አላዋቂ ሰው የከበረውን ታሪኩን እንደ ተረት ቆጥሮ ሲዘባነንና የአባቶቹንና የእናቶቹን የጀግንነት ትርክቶች እያጥላላ ራሱን አነሁልሎ ሌሎችን ሲያነወልል የተመለከቱ አበው፤ «በአላዋቂ ቤት ታሪክ ተረት ነው፤ አርበኝነትም ጀብደኝነት ነው» በማለት የጥበብ ሞገስ በተላበሰ አባባላቸው ትዝብታቸውን ይገልጻሉ። እውነት ነው ዓለም አቀፍ አድናቆት ላተረፈውና ለዓለማችን ጥቁር ሕዝቦች በሙሉ እንደ ዋና የነጻነት መልህቅ ለሚቆጠረውና እኛም ባለጉዳዮቹ «ነዎር» ብለን በአክብሮት ከወንበራችን ላይ ልንነሳላቸው ለሚገቡ አድዋን መሰል ሀገራዊ ጉዳዮቻችን የተዥጎረጎረ አመለካከት ባልነበረን ነበር።
ስለ አድዋ ጦርነትና የድል ታሪክ፣ ማስረጃዎችንና ቁጥሮችን እያጣቀሱ ለመተንተን የጋዜጣው አርብ ጥበት በእጅጉ እንደሚፈታተነኝ ስለተረዳሁ ሃሳቤን ይጠቀልልኛል ብዬ ያሰብኩት ለዚህ ጽሑፍ የሰጠሁት «የአድዋ ድልን ስንዘክር» የሚለው ሀረግ ነው። የአድዋ ድልን ለምን መዘከር አስፈለገ? ይህ ታላቅ ሀገራዊ ኩራታችን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ደብዝዞ እንዲቆይስ ማን ምን ሚና ተጫውቶ ነበር?
የአድዋ ድል ዝክር የወደፊት ዕጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ይችል ይሆን? እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች ከጋዜጣ ጽሑፍ በዘለለ ሕዝበ ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች ላይ በአግባቡ ሊወያይባቸው ይገባል። «በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ አኩል ይቆጠራል» እንዲሉ እኛ ተቀዳሚ ባለጉዳዮቹ የአድዋን ድልን ስናከብር የኖርነውና ዛሬም የምናከብረው በተባበረ ልብ ሳይሆን በተከፋፈል አመለካከት ነው። አንዳንዱ የአድዋ ድል ጉዳይ ሲነሳ የምኒልክም ስም አብሮ መነሳቱ ስለማይቀር ይህንን ስም በሰማ ቁጥር እንደ ዕንቆቆ እየመረረው ሲንገፈገፍ እናስተውላለን። አንዳንዱም «የአድዋ ጉዳይ ለእኔ ምኔ ነው?» በማለት «ውሻን ምን አገባው ከእርሻ» እያለ በራሱ ሲተርት እናደምጣለን። አንዳንዱም የአድዋን ድል እያጣጣለ «ጠርጥር ገንፎ ውስጥ ይገኛል ስንጥር» እያለ ይራቀቃል።
ያም ሆነ ይህ የአድዋን ድልና የድሉን ባለቤቶች ታላቅ ገድል ተንትነውና አስተንትነው «ተዓምራዊ» ድሉ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የሀገራችን ልሂቃን ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በተለይ ግን የውጭ ሀገራቱ ምሁራን ያደረጉት ጥረት ሺህ ጊዜ ሺህ ይልቃል ባይ ነኝ። የወራሪው ሀገር የጣሊያን ጸሐፍት እንኳ ሳይቀሩ ስለ ጦርነቱና ስለ ፊት ቀደም መሪዎቻችንና ጀግኖቻችን የጻፏቸው መጻሕፍትና የምርምር ሥራዎች ከብዛታቸው የተነሳ ለመዘርዘር ያዳግታል። በኋለኛው የዕድሜ ዘመናቸው ባልተገባ ድርጊታቸው ደማቁን የሕይወታቸውን ታሪክ በማጠየም ሀገርን ቢያስቀይሙም ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር የመጀመሪያ(?)
