
አራት ኪሎ ከቡና ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ጀርባ ስምንት ሜትር ገባ ብሎ በሚገኘው እማማ ግምጃ ሮባ ቤት ተገኝቻለሁ። እማማ ግምጃ ከተፈጥሮ ጋር ሙግት የገጠሙ አዛውንት በመሆናቸው መምሸትና መንጋቱን አይለዩትም፤ ቢለዩትም ከቁብ አይቆጥሩትም። እስከ ከቀኑ ስድስት ሠዓት ድረስ ይተኛሉ። የሆድ ነገር ሆኖባቸው ሲርባቸውና ሲሞረሙራቸው ብቻ ይነሱና በቻሉት አቅም ሰርተው ርሃባቸውን ለማስታገስ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ ይላሉ። በጃንሆይ እና በደርግ ዘመን ከኖሩበት ሃያሁለት አካባቢ ወደ አራት ኪሎ ከመጡ 12 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በአሁኑ ወቅት ለሚኖሩበት ቤት በየወሩ አምስት ብር ኪራይ የመክፈል ግዴታ ቢኖርባቸውም አንዳንድ ጊዜ ገንዘቡ እንኳ ቢገኝ ሄዶ የሚከፍልላቸው ሰው በማጣታቸው ይቸገራሉ።
ላለፉት 12 ዓመታት ቤታቸው ታድሶ አያውቅም። በበጎ አሳቢ ግለሰቦች ለማደስ ቢሞከርም ከሌሎች ቤቶች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ሳይሳካላቸው ቆይቷል። ከምንም በላይ ግን ክረምት ሲመጣ ለእማማ ግምጃ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ይሉት ሆኖ ቁሩ ያስጨንቃቸዋል። ዝናቡ በላያቸው ላይ ሲወርድባቸው ጭቃው ያዳልጣቸዋልና። የኑሮ ዝቅታ ሲፈትናቸው ኖሮ፤ አሁንም ክንዱን አፈርጥሞባቸዋል። እስከ ዕለተ ሞት ላለመለየት የተማማለ ይመስል የጉስቁልና ሕይወት በእማማ ግምጃ ላይ ጎጆውን ሰርቶባቸዋል። ምንም እንኳን ከማለዳው ተፈጥሮ ፊት ባትነሳቸውም፤ የጊዜ ዑደት አልፈው ከዕድሜ መግፋትና እና ከጤና እክል ጋር ተዳምሮ ብርሃናቸውን ቀምታቸዋለች። ከአራት ዓመት ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ማየት ተስኗቸዋል።
ሰዎችን በድምጽ ካልሆነ በቀር መለየት ባይችሉም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደመጣሁ ስነግራቸው በእርጅና እና በኑሮ ጉስቁልና ከተኮማተረው ገጽታቸው ላይ ተስፋና ፈገግታን ተመለከትሁ። ‹‹እናንተ እኮ የችግር ጊዜ ደራሾቼ ናችሁ። በአዲስ ዓመት በግና ለበዓል አስፈላጊ የሆኑትን በሙሉ ገዛችሁልኝ። ለገናም እንዲሁ ዶሮ፣ እንቁላል እና ሽንኩርት አመጣችሁልኝ። ኃላፊዎቻችሁና ሠራተኞቹ እየመጡ ጠይቀውኛል፤ ብርም ሰጥታችሁኛል። አቅም ኖሮኝ ውለታችሁን ባልከፍልም፤ እንዳሰባችሁኝ ፈጣሪ ያስባችሁ ሌላ ምን እላለሁ›› ሲሉ ሁለት እጃቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ሊያመሰግኑ ሲሉ ይዘዋት የነበረችው ዘንግ ከእጃቸው ከዳቻቸው።
