓመታት ይህን ማንነቷን ነው ያረጋገጠችልን። የቅርብ ሁለት ማሳያዎችን እናንስ። በሰሜን ዕዝ የፈጸመችው ጭካኔ የተሞላበት ክህደትና ማይካድራን ጨምሮ በወረራ በያዘቻቸው አካባቢዎች የፈጸመቻቸውን ዘር ማጥፋቶች ከፍርሀቷ የመነጨ አሪዎስነት መሆኑን ልብ ይሏል። በተረፈ ሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎች በጀግንነት ስለአገራቸው ነጻነትና ሉዓላዊነት አዋግተዋል። ተዋግተዋል። አፄ ቴዎድሮስ በመተማ በመቅደላና በሌሎች፤ አፄ ዮሐንስ በሰሀቲ በመተማና በሌሎች፤ አፄ ምኒልክ በአድዋና በሌሎች፤ አፄ ኃይለሥላሴ በሰገሌ በማይጨው፤ ፕሬዚዳንት መንግስቱ በቆሬና በሰሜን የጦር ግንባር ተገኝተው አዋግተዋል። ተዋግተዋል።
እነዚህ መሪዎች በተለያዩ ዘመናት የመጡና የሄዱ ወይም ዘመነ ጓዴነት (ኮንቴምፓራሪስ)” ስለሌላቸው ማነጻጸሩ ተጠየቃዊና አመክኖአዊ ባይሆንም፤ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ጠ/ሚ መለስ ባለው ዘመን አስፈላጊነቱ የተለያየ ቢሆንም መሪዎች በጦር ግንባር ተገኝተው ጦርነቱን መምራትና ሠራዊቱን ማበረታታት ግድ ይል ነበር። ዛሬ ላይ ግን አይደለም በአገር ውስጥ በየትኛው የዓለም ጥግ የሚካሄድን ጦርነት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ በጦር ግንባር የተገኙ ያህል ሆኖ በተዋበ ቢሮ ውስጥ ሆኖ ማኪያቶ እየጠጡ ማዋጋት ይቻላል። የዛሬ ዓመት የተካሄደው ጦርነት ከጠ/ሚ ጽሕፈት ቤት ከሚገኝ “ሲቹየሽን ሩም”ነበር የተመራው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የአሁኑን ጦርነት በዚህ አግባብ መምራት ይችሉ ነበር። ሆኖም እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከፊት ሆነው መስዋዕትነትን በመክፈል አገራችንን ሊያፈርስና የአዛዮቹን ተልዕኮ ለማስፈጸም የመጣን ከሀዲ ባንዳና አሸባሪ በአካል ሊፋለሙት ግንባር መዝመታቸው ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት ከጫፍ እስከጫፍ ቀፎው እንደተነካ ንብ እያተመመ ይገኛል።
ይህ ትውልድም ታሪክም በኩራት ሲዘክረው የሚኖረው ታሪካዊ ውሳኔ የደጀኑንም ሆነ የሠራዊቱን ወኔ እየቀሰቀሰው ነው። ጠላትም በዚህ ውሳኔ ተደናግጦ የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቷል። አፍሪካዊ እህት ወንድሞቻችን ደግሞ ጦርነቱ የእኛ ጭምር ነው በማለት ምዕራባውያን ያልጠበቁትና ያላሰቡት በቃ ! የሚል ንቅናቄ ፈጥረዋል። ምዕራባውያን ማጣፊያው አጥሯቸዋል። ዳግማዊ አድዋ ዳግማዊ ፓንአፍሪካኒዝም ዳግማዊ ብላክ ኮንሸየስነስ ዳግም ከኢትዮጵያ ምድር ተቀጣጥሏልና። ሳልሳዊ ምኒልክ ዳግማዊ አብቹ ተነስቷልና። አብቹ ማነው ለምትሉ፣ ጣሊያን የአድዋ ውርደቱን ለመበቀል ከ40 አመታት ዝግጅት በኋላ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታንክ መድፍና ጀት እስካፍንጫው ታጥቆ አገራችን በወረረ ጊዜ ከተከሰቱ ጀግኖች የሰላሌው ወጣት አርበኛ አብቹ ቀዳሚው መሆኑን የቼክ ሪፐብሊኩ አዶልፍ ፓርለስካ “ሃበሽስካ ኦዴሳ”፤ ተጫነ ጆብሬ፣ ”የሀበሻ ጀብዱ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በመለሰው መጽሐፍ አስገራሚ ጀግንነቱን ለትውልድና ለታሪክ ከትቧል።
ባለፈው ሰኞ ታሪካዊውንና ተምሳሌታዊውን ውሳኔያቸውን ይፋ ባደረጉበት ቃል ኪዳንና የክተት ጥሪ፤ “ይህ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ነው። ልጆቻችን አገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው። በዓለም ላይ በክብር የምንጠራበት ስም እንዲኖረን የሚደረግ ትግል ነው። መኖር ወይም አለመኖራችንን የሚወስን ትግል ነው። ያለ ጥርጥር ግን እናሸንፋለን። ኢትዮጵያን ጠርቶ መሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ “ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጊዜው አገርን በመስዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ ፤” ገልጸው ከህዳር 14 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ መከላከያን በግንባር ሆነው ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ የሚዘምቱ መሆናቸውን ይፋ አደረጉ።
