በሕትመት ጋዜጠኝነት ከ18 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ጋዜጠኛ ነው። በአሁኑ ሰዓት ከመደበኛ ሙያው በተጨማሪ ለተለያዩ ድርጅቶች በሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ በአማካሪነት በመሥራት ይታወቃል። ከጵሑፉ ጋር በተያያዘ ጰሐፊውን ማግኘት ከፈለጉ የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ። abebeferew@gmail.com
(ፍሬው አበበ) ዛሬ የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም፤ በታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያለው ቀን ነው። የአድዋ ጦርነት ተጀምሮ 24 ሰዓታትን ባልደፈነ ጊዜ ውስጥ በድል የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ቀን ነው። የአድዋ ድል የተለየ የሚያደርገው ኢትዮጵያውያን በጦርነት ስላሸነፉ አይደለም። ወይንም ጥቁሮች የነጭ ወራሪን ስለረቱም አይደለም።
የአድዋ ድል ለየት የሚያደርገው እስከአፍንጫው የታጠቀ የነጭ ጦር ከወኔ፣ ከጀግንነት፣ ከአገር ወዳድነት በስተቀር ብዙም ባልታጠቀ የጥቁር ሠራዊት አሳፋሪ ሽንፈትን የተከናነበበት የድል ቀን መሆኑ ነው። በጉልበታቸውና በያዙት ብረት የተማመኑ ፋሽስቶች አንገታቸውን የደፉበት ቀን በመሆኑ ነው። ድሉ፤ ለአፍሪካውያን የአንድነት፣ የመደመር፣ የፍቅርና የኩራት ተምሳሌት ለመሆን መብቃቱ ነው። ድሉ፤ አፍሪካውያን በወቅቱ በተናጠል ያደርጉ የነበሩትን አታካች የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል እንዲቀጣጠል የወኔ ስንቅ ማቀበል መቻሉ ሲጠቀስ የኖረ ነው።
የዛሬ 123 ዓመት፤ በዛሬዋ ቀን! የተለያዩ ድርሳናት እንዳሰፈሩት፤ ጦርነቱ የተጀመረው በታሪክ ውስጥ በዛሬዋ ቀን የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ከማለዳው 11 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ ላይ ነበር። ሸልዶ ተራራ ወይም (ሶሎዳ ተራራ)፤ ማርያም ሸዊቶ፤ አዲ ተቡን፤ ረቢ አርእየኒ (እግዚሃር አሳየኝ)… በመባል የሚታወቁት ገመገሞችና ተራራማ ሥፍራዎች ዋነኞቹ የጦር ግንባሮች ነበሩ። እቴጌ ጣይቱ ብጡል የኢትዮጵያን ጦር በሞራል በማነቃቃትና በማበረታት እንዲሁም ሠራዊቱን እግር በእግር እየተከተሉ በማበረታታት ረገድ ሚናቸው ግዙፍ ነበር።
እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ወይዘሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮቻቸው ታጅበው መታየታቸው ብቻ የወታደሩን ሞራል ገንብቷል። የጄኔራል አልቤርቶኔ ክፍለ ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ፣ በዋግሹም ጓንጉል፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ። የንጉሰ ነገስቱ ሠራዊት የመሐል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ከጣሊያኖች ጋር በተደረገው ጦርነት የተመሰከረለት ጀግና ነበር። ጎራዴውን መዞ በዋናው የትግል አውድማ ላይ ተወርውሮ ገባ።
በዚህም ጊዜ በጠመንጃ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አለፈ። በገበየሁ መሞት ተሸብሮ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ወዲያው መልሶ ተረጋጋ። በታላቅ ቆራጥነት አልቤርቶኔን እንደገና ገጠመው። በአራት ሰዓት አካባቢ ላይ አልቤርቶኔ ከመኮንኖቹ አብዛኞቹን አጥቷል። በጦርነቱ እንደተሸነፈ ግልፅ ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በድንጋጤ ተውጠው ፈረጠጡ። ከፊሉ ተማረከ፣ የቀረውም ወደ ሌሎቹ ክፍላተ ጦር በመሸሽ ራሱን አተረፈ። በዚህ ጊዜ ያልተነካው ክፍል የሚይዘውን አጥቶ ይተራመስ ገባ።
