fenote1971@gmail.com የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ሰንደቅ !!! የዘመናዊ ኢትዮጵያ ምስረታ የማዕዘን ድንጋይ !!! የአድዋ የድል በዓል የፊታችን የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ. ም ከንጉሱ ጋር አብሮ ዘምቶ በነበረው የጊዎርጊስ ዕለት 123 ዓመት ይሆነዋል። ከ100 ዓመት ፣ ከአንድ ምዕት አመት ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ “23” በአመትም በቀንም ለ2ኛ ጊዜ ተገጣጥመዋል። ያው የመጀመሪያው የአድዋ ድል በዓል ለ23ኛ ጊዜ በየካቲት 23 የተከበረ ዕለት መሆኑ ነው። የአድዋ የድል በዓል 100ኛ አመት የድል በዓል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታላቅ ድምቀት ሲከበር በተማሪነት በዚያ በመገኘቴ እድለኝነት ይሰማኛል።
የታሪክ ትምህርት ማይነሬ ስለነበር በሁሉም የበዓሉ ዝግጅቶች የመታደም ዕድል ነበረኝ ። በዝክሩ በተዘጋጀ ዓለምአቀፍ አውደ ጥናት በተለያዩ ምሁራን የቀረቡ ጥናታዊ ወረቀቶች የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን ከፍ ሲልም የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን የሚያረጋግጡ ነበሩ። የአድዋን ድል ከዚህ አንፃር ብቻ ማየት የአሸናፊዎች ታሪክ ብቻ እንዳደርገው ይሰማኛል።
ዳሩ ግን ታሪኩ የተሸናፊዎች ፣ የቅኝ ገዥዎች ፣ የተስፋፊዎች ፣ የወራሪዎች ፣ የነጮች ጭምር አድርገን ስናየው የአድዋ ድል ከጥቁር ሕዝቦች ድል አልፎ የሰው ልጆች ታሪክ ፣ ገድል ይሆናል። ፀሐፍት የአድዋ ዘመቻ ከወሰደው ጊዜና ከሚያካልለው የቦታ ስፋት እንዲሁም በድል ከመደምደሙ አንፃር ሲታይ የ19ኛው መ. ክ .ዘ ታላቁ ጦርነት ይሉታል። አድዋን አንድ እርከን ከፍ በማድረጉ ላይ ከተግባባን ፤ ይሄን የሰው ልጅ ታላቅ ታሪክ ያነበሩትን መግፍኤዎች ፣ ምክንያቶች ፣ ውጤቶችን አክለን ትምህርቱን የዘመናዊ ኢትዮጵያ እርሾነቱንም ለጋዜጣው እንዲመጥን ቀንጨብ አርገን እንመልከታለን ፤ የፈረንሳይ ቱኒዚያን የመያዝ ፣ የናፒየር ዘመቻ ፣ የቤልጅየሙ ንጉስ ኮንጎን የመቆጣጠር ፣ የአውሮፓውያን የተስፋፊነት ሕልም ፣ የስዊዝ ካናል መገንባትን ተከትሎ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከፍ ማለቱና በወቅቱ የነበረው የዘውድ ሽኩቻ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ ለመቋመጧ በመግፍኤነት ከሚጠቀሱት ዋነኞቹ ናቸው ።
በጊዜው የምኒልክ ወደዙፋኑ መቃረብ ያስደሰተው የጣሊያን ወኪል ፔትሮ ኢንቶኔል ግንኙነቱን በፊርማ ለማረጋገጥ ሚያዚያ መገባደጃ ላይ በ1881ዓ.ም ውጫሌ ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም በቃ። ስምምነቱ ስውር ደባ ያለው ቢሆንም ዋና አላማ አድርጎ የተነሳው የባሪያ ንግድን ለማስቀረትና ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ላሰበችው የንግድ ልውውጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያገለግል ነበር።
ዳሩ ግን ውሎ ሳያድር የስምምነቱ አንቀፅ 17 ውዝግብ አስነሳ። በዚህ አንቀፅ መሰረት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታደርገው በጣሊያን በኩል እንደሆነ የሚያስገድድ መሆኑ ሀገሪቱን በጣሊያን ሞግዚትነት የምትተዳደር ያደርጋታል። በስምምነቱ አንቀፅ 19 ላይ የአማርኛና የጣሊያንኛ ቅጅዎች እኩል ተቀባይነት እንዳላቸው ቢደነግግም ቅጅው የተለያየ መሆኑ አለመግባባት ፈጠረ። ይህ ልዩነት ተካሮና ጦዞ የአድዋን ጦርነት ቀሰቀሰ። በ1887 ዓ.ም በወርሀ መስከረም በገበያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒልክ የወረ ኢሉን ክተት አዋጅ አስነገሩ ።