በማስከተል፤ “ድሮም ሆነ ዛሬ የእያንዳንዳችን ፍላጎት፣ የሁላችንም ሕይወት ከኢትዮጵያ በታች ነው። እኛ ኖረን ኢትዮጵያ ከምትሞት እኛ ሞተን ኢትዮጵያ እንድትኖር እንፈልጋለን። የሁላችንም የሆነች፣ ነጻነትና ፍትሕ የሰፈነባት፣ በገናናነቷና በነጻነቷ በዓለም አደባባይ የምትጠራ አገር እንድትኖረን ምኞታችን ነው። ለኢትዮጵያ ትልቅ በመመኘት፤ አገራችን አንገቷ ቀና እንዲል በመፈለግ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል። ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በሰው አገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ ለማድረግ ሞክረናል። ካለፈው በጎውን ወስደን ጥፋቱን በይቅርታ ለማረም ተንቀሳቅሰናል።
‘በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር ‘ ብለን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። የመለያየትና የጥላቻን ግንብ አፍርሰን የመደመርና ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን ልንገነባ ቃል የገባነውን ወደ ተግባር ለመተርጎም አቅማችን የፈቀደውን አድርገናል፤ ‘ኢትዮጵያ ‘የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች አገር ናት። ይሄን ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል። ድንበሯን ሊደፍሩ የሞከሩ አይበገሬ ክንዷን አይተዋል። ሊያስገብሯት የቋመጡ አቀርቅረው ተመልሰዋል።
ክህደት ለፈጸሙባት ተገቢውን ትምህርት መስጠት ፣ ከጀርባ የወጓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣትን ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ለሺህ ዘመናት የተጎናጸፈችው ነጻነትና ሉዓላዊ ክብር በችሮታ የተገኘ አይደለም። ያለ ዋጋ ነጻነትን አጽንቶ መጠበቅ አይቻልምና፤ ኢትዮጵያ የሚለው የነጻነት ስም የደም ዋጋ ተከፍሎበታል፣ ብርቱ ጀግኖች ሞተውለታል። በታሪክ የምናውቃቸው አባቶቻቸው በአስተዳደርና በርዕዮተ ዓለም ይለያያሉ፤ ለመብት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በነበራቸው አመለካከት
ይለያያሉ። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ባላቸው ቦታ ግን ልዩነት አልነበራቸውም። በቋንቋ፣ በብሔርና በጎሳ ብዙኃነት ቢኖራቸውም የአልደፈርም-ባይ ቆራጥነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል ። የግል ፍላጎታቸው የቱንም ያህል የተራራቀ ቢሆን ፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነታቸው በላይ ይቀመጣል።
ኢትዮጵያ የምታጓጓ አገር ናት። ከትናንትናዋ ይልቅ ነገዋ ታላቅ ነው። መከራ ማለፍ ነባር ችሎታዋ ነው። ይሄንን የገጠመንን መከራም እናልፈዋለን። ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል። በአንድ በኩል ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራሷ ፈቃድና በራሷ መንገድ ብቻ የምታድግ ኢትዮጵያ ላለማየት የጥፋት በትር ሰንዝረዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ ከተነሣች፣ ተነሥታም ካሸነፈች፣ ከዚህ በኋላ ለማንም የማትመለስ ትሆናለች።