በዚህ ሰዓት ቀጥታ በአጼ ምኒልክ የሚታዘዘው ጦር ከውጊያው ገባ። በጦርነቱ ወቅት አጼ ምኒልክ በትክክል ወዴት እንደሚገኙ ጣልያኖች አያውቁም ነበር። ሁልጊዜ ሳይለዩት አብረውት ከሚገኙት ሁለት ሊቀመኳሶች አንዱ በአለባበሱ ንጉሱን መስሎ በስፍራው ይገኛል። ከሊቀመኳስ ተግባሮች ውስጥ አንዱ የጠላትን ትኩረት ወደ እሱ በመሳብ ንጉሰ ነገስቱን መጠበቅ ነው። በጦርነቱ ስፍራ አጼ ምኒልክ እንደ አንድ ተራ ወታደር ለብሶ በጦርነቱ መካከል ተገኝቶ ያዋጋም ይዋጋም ነበር። ቀኑን ሙሉ ውጊያ ሆኖ ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ ድሉ የኢትዮጵያውያን መሆኑ ታወቀ። ዓለምን ያስገረመ ታሪክም ተመዘገበ።
በመቶ ሺህ የሚሠላ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የኢጣልያ ቅኝ ገዢ ወራሪዎችን ድባቅ ከመታና ረግጦ ካስወጣ በኋላ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም (የካቲት 23 ቀን) እንዳማርያም ላይ ተሰባስቦ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን (ድሉን) ለሰጠው አምላክ ምሥጋና አቅርቧል። መሰሪው የውጫሌ ውል ከተለያዩ ድርሳናት የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን በተቀራመቱበት ዘመን ኢጣሊያም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ መንገድ የሚከፍትላትን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር ውጫሌ ከተማ ላይ በተወካይዋ አንቶሌኒ በኩል ተዋዋለች።
ከተደረገው ውል አንቀፅ 17 ግን የአማርኛ እና የጣልያንኛ ትርጓሜው የተለያየ ነበር። በአማርኛ የተፃፈው ‹‹ግርማዊ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ሊያደርጉ ይችላሉ።›› የሚል ሲሆን የኢጣሊያንኛው ትርጉም ግን እንዲህ የሚል ነበር ‹‹ ግርማዊ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ያደርጋሉ።››
የዚህ ፍቺው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ሞግዚት አስተዳደር ስር መሆኗን የሚገልፅ ነው። ይህንንም የኢጣሊያ መንግስት ለአውሮፓ መንግስታት በደብዳቤ አሳውቋል። የጦርነቱ መነሻ ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣው የውጫሌ ውል የያዘው መሰሪ ሀሳብ ከታወቀ በኃላ ነው። አፄ ምኒልክ የውጫሌውን ውል በተዋዋሉ በ4ኛው ዓመት ለአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ሁሉ አድራሻው እየተለዋወጠ ቃሉ አንድ አይነት የሆነውን የውጫሌን ውል ያፈረሱበት ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ጻፉ::
«ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ’’ ይድረስ ለክቡር ንጉሠ ነገሥት ጉሊየልሞ ዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት ዘነምሳ። ብዙውን እንዴት ነዎት፤ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ከሠራዊቴ ጋር ደህና ነኝ። በዚህ ደብዳቤ ውጫሌ ላይ በ 25 ሚያዝያ 1881 ከኢጣልያ መንግስት ጋራ የተደረገ ውላችንና በ12 መስከረም በ1882 የተጨመረ ውል በ24 ሚያዝያ በ1886 እንዲጨረስ ዛሬ ለክቡር ንጉሠ ነገሥት ኡምቤርቶ ማስታወቃችን ስለሆነ ይኸው ዛሬ ለእርስዎ ማስታወቄ ነው።በፍቅር አስመስለው ሀገሬን በብዙ ተንኮል ለመያዝ ፈልገውብኛልና እግዚአብሔር ዘውድና ሥልጣን መስጠቱ ያባቴን ሀገር ለመጠበቅ ስለሆነ ይህንን ውል ጨርሼ ማፍረሴ ነው፤ ፍቅሬን ግን አላፈርስም። ከዚህ በቀር ሌላ ውል የምፈልገው የለኝም እርስዎ ይወቁት። መንግሥቴም ራሱን የቻለ መንግሥት ነውና የማንንም ጥገኝነት አልሻም። ደግሞ አስመራ ላይ ያስቀመጥኩት ሹሜ ደጃዝማች መሸሻ ከኢጣልያ ሹማምንት የተቀበለውን ግፍና መከራ የሮጳ ነገሥታት ሁሉ በወሬና በጋዜጣ ሰምተዋል። ይህንን ቃላችን እንዲቀበሉን ተስፋ አድርገን ሀገርዎንና እርስዎን እግዚአብሔር እንዲጠብቅልን እንለምናለን»
በየካቲት 4 ቀን በ1885 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ ይህ የምኒልክ ደብዳቤ የደረሳቸው መንግሥታት በሁለት ተከፈሉ። ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ሐሳብ የሌላቸውም ሆኑ ያላቸው መንግሥታት ኢጣልያ ባላት ዘመናዊ የጦር ኃይል ኢትዮጵያን እንደምትረታት እርግጠኛ ሆኑ። የቅኝ ገዢነት ምኞት የነበራቸው ያዘኑበት ዋናው ምክንያት ኢጣልያ ከሁሉም ቀድማ ኢትዮጵያን ለመያዝ የሚያስችላት መንገድ ስለተጠረገላት ነበር። የምኒልክ ወዳጅ የነበሩ መንግሥታትም ቢሆኑ ኢጣልያ ኢትዮጵያን በቀላሉ መያዝ እንደምትችል አወቁ። ምናልባትም የኢትዮጵያን መንግሥት ባለበት ሁኔታ ማለት ባገሩ ሰው የውስጥ አስተዳደሩን እየመራ እንዲቆይ ማድረግ የተሻለው ዘዴ መሆኑን አምነው ኢትዮጵያ የኢጣልያን ጥገኝነት ተቀብላ በውጫሌው ውል እንድትረጋ የሚያስፈልግ መሆኑ ያግባባል ብለው አሰቡ።
ይህንኑም በመግለጽ የእንግሊዝ መንግሥት ከኢጣልያ መንግሥት ጋር በተዋዋሉት ኮንቬንሽን ኦፍ ሮም በተባለው ውል መሠረት የእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ ለምኒልክ በጻፉት ደብዳቤ በኢጣልያ ጥገኝነት ሥር እንዲቆዩና ለኢትዮጵያም የሚሻለው ዘዴ ይኸው መሆኑን መከሩ። የጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት ደግሞ በኢጣልያ ጥገኝነት ሥር መቆየቱ ለኢትዮጵያ የሚበጅ መሆኑን በመግለጥ ነገሩን እንደገና እንዲያስቡበት የሚመክር ደብዳቤ ለምኒልክ ጻፉላቸው። ምኒልክ ከየነገሥታቱ የሚደርሷቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ለኢጣልያ መንግስት የሚያግዙና ኢትዮጵያ በኢጣልያ ሥር ትተዳደር እያሉ የሚመክሯቸው በመሆናቸው ተበሳጩ።
ኤሮፓም ባንድነት ተባብሮ ኢትዮጵያን ለመውጋት እንደሚነሳ ገባቸው። በዚህ ምክንያት «…በአገሬ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢጣልያኖች ሁሉ እየወጡ ካገሬ ይሂዱ…» ብለው ለየመኳንቶቻቸው ሁሉ አሳወቁ። ለኢጣልያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም «…ወደፊት ማንኛውም የኢጣልያ ሰው ወደ አገሬ እንዳይመጣብኝ ይሁን…» ብለው በደብዳቤ ገለፁ። የኢጣልያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳግማዊ አጤ ምኒልክ ደብዳቤ እንደደረሰው ነገሩ በሙሉ መበለሻሸቱ ስለገባው ስለውጫሌ ውል እንዲነጋገር ዶክተር ትራቨርሲን ሁለት ሚሊዮን ጥይት ገፀ በረከት አስይዞ እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ላከው። አጤ ምኒልክም ከዶክተር ትራቨርሲ ጋር በተገናኙ ጊዜ «…እኔ በማንኛቸውም ጊዜ ቢሆን ከኢጣልያ መንግሥት ጋር የጀመርሁትን ወዳጅነት ለመተው አሳብ አልነበረኝም እናንተ ግን አሳባችሁ ሁሉ ለጠብ እንጂ ለፍቅር አለመሆኑን ሥራችሁ ይመሰክራል…» በማለት ነገሩት።