የሚሰኘውን ጦቢያን የመሰለ ልቦለድ መጽሐፍ የደረሱት ተጠቃሹ የብዕር ሰውና ምሁሩ አፈወርቅ ገ/የሱስ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ» በሚለው መጽሐፋቸው የአድዋን ድል የገለፁት እንደሚከተለው ነበር፤ «ካዷ (ከአድዋ) ጦርነት ወዲህ የኢትዮጵያ ስም ፀሐይ ባየው ሁሉ አገር ታወቀ። ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ምንም ከጥንት ከመሰረት ጀምራ ራሷን ችላ ብትኖርም ከቶውንም በነፈርዖን ጊዜ ተባሕር ወዲያ እስከ ምስር (የዛሬዋ ግብፅ) ባንድ ወገንም አደን ካረብ አገር ተሻግራ ብትገዛ በኤውሮፓ ስሟ [እጅግም አልታወቀም] ነበረ። በዳግማዊ ምኒልክ ኃይል፣ በዳግማዊ ምኒልክ እውቀት ዛሬ ግን ኢትዮጵያ የእውነተኛ ስሟ ተገለጠ፤ በእውነተኛ ማዓርጓ። የኢትዮጵያ ዓለም ካዷ (ከአድዋ) ጦርነት ወዲህ ተጀመረ። . . . እውነትም ከዚያ ወዲህ ኢትዮጵያ አበበች» በማለት የሀገራቸውን ድንቅ የታሪክ እውነታ አድምቀው ጽፈዋል።
የዚህን ምስክርነት እውነታ ለማረጋገጥ የፈለገ ሰው የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመንና የሩሲያ ቤተ መዘክሮችን ቢጎበኝ እውነታውን በሚገባ ማረጋገጥ ይችላል። በሴሜቲክ ቋንቋዎችና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ብዙ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ኤንሪኮ ቼሩሉ የተባሉ ታላቅ ኢጣሊያዊ ምሁር የአድዋን ድል በተመለከተ እንዲህ ጽፈው ነበር፤ «ኧረ እንዲያው አውሮፓ የምን ዓይነቱ ጅል መሰብሰቢያ ነሽ። ለምን ይሆን መሣሪያ ሠርተው ለሌላ የሚሰጡብሽ? ጣሊያን ራሱ ባመጣው ጥይት፣ ራሱ በሰራው ጠብመንጃ፤ በራሱ ትምክህት ምኒልክና ሠራዊቱ ልክ እንደ ቆሎ ጠበሱት።» ፒተር ማልኮም ሆልት የተባሉ በሱዳን መሃዲስቶች ላይ በርካታ ጥናት ያቀረቡት ምሁርም ስለ ምኒልክ በጥበብ የተከሸነ አመራርና ስለ አድዋ ድል ውጤት በመጽሐፋቸው ውስጥ የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር፤ «ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አርቀው የሚያስቡና አንዳንዴ እንደ ጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ዓይነት በርካታ አማራጮችን እያዩ የመንቀሳቀስ ክህሎት ያላቸው ዲፕሎማት ናቸው። ከማንም የማይወግነው የውጭ ፖሊሲያቸው የአድዋን ድል ሲያጎናጽፋቸው ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ያላትን ተሰሚነት እና ኃይል አጠናክሯል።
በተጨማሪም ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝና ከሱዳን ብዙ ጥቅሞችን በድርድር ለማግኘት አስችሏታል። እናም ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ምክንያት ብዙ ቀውስ ውስጥ ብትገባም ራሷን አጠናክራ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍ ባደረጋት መልኩ እንድትወጣ ያስቻላት በመሪዋ በምኒልክ የውጭ ፖሊሲ ንድፍ ክህሎት ነው ብሎ መስማማት ይቻላል። የግዛቷ ደህንነትም ምኒልክ በሚመሩት ዘመናዊ እና በሚገባ በታጠቀ ጦር አማካይነት ተጠብቋል» የምኒልክን ስብዕናና የአድዋን ጦርነት በማያያዝ ከዘገቡት የዘመኑ በርካታ የአሜሪካ ጋዜጦችና አምደኞች መካከል ዊሊያም ኢ. ከርቲስ የተባሉ ጸሐፊ በቺካጎ ሄራልድ ጋዜጣ ላይ እ.