ዓለም ስለ ኢትዮጵያ እኛ ከምናውቀው በላይ ታውቃለች። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቂ መረጃ አላት። ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ፣ አሸባሪው ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን እንደነበር፤ አሁንም ምን እያደረገ እንደሆነ አሜሪካና ግብረአበሮቿ በደንብ ያውቃሉ።ጥልቁ ነገር እውነታውን መቀበል አለመፍቀዳቸው ነው። ይሄ ብቻ አይደለም በአሁኑ ሰዓት ሕዝብ መንግሥትን ደግፎ ቡድኑን ለመታገል አደባባይ የወጣበትን ምክንያትና ሕዝብ ከመንግሥት መንግሥትም ከሕዝብ ጋር ያበሩበትን እውነት አልሳቱትም ግን ከዚህ እውነት በተቃራኒ ናቸው።
አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በተመለከተ ሀቁ አልጠፋቸውም፤ እውነት የጠፋቸው መስለው የሚደናበሩት ሆን ብለው ነው። ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የተመሳሰለ አላማ ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያን የማፈራረስ፣ ደካማና የይስሙላ መንግሥት የመፍጠር አላማ ስለተዋሀዳቸው ነው። ይሄ አላማቸው እንዲሰምር ደግሞ አስታራቂ መስሎ መግባት አዋጪ መስሎ ስለታያቸው ነው።አሁን ላይ በአሸባሪው እና በኢትዮጵያ መካከል ለመግባት የሚታትሩት።
የእባብ ልጅ እባብ ነው..የእባብ ልጅ ዕርግብ ሆኖ አያውቅም። የእባብ ልጅ ግብሩን አይረሳም። ዛሬ ላይ እየነደፉን ያሉት፣ ዛሬ ላይ እያደሙን ያሉት አሸባሪው ሕወሓት ወልዶ ያሳደጋቸው ጀሌዎቹ ናቸው። ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ መከራ እየሆኑ ያሉ ኃይሎች ትናንትና በቡድኑ የተፈጠሩ መሰሪዎች ናቸው። አሜሪካና አሸርጋጅ የውጭ ኃይሎች ዛሬ ላይ የብዙኃኑን ኢትዮጵያ ሕዝብ እውነት ገፍተው ከነፍሰ በላው ቡድን ጎን የቆሙት የባህሪ አንድነት ስላላቸው ነው።
አሸባሪው ሕወሓት አድጎ አሁን ላለበት የደረሰው በአሜሪካ ነው። ይሄን ለማወቅ ደግሞ እንዴት ብሎ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ጥቂት አመታትን ወደ ኋላ ሄዶ ማየት ይበቃል። ቡድኑ ሕዝብ የመረጠው ድርጅት አይደለም። በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን የያዘ ቡድን አይደለም። ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም በአሜሪካ ከፍያለ ድጋፍ ሥልጣን የያዘ ነው። በሥልጣን በነበረባቸው ሃያ ሰባት አመታት ውስጥም ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት እንደነበረ በግልጽ አሳይቷል። አሁን ድረስ መከራ እያየንባቸው ያሉ ስቃዮቻችን በዚህ ከሀዲ ቡድን የተፈበረኩ የተንኮል ሀሳቦች ናቸው።
ትናንትና በነአሜሪካ ታቅፎና ተደግፎ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በምክንያት ነበር፤ ዛሬም አንቅሮ በተፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥላቻ ውስጥ አሜሪካ ገብታ ላሸማግል ማለቷ አላማው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው። አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወሓት አስተሳሰብ ነፃ ለመውጣት እየታገለች ነው። እውነትና ንጋት እያደር መጥራታቸው አይቀርምና ኢትዮጵያዊነት በመከራ ውስጥ ተፈትኖ የሚወጣበት ጊዜ ላይ ይገኛል። በዚህ አገር የመፍጠር ሂደት ውስጥ ሕወሓት ከነአስተሳሰቡ፣ ከነክፋቱና ከነእብሪቱ ወደ ኋላ እየቀረ ኢትዮጵያዊነት እየለመለመና እየጎመራ የመጣበት ሰሞን ላይ ነን።
ኢትዮጵያ ምን ፈልጋና ምን ይዛ እንደምትታገል ዓለም ያውቀዋል። ኢትዮጵያ እውነትን ፈልጋና ፍትህን ሽታ ነው እየታገለች ያለችው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪውን ሕወሓት እንደማይፈልገው በግልጽ ያሳወቀ ቢሆንም ግን ጥቂት ራስ ወዳድ አገራት ይሄን የሕዝቦች ስሜት ወደ ጎን ብለው ለነፍሰ በላው ቡድን ሽፋን በመስጠት ከማይችሉት ኢትዮጵያዊነት ጋር ግብ ግብ ውስጥ ናቸው። አሁን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለአሜሪካና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ለቀባሪ የማርዳት ያክል ሹፈት ነው የሚሆነው።