“…ሀገርንና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል። እኔም የአገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም ፤ እያለፍ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ፤ …” አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት ፣ ከመላው ሀገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100 ሺህ በላይ ወዶ ገብ በኢትዮጵያዊ አንድነት ፣ ጀግንነት፣ ቆራጥነት ፣ አልበገር ባይነት ፤ ዳር ድንበሩን ፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ወደ ሰሜን ተመመ ። ጄነራል ባራቲየሪም ሰራዊቱን ወደ መሀል ትግሬ እንዲንቀሳቀስ ትዕዛዝ ሰጠ።
አፄ ምኒልክ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወራሪው ፣ ተስፋፊው ጣሊያን ከግዛታቸው ለቆ እንዲወጣ ቢጠይቁም ፤ ጄኔራሉ አሻፈረኝ ከማለቱ ባሻገር በዕብሪት የማይሆን ቅድመ ሁኔታ ይደረድር ጀመር ፤ የአፄው ጦር ትጥቅ እንዲፈታ ፣ ራስ መንገሻ እንዲታሰሩ ፣ መላውን ትግሬን እንዲያስረክብ እና የጣሊያንን የበላይነት እንዲቀበል ጠየቀ። በዚህም ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ እርግጥ ሆነ ።
ወራሪው ጣሊያን የመጀመሪያውን የሽንፈቱን ኩታ በሁለት ሰዓት ውጊያ አምባላጌ ላይ ተከናነበ። የአምባላጌው አኩሪ ድል ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው ታላቅ ድል ቢሆንም ፤ከወታደራዊ ስኬቱ በላይ ስነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ፣ ውጤቱ ከፍተኛ ነበር። ኢትዮጵያውያን የአውሮፓን ጦር ድል መንሳት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ፤ የአፄ ምኒልክን ጦር የውጊያ ሞራል ያነቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በሀገር ውስጥም በውጭም የንጉሱን ክብር ፣ ተቀባይነት ከፍ አደረገ። የአፄ ምኒልክ ጦር ግስጋሴውን ቀጥሎ መቀሌን ተቆጣጠረ። ይሄን ተከትሎ ስብሀትና ሀጎስ የተባሉ ለጣሊያን ያደሩ ባለሟሎች ከድተው ለንጉሱ መግባታቸው ለወራሪው አስደንጋጭ መርዶ ነበር። የንጉሱ ጦር በወርሀ የካቲት እኩሌታ ለአድዋ ጥቃት ዝግጁ ሆነ። የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦር ተፋጠጠ።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ሙሉ ቀን በተካሄደ ጦርነት የጀኔራል ባራቲየርና የሌሎች ጄኔራሎች ጦር ተፈታ፤ ተሸነፈ፤ ሸሸ። ወደ 10ሺህ የሚጠጋ የጣሊያን ጦር ሙት ፣ ቁስለኛ ፣ ምርኮኛ መሆኑን አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ሲያትቱ ፤ ሌሎች ደግሞ የሟቹን ቁጥር 11ሺህ ፣ የተማረከውን 4ሺህ ያደርሱታል። ከጄኔራሎች አርሞንዲና ዳቦርሚዳ ሲሞቱ ፤ በ1850ዎቹ የሀገራቸውን ነፃነትና አንድነት በማስከበሩ ብሔራዊ ጀግና ከነበረው ጁሴፔ ጋሪባልዲ ጋር ይነፃፀር የነበረው የጄኔራል አርቤርቶኔ መማረክ ለጣሊያናውያን ሌላው አስደንጋጭና በሀፍረት አንገት ያስደፋ መርዶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ከጦር መሳሪያም መድፍ ፣ 11ሺህ ጠመንጃ ፣ በርከት ያለ ጥይትና ቁሳቁስ ተማርኳል ። ከኢትዮጵያ የጦር አበጋዞችና የንጉሱ የቅርብ ባለሟሎች ጀግናውን ፊታውራሪ ገበየሁ ፣ ልዑል ዳምጠው ፣ ደጃዝማች መሸሻ ፣ ደጃዝማች ጫጫ ፣ ቀኛዝማች ገነሜና ሌሎች ለሀገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት መውደቃቸውን ፤ በተጨማሪም 4ሺህ ሲሞቱ 6ሺህ ኢትዮጳውያን መቁሰላቸውን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ቢያትቱም ቁጥሮ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገምታሉ ። ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከአፍንጫው የታጠቀው የጣሊያን ጦር አፍሪካዊና ጥቁር በሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ መረታቱ ለማመን የሚቸግር መነጋገሪያ ሆነ።