አ.አ ሴፕቴምበር 24 ቀን 1903 ዓ.ም ምኒልክን አስመልክተው ቅኔዊ በሆነ አድናቆት ከጻፉት ረጂም አርቲክል መካከል የሚከተሉትን ዐረፍተ ነገሮች ለምስክርነቱ መደምደሚያ እንዲሆን መርጫለሁ፤ «ረጅም ዕድሜ አላቸው ከሚባሉት ከጀርመን፣ ከኢጣሊያ እና ከሌሎችም የአውሮፓ ነገሥታት ቤተሰቦች የዘር ሀረግ ጋር የምኒልክን እናነፃፀር ብንል በእውነቱ የሌሎቹ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ምኒልክ የሰለሞንን ክብርና ጥበብ ለማየት እየሩሳሌም ድረስ የሄደች ቅድመ አያት ያላቸውና በሕይወት የሚገኙ ብቸኛ ሰው ናቸው።» ለመሆኑ አድዋን በሚያክል የከበረ ታሪካችን እንዳንኮራና ያን የመሰለ ህያው ታሪክ በሠሩ መሪዎቻችንና ጀግኖቻችን እንድናፍርና እንድንሸማቀቅ አዚም ያደረገብን ማን ይሆን?
በእኔ አመለካከት ባለፉት ተከታታይ ሥርዓተ መንግሥታ ውስጥ የነበረው መሻኮትና የሥልጣን ጥሎ ማለፍ ፍትጊያ በቀዳሚ ተወቃሽነት ሊጠቀስ ይገባዋል ባይ ነኝ። የዘመነ ልጅ ኢያሱን፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱንና የዓፄ ኃይለ ሥላሴን የሥልጣን ግብግብና ጥሎ ማለፍ ማስታወስ ይቻላል። ከእያንዳንዱ መሪ ጎን የወገኑት ሹማምንት ሤራም አብሮ ሊታይ ይገባዋል። የቀዳሚ መሪን ዝና ማግዘፍ በተከታዩ ዙፋን ተረካቢ ዘንድ እንደ ግርዶሽ እንዳይቆም ለመከላከል ሲባል የአድዋ ድል፣ የምኒልክ፣ የጣይቱ እና የጀግኖች አርበኞቻችን ገድል ጎልቶ እንዳይነገር የመሪዎቹና የጋሻ ጃግሬ ሹማምንቱ የእጅ ዙር ጫና ለዚህ ታላቅ ድል መደብዘዝ አስተዋፅኦውበቀላሉ የሚገመት አልነበረም።
በዘመነ ደርግም እንዲሁ ታላቁን የአድዋ ድል አሳንሰንና እየተሽኮረመምን ብናከብረውም የፊውዳሊዝም ሥርዓተ ማኅበር በአገዛዙ የተጠላና የተወገዘ ስለነበር የአድዋ ድል፣ ምኒልክ፣ ብልኋና ጀግኒት ጣይቱ ከጦር ሜዳ ጀግኖች ጋር እንዲታወሱ ተፈቅዶ የነበረው በድርበቡ ነበር። የደርግ መንግሥትማ እንኳንስ የሩቅ ዘመኑን የአድዋን ክብር ለማጉላት ቀርቶ የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ድል የተመታበትን የኋለኛውን የድል ቀን ከሚያዝያ 28 ወደ መጋቢት 28 ለውጦት አልነበረም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ቢሆን በርካሽና በጊዜያዊ የፖለቲካ ንፋስ በሚፍገመገሙ የራስ ክብር ጠል በሆኑ አንዳንዶች ዘንድ የአድዋ ድልም ሆነ ምኒልክ፣ ጀግኒቷ ጣይቱም ሆኑ ዋነኛ የድል ብሥራት አብሣሪ ጀግኖች አርበኞች እንደ ጠላትና ወራሪ የተቆጠሩበት፣ የመታሰቢያ ሐውልቶችም እንዲፈርሱ ሰልፍ የተወጣበት፣ የአድዋ ጀግንነት የጥፋት ተልዕኮ ተደርጎ የተቆጠረበት፣ድሉም «ለእኛ የተረት ያህል የቀለለ ነው» ተብሎ መዘባበቻ የሆንበት ጊዜ አልነበረም? ብርሃን እየፈነጠቀልን ላለው ሰሞንኛው ሀገራዊ ለውጥ ገለታ ይግባው። ታሪክ ለወደፊቱ ለሚዘክራቸው ለቁምነገረኞቹና ክብር ለሚገባቸው «የጉዞ አድዋ» ሃሳብ አመንጭዎችና ተጓዥ ወጣቶችም ፈጣሪ ዕድሜያቸውን ያለምልምልን።