ዘንጓን ለማንሳት ዝቅ ሲሉ የፈራረሰ መደብ ላይ ቁጢጥ አሉ። ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ያደረገላቸውን ድጋፍ በደስታ ስሜት እየገለፁ፤ ወዲህ ደግሞ ያለፉበትን የተደላደለ ኑሮ በዓይነ ህሊናቸው እየቃኙ፤ ወዲያው በትካዜ ስሜት እንባቸው ከዓይናቸው ቁርርር… ብሎ መውረድጀመረ። ወይዘሮ ግምጃ ሮባ ፍቼ ሰላሌ ‹‹ዶዩ›› በምትባል መንደር ነው የተወለዱት፤ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣች ጊዜ የስድስት ወር ህፃን ነበሩ። አሁን ‹‹በግምት 83 ዓመት ሳይሞላኝ አይቀርም›› ይላሉ። የ14 ዓመት ታዳጊ ሳሉ እናታቸውን በሞት ተነጥቀዋል። 15 ዓመት ሲሞላቸው ባልጠና አቅማቸው፤ ባልደረጀ የልጅነት ዕድሜያቸው ከእርሳቸው በእድሜ ብዙ ለሚልቅ ጎልማሳ ተዳሩ። በመጀመሪያ ጋብቻቸው ሪቼ ፈይሳ የሚባል ሰው አግብተው በተደላደለ ኑሮ ውስጥ ነበሩ።
ይሁንና ከባለቤታቸውም ሆነ ከቤተሰባቸው ጋር አንድ ያልወደዱት ነገር ነበር። በቤተሰቡ ውስጥ ይመለክ የነበረውን ‹‹ጨሌ››። ስለሆነም ማምለክ ባይፈለጉም በጫና ውስጥም ሆነው በትዳር ለመቆየት ተገደዱ። በ15 ዓመታቸው ሴት ልጅ ቢወልዱም፤ በስድስት ወሯ በሞት ተለየቻቸው። ይህን ጊዜም የህጻኗ መሞት ‹‹ጨሌ›› ባለማምለክ የመጣ ነው ሲሉ ባለቤታቸው በየሰበብ አስባቡ የዱላ ናዳ ያወርዱባቸው ጀመር። ልጅም ሳይገኝ 15 ዓመታት እንደቀልድ ነጎደ። ከዚያን በኋላም ዱላው ሲበረታባቸውና ልጅም ሲናፍቃቸው ከተጋቡ ከ15 ዓመት በኋላ ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸው እህል ውሃ መቋጫውን አግኝቶ ተፋቱ።
ከዚያም መንገድ አጠያይቀው ከፍቼ ሰላሌ ‹‹ሎንቺን›› በምትባለው መኪና በአንድ ብር ተሳፍረው ከማያውቋት አዲስ አበባ ከተሙ። አሁንም ጥሩ ሕይወት የመኖር፤ ሕይወትን የማሸነፍ ህልማቸው በውስጣቸው አለ። ጥሩ ትዳርም ናፍቋቸዋል፤ ልጅም እንዲኖራቸው ይመኛሉ። በዚህ መሃል አፍሪካ ሕብረት ጋራዥ አካባቢ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቁ፤ በትዳርም ተሳስረው ጎጆ ቀለሱ። በወቅቱ ባለቤታቸው ጋር ሲተዋወቁ ደመወዛቸው አንድ ብር ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላም ወንድ ልጅ ወለዱ። የባለቤታቸው ደመወዝም አንድ ብር ከሃያ አምስት ሆነ። የባለቤታቸው ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ፤ ወይዘሮ ግምጃ እንጀራ እየጋገሩ፤ ፈትል እየፈተሉ ኑሮን ይገፉት ያዙ። የመጀመሪያ ባላቸው «ጨሌ አምልኪ» ሲሏቸው አምቢ ብለው ቢፋቱም፤ ሁለተኛው ባላቸውም የጠሉትን ‹‹ጨሌ›› ያመልኩ ስለነበር በትዳራቸው አሁንም ደስተኛ እንዳይሆኑ አደረጋቸው።