በመጨረሻውም ከኢጣልያ አገር ድረስ ያመጣኸውን ጥይት አልቀበልም ብዬ ብመልሰው ግርማዊ የኢጣልያ ንጉሥ ወዳጅነታቸውን የጠላሁ መስሏቸው እንዳያዝኑብኝ ስል ተቀብያለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ ብለው አሰናበቱት። በዚህ መሀል በ1887 በጄኔራል አሬሮ የሚመራው የኢጣልያ ጦር አድዋ ገብቶ አገሩን ያዘ። አዲግራትና መቀሌም መጋቢት 16 ቀን ተያዙ። እስከ አክሱም ዘልቆም ለህዝቡ ልብስና ማባበያ በመስጠት «ከምኒልክ አገዛዝ ነፃ ላወጣችሁ ነው» እያለ ይሰብክ ጀመር። አጤ ምኒልክም ይህን ነገር ወደ ኢጣልያው ንጉሥ ቢያስታውቁ ነገሩ የተፈፀመው በስህተት ነው የሚል የውሸት መልስ አገኙ።
ኢጣልያኖች አድዋንና አክሱምን እንደያዙ ወዲያው እየገፉ አጋሜንና እንደርታን አምባላጌን ሁሉ ያዙ። ምንም እንኳ በአገሪቱ ላይ አምስት ዓመት የቆየ ከባድ ረሃብ የደረሰ ቢሆንም ያንኑ ረሃብተኛ ሕዝብ ለማዝመት ምኒልክ ቀጥሎ ያለውን አዋጅ አወጁ። አዋጅ!..አዋጅ!… «እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም።
እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሠጠውም። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለምሽትህ (ለሚስትህ) ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።
ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።» ምልዐተ ሕዝቡ፣ መሳፍንቱንና መኳንንቱን በኢጣሊያ ላይ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብሎ ዘመተ። ሆ ብሎ በአንድነት፣ በመደመር መንፈስ የተመመው ሕዝበ ሠራዊት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪን ድባቅ መታ። እነሆ አገራችን ኢትዮጵያም በዓለም ታሪክ ውስጥ በደማቁ አኩሪ ገድል ለመጻፍ በቃች።
ስለአድዋ የባለቅኔዎች ምህላ!
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ፡-
«…የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት።
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር ዓድዋ ትናገር ትመስክር
ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።
ጸጋዬ ገብረመድህን፡-
«…አድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነቱዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ እለት
አድዋ …
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያነት ምስክርዋ
አድዋ! …
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፡-
«ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሦስቱን ቀለማት፤
እባካችሁ ሰዎች እንዳለ ተውት፤
ሰሀጢና ጉንደት፣ መተማ፣ አድዋ ላይ ማይጨው ያለቁት፤
ለዚች ባንዲራ ነው መልኳን አታጥፏት።
ሕዝባዊ ሥነቃሎች
ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ እንቀላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፤
***
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤
***
የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤
መልካም የአድዋ በዓል!!