በልዩ ጥበባዊ ተስረቅራቂ ዜማዋ «ሰው ተከፍሎበታል» እያለች አድዋን በልባችን ውስጥ ላተመችን ለተወዳጇ ድምፃዊት እጅጋየሁ (ጂጂ) ሽባባውና ለመሰል ከያኒያን ረጂም ዕድሜ ያድልልን። የሀገራችን ሚዲያዎችም በጎ ጥረት ሳይዘነጋ የአድዋ መንፈስ ከምን ግዜውም በተሻለ ሁኔታ መነቃቃት እየታየበት ነው። «የአድዋ ዩኒቨርስቲ»ን በተመለከተ ግን መሠረቱ ሲጠብቅ እናመሰግናለን። ታሪካችንን እየሸረሸረ፣ የአድዋን መሰል ድልና ክብራችንን እያደበዘዘና እያደነዘዘን ያለውና ስቃያችንን እያባባሰብን ያለው የውስጥ በሽታችን ብቻ እንዳልሆነ ግን ልንገነዘብ ይገባል። እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ስላለው የውጭ ጥቃትም ጎን ለጎን ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። ሉላዊነት (Globaliazation) ነባር ባህሎችንና ዕሴቶችን፣ የንግድ ሥርዓትን፣ የካፒታል ዝውውርን፣ የዕውቀትና የሕዝቦችን የተገደበ እንቅስቃሴ «አርነት አውጥቶ» ዓለምን በአንድ መነፅር የመመልከት ወቅት ወለድ ፍልስፍና መሆኑ ይታወቃል። የፍልስፍናው ዋና ማስፋፊያ ደግሞ የተራቀቁት የመገናኛና የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በፈጣን ሁኔታ እየተዋወቁ ያሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች ናቸው።
ዛሬ ዓለማችን እያስተናገደችው ያለው የቅኝ ግዛት ወረራ በመደበኛ የጦር ሠራዊት የሚመራ ሳይሆን ስልቱ ያነጣጠረው በዋነኛነት በባህል ወረራ ላይ ነው። የጦርነቱ ፊትአውራሪ አዝማቾች ደግሞ መገናኛ ብዙኃን፣ በቢሊዮን ቁጥር የሚገመቱ የድረ ገፅየሀገራቸውን የአርበኝነት ገድል ከማንበብና ከማጥናት ይልቅም የሆሊውድን ተዋናዮች፣ የእንግሊዝን የእግር ኳስ «ጀግኖች» እና የፋሽን ዲዛይነሮችንና የፊልም ባለሙያዎችን ታሪክ፣ ገድልና የግል ሕይወት ቢያነቡና ቢከራከሩ ይመርጣሉ። ሉላዊነት እንደ ብዙ ምሁራን አገላለፅ (A Blessing in Disguise) ወይንም በእኛው አገላለፅ «በረከተ መርገም» እንደምንለው ሆኖብናል።
ካላመዛዘን በስተቀር ጥቅሙም ላቅ ያለ ጉዳቱም የገነነ ስለሆነ። የአፍሪካ መሪዎቻችን በወሰኑት አህጉራዊ ውሳኔ ላይ ሂሳዊ ክርክር ለመክፈት ወቅቱ ያለፈ ቢሆንም አድዋን ከመሰለ ታላቅ የተጋድሎ ታሪክ አንፃር የዓለም አቀፉንና የአህጉራችንን መሪዎች አካሄድና ውሳኔዎች ጠቀስ አድርጎ ማለፉም አይከፋም። በ2063 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች አንድ የተባበረ የፖለቲካ ማኅበረሰብ፣ የተጠናከረ የጋራ ባህል፣ ውርስና ዕሴቶች ለመፍጠር እንደተስማሙ ይታወቃል። ይህ ህልም ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች ሀገራት መሪዎችም በየአህጉራቸው ክልልና ቀጣናዎች ለመተግበር የሩቅና የቅርብ ጊዜ ዕቅድ ነድፈው ለተግባራዊነቱ በትጋት እየሰሩ ይገኛል። ይህ አንድ የመሆን ፍላጎት እውን ተግባራዊ ቢሆንና በየሀገራቱ ፈጥኖ ቢተገበር ምን ውጤት ሊያስከትል ይችል ይሆን?
የእኛ የምንለውና በዘመናት ውስጥ ሥር የሰደደው የአድዋና የአርበኝነት መንፈስስ ይደበዝዛል ወይንስ ይፈካል? መልካም ብለን አክብረን የያዝናቸው ሀገራዊ ዕሴቶቻችንስ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል? በዜጎቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን የማንነት ቀውስስ እንደምን መቋቋም ይቻላል። ሉዐላዊነትንስ ከሀገራዊ አርበኝነት ጋር እንደምን አዛምዶ መጓዝ ይቻላል? የዕንቆቅልሹን ፍቺ ጉዳይ አጥብቀን ልንወያይበት ይገባል። ባሕር ተሻግሮ በመምጣት ማንነታችንን ንቆና አዋርዶ ሊያጠፋን የተፈታተነን የኢጣሊያ ጦር አባቶቻችን በአድዋ ተራሮች ሥር አራግፈውት አልፈዋል። ይህ ታሪክ ማንም ምንም እያለ ቢቃዥ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም። መጣንባችሁ ታጠቁና ቆዩን በማለት በግፍ የወረሩን ጠላቶቻችንን በተመለከተ ለጀግኖቻችን ክብር ይሆንና አዋርደው መልሰዋቸዋል። ፍርድ ጥሶ በእብሪት ሀገር የሚያጠፋውን እብሪተኛ ጠላት ወሮበላ ቢሉት ስሙ ነው።
ልንቆጣጠረው የማንችለውን የዘመናችንን የሉዐላዊነት ወረራስ ምን ስም እንስጠው? ውጤቱስ ውሎ አድሮ ምን ሊሆን ይችላል? የሆነውስ ሆኖ ሀገራዊው የአድዋ መንፈስ በአግባቡ እየጎለበተ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ምን መደረግ ይገባዋል? የሚከተሉት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ቢወስዱ መልካም ይመስለኛል። ዋናው ባለድርሻ መንግሥት ነው። ሕዝቡ መንግሥትን መንግሥት ብሎ ፈቃዱን የለገሰው የዕለት ዳቦ እንዲያቀርብለት ብቻ ሳይሆን የሀገሩን ሉዓላዊ ክብር እንዲያስጠብቅለትና የጀግንነቱን ውርስ አፅንቶ እንዲያሸጋግርለት ጭምር ነው። የአንድ ሕዝብ የአርበኝነት ስሜት ከመንፈሱ ውስጥ ከጠፋ ተስፋውይደበዝዛል። ኩራቱም ይመነምናል። ብሔራዊ ስሜቱም ይቀዛቀዛል።
በውጤቱም ልማትም ሆነ ሀገራዊ የዜጎች ደህንነት ለአደጋ መጋረጡ አይቀርም። ስለሆነም የሀገር ባለውለታ አርበኞችና አርበኝነት በክብር ተጠብቀው ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። በወጣቱ ትውልድ ውስጥም ያው መንፈስ እንዲተላለፍ ብዙ መሠራት ይኖርበታል። የአርበኝነት መንፈስ የሚጠበቀውና ቀጣይነት የሚኖረው ዜጎች በየተሰማሩበት የተግባር መስክ ከራስ ባለፈ ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ፈጽመው ለሚያበረክቱት የአርበኝነት አስተዋጽኦ መንግሥት በዕውቅናና በሽልማት አጅቦ በይፋ ሊያመሰግናቸውና ለልዩ ልዩ ዘርፎች አርበኞች ባበረከቱት አስተዋፅዖ ልክ «ጀግኖቻችን» በማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕዝቡ ስም አክብሮቱን ሲገልፅላቸውም ነው። በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት አንድ ጀብድ የፈፀመ የሠራዊቱ አባል በብዙኃን ፊት እንደሚሾመውና እንደሚሸለመው ሁሉ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኪነ ጥበባትና ሥነ ጥበባት ዘርፍ፣ በግብርናና በንግድ፣ በሚዲያ ዘርፍና ወዘተ. በመሳሰሉት መስኮች ሀገርን የሚያኮራ የጀግንነት ሥራ ላከናወኑ የሕዝብ ልጆች ዕውቅናና ሽልማት ሊሰጥ ይገባል።
በዚህ ጉዳይ ንጉሡን የሚተካካል መሪ እስከዛሬ አልተነሳም። በልዩ አደረጃጀት ተቋቁሞ በየዘርፉ ብሔራዊ ሽልማት ሲሰጥ የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅትን አስታውሶ ማለፉ ብቻ ይበቃል። ሀገራዊ አቅም በፈቀደ መጠን በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች በጦር ሜዳ መስዋዕትነት ለከፈሉትና በተለያዩ ሀገራት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ተሰልፈው ሀገራቸውን ላኮሩና ላስከበሩ አርበኞችም ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግ ይገባል። በአርበኞችና በዘማቾች ስም የተቋቋሙ ልዩ ልዩ ማኅበራትም በአንድ የፌዴሬሽን ጥላ ሥር ተሰባስበው ተገቢው ድጋፍ ቢደረግላቸው መልካም ውጤት ሊገኝ ይችላል።
የመታሰቢያ ሐውልቶች፣ ሙዚዬሞችና ዓመታዊ ክብረ በዓላትም ሀገራዊ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ ቢዘከሩ የወጣቱን የአርበኝነት መንፈስ ከፍ ለማድረግና ለማስቀጠል ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል። የሲቪልና የሙያ ማኅበራትም በዋናነት የተቋቋሙበትን ዓላማ የሚያስፈፅሙት በወገንተኝነት ለቆሙለት ቡድን ከመሆኑ አኳያ በየዘርፋቸው ከሚወክሉት ቡድንና ሙያ በምሳሌነት የሚጠቅሷቸውን የሀገርና የሕዝብ ጀግኖች ይፋ የማድረግ፤ በአቅማቸው ልክ ዕውቅና በመስጠት ሊሸልሟቸውና በስማቸው መታሰቢያ እንዲቆምላቸው አጥብቀው ሊሟገቱና ሊተጉ ይገባል።
የምርምርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ የአርበኝነትን መንፈስ ለማስረፅና ከሌሎችም መሰል የውጭ ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት አቅማቸውም ሆነ የኃላፊነታቸው ወሰን የተመቻቸ ስለሆነ «የክብር ማዕረግ» መስጠቱን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ወጣቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው አሰቀድሞ በሀገራችን ይደረግ እንደነበረው የብሔራዊ አገልግሎት ግዳጃቸውን እንዲወጡ ሥርዓት ቢዘረጋ መልካም ነው።
ወቅቱ ለሚጠይቀው የአርበኝነት መንፈስ መነቃቃት ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት ይቻላል። በሀገሪቱ የሚሰጠው የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር እና የታሪክ ትምህርቶችም በሚገባ ተፈትሽው ለሀገራዊ የአርበኝነት መንፈስ መቀጠል በሚያስችል ደረጃ ሊሻሻሉ ይገባል። ዜጎች ሁሉ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራዊ የአርበኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻልም የጎጠኝነትን፣ የቡድናዊነትንና የከረረ የብሔረተኝነትን ስሜት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በአግባቡ ሊስተናገዱ ይገባል። የአድዋን ድል ስንዘክር እነዚህን ጉዳዮች አብሮ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። ሰላም ይሁን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
በጌታቸው በለጠ – (ዳግላስ ጴጥሮስ)