ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከውጭ አንገታቸው በረዘመ፣ ከውስጥ እይታቸው በጨለመ ጠላቶቿ እየተፈተነች ትገኛለች::ፋሽስቱ የወሮበሎች ቡድን አሸባሪው ሕወሓት በተለይም በአማራና በአፋር በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ እጅግ ዘግናኝ ግፎችን እየፈፀመ፣የኢትዮጵያን ክብር እያዋረደ ይገኛል::
በእርግጥ አሸባሪው ሕወሓት አሁን ላይ ከመኖር ወደ አለመኖር ተሸጋግሯል::ጠውልጎ ከስሟል::ይሁንና የትርፍራፊና ጋሻ ጃግሬዎቹ ግብአተ መሬት ግን ሙሉ በሙሉ አልተፈፀመም::የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ ቡድኑ በመጨረሻ የሚፈራው ለውጥ እራት ሊሆኑ ተቃርበዋል::ወድቆም ቢሆን ግን መፈራገጥና መላላጥ አላቆመም:: ኢትዮጵያን አጥፍቶ ለመጥፋት እየባዘነ ነው::ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሲኦል ድረስ እንደሚሄዱም በአደባባይ ሳይቀር ሳያፍር ሲያውጅ ተሰምቷል::
ኢትዮጵያ ከአንድ የታሪክ ምእራፍ ወጥታ ወደ ሌላ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የምትሸጋገርበት ወቅት ላይ ነች፤ ለዚህም ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም ሰንደቋን ከፍ አድርገው ወደ ታላቅነት ክብሯ የሚመልሱ አገር ወዳድ ልጆች ፈልጋለች። በምእራባውያኑና በባንዳዎች የተከፈተባትን የህልውና አደጋ በድል ለመወጣት ጀርባቸውን ሳይሆን ግንባራቸውን የሚሰጡ ልጆችን ትሻለች::
አገራችን በቀደመው ታሪኳ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ ያላት ናት። ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው በልጆቿ ነው::ልጆቿ በታሪኩ የሚታወቁት አገራቸውን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቁና ደማቸውን አፍስሰው የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉላት ነው::
የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ገድልና ቆራጥነት በአብዛኛው በህዝቦች ብቻ ሳይሆን በመሪዎች ፊት አውራሪነት የታጀበ ነው::በተለይ በጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መሪዎች ግንባራቸውን ለጥይት በመስጠት ህዝባዊ ጦራቸውን በአውደ ውጊያ መርተዋል::አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ አፄ ዮሐንስ በመተማ፣አፄ ምኒልክ በአድዋ፣ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያምም ቢሆኑ በካራማራ መክተታቸውም ለዚህ ጥሩ ማሳይ የሚሆን ነው::
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዶክተር አቢይ አሕመድም የዚህ የተንሰላሰለ ታሪክ አካል ለመሆን ዘመቻውን በአካል ተቀላቅለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም የዘረጉት እጅ ተቀባይ ባለማግኘቱ የአሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት መላ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲተባበር በማድረግ ረገድ በርካታ ተግባራት አከናውነዋል::በሳል ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል::እንደ ቀድሞ መሪዎች በግንባር ተገኝተውም ከሠራዊት ጎን፤ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አጠገብ ቆመዋል::
እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆሜ አልመለከትም፣ ህዝቤ ሆይ ግንባር እንገናኝ ››ብለው፣ ከተዋል:: በ21ኛው ክፍለ ዘመን መሪዎች ሊያደርጉት አይደለም ሊያስቡት የሚከብዳቸው ውሳኔ በመወሰን ለኢትዮጵያ ክብር ከፊት ተሰልፈዋል::
የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ወራሪ ሃይል ለመመከትና ድል ለማድረግ በጦር ሜዳው መንደር ተገኝተው የፈፀሙት የመሪነት ሚናም በዶክተር አቢይ ዘመን አሸባሪን የሕወሓት ቡድን ድል በማድረግ ሊደገም ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል::
ለዚህ ድል ፍጥነት ደግሞ ግን መላ ኢትዮጵያውያን ከፊት መቆም ለአገራችን መዝመት ይጠበቅብናል:: ከዚህ ቀደም በጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ተጋድሎ አገራቸው ታፍራና ተከብራ እዚህ መድረሷን ስንዘክር እኛም በተራችን የተላለፈልንን አደራ የመወጣት ኃላፊነት እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባናል::
ከዚህ በኋላ ምን እንጠብቃለን?! አገራችን የጠላት መጫወቻ ስትሆን፤ ታሪካዊና ህሊናዊ ኩራታችን ለመስለብ ከውጭም ከውስጥም ሲታደምብን፤ ከሶስት ምዕተ-ዓመት በላይ የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገርህ ተቆራርሳ ሚጥጥዬ አገር ለማዋለድ የውጭ ጠላቶች ደጃፋችንን ሲያንኳኩ ማየትን ያህል ምን ውርደት አለ?!::ለልጅ ልጆቻችን ታሪካዊቷን አገር ነጻነቷን አስጠብቀን እናስረክባቸው?! ወይንስ ደግሞ ባንዳነትና ባርነት እናቆይላቸው?
ኢትዮጵያ በጠላቶቿ በተፈተነችበት በዚህ ወቅት ልዩነትን ወደ ጎን በማለት አገር የማዳን ጥሪን ከመቀላቀል ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም::ኢትዮጵያ ትድን ዘንድ፣ የቱንም አይነት መስዋዕትነት ለመቀበል ዝግጁ መሆን የምርጫ ጉዳይ አይደለም::በዚህ ሰዓት የምንውሸለሸልበት ጊዜ ሳይሆን አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ሳንሰስት የምናበረክትበት ነው::
መሪያችን ግንባር ሲሄድ እኛስ? የሚል ጥያቄ መጠየቅ ይኖርብናል:: ዶክተር አቢይ አሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎንና ከሰንደቅ ዓላማ አጠገብ መቆማቸው ተነሳሽነትን ሊፈጥርብን ይገባል::በፀሎትም በጉልበትም በስንቅም ሆነ በተለያየ መንገድ ለእናት አገር ጥሪ ልንከት ይገባል:: ከሁሉ በላይ ያለችንን አንዲት አገር መጠበቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታችን መሆኑን ልናውቅ የግድ ነው::
ታሪኩን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩበትን ቀን እርግጠኛ አይደለሁም::ይሁንና ሁሌም ከማስታውሳቸው ታሪኮች በግንባር ቀደምትነት ይመደባል::ታሪኩን ከግለሰባዊ ዕይታ ወጣ አድርገን አገራዊ ገጽታ ስናላብሰው ውስጣዊ ስሜትን የሚገዛና ሕዝብ ለራሱ ለአገሩ ሲል ምን ማድረግ እንዳለበት ታላቅ ትምህርት የሚሆን ነው::
ታሪኩ የአንድ ወጣት ልጅና ብልህ ሽማግሌ ነው::በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ለአመራርና ለምክር የሚጠይቃቸው አንድ ብልህ ሽማግሌ ይኖሩ ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን ብልሁ ሽማግሌ በትክክል ለመመለስ የማይችሉትን ጥያቄ ወጣቱ ልጅ በመጠየቅ አዋርዳቸዋለሁ በማለት ወሰነ::
አንዲት ትንሽ ወፍ ከእጆቹ መዳፍ ውስጥ በማስገባትም ወደ ሽማግሌ ቀረብ ብሎ በእጆቹ መዳፍ ውስጥ ያለችው ወፍ በህይወት አለች ወይስ ሞታለች እስቲ ይገምቱ ይላቸዋል:: ሽማግሌው በምላሻቸው ወፏ ሞታለች የሚል መልስ ከሰጡ ወጣቱ ልጅ ወፏን እጆቹን ከፍቶ በመልቀቅ እንድትበር በማድረግ ሽማግሌውን ብልህ አይደሉም ሊያስብል ነው::
ብልሁ ሽማግሌ ወፏ በህይወት አለች በማለት ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ወጣቱ ልጅ በእጆቹ መዳፎች ስር ያለችውን ወፍ በመደፍጠጥ ይኸው ሞታለች በማለት ሽማግሌ የማያውቁ መሆናቸውን ማጋለጥ ነበር::
በዚህም መሰረት ወጣቱ ልጅ ብልሁን ሽማግሌ በዚህ መልኩ ተዘጋጅቶ ጠየቃቸው፣‹‹ብልሁ ሽማግሌ በእጆቼ ምን እንዳለ ሊነግሩኝ ይችላሉ? ብልሁ ሽማግሌ ረጋ ብለው‹‹በእርግጥ እችላለሁ››በማለት መለሱ::‹‹በእጆችህ ጣቶች መካከል ወጥተው ከማያቸው ላባዎች አንጻር በእጆችህ ውስጥ ትንሽ ወፍ ያለች መሆኑን ልነግርህ እችላለሁ››በማለት መለሱለት::
‹‹የተናገሩት እውነት ነው!››ሆኖም ግን‹‹እንደ ብልህ ሽማግሌ በመዳፎቼ ውስጥ ያለችው ወፍ ሞታለች ወይስ በህይወት አለች?››በማለት ወጣቱ ልጅ ጠየቃቸው::ብልሁ ሽማግሌ ለጥቂት ጊዜ ዝም በማለት ልጁን በአንክሮ ከተመለከቱ በኋላ ፣‹‹የወፏ በህይወት መኖርም ሆነ መሞት በእጆችህ ላይ ነው:: ምርጫው የአንተው ነው›› አሉት ይባላል::
ታሪኩን ከግለሰባዊ ዕይታ ወጣ አድርገን አገራዊ ገጽታ ስናላብሰው ውስጣዊ ስሜትን የሚገዛና ሕዝብ ለራሱ ለአገሩ ሲሉ ምን ማድረግ እንዳለበት ታላቅ ትምህርት የሚሆን ነው::አሸባሪው ቡድንና ምእራባውያን ጭፍራዎቹ በድፍረት ተሞልተው በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየባዘኑ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ታዲያ ኢትዮጵያ በሁላችንም እጅ ላይ ነች:: እያንዳንዳችን እጅ ለእጅ በመያያዝና መዳፎቻችንን አጠንክረን በመያዝ በአንድነት የመጓዝና በቁጣና በወኔ በመነሳሳት ኢትዮጵያን ከአደጋ የመጠበቅ፣ ክብሯንና ዝናዋን የማስመለስ ምርጫው በእኛ እጅ ላይ ተቀምጧል::
እጃችንን በማዛልና ጥንካሬያቸውን በማልፈስፈስ ኢትዮጵያን መዳፋችን ላይ በማውጣት እንድትሰበር የማድረግ ምርጫውም በእኛ እጅ ላይ የወደቀ ነው::ለኢትዮጵያ ህልውና ደግሞ ሰላም ቀዳሚና ዋና ጉዳይ ነው:: ሰላም ደግሞ በሁሉም ዜጋ ጥረት የሚገኝ ነው::የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ግዴታና ኃላፊነት የህዝብ ነው::ህዝቡ በያለበት ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጠው የትኛውም ኃይል ሃሳቡን ማሳካት አይችልም::
“የእኔ እና የእናንተ አባት እናቶች በዘመናችን አትፈርስም ብለው ላቆሟት አገራችን ኢትዮጵያ ህልውና፣ ሰላምና ነጻነት ደግሞ የአገርና የህዝብ ጠላት የሆነው ወያኔና አጫፋሪዎቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማንኮታኮት ይገባናል:: ለታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ የሚከፍቱ ተላላኪዎችን አደብ ማስያዝ የግድ ይለናል:: ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር የሚያብርና የጠላት መዝሙር የሚዘምርን መፋለም የነገ ሳይሆን የዛሬ ሥራችን ሊሆን ይገባል::
