መስታወት ፊትን ያሳያል፤ ቃል በተግባር ይፈተናል
ማለዳ ወደ ሰርክ ውሏችን ከመሰማራታችን አስቀድሞ ራስን በመስታወት ማስፈተሸ የተለመደ የብዙዎች ልማድ ነው። ውበታችንን ለማድነቅም ሆነ ጉድፋችንን ለማስወገድ የመስታወትን አገልግሎት የምንፈልገው ያለ ይሉኝታና ያለ አድልዎ ማንነታችንን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳየን ነው። ፍተሻው ከሙሉው ማንነታችን አያጎልም ወይንም አያሳንስም። ይህ የመስታወት የዘወትር አገልግሎት ነው።
ማነጻጸሪያው ባይመጥናትም ኢትዮጵያም እንዲሁ በማንነታችን መፈተሻ መስታወት ልትመሰል ትችላለች። እርሷ የምትፈትሸን አካላዊና ውጭአዊ መልካችንን ሳይሆን የኅሊናችንን ጓዳና በዜግነት ድርሻችንና ግዴታችን የሆነውንና እየሆንን ያለነውን ውስጣዊ መልክ ነው።
በተለይም ሀገር በፈተና ስታምጥ፣ የመከራው ጫና ከብዶባት ልጆቿን እንዲታደጓት የምትፈልገው በጊዜና በትውልድ ፊት መስታወቷን ዘርግታ ነው። ይህ መስታወቷ የሚሞግተው ውጭአዊ ሰብእናችንን ሳይሆን ውስጣዊ አቋማችንንና ማንነታችንን መሆኑን ደግመን እናረጋግጣለን። ቁሱን መስታወት በሜክአፕና በቅባት ወዝተን የውበታችንን ማማር እንዲመሰክርልን ልንሸነግለው እንችላለን። የሀገርን መስታወት ግን በኮሜዲና በትራዤዲ ትወና አማልለን ወይንም አስተዛዝነን ዓላማችንን ልናስፈጽም በፍጹም አንችልም። ምክንያቱም ሀገር ከመስታወትም በላይ እውነተኛ ምስክር ናት!
ኢትዮጵያ ሆይ! እነሆ ፈትሽን!
ስለ ሀገር ውበት፣ ስለ ሀገር ክብር፣ ስለ ሀገር ነፃነት፣ ስለ ሀገር ታሪክና ቋንቋ፣ ስለ ወግና ልማዷ፣ ስለ ተፈጥሯዊ ድንቅነት፣ ስለ ተጋድሎዋና የዘመናት ጉዞዋ ወዘተ. ያልተጻፈ፣ ያልተዘመረ፣ ያልተዜመና ያልተነገረ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ስለ ሀገር መውደድ፣ ስለ ዜግነት ክብርና ስላለፈችባቸው ደስታዎችና መከራዎች በቁጥር ሊገለጹ፣ በወርድና ስፋት ሊተመኑ የማይችሉ እጅግ የበዙ ብራናና ወረቀቶች በተዋቡ ኅብረ ቀለማት ተከትበዋል። ዜማዎችና ቅኔዎች እንደ ማለዳ ጠል አረስርሰውናል። በትውፊትና በቃል ምስክርነት እየተወራረሱም ከእኛ ዘንድ ደርሰው አክብረን ተቀብለናቸዋል።
የቀደምት ሥልጣኔዋ ክብር ሲዘረዘርልን እየተንዘረዘርን በሀሴት ፈንድቀናል። የማህጸኗን ሀብት እየዘገንን ለመበልጸግ ጓጉተናል። የቀደምት ጀግኖችና የሀገር ባለውለታ ዜጎች ተግባርና ገድል ሲተረክልን ደማችን እየሞቀ፣ ስሜታችን እየጋለ፣ ወኔያችን እየኮሰተረ ውስጣችን በኩራት ያብረቀርቃል። ኢትዮጵያዊነታችን ነፍስ ዘርቶና ግዘፍ ነስቶ በውስጣችን ሲንቀሳቀስ ይሰማናል።
ከላይ ለጠቃቀስናቸው እውነታዎች እልፍ ጊዜ እልፍ ምሳሌዎችንና ምስክሮችን ከቅርብም ይሁን ከሩቅ የዘመናት ቀመር እየቆነጠርንና እያጣቀስን መወራረድም ሆነ መተማመን የሚገድ አይደለም። የሩቁን አክብረን፣ የቅርቡን ማስታወሱ ለዚህ ርዕሰ-ዐውድ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል ብለን ስላሰብን አንድ ክስተት እናስታውስ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በተከናወነው በዓለ ሲመታቸው ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቆመው በተመጠኑና አይረሴ በሆኑ አገላለጾች ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካስታወሱት የታሪካችን ኩራቶች (Historical significances) መካከል ከላይ ለጠቃቀስናቸው በርካታ እውነታዎች በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱትን ውሱን ዐረፍተ ነገሮችን እናስታውስ።
“አማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ሕይወቱን ሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግሬው በመተማ ከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለ ሀገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ጋር ተቀላቅሏል። ሶማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሃዲያው፣ ሐረሪው፣ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ በባድማ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድማ አፈር ተዋህደዋል። … እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን። የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።”
ኢትዮጵያ መስታወቱን ከፊታችን ዘርግታ ራሳችንን እንድንመረምር የምትሞግተን ይህን የታሪካዊ ክብሯን ገድል በማስታወስ ነው። ለካስ የቆምነው ለሀገሩ ሉዓላዊነት የከበረ ነፍሱን ሰውቶ አፈር በሆነ የጀግኖች አጽም ላይ ነውና!። ዛሬ የሀገር ጀግኖች እየተዋደቁባቸው ያሉት ተራሮች፣ ኮረብቶችና ሸለቆዎች በእነዚያ ጀግኖች አጽም የታጠሩ ናቸውና። ደማቸው ከአፈሩ ጋር ተቀላቅሎ የበቀለለን ነፃነት የሚያስተጋባው ይህንን ክቡር መልዕክት ነው።
ተመስጋኟ ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው ስሜትን ሰርስሮ በሚዘልቀው ተስረቅራቂ መረዋ ድምጽዋ በዜማ ለውሳ ያስታወሰችንም ይህንኑ እውነታ ነው፤
”የተሰጠን ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት።”
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በጥሞና አድምጦና የዚህችን ድንቅ ዜመኛ የሙዚቃ ስንኞች ሰምቶ ስሜቱ የማይግል፣ ነርቩ የማይነዝር፣ ነፍሱ የማትሞግተው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ካለ “በመስታወቱ ተፈትሾ” ራሱን ለማየት ያልታደለና የልቡ ብርሃን የጨለመበት “ስመ ኢትዮጵያዊ” ዜጋ ብቻ ነው።
እርግጥ ነው ይህንን መሰል ታሪክ መስማት ደጋግመን እንደገለጽነው ስሜትን ያሞቃል፤ ወኔንም አኮምጥጦ ያኮሰትራል። በተከፈለልን የደምና የአጥንት መደላድል ላይ ጸንተን እንድንቆምም ብርታት ይሆነናል። ጥያቄውና ሙግቱ ግን ከዚህ እውነታም ዘለግ ይላል። “እኔስ ዛሬ፣ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ መስታወት ስፈተሽ አቋሜና ደረጃዬ ምን ምን ይመስላል? ምን አጉድያለሁ? ምንስ አበርክቻለሁ? ከመስታወቱ ጋር ልንገጥም የሚገባው የእንካ ሰላንትያ ወቅታዊ ተግዳሮት ይህ መሆን አለበት።
አሸባሪውና አረመኔው የትህነግ ወራሪ ቡድን የተዳፈረውና እየተረማመደ የክፋት ተልዕኮውን ለማስፈጸምና የፍርፋሪ አጉራሾቹን እጅ የሚልሰው አጥንትና ደም የተከፈለበትን ይህን መሰሉን የሉዓላዊነት ክብር ለማዋረድና ለማቆሸሽ እየቃዠ ነው። አልገባውም እንጂ ተኩሶ ያቆሰላት የሰላም ርግብ ለጊዜው ገመምተኛ ብትመስልም በአጭር ጊዜ ውስጥ የወይራ ቀምበጥ በአፏ ይዛ የድል ዝማሬ እያዜመች ለመላው ሕዝብ ብሥራቱን ለማዳረስ ጊዜው ሩቅ አይደለም።
”አክትሟል አበቃ የእናንት ምዕራፋችሁ፣
የማይሆን ቅዠት ነው ከንቱ ነው ህልማችሁ።
ስትቅበዘበዙ አልፋችሁ ከልኩ፣
[ትቢያ አፈር መሆን ነው የዕብሪታችሁ ልኩ።]
የሚለው ግጥም በዚህች የሰላም ርግብ የሚቀነቀን ዜማ መሆኑ ያልገባቸው ይግባቸው፤ የገባቸውም ላልገባቸው ይናገሩ።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን፣ የክፉ ቀን ታዳጊዎቹ የየክልሎቹ የሕዝባዊ ሠራዊትና የሚሊሽያ አንበሶች ከሃዲዎቹን የሀገር ጠንቆች በአፈሙዝ የሚያናግሯቸው የዕብሪታቸውን እብጠት ለማስተንፈስ ብቻም ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ውሸት የሚያመርተውን ልሳናቸውን ለመዝጋትና የታሪካቸውን ምዕራፍ ሰርዞ ለመደምሰስ ጭምር ነው።
ጦርነቱ እየተፋፋመ ያለው ጀግናው የሀገር ልጅ ወራሪውን ምናምንቴ እያሽመደመደ ባለባቸው የጦርነት ዐውድማዎች ላይ ብቻ አይደለም። ሆዳቸው አምላካቸው፣ ነውራቸው ክብራቸው የሆኑ በርካታ ኅሊና ቢስ የውስጥ ባንዳዎችም በመሃል ሀገርና በሰላማዊ አካባቢዎች ሽብር እየነዙ ሕዝቡ እንዳይረጋጋ ለማድረግ ከቀን እረፍት ከሌት እንቅልፍ ከተፋቱ ሰነባብቷል።
ከዱር እንስሳት ባነሰ አስተሳሰብ ሰብእናቸውን ያዋረዱ እነዚህ የሀገር ጉዶች የሚሸርቧቸው ሴራዎችና የተንኮል ድርጊቶች ምን ያህል የረቀቁና የተወሳሰቡ እንደሆኑ ዕለት በዕለት የምናደምጠውና የምናስተውለው ነው። ይህ ባህርያቸው ደግሞ የፍጥረታቸው መለያ ስለሆነ እጅግም ላይደንቅ ይችላል። የንጹሐን ደም ሲፈስ ካልተመለከቱ የተቆራኛቸው አጋንንታዊ ቆሌ ያቅበዘብዛቸዋል። እጃቸውን ለዘረፋና ለውድመት ካልዘረጉ በስተቀር የተጠናወታቸው የሌብነት ሱስ ሊረካ አይችልም። ክህደትና ውሸት ያደጉበት ባህልና ወጋቸው ነው። ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር እያሉ መስበካቸውም የተቃኙበት የመሃላቸው ኪዳን ስለሆነ ነው።
በግምባር የሚፋለሙት ከሃዲዎች አንደኛውን ጭንብላቸውን ገላልጠው የአውሬነታቸውን ምስል እያሳዩ ስለሆነ ለይቶላቸዋል። ችግሩ በዓይነ ርግብ ተሸፍነው በሕዝብ መካከል እየኖሩ ያሉትን የሰላም ቅንቅኖች መለየቱ ላይ ነው። እነዚህ የክፋት መልእክተኞች ሲያሻቸው የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር ሕዝቡን ለማስጨነቅ ይተጋሉ። አልሆን ሲላቸው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመክፈት መረጋጋት እንዳይኖር ይጥራሉ። ይህም ሲነቃባቸው ፖለቲካዊ ሴራ እያውጠነጠኑ የባንዳነታቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ይጨክናሉ። ሲዖልን ያስመኛቸው ምክንያቱም ይሄው ነው።
ቃላት ሊገልጻቸው ከሚገባው በላይ በላኤ ሰብ፣ በላኤ ታሪክ፣ በላኤ አውነት የሆኑት እነዚህ ጉግ ማንጉጎች ከኢትዮጵያ መስታወት ፊት ለመቆም የሞራል ብቃት እንደሌላቸው ስለሚያውቁ እያቀረሹ ያሉት የሰሞኑ የዝቅጠታቸው የመጨረሻ ማረፊያ ወለል ምን እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ በመሪዎቻቸው አንደበት እየተገለጠ ነው። ኢትዮጵያን አፈራርሰን ትግራይን እንገነጥላለን የሚል ቀዠት።
ከእነርሱ ጎን የተሰለፉ አስመሳዮችም ኢትዮጵያ በዘረጋቸው መስታወት ፊት ተገሽረው በአርቴፊሻል ማስክ በመለበጥ በአንደበታቸው እየሸነገሉ በተግባራቸው ግን ሰይጣናዊ ድርጊቶች ለመፈጸም ከብጤዎቻቸው ጋር ሽርክና በመግባት ከአንዳንድ መንግሥታትና ቡድኖች ጋር እየፈጸሙ ያሉትን ድርጊቶች እያስተዋልንም እየሰማንም ነው።
በቀዳሚ አርበኞቻችን ብቻ ሳይሆን በዛሬዎቹ የሀገር ባለውለታዎች ሰማዕታት ጀግኖች ጭምር በፈሰሰ ደምና በተከሰከሰ አጥንት በተለበጠ ነፃነት ኮርተን እየኖርን ያለን ዜጎች ከምንጊዜውም በላይ መንቃት ብቻ ሳይሆን በተከበረው የታሪካችን ምዕራፍ ውስጥ አሻራችንን ልናኖር ዕድል ደጃፋችንን እያንኳኳ ነው።
በግንባር ላይ ለሚፋለሙት ጀግኖች የኋላ ደጀን በመሆን ባለን ሀብትና ጉልበት ለመደገፍ መሽቀዳደም መታደል ብቻ ሳይሆን ክብርም ጭምር ነው። የጠላትን የፕሮፓጋንዳ ልሳን ለመዝጋት መረባረብም ሌላው አስተዋጽኦ ነው። ከዲፕሎማሲ ተሟጋቾች ሰልፍ ውስጥ በመቀላቀል ባለን እውቀትና ልምድ “አለሁ!” ማለትም ዋጋው የላቀ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት የሚጠመቁ የእንክርዳድ መጠጦችን ተሸቀዳድሞ በመጎንጨት ከመንገዳገድ መጠበቅና የክፋት ዋንጫውን እየገለበጡ መድፋቱ ብዙዎች ሰክረው እንዳይናውዙ ስለሚያግዝ ይህም ጉዳይ ርብርብ ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያ ልጆቿን የምትመክረው እነዚህን መሰል እውነታዎችን በማስታወስ ነው።
ሀገራችንን የከበቧትና የሚጎነታትሏት የውስጥና የውጭ ጠላቶች መልካቸው፣ ብዛታቸውና ድርጊታቸው የተዥጎረጎረ ይምሰል እንጂ ኢትዮጵያ ተሸንፋ እጅ የምትሰጥ ያለመሆኗን ለእኛ ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቿም ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። ኢትዮጵያ በጋለ አሎሎ መመሰሏ የዛሬ እውነታዋ ብቻም ሳይሆን ለዘመናት የኖረችበት መታወቂያዋ ጭምር ነው። በተዘረጋው መስታወቷ ውስጥ እኛ የምንመለከታት ኢትዮጵያ ይህቺ ነች።
እርሷም ለእኛ የቁርጥ ቀን ልጆቿ መስታወቷን ከፊታችን ዘርግታ የምትፈትሸን ታሪክና ትውልድ አቁማ ልትታዘበን ነው ። በዘመናት መካከል በመስዋዕትነት የደም ቃል ኪዳን ሲጻፍ የኖረው ታሪኳ የሚያስነብበው ገድሏና ዜና መዋዕሏ ይሄንንው ነው። ኢትዮጵያ እንደታፈረች ለዘለዓለም በክብር ትኖራለች። ዳሩ ለዚህ እውነታ ጠላቶቿ ካልሆኑ በስተቀር ማን ይጠራጠራል። ይሄው ነው! ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014