ምክንያቱም ከትናንት እስከዛሬ በዚች አገር ላይ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝቦች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ያውቃሉና ነው። አሁን ላይ የኢትዮጵያውያን አላማ ምን እንደሆነ፣ ምን ፈልገን እንደምንታገል ዓለም ያውቀዋል። አሁን ላይ የመንግሥትም ሆነ የዜጎች ፍላጎት፣ አላማና ሀሳብ ምን እንደሆነ ከጅምሩ ጀምሮ ይታወቃል።እየሆነ ያለው ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ምክንያቱም አሸበሪው ሕወሓትም ሆነ አሜሪካ የኢትዮጵያን ከፍታ ማየት አይሹምና ነው። አላማና እቅዳቸው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የራሳቸውን ቤት መስራት ነው።
ሁሉን ትተን እንኳን ሰሞነኛውን የቢቢሲና የሲኤን ኤን የሀሰት ዘገባ ብናይ እንኳን ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንደርስበታለን። ‹አዲስ አበባ ተከባለች፣ ሕወሓት አዲስ አበባን እየተቆጣጠረ ነው› የሚል ዘገባ በቢቢሲና በሲኤን ኤን በኩል ከሰሞኑ ወጥቶ ነበር። እነሱ እንደሚሉት የሆነ ነገር እዚች አገር ላይ ምንም የለም። አዲስ አበባ ተከባለች ሕወሓት አዲስ አበባን እየተቆጣጠረ ነው የሚሉት የሀሰት ወሬ ከየት ያመጡት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው። በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ሁላችሁም የምታውቁት ነው። አዲስ አበባ በሕወሓት ኃይሎች ተከባለች ተብሎ የወጣው ዘገባ ምን ያክል ከእውነት የራቀ እንደሆነ እናንተ ምስክር ናችሁ።
በአሁኑ ሰዓት ሕወሓት አይደለም አዲስ አበባ ሊገባ ቀርቶ ካለበት ስፍራ እንኳን መሸሽ አቅቶት በመከላከያ ሰራዊታችን አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ያው እንደምታውቁት አሜሪካ የምታወራው የሕወሓትን ሁኔታ እያየች ነው። ሕወሓት ንጹሃንን ሲገድልና ሲያፈናቅል የአሜሪካ ድምጽ አይሰማም በተቃራኒው በሕወሓት ላይ የመከላከያ ሰራዊት ርምጃ ሲወስድ አሜሪካና ምዕራባውያን ዝም ያለ አፋቸውን ይከፍታሉ። የሰሞኑ የሀሰት ዘገባው ከዚህ የመነጨ ነው። የአሜሪካ ድንፋታ የኢትዮጵያውያን የማሸነፍ ምልክት እንደሆነ ነው የምረዳው። አሁን ላይ ሕወሓት ኃይሉንና አቅሙን ጨርሶ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።
ሰሞነኛው የአሜሪካ እገዳና የሀሰት ዜናም የሕወሓትን ውድቀት ተከትሎ የመጣ ነው። በሕወሓት ፍጻሜ ውስጥ ገና የምንሰማቸው ሌሎች የተቃውሞና የቅሬታ ድምጾች ይኖራሉ። ከሆነብን በላይ ሌሎች እገዳዎችና ጫናዎች ሊበረቱብን ይችላል፤ እኛ በአንድነት ወደ ፊት ማለት ነው የሚኖርብን። ከፊታችን አገር አለን..ከፊታችን የምናየው እውነት አለ፣ ልንደርስበት የምንሮጠው ትንሳኤ አለን..ፍጻሜያችን እርሱ ነው። እርሱ ጋ ሳንደርስ የሚያቆመን ምድራዊ ኃይል የለም።
የአሜሪካም ሆነ የምዕራባውያን ጩኸት ከሩጫችን ሊያደናቅፈን አይገባም። በጀመርንው ጎዳና መቀጠል እንጂ ለምንም ነገር እድል መስጠት አይኖርብንም። በዚያም በዚህም ጩኸት ቢበረታብንም የያዝነው አላማ ትልቅ ነውና በአላማችን ኃይል ልንበረታ ይገባል እላለሁ። መከራዎቻችን ሁሉ የአሸባሪው ሕወሓትን ውድቀት ተከትለው የተከሰቱ ናቸው። ጊዜው ለአሸባሪው ሕወሓት የምጽአት ቀን፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የትንሳኤ ዋዜማ ነው። ሕወሓትን ጥለን በትንሳኤ ለመቆም ሰሞነ ህማማት ላይ ነን። በትንሳኤ ዋዜማ ሁሌም ስቃይና መከራ አለ። አሁን ላይ እየሆነብን ያለው ነገር የሳቃችን ዋዜማ ነው። ይሄ ጊዜ ለአሸባሪው ሕወሓትና ለአስተሳሰቡ የፍጻሜ ዋዜማ ነው። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጠላቶች ዳግም እንዳይነሱ ሆነው እየተቀበሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በመከራዎቻችን ደስ ሊለን ይገባል እንጂ ተሸንፈን ወደ ኋላ ልናፈገፍግ አይገባም ምክንያቱም እያሸነፍን ነውና።