በእርግጥ ‹‹ማን ነው ኢትዮጵያ አገሩን የሚወድ? እጁን ያውጣ›› ቢባል ሁሉም እጁን ያወጣል።‹‹ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የሚፈልግስ?››ተብሎ ቢጠየቅ፤ አሁንም ሁሉም የአገሩን ሰላም እንደሚፈልግ ይናገራል። አበው ‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይሉናል።ይህንን የሚሉን ‹‹ቃል›› ምን ያህል ከባድ እንደሆነና፤ ከወለዱትም ልጅ በላይ ሊጠብቁት የሚገባ መሆኑን ሲያዝገነዝቡን ነው።
‹‹አገሬን እወዳለሁ››ስንል ግን የእለት ተእለት ተግባራችንም ይህንኑ ቃላችን የሚያስታውስና የሚያስመሰክር ሊሆን ይገባዋል። አገሩን የሚወድ በአገሩ ጉዳይ ዳር ተመልካች አይሆንም::አገሩን የሚወድ የአገሩን ጥቅም ያስከብራል::አገሩን የሚወድ ለአገሩ ዘብ ይቆማል::አገሩን የሚወድ ፍላጉቱን ከአገሩ ፍላጎት አያስበልጥም:: በአጠቃላይ አገሩን የሚወድ ማንኛውም ዜጋ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለአገሩ ህልውና መሆን አለበት::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት አኩሪ ፀጋዎች መካከል ዋናው አስተዋይነቱ ነው::ያለንበት ጊዜ ደግሞ እጅግ በጣም አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነው::ኢትዮጵያችን ከዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ እንድትወጣ በዚህ ወሳኝ ጊዜ የሚፈለገው አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ነው::ይህ ወቅት ደግሞ አስተዋይነታችን በእጅጉ የሚመዘንበትና በተለይም ኢትዮጵያችን በእጃችን ላይ መሆኗን የምንረዳበት ነው::
በተለይ በዚህ ወቅት ምእራባውያኑ በመካከላችን ለመግባት የሚንጠላጠሉበትን ግንብ በማፍረስ ላይ እንደ ጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በአንድነትና በጋራ መቆም እንዲሁም እርስ በእርስ መተባበር የግድ ይለናል::ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል::ኢትዮጵያውያንን የዓድዋ የጀግንነት መንፈሳቸውን በመስበር ለማንበርከክ የሚፈልጉ ኃይሎችን ምኞት ማክሸፍ ይገባል::
ኢትዮጵያውያን ለለውጥ አንድ ስንሆን ማንም የሚያቆመን የለም::ኢትዮጵያ አገራችንን ሉአላዊነቷ ተከብሮና ነጻነቷ ተጠብቆ እንድትኖር ታጥቀን መነሳት አለብን::ኢትዮጵያን በመጠበቅ ፣ በማክበርና በማስከበር ላይም ልዩነት ሊኖረን አይገባም::
ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ቤታችን በችግር ውስጥ መኖሯን የዘነጉ፣ ወይም እያወቁ እንዳላወቁ የሚሆኑ አስመሳዮችን መታገል የግድ ነው::አገርን ለማተራመስና ሕዝብን የማይወጣበት ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚጣጣሩ፣ የሕዝቡን አንድነት የሚፈታተኑና በሕዝብ መካከል መጠራጠርና ጥላቻ የሚዘሩ እንዲታቀቡ ማድረግ ይገባናል::
የትኛውም አገር የኢትዮጵያ መበተን አይገደውም::ህመማችንን የምንታመመው ብቻችንን ነው::ለእኛ ያለነው እኛ ብቻ ነን::በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ አንድነት ያስፈልገናል::ልዩነቶቻችን እንዲሁም የግልም ሆነ የቡድን ፍላጎታችንን በየኪሳችን አስገብተና እጅ ለእጅ የምንያያዝበት ጊዜው አሁን ነው::
በአሁኑ ወቅት የመኖር እና ያለመኖር ውሳኔ ላይ እንገኛለን::ከረፈደ አገር ከፈረሰች በኋላ ብንጮህ ብናብድ ምንም ፋይዳ የለውም። ለመላው ዓለም በዚህ መልኩ ድምጻችንን ማሰማታችን እጅግ ጠቃሚ ነው::ወያኔዎች አገር ካላፈረስን ብለው በየቀኑ በውጭ አገር ጎዳናዎች ሲንደባለሉ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል መሰል ሰልፎችን በየሳምንቱ መደጋገምም ይኖርብናል::
ከአገራችን የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን መዘምር ከፊት አድርገን የመጣብንን ወቅታዊ ፈተና የምንወጣው አንዳችን እንደ ሺ በመሆን ብቻ ነው::ይበልጥ ድምጻችንን ማሰማት ግድ ይለናል:: ተቃውሞአችንን ከፍ ማድረግ ይኖርብናል::
ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ዙሪያችንን በንቃት እንጠብቅ:: የሚያጠራጥር ነገር ስንመለከት ለህግ አካላት በፍጥነት እናሳውቅ:: ሳንቀደም እንቅደም:: በየቀኑ በተለያዩ ከተሞች በአሸባሪው ሕወሓትና የምእራባውያን ፍርፋሪ ተቀላቢዎች እጅ በቁጥጥር ስር ዋሉ በሚል የምንሰማቸው ቁሳቁሶች ለሠርግ ሳይሆን ለለቅሶ፣ ለሳቅ ሳይሆን ለሃዘን የተከማቹና ጥቅም ላይ ሊውሉ የተዘጋጁ እንደሆነ ጠንቅቀን ልናውቅ የግድ ይለናል::
ይህ እንደመሆኑም‹‹ነግ››በእኔ በሚል ስሜት ሁላችንም አካባቢያችንን ከወትሮው በተለየ ቀን ከለሌት መጠበቅ፣ ወንጀለኞችን መንጥረን ማውጣትና ማጋለጥ ይጠበቅባናል::ለራስ ነውና ፍተሻን ጨምሮ ለፀጥታ አካላት ተባባሪ መሆንም ይገባናል:: ኢትዮጵያ በእጃችን እንደመሆኗ ከሁሉ በላይ በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ከልዩነት ግድግዳዎች የበለጠ የአንድነት ድልድዮችን መስራትና በታላቁ የዓድዋ ድል መንፈስ መተባበር ግድ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይኖርብናል::
የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባችን በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ የሃሳብ ልዩነቶች በነፃነት እየተደመጡ አገር የዴሞክራሲ ጮራ እንድትሆን፣ ከአሳፋሪውና ከአሸማቃቂው ድህነት ለመገላገል፣ ዜጎች ከስደት ይልቅ በአገራቸው በመረጡት ስፍራ እየኖሩና እየሠሩ ሀብት እንዲያፈሩ አንድነት ማጠናከር እና ለህልውና ትግል በጋራ መቆም የግድ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ እንዳሉትም፣ “ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም ነው፤ የነጻነት ምልክት ነው። አልጠራጠርም፣ የእኔ ትውልድ ለአሸናፊ ስሙና ለነጻነት ምልክቱ የሚጠበቅበትን ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር መዝገብ ላይ በወርቅ ብዕር ያትማል”:: ይሄን ብለውም የፍጻሜውን ጅማሬ ሊያበስሩ ወደ ግንባር ዘምተዋል::
ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ሁሉ ታሸንፋለች::ዳግምም ታብባለች::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2014