የሆነው ሆኖ ሁለት ልጅ ሲወልዱ አዕምሯቸው በተወሰነ መንገድ ተረጋጋ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ሃያ ሁለት በሚባለው አካባቢ የመንግስት ቤት ተከራይተው ሲኖሩ፤ ኢህአዴግ አገሪቱን ተቆጣጠረ። በዓመቱ ባለቤታቸው ታመው ሞቱ። ቀጥሎም በጣም የሚወዱትና ደፋ ቀና ብሎ ቤቱን ይመራ የነበረው የመጀመሪያ ልጃቸው ባላቸው በሞቱ በዓመቱ እርሱም በሞት ተለያቸው። ሁለተኛ ልጃቸው በአሁኑ ወቅት አብሯቸው ቢሆንም፤ የአዕምሮ ታማሚ በመሆኑ አማኑኤል ሆስፒታል ተመላላሽ ሆኗል። የቅርቤ የሚሏቸውንሁሉ በሞት ተነጥቀዋል። አንድ ታናሽ እህታቸው ‹‹ጉንቡቹ›› በሚባል ቦታ ታማሚ ሆነው ሰው ዘንድ ተጠልለው እንደሚኖሩ ሰምተዋል። ሰባት ታላላቅ እህትና ወንድሞቻቸውንም ቀብረዋል እርሳቸውም ሰባት ላሞች ከሚያልቡበት፤ ሁሉ ነገር ከሞላበት ቤታቸው ወጥተው ብቻቸውን ቀርተዋል። ህይወት እንዳሰቡትና እንደተመኙት አልሆነችላቸውም። የጥሩ ትዳር ምኞት፤ የልጅ አምሮት፣ የዘመድ ናፍቆት እንዳሰቃያቸው አራት የአገር መሪዎች በኢትዮጵያ ተራርቀዋል። እማማ ግምጃ «ፈጣሪ ያለው ካላመሰገንክ የበለጠ አለና አታማርር ነው» እያሉ ህይወትን ይገፋሉ። አሁን የሚኖሩበት አካባቢ የጋራ መፀዳጃ ቤቱ ለቤታቸው በጣም ቅርብ ነው። ንፋስ ሽታውን ቀጥታ ወደ ቤታቸው ይዞት ይገባል። አለፍ ሲልም ፍሳሹ ቤታቸው ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ አለ። ቀደም ሲል ዘመዶቻቸው ይጠይቋቸው ነበር። ከሰባት ዓመት በፊት ቅድስተማርያም ለመሳለም ሄደው መኪና ትንሽ ገፋ አድርጓቸው ወድቀዋል። ቢሆንም ብዙም ስላልተጎዱ አሽርካሪውን መክሰስ አልፈለጉም። «በውሸት ተጎዳሁ ብዬ ገንዘብ አልቀበልም።
ቤተክርስቲያን ቄጠማ ጭኖ መጣ እንጂ እኔን ሊጎዳኝ አስቦ አይደለም የመጣው» ብለው መታከሚያ እንኳን አልተቀበሉም። ይሁንና የቤተሰቦቻቸው ፍላጎት ከዚህ በተቃራኒ ነበርና እንዴት ተጎድቻለሁ ብልሽ ገንዘብ አትቀበይም አሏቸው። እርሳቸው ግን ከእምነታቸው ፈቀቅ አላሉም። በዚህ የተነሳ ብዙ ቤተሰቦቻቸው ርቀዋቸዋል። ቀደም ብሎ ግን እህል ጭነው ይጠይቋቸው እንደነበር ቢያስታውሱም ከሠባት ዓመት ወዲህ ግን አንድም ዘመድ መጥቶ አይቷቸው አያውቅም። ዘመዶቻቸው እንደናፈቋቸው፤ ቀንና ሌት ተደበላልቆባቸው በጠባቧ ቤት ውስጥ እንቅስቃሴያቸው ተወስኗል። ከአምስት ዓመት በፊት እሳቸው የማያውቋቸው ሰዎች ወደቤታቸው መጥተውና አኗኗራቸውን ተመልክተው በየወሩ 300 ብር ያግዟቸው ነበር። አሁን ላይ በወር ወደ 500 ብር አሳድገውላቸዋል። ተመላላሽ እንጀራ ጋጋሪም ተቀጥሮላቸዋል። ይሁንና እማማ ግምጃ ራሳቸውን ችለው ወደ መፀዳጃ ቤት መሄድ አይችሉም። በዚህ ሁኔታ ደግሞ የአዕምሮ ታማሚ ልጃቸው ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ የተፀዳዱትን ቤት ውስጥ ይደፋዋል።