ከእንግዲህ መከራዎቻችን አይኖሩም። መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ጊዜ ነው። እርግጥ እንደናቀፍ ይሆናል፣ በክፉ እንፈተን ይሆናል መጨረሻችን ግን በብርሃን እንደሚሆን አትጠራጠሩ። የመጨረሻ ቀን ሁልጊዜም መከራ አለው። ሊነጋ ሲል እንደሚጨልም ሁሉ በአዲስ ቀን ሰሞን መፈተን ግድ ነው። ከእንግዲህ እኛ እንጂ የአሸባሪው ሕወሓትና አሸርጋጆቹ አይኖሩም። ሰሞነኛውን የምዕራባውያን ጫጫታ ከዚህ የዘለለ ትርጉም የለውም።
የቢቢሲና የሲኤንኤን የሀሰት ትርክትም ምክንያቱ የሕወሓት ስንብት ነው። ጊዜው ለሕወሓት ስምንተኛው ሺ ነው። ድጋሚ በሰውነት፣ ዳግም በአስተሳሰብ ወደዚች ዓለም አይመጣም። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያን ይሰናበታታል። በመጨረሻው ሰዓት አሸናፊዎች መከራ ይበዛባቸዋል..መከራ በገጠመን ቁጥር እያሸነፍን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። በዚህ ሳምንት ብቻ ከውጭው ማህበረሰብ በተለይ ከአሜሪካ ብዙ ነገር ደርሶብናል እነዚህ ሁሉ መከራዎቻችን በጽናት የሚያቆሙን እንጂ የሚያብረከርኩን አይደሉም።
የአሸባሪው ሕወሓት ውድቀት ገና ብዙ ነገር ሊያሰማን ይችላል። በዚህ አንድ አመት ውስጥ የደረሱብን የውጭ ተጽዕኖዎች በቡድኑ የስቃይ ድምጾች የተፈጠሩ ናቸው። በዚህ አንድ አመት ውስጥ ከወደ አሜሪካም ሆነ ከወደ ምዕራቡ በኩል የተሰሙ የዛቻና የማስፈራሪያ ድምጾች የቡድኑ የድረሱልኝ ተማጽኖ የወለዳቸው ናቸው። የውጭ ጫናዎች በበረቱብን ቁጥር ሕወሓት እየሞተ እኛ እየተነሳን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። አሜሪካ በሕወሓት ውድቀት ውስጥ እንጂ መነሳት ውስጥ ጮሀ አታውቅም። ስለዚህ በጀመርነው ጎዳና መቀጠል ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወሳኝ ነው።
የአሜሪካ ድምጽ ወንበዴ የማንገስ ድምጽ ነው። በአሁኑ ሰዓት አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ የሚሆን የፍትህ ድምጽ የላቸውም። የፍትህ ድምጽ ያለው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ነው። ይሄ ድምጽ ኢትዮጵያን ካልፈጠረ ሌላ ኢትዮጵያን የሚፈጥር ድምጽ የለም። አሸባሪው ሕወሓት አገር ለማፍረስ የተነሳ ቡድን ነው እነአሜሪካ ደግሞ ይሄን ቡድን ከበው በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ እጣ የሚጣጣሉ ናቸው። ስለዚህ ከውጭው ማህበረሰብ የምንጠብቀው አንዳች ፍትህ የለም ፍትህን ከሕዝባችን ጋር ሆነን እናመጣዋለን።
አሜሪካ ከትናንት እስከዛሬ አሸባሪውን ሕወሓትን ስትደግፍ ነበር። የሕወሓት ከሀዲ ቡድን የሰሜን እዝን ወግቶ ጦርነት እስካወጀበት ጊዜ ድረስ በርካታ ኢ ሰብዐዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም አሜሪካንን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መልስ ዝምታ ነበር። በማይካድራና በአፋር ክልሎች በንጹሃን ላይ ሞትና ስቃይ ሲፈጥር ቃል አልወጣቸውም። ጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሲወድሙና ሲዘረፉ የተናገረ አልነበረም። ሕፃናት ያለ ዕድሜአቸው ለውትድርና ሲመለመሉ፣ ሴቶች ሲደፈሩ ድምጹን ያሰማ የለም።
ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ ቁሳቁስ ጭነው የገቡ ተሽከርካሪዎች ደብዛቸው ሲጠፋ፣ ስንትና ስንት ግፍና በደል ሲፈጸም ያገባኛል ያለ አልነበረም። ከሰሞኑ እንኳን በሰሜን ወሎ ደሴና አካባቢዋ ላይ የተፈጸመውን የንጹሃን እልቂት እንዳላየ ማለፍን ነው የመረጡት። ይሄ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ ላይ እውነትን ይዞና ፍትህን ናፍቆ በሚታገለው የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አላስፈላጊ ነገር ለማድረግ መነሳት አይን ያወጣ ሴራ ከመሆን ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014