ይሄን አፍሪካዊ መንገድ ለማደናቀፍ ሁሉንም ዓይነት የክፋት መሣሪያዎች ማሰለፋቸውንና የእነርሱን ብርታት በኢትዮጵያ ድካም ላይ ለመገንባት ተነስተዋል። ጥቁር ሕዝቦች የራሳችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር እንዳይኖረን ሆን ተብሎ የሚደረግ አንገት የማስደፋት ትግል ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ እንዳያገኙ የተከፈተ ዘመቻ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ሲሉ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁሉም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ “ጥሪ አቀርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ተከትሎም የፓርላማ ተመራጩና የአብን አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ከፍተኛ አመራር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ አርበኛው ነአምን ዘለቀ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ካሳየ ጨመዳ፣ የትዴፓው ዶ/ር አረጋዊ በርሔ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ አርቲስት አቡሽ ዘለቀ፣ አርቲስት መስፍን በቀለ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፣ አርቲስት ደመረ ለገሰ፣ አክቲቪስት ታየ ቦጋለ፣ አክቲቪስት ቹቹ አለባቸው፣ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንንና ሌሎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አብረው ለመዝመት መወሰናቸውን አሳውቀዋል።
እንደ መውጫ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ቀደሙት ጀግኖች መሪዎቻችን የአገራችንን ሉዓላዊነት የግዛት አንድነትና ነጻነት ለማስከበር የሚደረገውን ጦርነት በግንባር ተገኝቼ እመራለሁ ማለታቸው በኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የመጣ አንገቴ ይቀላል እንጅ አልደራደርም ያሉትን ቃል ለመፈጸም የሄዱበትን ርቀት ያሳያል። መሪነት ቀድሞ ከፊት መገኘት፣ በተግባር መገለጥና አርዓያ ሆኖ መገኘት መሆኑን አረጋግጠውልናል። ከሁሉም በላይ ውሳኔያቸው ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈ ከመሆኑ ባሻገር የሠራዊቱንና የደጀኑን ሕዝብ ሞራልና ሥነ ልቦና ከፍ በማድረግ የፈጠረው አገራዊ ንቅናቄ የጦርነቱን ሒደት ምድረ አርዳዊ በሆነ አግባብ (ሳይዝሚክ ሺፍት)እንደሚቀይረው ገና ከጅምሩ መስተዋል ጀምሯል። የምዕራባውያን ሚዲያዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ “የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ጠ/ሚ ጦርነቱን በግንባር ተገኝቼ እመራለሁ፤”አሉ በማለት ለመሳለቅ ቢሞክሩም ውሳኔው የጦርነቱን ገጽታ ፍጹም የሚቀይር መሆኑ አያጠያይቅም።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ተከትሎ በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮኖች ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት መነሳሳታቸው ስለማይቀር ይሄን የሚያስተናግድ አሠራርና አደረጃጀት መፍጠር፤ የደጀኑ ሕዝብ የሚያደርገውን የገንዘብና የስንቅ ድጋፍ አቀናጅቶና አደራጅቶ ግንባር የሚያደርስ የተሳለጠ ግልጽ አሰራር ማስፈን፤ ከተሞችን ከጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ሌት ተቀን በንቃት መጠበቅ፤ ሰርጎ ገቦችንና የሕወሓት ቡችሎችን ለይቶ ለሕግ ማቅረብ የክተት ጥሪውን ሙሉኡ ያደርገዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች !!!
እናሸንፋለን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014