በዚህ የተነሳ ቤቱ ሰው የሚኖርበት አይመስልም። ይህን ሕይወት ላለፉት ሦስት ዓመታት ገፍተውታል። ርሃቡ ሲጠናባቸውና ህይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ በቻሉት አቅም ይጥራሉ። ምግባቸውን ለማብሰል ሽንኩርት ልጠው ይከትፋሉ፣ እቃ ያጥባሉ፣ መብራት ያለበትን ቦታ በዳበሳ ፈልገው ያበሩታል። ከዚያን በዘለለ ቡና ከፈለጉ ልጃቸው ሻል ሲለው ያፈላለቸዋል። ግን አንዳንድ ጊዜ ብስጭቱን የሚወጣው በእርሳቸው ላይ ነው። ሲያሻውም ይደበድባቸዋል። እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም እንጂ የዓይናቸውን ብርሃን ለመመለስ ሃኪም እንዲታደጋቸው አቅማቸውበቻለ ጊዜ ብዙ ጥረዋል። እንደዛም ሆኖ በህይወት ላይ ተስፋ አልቆረጡም። «ምንም እንኳን ጤና ባጣም፤ ቀምሼ አድራለሁና እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ» ይላሉ።
እማማ ግማጃ እንደ ዛሬ ጉልበት ሳይከዳቸው፣ ዘመድ ሳይርቃቸው፤ ብርሃን ሳይጋርዳቸው ቀን ከሌት ሳይደበላለቅባቸው የአንድ ጋቢ ጥጥ እየፈተሉ በ25 ብር ይሸጡ ነበር። አሁን ግን ለዘመናት ጥጥ ከጥፍጥሬ ፍንትው አድርጎ ለይቶ፤ ከቀላል እስከ ከባድ አገላብጦ ያኖራቸው የነበረ ጉልበታቸው ከዳቸው ብርሃናቸውም ሸሻቸው። እናም ‹‹ባገኝ በልቼ፤ ባጣ ተደፍቼ አድራለሁ ብቻ ፈጣሪ የፈቀደው ይሁን» በሚል ተስፋ አጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። ለእማማ ግምጃ ከማለዳው ጀምሮ ኑሮ ‹‹አላውቅሽም›› ብሎ ፊት የነሳቸው ይመስላል። «የእኔ ነገር ቢቀር ይሻላል። አኗኗሬ ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች ነኝ›› የሚሉት አዛውንቷ ከምንም በላይ አንድ ነገር ይመኛሉ። እንደ ብሌናቸው የሚሳሱለት አንድ ልጃቸው ጤናውን አግኝቶ በቁም ባይጠቅመኝ እንኳን ስሞት ቢቀብረኝ ብለው ይፀልያሉ። በሕይወት ዘመናቸው ኑሮ ቢያጎሳቁላቸውም፤ መብላትና መጠጣት ተፈጥሯዊ ግዴታ ቢሆንም፤ ይህንንም ለማግኘት በሰዎች ለጋስነትና መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሕይወታቸው ግን ሁሌም በትካዜ ማዕበል ውስጥ ትንጣቸዋለች። ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል። እንዲህም ይኖሯል ይሏል ይህ አይደል?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር