ወትሮውኑም በይዘቱ እንጂ በአቀራረቡ የማይታ ማው የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን አውታር እያደር ባለ መንታ ሰብዕናነቱ እየተጋለጠ መምጣት ከጀመረ ሰንብቷል። ምንልባትም እንዲህ እንደዛሬው በእኛ ላይ ዘገሩን ስላልነቀነቀብን ብዙም አልታዘብነው ይሆናል እንጂ ዘርፉ ከሰውነት ተራ ከወጣ ከራርሟል። የሸመተው ተአማኒነት (ክሬዲቢሊቲ /ትረስት) ከእጁ ከወጣ፤ በምስራቁ ዓለም ሚዲያ ዘንድ መሸንቆጥ ከጀመረ ጊዜው ዛሬ ሳይሆን ሁለት አስርትን አልፏል።
በራሳቸው፣ በምዕራባውያኑ እንደተነገረን፣ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ጥርሶቹ ከወየቡ፣ ብዕሮቹ ከዶለዶሙ፣ አንደበቱ ከተኮላተፈ፣ የሙያ መሰረቱ ከተነቃነቀ ጊዜው ዛሬ ሳይሆን፣ ወደ ኋላ የትየለሌ ነው።
ብናምንም ባናምንም፣ ዝቅ ብለን የምናገኛቸው ምንጮቻችን ሹክ እንደሚሉን የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ዘቅጧል። መዝቀጡን ለማረጋገጥ ደግሞ የጣቢያዎቹን አሁናዊ ይዞታ መመልከትና “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተበትኗል”፤ “ደብረ ብርሃን ገብተዋል” ወዘተ ዜናቸውን ማየቱ ብቻ በቂ ነው።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የጠቀስናቸው ምንጮች እንደሚያሳዩት የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በደለቡ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም አራማጆች ከተጠለፈ ቆይቷል። በቀኝ እና ግራ ዘመሞች ሊዋጥ የቀረው እዚህ ግባ የሚባል ጊዜ አይደለም። በስለላ ድርጅቶች መዳፍ ውስጥ ከገባ ዘመን የለውም። ያለበት ደረጃ ለ”ኮክቴል”ም እንበለው ለ”ግብዣ ጋዜጠኝነት” እንኳን የሚያበቃው አይደለም።
የጉዞ አቅጣጫውን ከፖለቲካ መምሪያዎች መቀበል ከጀመረ የአንድ ትውልድ እድሜን እያስቆጠረ ነው። የዛሬው በእኛ ላይ እየተደረገ ያለው የሀሰት ትርክት (“strategic narratives” ይሉት አይነት) በእቅድ የተያዘ፣ የተቀናጀና በተናበበ መልኩና በደቦ እየተከናወነ ያለውም ከዚሁ ከምዕራቡ ዓለም የቆየ ማንነት የመነጨ እንጂ ድንገት መጥ አይደለም።
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በአዋጊነት ጦር ሜዳን ከተቀላቀለ ቆይቷል። ቁልፍ ከሆነው የሚዲያ ስነምግባር (ታማኝነት፣ ሚዛናዊነት …) ጽንሰ ሀሳብ ጋር ተፋትቷል። የፖለቲካ መርከብ ላይ ከተሳፈረ ሰንብቷል። በየ አገሩ ሿሚና ሻሪ ሆኗል። ሲፈልግ ያጋባል፤ ሳይፈልግ ያፋታል። መረጃዎቻችን ግልጽ አድርገው የሚነግሩን፤ ፍንትው አድርግው የሚያሳዩን እውነት ቢኖር ይሄው ነው።
አመንም አላመንን፣ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ጭራውን የእግሮቹ ጉያ ውስጥ ሸጉጦ በሽብርተኞች ቁጥጥር ሥር ውሏል። በመሆኑም አገልግሎቱ ለዚሁ አካል ነው፤ ተግባሩ ሽብርተኝነትን ማሳለጥ፤ በሰብዓዊ መብቶች ተገን አገራትን እንዳሻው ማድረግ፤ በ”የውጪ ፖሊሲ” ሰበብ ሕዝቦችን እርስ በእርሳቸው ማጫረስና የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶቻቸውን መዝረፍና ማዘረፍ ነው።
እንደ ምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ሰው ጤፉ፤ ገንዘብ ነፍሱ የሆነ ተቋም በዓለም አናገኝም። የአንድ አገር ዜጎች እርስ በርሳቸው ተጫረሱ አልተጫረሱ ለእሱ ምኑም አይደለም። የነተበ ይዘቱን ባሸበረቀ አቀራረቡ ጀቡኖ እንካችሁ ሲል እፍረት የሚባል ነገር አያውቅም። ሚዲያው ሲበዛ አይናውጣ ነው። ዝቅ ብለን የምናገኛቸው ምንጮቻችን እንደሚነግሩን፣ ከሚዲያ ደብርና ጋዜጠኝነት ማማ ላይ ወድቋል። ይህ ውድቀት ደግሞ ቢቢሲንና ሲኤንኤንን ብቻ የሚመለከት፣ ሮይተርስን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን “አንቱ” ሲባሉ የኖሩትን እነ ዋሽንግተን ፖስትን፣ ዘ ኢኮኖሚስትን ወዘተ ሁሉ ይጠቀልላልና ውድቀታቸው በፓኬጅ ነው።
ሩዋንዳን፣ ኮሶቮን፣ ምስራቅ ቲሞርን እንዲያ ያደረገው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ፣ ዛሬም ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል (Roff, Katherine Louise; 2013)። ፕሪንት ሚዲያው ሳይቀር በአገራት የእርስ በርስ ግጭቶች ይፈጠሩ ዘንድ ተግቶ ከመስራት ለአፍታም ዘግይቶ አያውቅም። ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ለእነሱ አዲስ አይደለምና ያፍሩበታል፣ ይፀፀቱበታል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው የውስጥ አንድነት እንጂ ሌላ አለመሆኑ ነው እየተመሰከረ ያለው። (ለተጨማሪ መረጃ “Media ethnicization and the international response to war and genocide in Rwanda”ንም መመልከት ይቻላል።)
(በእነ Roff, Katherine Louise የቀረበውና በወሰኑ የእንግሊዝን፣ አሜሪካንና አውስትራሊያን የህትመት ሚዲያዎች በሸፈነው በዚህ ጥናት ውስጥ ቁልፍ (Keywords) ሆነው የተጠኑት ጽንሰ ሀሳቦች፤ Intervention; humanitarian intervention; interventionist narratives; ethnic conflict; media; media framing; war reporting; empathy framing; distance framing; barbaric; primordial; war; genocide; Rwanda; Kosovo; East Timor; Timor Leste; hero; victim; villain መሆናቸውን መጠቆም፤ በተለይ በዚህ ዘርፍ ጥናት ለሚያደርጉ ወገኖች ጠቃሚ ነው።)
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ቀዳሚ አጀንዳ የሴራ ፖለቲካን ማጠንጠን ከሆነ ጊዜው ረጅም ነው። የብሔር ግጭት ለምዕራቡ ዓለም ከዳማ ጨዋታ የቀለለ ነው፤ የሰዎች መተላለቅ ለዚህ ሚዲያ የሰርጉ ያህል ያስደስተዋል። ሥራው ሁሉ አዛኝ ቅቤ አንጓችነት ነው። ያዘነ፣ ያሰበልን መስሎ ሲያጋድለን ውሎ ማደሩን ተክኖበታል። የራሷ እያረረባት … እንዲል ብሂላችን የራሱን ጉድ በጉያው ስር ቋጥሮ የሌላውን ለአደባባይ ማብቃት ላይ ነው የሁሌም ትርክቱ (እድሜ ለምሥራቁ ዓለም ሚዲያ፣ በተለይም የሩሲያው RT ቴቪ አይተንላቸዋል)። እነ ሲኤንኤን ያልነገሩንን የአሜሪካ ገመና ዓይን ከሰበከት እያገላበጠ የሚያስኮመኩመን ይህ ጣቢያ በግልባጩ የእነ ሲኤንኤንን በፖለቲካል አይዲዮሎጂ መጠለፍንም እንድንረዳ እያደረገን ነውና ሳናመሰግነው አናልፍም። የምዕራቡን በምሥራቁ ለማጣፋት እድል ሰጥቶናልና አሁንም እናመሰግነዋለን።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ (ሁላችንም የምናውቀው እንዳለ ሆኖ) ላይ ትላልቅ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችን የተቀነባበረ፣ ከአንድ ማእከል የሚፈስ ፕሮፓጋንዳቸውንና የሚዲያዎቹን ቅሌት ሲገልፁ “አዲስ አበባ ተከቧል፣ ኬኒያ ድንበሯን ዘግታለች፣ የከተማ ውስጥ ግር ግር ተፈጥሯል ወዘተ” በማለት በማሳያነት ያነሱትን ለዚህ እየተነጋገርንበት ላለነው ጉዳይ ዋልታና ማገር ነው፤ “የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ” ስንል በወኔ ተነሳስተን፤ ወይም፣ በስሜት ተገፋፍተን አለመሆኑንም ያሳይልናልና ውይይታችንን እንቀጥል።
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ እንደምናውቀው ሳይሆን እንደምናየው ከሆነ ቆይቷል። የCJ Estes ጥናት እንደሚነግረን ከሆነ ያለው ተጨባጭ እውነታ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ መውደቁን (Western media’s failure ይሉታል) የሚያረጋግጥ እንጂ ሌላ አይደለም። ወደድንም ጠላንም በጋዜጠኝነት ፍልስፍና ውስጥ ተገቢ ስፍራን ይዞ የሚገኘው የሚዲያ አጀንዳ አቀራረጽ ንድፈ ሀሳብ (agenda setting theory) ባፍጢሙ ተደፍቶ፣ ለሚዲያ አጀንዳ ቀራጩ የፖለቲካው ዲፓርትመንት ሆኗል።
ገጣሚው “መለየት አቃተኝ ዳንሱን ከዳንሰኛ” እንዳለው፤ እኛም ባይደን/ኋይት ሀውስን ከሲኤንኤ፤ ሲኤንኤንን ከባይደን መለየት አቅቶናል። በየምዕራቡ ቢቢሲና በመካከለኛው ምስራቁ አልጀዚራም ይሁን አል- አርሀም መካከል ያለው ድንበር ፈርሶብናል። ሌላውም እንደዚሁ።
እመኑኝ፣ እንደ ፈለገው ብንሆንለትም፣ ብንለማመ ጠውም የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የምዕራቡ ዓለም ነውና ለእኛ መቸም ቢሆን አይተኛልንም። እዚህ የሚደረገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ (ወይም ግጭት) የብሔር፣ ጎሳ ወዘተ ገጽታን ከማላበስ አይቦዝንም። መፍትሄው እንደ እሲያ አገራቱ ሚዲያ ቀድሞ መገኘት ነው፤ ዝቅ ብለን እንመለከተዋለን።
የምዕራቡ ሚዲያ በሰው ስቃይ የሚደሰት ሳዲስት ከሆነ ሰነባብቷል። አወቀውም አላወቀውም ሥራው ሁሉ ከጋዜጠኝነት አጠቃላይ ሙያ የወጣ ብቻ ሳይሆን ሙያውን ከሸቀጥ ያልለየና ለደለበ ትርፍ ሲል መልኩን አሳምሮ ገበያ የሚወጣ ይሉኝታ ቢስ ነው። እስካተረፈው ድረስ ለእሱ የንፁሀን ደም ማለት የአውሮፓ ውስኪ ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ቀጥሎ ያለው አንቀጽ በቂ ማረጋገጫ ነው።
የምዕራቡን ዓለም ሚዲያና ጋዜጠኝነት ከሩዋንዳው እልቂት ጋር አያይዘው ያጠኑት M McNulty ይህንን ሀሳብ አሟልተው ሲገልፁት “Western media’s ethnicization of the conflict justified Western intervention” እንዳሉት ነውና ይህ የአንድን አገር ሉዓላዊነት በመዳፈር፣ ግጭቶችን ሁሉ ከብሔር ጋር በማያያዝ እርስ በርስ ማጫረስ የኮምፒዩተር ጌም የመጫወት ያህል እንኳን ከባድ አይደለምና ለጣልቃ ገብነታቸው ጉልህ ማረጋገጫ ነው።
እዚህ ላይ “የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ” በማለት ነጥለን ስንነሳ ሌሎች የሉም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ግዙፉ የሚዲያ ተጽእኖ ከዚሁ ከምዕራቡ ዓለም ይሁን እንጂ የእሱው ጋሻ ጃገሬዎችና አገልጋዮች እዚህም እዛም የሉም ማለት ግን አይደለም፤ አሉ።
በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻን ከፍተው ከፍተኛ በጀት መድበው ከሚንቀሳቀሱት መካከል በግብጽ ተፅእኖ ስር በወደቀው መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙት የሚዲያ አውታሮች ተጠቃሽ ናቸው። አልጀዚራና አል- አራቢን መጥቀስ ይቻላል። የእነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዘመቻ ዛሬ ከምዕራቡ ጋር ግንባር ይፍጠር እንጂ ወትሮም ቢሆን፣ በተለይ ከታላቁ የህዳሴ ግድባችን የመሰረት ድንጋይ መጣል ማግስት ጀምሮ ያለ እንቅልፍ ሲሰራብን፤ ግድቡን እናቆም ዘንድ ሲያስፈራራን የኖረ መሆኑ ሊታወቅ ብቻ አይደለም ሊሰመርበትም ይገባል።
የምዕራቡን ዓለም ሚዲያ ገበና የሚያጋልጠው የምስራቁ ዓለም ባይኖር ኖሮ፣ ምናልባትም የምዕራቡን ዓለም ሕዝቦች ሰቆቃ ላናውቅ እንችል ነበር። ግን በምስራቁ ሚዲያ አማካኝነት እየተመለከትን ያለነው የምዕራቡ ዓለም ቀውስ ምዕራቡ ዓለም ሌላው ዓለም አለ ብሎ ከሚያራግበው ቀውስ በእጅጉ የበዛና የከፋ እንጂ በምንም መልኩ አንሶ አይታይም።
እነ ሲኤንኤ የሌላውን ዓለም ጠጠር ቋጥኝ አሳክለው ሲያወሩ አሜሪካ ውስጥ እየሆነ ያለውን ግን ትንፍሽ ሲሉ አይታዩም። እነሱ ትንፍሽ አይበሉ እንጂ የምስራቆቹ RT (የሩሲያው) እና የቻይናው CGTN ቴቪ የአሜሪካውያንን የእለት ተእለት ሰቆቃ ፈልፍለው በማውጣት ከዛው “በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከእኔ ወዲያ ላሳር” ከምትለው አሜሪካ ምድር እያሳዩን ነው። እዛው ያለው ሲኤንኤ ግን “አዲስ አበባ ተከባለች፣ ሰራዊቱ ተበትኗል፣ የትግራይ ሰራዊት አዲስ አበባ …፣ አገሪቱን ለቃችሁ ውጡ ….” የሚል በሬ ወለደ ዜና ላይ ተ ጠምዶ ውሎ ያድራል።
እርግጥ ነው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ከሌላው ዓለም ሚዲያ የሚለይበት (ትርፍ ማጋበስ እንዳለ ሆኖ) የራሱ የሆነ ርእዮት ዓለማዊ መርህ አለው። ይህ መርሁም ዓለምን በኒዮሊበራል አስተሳሰብ ስር ማስገባትና ሌላው ዓለም ለምዕራቡ ዓለም እንዲገብር ማድረግ ነው። ችግሩ አሁን ላይ ከማንም በተለየ፣ አይኑን በጨው አጥቦ፣ ጥርሱን አግጥጦ በእኛ (በኢትዮጵያችን) ላይ፣ በደቦ መሰማራቱና በሬ ወለደ ዜናውን በሰዓት በሰዓቱ አየር ላይ መዋሉ ነው።
እርግጥ ነው እንደ አህጉር፣ ለምዕራቡ ዓለም ሚዲያ መግነንና ተፅእኖ ፈጣሪነት እንደ አፍሪካ ሚዲያ አስተዋጽኦ ያደረገ አለ ማለት በፍፁም አይቻልም። ይህም ሊሆን የቻለበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የአፍሪካ ሚዲያ በየቦታው ተገኝቶ ለመዘገብ ባለበት የአቅም ውስንነት ምክንያት ቀኑን ሙሉ ሲያስተጋባ የሚውለው የምዕራቡን ዓለም ዜና መሆኑ ነው።
በዋናነት ችግሩ ይሄ ነው። በዚህ የሚተማመነው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያም በሰዓት በሰዓት የሀሰት ትርክቱን በብሔር እየለወሰ አፍሪካን እንደ ፈለገው ሲያምስና ሲያተራምስ እየዋለ ያድራል፤ “በጥልቀት አዝነናል” – we are deeply concerned ነጠላ ዜማውን (ግጥምና ዜማው ከኋይት ሀውስ እንደሆነ እናውቃለን) ያለ እረፍት ያቀነቅናል። የአፍሪካ ሚዲያም (ድህነት ነፍሱን አይማረውና) ያለ ምንም ማጣራት ተቀብሎ …
ይህ በአፍሪካ የበላይነትን የያዘው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በሌሎች ዓለማት የዚህን ያህል የመንፈላሰስ እድልን ሲያገኝ አይታይም። ይህንንም የእሲያ አገራትን ሚዲያ በመውሰድ ማየት ይቻላል።
የእሲያ አገራት ልማትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ርእዮትን የሚከተሉና ልማት ላይ አተኩረው የሚሰሩ፤ በዚህም በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ናቸው። ባስመዘገቡት እድገትም ግዙፍ የሚዲያ ተቋማትን ለመገንባት ችለዋል። በመሆኑም በምዕራቡ ዓለም ተጽእኖ ሥር የመውደቅ እድላቸው ያከተመ ነው። የምዕራቡም በእሲያዎቹ (በምስራቅ አውሮፓም ጭምር) ሚዲያዎች ላይ ተጽእኖ የሚፈጥርበት እድል ተዘግቷል። እዛ ቢቢሲ እንዳለው፣ ሮይተርስ እንደዘገበው … ብሎ ነገር የለም።