አንዳንድ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች የኢትዮጵያውያንን ጥቁርነት እስከ መካድ ደርሰው ነበር። የታላቁ የአድዋ ድል አገራችንን ከአፅናፍ አፅናፍ የዓለምን ትኩረት እንድትሰብ አደረጋት። ድሉ ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉ በማሳየቱ ፤ በቅኝ ግዛት ፣ በጭቆና ለሚገኙ የዓለም ሕዝቦች በተለይ ለአሜሪካ ጥቁሮች መነቃቃትን ፈጥሯል። ለማርከስ ጋርቬ ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለስቲቭ ቢኮ ብላክ ኮንሽየስ ንቅናቄዎች እርሾ በመሆን አገልግሏል ።
ለደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት ሆኖ አገልግሏል ። የአረንጓዴ ፣ ቢጫ ፣ ቀይ ባንዲራችን በብዙ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት ሰንደቅ በተለያየ ቅርፅ የመገኘቱ ሚስጥርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ። የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነትም የራሳቸው ጥረት እንዳለ ሆኖ መነሻው አንፀባራቂው የአድዋ ድል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ ። አንዳንድ የፖለቲካና የታሪክ ልሂቃን የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ሆነ የዛሬውየአፍሪካ ህብረት (አህ) የምስረታ ሃሳብ የአድዋ መንፈስ የበኩር ልጅ የሆነው የፓን አፍሪካኒዝም የመንፈስ ክፋይ ነው የሚሉት ለዚህ ነው ።
አድዋ ያስተማረን ፦ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ የአድዋን ድል ትምህርት ፣ አንድምታ ፣ ትርጉም እንዲህ ሲል ይገልፀዋል ፦ “…ምኒልክ እና ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ስልጣናቸውን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ብቻ አልነበረም ። …የትግራይ ፣ የሸዋ ፣ የኦሮሞ ፣ የወላይታ እና የሌሎች ሕዝቦችን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ አገር ለመገንባት እንጅ ፤ የሕዝቦች ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ሃይማኖት ፣ ማንነት ብሔር ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የጋራ ነፃነትን ለመቀዳጀት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው ።
ይህ አይነቱ መተሳሰር ብቻ ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ ፤ የአድዋ ትምህርትም ይኸው ነው ። ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ መሆን እንዳለበት አድዋ ያስታውሰናል። የአድዋ ድል ያስገኘው ነፃነት ብቻ ሳይሆን የተገኘበትን መንገድ ብናጤነው የዘመናችንም ታላቅ ወታደራዊ ድል እንድሆንን እንረዳለን። በጠመንጃ ብቻ በመታገዝ የተገኘ ድል አይደለም። የበርካቶችን ልብ በማሸነፍ እንጅ ፤ …” ይህ የሬይሞንድ ጥልቅ ፣ ምጡቅ የአድዋ ትምህርትና ፍልስፍና የምንገኝበትን ዘመን የዋጀ ፤ እኛን እንደ ዜጋ የፍትህ ሳጥኗ ላይ አቁሞ የሚሞግትና የሚዳኝ ሆኖ ይሰማኛል።
አዎ ! በጀግኖች አባቶቻችን ከ123 ዓመታት በፊት የተቀዳጀነውን ታላቅ ድልም ሆነ ፤ ከጣሊያን የአምስት ዓመቱ ቆይታ ፤ ከንጉሳዊ አገዛዙ ፤ ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነፃ የወጣንባቸውን ድሎች ልንከላከላቸውና ልንጠብቃቸው ባለመቻላችን ለአንድ ምዕተ ዓመት ከሩብ ዋጋ እንዳስከፈሉን ስንቶቻችን ነን የምናሰላስለው! የሚያሳዝነው ግን ከእነዚህ የታሪክ መታጠፊያዎች ዛሬም አለመማራችን ነው።