እንደ እሲያው ሁሉ የምስራቅ አውሮፓ ሚዲያም ለምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ብዙም ትኩረትን የሚሰጥ አይደለም። በሽግግር ላይ ያለ ቀጠና ከመሆኑም አኳያ በውስጡ ብዙ ቅሬታዎች ያሉበት ነው። ይሁን እንጂ ብዝኃነትን የማስተናገድ አቅጣጫን የሚከተሉ ሚዲያዎች ያሉ ከመሆኑ አኳያ ለምዕራቡ ሚዲያ የሚንበረከክ አካል ብዙም የለም ማለት ይቻላል።
ለምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በሬ ወለደ ወሬ ምቹ ሁኔታና ማረፊያ ስፍራ ያለው ከሁሉም ከሁሉም በአፍሪካ ምድር ነው፤ ከራሱ፣ እሱ ካስተጋባው በላይም ዜና ዘገባዎቹ ተደጋግመው የሚስተጋቡለት በዚሁ ምድር ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከኢኮኖሚ ጋር የተገናኘ እንደ መሆኑ መጠን ዛሬውኑ መፍትሄ የሚገኝለት አይመስልምና ችግሩ የአህጉሪቱን ቁርጠኝነትና የመሪዎቿን የጋራ ትብብርና አንድነት የግድ ይላል። (አሁን አሁን የአፍሪካ ሚዲያ ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን በሚገባ ወደ መዘገቡ፤ የምዕራቡን ዓለም ሚዲያ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ወደ ማጋለጡ እየመጣ ነውና ይህ በማለፊያ ጅምርነት ሊወሰድ ይገባዋል።)
ባጠቃላይ፣ እኛ እየደረሰብን ያለው ጫና እንዲህ በቀላሉ ተጽፎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። በተለይ ችግሩን ከተሻገርነው በኋላ በአስተማሪነቱና ታሪክነቱ በዳጎሰ መልኩ ሊሰነድ የሚገባው ብዙ ጉድ አለ። አሁንም በአሜሪካ መዳፍ ሥር ከወደቀው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያም ሆነ በግብፅ የበላይነት ከሚሽከረከረው የመካከለኛው ምስራቅ ሚዲያ ምንም ልንጠብቅ አይገባም። እንደውም ካፈርኩ አይመልሰኝ እንደሚባለው የባሰም ሊያወሩ ይችላሉ። መፍትሄው አሁንም የውስጥ አንድነት!!!
እኛ መስራት ያለብንን መስራት ነው ያለብን። መንግሥት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ መስራት ይጠበቅበታል፤ ፊቱንም ወደ እሲያ አገራት (በተለይም ቀጣናው ከዓለም ሕዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዘ ከመሆኑ አኳያ) ሚዲያዎችና ብዙም ትኩረት ወደ አልተሰጠው የአፍሪካ ሚዲያ በማዞር አብሮ ለመስራትና የአገሪቱን ተጨባጭ እውነታ ዓለም የሚረዳበትን፤ የምዕራቡ ዓለም የሚጋለጥበትን እድል መፍጠር አለበት።
በተለይ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የሚባለው መስሪያ ቤት እንደ ሌሎች አገራት፣ ለምሳሌ እንደ ቻይና አቻው መስራት ይጠበቅበታል። ሕዝቡም ጆሮውን ለምዕራባውያኑ ሚዲያዎች መስጠትን ትቶ የአገሩ ሰላም እድገትና ብልፅግና ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል፤ ለሀሰት ትርክት እውነተኛ መረጃዎችን በማቅረብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እውነታችንን እንዲገነዘበው ማድረግ ይኖርበታል። ሚዲያውን የምዕራቡ፣ ምስራቁ፣ ምእራብ አውሮፓው፣ እሲያው፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካው ወዘተ በማለት ከባህርይውና ርእዮቱ አኳያ በልተን አይተናል። አምባሳደሮቻችን ደግሞ የበለጠ ይጠቀሙበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለጊዜው ይሄው ነው።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014