በዚህ መነሻነት በእርግጥ!? ባለፉት 11 ወራት የተጎናፀፍነው የነፃነት ቀብድ ለመከላከል ፣ ለመጠበቅ በሙሉ ልባችን ተዘጋጅተናል!? የእነዚህን ጥያቄዎች መልሱን ለእናንተ ልተወው ፤ የዘመናው ኢትዮጵያ ምስረታ የማዕዘን ድንጋይ ፦ ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ ፣ ምኒልክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠረ። ከታላቁ የአድዋ ድል ማግስት ጀምሮ የአፄ ምኒልክ ፣ የእቴጌጣይቱ ፣ የኢትዮጵያ ዝና በመላው ዓለም ፣ ከአፅናፍ አፅናፍ ናኘ ። እንደ ዛሬው TIME መፅሔት በጊዜው ታዋቂ የነበረው “ Vanity Fair “ የአፄ ምኒልክን ምስል ይዞ መውጣቱ ፤ ከእነ ቻርለስ ዳርዊን ፣ ከታላቁ አሌክሳንደር፣ ከናፖሊዮን ሳልሳዊ እኩል ታዋቂ አድርጓቸዋል።
አውሮፓውያን ለልጆቻቸው “ምኒልክ” የሚል ስም እስከማውጣትም ደርሰው ነበር። የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት ከመላው ዓለም በሚጎርፉ ደብዳቤዎች ተጨናንቆ እንደነበርም የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መስክረዋል። አፄ ምኒልክ በተቀዳጁት ሞገስ ተኩራርተው እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ ይህን ዝናቸውን በመጠቀም የዘመናዊ ኢትዮጵያን መሰረት ጥለዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥም በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ካቢኔአቸውን ከማቋቋም ጀምሮ 61 አዳዲስና የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ፣ አሰራሮችን ፣ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ ችለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የውሃ ቧንቧ ፣ የኤሌክትሪክ መብራት ፣ በመንገድ የሚሄድ ሰርኪስ ባቡር ፣ የሀዲድ ባቡር ፣ የብረት መኪና ፣ አውቶሞቤል ፣ የፅህፈት ማተሚያ መኪና ፣ ስልክ ፣ ፖስታ ቤት ፣ ባንክ ፣ ሀኪም ቤት ፣ የቋንቋ ት/ቤት ፣ ሆቴል ፣ ባህር ዛፍ ፣ የድንጋይ ንጣፍ ፤ ይገኙበታል ። እንደ መውጫ ፦ በአፄ ቴዎድሮስ መሰረቱ የተጣለው የሀገረ መንግስት፣ የአንድነት ግንባታ ህልም ፤ በአፄ ዩሐንስ እውን ሊሆን ሲል ሞትና የእርስ በእርስ የስልጣን ሽኩቻ መንገድ ላይ አስቀርቶታል። በመጨረሻ በአፄ ምኒልክ እና በእቴጌ ጣይቱ ዋልታና ማገርነት በአድዋ የማዕዘን ራስነት ፤ በመላው ኢትዮጵያውያን ክዳንነት እውን ሊሆን ችሏል ።
ለ19ኛው መ/ክ/ዘ ታላቁ ዘመቻ ጀግኖች አባቶቻችንን ፣ እናቶቻችንን በጥበብ ፣ በማስተዋል በፊታውራሪነት መርተው አኩሪ ድልንና ነፃነትን ላቀዳጁን ፤ በጊዜው ዓለም ከእነ ናፖሊዎን ሳልሳዊ እኩል ክብር ፣ ሞገስ የሰጣቸውን ፤ የጣሊያኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒን ከስልጣን ያወረዱትን ፤ የሰው ልጆች የነፃነት ምልክት የሆኑትን አፄ ምኒልክንም ሆነ እቴጌ ጣይቱን ያለ ልዩነት ዕውቅና ለመስጠትና ብሔራዊ ጀግና ለማድረግ በማንነት ፖለቲካ የተቀየደው እግራችን ወደኋላ ሲጎተት ስመለከት እንደዜጋ ኃፍረት ይሰማኛል ።
ባለፉት 50 ዓመታት በአንድ ሕዝብ ላይ አነጣጥሮ የተሰራ የጥላቻና የፈጠራ ታሪክ ሀገራችንን የብሔራዊ ጀግኖች ሾተላይ አርጎት ቆይቷል። ወደፊት ለምንገነባት ዴሞክራሲያዊ ፣ ፍትሐዊ ሀገር ይሄ አሜካላ ፣ ኩርንችት በጥንቃቄ መለቀም አለበት። ትርክቶቻችን በሀቀኛ ፣ ተጨባጭ ፣ ተጠየቃዊ ፣ አመክኖአዊ እነ ዘመነ ጓዴነትን contemporary በተከለ ገለልተኛና ሳይንሳዊ ስነ ዘዴ ላይ ሊመሰረቱ ይገባል *** *** (ለዚህ ዘካሪ ፁሑፍ የሚከለተሉትን መፅሐፍት በዋቢነት ተጠቅሜአለሁ ። የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ፣ የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክን ፤ አፄ ምኒልክና የአድዋ ድል ፣ የሙሉቀን ታሪኩ ትርጉም የሆነውን የሪሞንድ ጆናስን ፤ የሐያኛው ክፍል ዘመን መባቻን ፣ የመርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ፣ በአለማየሁ አበበ / ትርጉም
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን)