አንጎላ በደቡብ-ምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ ሀገር ስትሆን ከናሚቢያ ፣ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ እና ከዛምቢያ ጋር ድንበር ትጋራለች። በምዕራብ ጫፍ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ትገናኛለች። የፖርቹጋል ቅኝ-ተገዥ የነበረችው ይህችው ሀገር ነዳጅ እና አልማዝን በመሳሰሉ የከበሩ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ትታወቃለች።ይሁንና ለበርካታ ዓመታት በፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ስር መውደቋን ተከትሎ ዜጎቿ የአገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሀገሪቱ ነጻነቷን የዛሬ 46 ዓመታት ከተቀዳጀች በኋላም ቢሆን ለብዙ አሥርተ- ዓመታት የሚቀጥል የእርስ በርስ ጦርነት ገጠሟት ቆይታለች። ይህ ውጊያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞትና ስደት ዳርጓል። ከአልቮር ስምምነት በኋላ ሶስቱ ትልቅ የትግል ግንባሮች የሽግግር መንግሥትን ለማቋቋም በጃኑዋሪ 1975 እ.ኤ.አ. ተስማሙ። ነገር ግን በሁለት ወራት ውስጥ እነዚህ ግንባሮች ወደ ውጊያ ተመልሰው ሀገሪቱ ወደ ክፍፍል የምታመራበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በዚህ ወቅት የቀዝቃዛው ጦርነት ኃያል አገራት የነበሩት ሶቭየት ሕብረትና አሜሪካ አንዱን ወይም ሌላውን ወገን ደግፈው ወደ ጦርነቱ ገብተዋል። ሌሎችም እንደ ፖርቱጋል፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካና ኩባ የመሳሰሉት ሀገራትም ከማገዝ ወደ ኋላ አላሉም። አንጎላ እ.አ.አ ከ1975 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው በዚሁ ደም አፋሳሽ ጦርነት ኢኮኖሚዋ ክፉኛ ቢዳከምም፤ አሁን በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራሩ ካሉ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች።
ኢትዮጵያ እና አንጎላ የቆየና ታሪካዊ ዲፕሎማ ሲያዊ ግንኙነት አላቸው። አንጎላ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከከፈተችበት ከእ.አ.አ 1979 ዓ.ም ጀምሮ ሁለቱም ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ የአንጎላ ፓይለቶችን በማሰልጠን ትልቅ ድጋፍ እያደረገችም ትገኛለች። በተለይም ሀገራቱ በአቪዬሽን የጀመሩት የትብብር ማዕቀፍ እ.አ.አ ከ2019 ዓ.ም ወዲህ ወደ ቴክኒካል ደረጃ አድጎ በተለያዩ መስኮች በጋራ እየሰሩ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደረጃ የፖለቲካ ምክክር በማድረግም የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ላይ መሆናቸው ይጠቀሳል።
አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበትን 46ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እንዲሁም የሁለቱን አገራት ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆዜ ዳ ክሩዥን አነጋግሯቸዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የአንጎላ ህዝብ ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ለመውጣት ለበርካታ ዓመታት ያደረገውን ትግል ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- ሀገራችን አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ ገዛት ነፃ የወጣችበትን 46ኛ ዓመት ያከበርነው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነው ። እኛ አንጎላውያን ከ14 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ ነው ነፃነታችንን የተጎናፀፍነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ሀገራችን ነፃነቷን ያገኘችው ደግሞ ልክ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በሚከናወንበት ወቅት ነበር። በዛው ወቅት እንደአገር አንድ ለመሆን ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ስለነበሩን የሀገሪቱ ህዝብ የመከፋፈል አደጋ አጋጥሞት ነበር። በመሆኑም ምንም እንኳን ከነጭ ወራሪዎች አገዛዝ ነፃ ብንወጣም እ.ኤ.አ 1975 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ በሀገራችን ውስጥ ሰላም፣ መረጋጋትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖብን ነው የቆየው። ከዚያ ወዲህ ነው እንደ አንድ አገር ተጠናክረን የግዛት አንድነታችንን ማስቀጠል የቻልነው። በጥቅሉ አሁን ለተፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያንዳንዱ አንጎላዊ ብሎም የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ እርስበርስ ይተባበሩና ይደጋገፉ እንደነበር ይታወቃል። እስቲ በወቅቱ አፍሪካውያን ያደርጉት የነበረውን ትብብርና በመካከላቸው የነበ ረው ህብረት ምን ይመስል እንደነበር ይግለፁልኝ?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- እውነቱን ለመናገር እኛ አንጎላውያን ነጻነታችንን የተጎናጸፍነው በመላው አፍሪካውያን ብርቱ ትግልና ድጋፍ ነው። ለዚህም እኔ መላው የሀገሬን ህዝብ ወክዬ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። እኛ ነፃ ከወጣን በኋላ ደግሞ በተለይም ለበርካታ የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ነፃ መውጣት ጥሩ ምሳሌ መሆን ችለናል ብዬ አምናለሁ። ብዙዎቹን ሀገራት ነፃ እንዲወጡ የበኩላችንን ድጋፍ አድርገንላቸዋል። በተለይም ናሚቢያ፤ ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በነበረው አገዛዝ ስርነቀል የሆነ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣና የአፓርታይድ አገዛዝ እስከወዲያኛው እንዲያከትምለት ሀገራችን ያበረከተችው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁና የግዛት አንድነታቸውን አስጠብቀው እንደሀገር እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ሁሉም አፍሪካውያን የነበራቸው ህብረትና ትብብር ወሳኝ ሚና ነበረው ማለት እንችላለን። ህብረትና መደጋገፉ በመኖሩም ነው እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት መመስረት የቻሉት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ይህ የመተባበራቸውና መደጋገፋቸው አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ አመላካች ነው ማለት እንችላለን?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- ልክ ነው፤ አስቀድመን እንዳልነው እኛ አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎች ተላቀን ነፃነታችንን መጎናፀፍ የቻልነው በመሪዎችና በህዝቡ መካከል የነበሩብንን ችግሮች በመፍታት በአንድ ልብ በመቆማችን ነው። እርግጥ ነው፤ ዛሬም ቢሆን ጥቂት የማይባሉት የአፍሪካ ሀገራት ሠላምን፣ መረጋጋትና ልማትን ማረጋገጥ ፈተና ሆኖባቸው ቀጥሏል። እንዲሁም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አሁን ላይ የህዝባችንን ደህንነት ማስጠበቅና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ማምጣት ብዙ ይጠበቅብናል። ለዚህም ነው የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት አለባቸው የሚል ስትራቴጂ ነድፎ እንዲተገበር እያደረገ ያለው። ይህ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አቅጣጫ በመላው አህጉሪቱ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እያንዳንዱ ሀገር ሊተገብረው ይገባል። ምክንያቱም አሁን አሁን እየገጠመን ያለው ችግር በየሀገራቱ ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ደግሞም አፍሪካውያን እያጋጠማቸው ያለውን ችግር መላቀቅ የሚችሉት ራሳቸው የመፍትሄ አካል መሆን ሲችሉ እንደሆነ ነው የሚታመነው።
አዲስ ዘመን፡- አንጎላ ነፃነቷን በተጎናፀፈች ማግስት ረጅም ጊዜ የፈጀ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ እንደገባች ይታወቃል። አንጎላውያን እንዴት ነው ይህንን ችግር መፍታት የቻሉት? ሌሎች አፍሪካውያንስ ከዚያ ምን ሊማሩ እንደሚችሉ ቢያስረዱን?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡– እንደሚታወቀው እኛ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ወቅት ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የተነሳበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ፈታኝ የሚባሉ ችግሮች ስላጋጠሙን ነፃነታችን በአግባቡ ማጣጣም እንኳን አልቻልንም ነበር። አንጎላውያን የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ሰለባ ከመሆናቸውም ባሻገር ብሄራዊ መግባባትና አንድነትን ማምጣት ከባድ ሆኖብን ነው የቆየው። መሪዎቻችን ሁልጊዜ የውጭ ጣልቃገብነት ስለነበረባቸው የተረጋጋች አንጎላን ለመፍጠር ተቸግረውም ነበር። በዚህ የተነሳም ሠላማዊ የሆነ ስምምነት ላይ መድረስ እንደ ሀገር ፈተና ሆኖ ነው የቆየብን። ይሁንና በመንግሥት ቁርጠኝነትና ጠንካራ አመራር በመስጠቱ በእ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ሀገራዊ መግባባት በመፈጠሩ እንደሀገር መቀጠል ችለናል።
ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ግን አንጎላ ሁሉንም አካል እኩል የሚያስማሙ የመፍትሄ አማራጮችን መከተል ግድ ብሏት ነበር። በመቀጠልም በዙሪያችን ባሉ አገራት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ትኩረት መስጠትና ሉዓላዊነታቸውን እንዴት አስጠብቀው እየኖሩ መሆኑን ማጤን ጀመርን። ከዚያ በመነሳት መንግሥታችን ለሀገራችን ጥቅም መጠበቅ፤ የህዝባችን ቀጣይነት ያለው ውሳኔና ስልጣን የሚወጡ መሪዎች ለመረጣቸው ህዝብ ተጠያቂ የሚሆንበት ስርዓት ለመዘርጋት ጥረት አድርጓል። ይህም ቢሆን ግን እኛ የተማርነው ከራሳችን ታሪክ መሆኑ
ልብ ሊባል ይገባል። በተለይም የብሔራዊ ጥቅም ሁልጊዜም ቢሆን ሊቀድም እንደሚገባና ለዚያ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት የተገነዘብነው እንደሀገር ካሳለፍነው አታካች ውጥንቅጥ ነው። ሌሎች ሀገራት ግን ከኛ ተሞክሮ ብዙ የተማሩ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያና የአንጎላ የሁለትዮሽ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- አንጎላና ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ታሪካዊ ግንኙነት ነው ያላቸው። ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ ከ1978 ዓ.ም ወዲህ ነው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተለይም የቴክኒክ ድጋፍ ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ግንኙነት መስርተዋል። በተለይም የእኛ የአውሮፕላን አብራሪዎች እዚህ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ስልጠና ይወስዳሉ፤ የአቅም ግንባታ ድጋፍም ይደረግላቸዋል። አውሮፕላኖቻችን ጥገና የሚደረግላቸው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ነው። ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት መሆኑ አንጎላ ተጠቃሚ ሆናለች ማለት እንችላለን።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮረና ቫይረስ በዓለም ላይ ከመከሰቱ በፊት በሳምንት አምስት ቀን ወደ አንጎላ ይበር ነበር። ይህንን ቁጥር ወደ ሰባት ቀን የማሻገር እቅድም ነበረን። ይሁንና ወረርሽኙ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የበረራው ቀናት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። እንደሚታወሰው በ2019 እ.ኤ.አ ታህሳስ ወር በአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ላይ ሁለቱ ሀገራት ወሳኝ የሆነ ስብሰባ አካሂደው ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር እንደሚገባቸውም ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
በዚህ ውስጥም ሶስት የህግ ማዕቀፍ ያለው ስምምነት ፈፅመናል። አንደኛው አጠቃላይ የትብብር ስምምነት ሲሆን ሌላኛው ፖለቲካዊ የምክክር ላይ ያተኮረና የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ የሚሰሩበት ሰነድ ነው። በተጨማሪም ለሀገራቱ ዲፕሎማቶች የቪዛና የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ የሚሰጥበት የአሰራር ስርዓት ላይ ያተኮረ ስምምነት አድርገናል። ከዚህም ባሻገር አንጎላና ኢትዮጵያ ባላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንዳቸው ከሌላቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። በግብርና በማዕድን ልማት፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚ መሆን በምንችልባቸው አማራጮች ላይ እየመከርንም እንገኛን።
አዲስ ዘመን፡- አንጎላ እንደአፍሪካ ህብረት አባል ሀገር በአህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ምን ያህል አስተዋፅኦ እያደረገች ነው?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡– እንደሀገር አህጉራዊ የዲፕሎማሲ አጀንዳዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ነው እያደረግን ያለነው። በተለይም ግጭት አፈታት ላይ ከራሳችን ተሞክሮ በመነሳት አባል አገራቱ አብነት የሚሆኑ ድጋፎችን እያደረግ ነው የምንገኘው። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ በእርስ በርስ ግጭት ላይ ለሚገኙ ሀገራት ተሞክሯችንን አካፍለናል። በተለይም በሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ የነበረው አለመረጋጋትና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲፈታ የአንጎላ ሚና ከፍተኛ ነበር። እኛ አንጎላውያን ከራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ሁሉም ሀገር ውስጥ ግጭት ሊፈጠርና ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል እንገነዘባለን፤ ሆኖም ሰላምና መረጋጋት የማምጣቱ ኃላፊነት ደግሞ በሁላችንም እጅ ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑን ነው የምናምነው። እኛ የነበረብንን የውስጥ ችግር የፈታንበትን ስትራቴጂም ለመላው የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እንዲሆን ሰርተናል።
ከዚህ በመነሳት አንጎላ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኑ እሙን ነው። ደግሞ እስከ አለፈው ዓመት መጋቢት ወር ድረስ በህብረቱ የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ነበረች። በምክር ቤቱ በተሰጠን ኃላፊነት መሰረት ለሁለት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የሚባሉ ሥራዎችን አከናውነናል። ከዚህ በተጨማሪም አንጎላ አፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ተኩስ አቁም እንዲፈጠር ከፍተኛ ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። አሁንም ቢሆን በዲፕሎማሲው መስክ ከምናደርገው ድጋፍ ባሻገር በተጠየቅንበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን የግብዓት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን ለመግለፅ እወዳለሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር ሀገራችሁ ህብረቱ እየተገበረ ላለው አጀንዳ 2063 የልማት መርሐግብር መሳካት ምንአይነት አስተፅኦ እያደረገች ትገኛለች?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡– እንደማንኛውም አባል ሀገር እኛም ለአጀንዳ 2063 ተፈፃሚነት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ኃላፊነት አለብን። በአጀንዳው ከተካተቱት ተግባራት መካከልም ሰላማዊ የሆነች ፤ የበለፀገች አህጉርን ለመፍጠር መላው አፍሪካዊ በባለቤትነት መስራት ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ አስቀድሜ እንደገለፅኩት በሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆነን በቆየንባቸው ዓመታት ጠንካራ የሚባሉ ሥራዎችን ሰርተናል። ደግሞም በእ.አ.አ ከ2020 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ጃዎ ሎሬንሶ አማካኝነት የአፍሪካ ህብረትን ቁልፍ የአመራር ቦታ የተረከብን እንደመሆናችን በአህጉሪቱ ከባድ ፈተና የሆነው ሽብርተኝነትን በመታገሉ ሂደት ላይ ሀገራችን ትኩረት አድርጋ እየሰራች ነው። የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን ለመግታት እንዲቻልም ተጨማሪ ምክክሮችንና ውይይቶች እንዲደረጉ ምክረ ሃሳብ አቅርበናል። ይህም ተጨባጭ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆነው እንዴት ነው አጃንዳ 2063ን ማሳካት የሚችሉት?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- እንደእኛ እምነት አፍሪካ ህብረት ላቀዳቸው የልማት ግቦች መሳካት በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ድርሻ አለው። ለዚህም ነው እያንዳንዱ የህብረቱ አባል ሀገር በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ የሚገባው። በጥቅሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በመላ አህጉሪቱ ተኩስ አቁም ሊኖር ይገባል። ምክንያቱም ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው የልማት እቅዶቻችንን ከግብ ማድረስና ለህዝቦቿ ምቹ የሆነችን አህጉር መፍጠር የምንችለው። በተለይም በዚህ የውድድር ዓለም ጥቅማችንን ማስከበርና ተፎካካሪ መሆን እንድንችል መላው አፍሪካዊ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ህብረቱን ሊያጠናክር ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካውያን ምንም እንኳን ከቅኝ ግዛት ቢላቀቁም አሁንም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንደሆኑ ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ አሁን ከገጠማቸው የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት (ኒዮ ኮሎኒያሊዝም) እንዴት ነው መላቀቅ የሚችሉት ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- እንደእኔ እምነት እያንዳንዱ አገር አንዴ ከቅኝ ግዛት ወጥቻለሁ ብሎ አርፎ መቀመጥ የለበትም። ይልቁኑ በየእለቱ ሉዓላዊነቱንና የግዛት አንድነቱን ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ። የእያንዳንዱ አገር መንግሥት በውጭ ኃይል የሚደረገውን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ሰለባ እንዳይሆን በየቀኑ አሰራሩን ሊፈትሽ ይገባል። ዓለምአቀፍ ግንኙነትን ማጠናከር ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆንም እያንዳንዱ መንግሥት ከሌሎች አገራት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት የአገሩንና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ባገናዘበ መልኩ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አለበት። የምንመሰርተው የሁለትዮሽ ስምምነትና የትብብር ማዕቀፍ ሁልጊዜም ቢሆን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርገን ሊሆን ይገባል።
እኔ እዚህ ጉዳይ ላይ አበክሬ ልናገር የምፈልገው ጉዳይ እኛ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ በከፈልነው ዋጋ ነፃነታችንና ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ የምንችለው በየእለቱ ያንን ያገናዘበ አቅጣጫ ተከትለን ከውጭ ዓለም ያለንን ግንኙነት በጥንቃቄ መጠበቅ ስንችል መሆኑን ነው። በየዓመቱ የነፃነት ቀናችንንም ስናከብርም ይህንን አብይ ጉዳይ ታሳቢ አድርገን ሊሆን ይገባል።
አስቀድሜ እንዳነሳሁት እኛ አንጎላውያን ምንም እንኳን ከቅኝ ግዛት ብንላቀቅም ነፃ በወጣን ማግስት የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ መግባታችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ችግሩ የከፋ እንዲሆን እና ዓመታትን የፈጀ አድርጎታል። አሁንም ቢሆን በአንጎላም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ በውጭ ኃይሎች በኢኮኖሚ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ይኖራል። በዚህ ረገድ አፍሪካውያን ነቅተው ካልጠበቁ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ሰለባ መሆናቸው አይቀርም። በአጠቃላይ ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት አንድ ምዕራፍ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን ነፃነታችንን የመጠበቁ ሥራ የየእለት ሥራችን ነው ሊሆን የሚገባው።
በተጨማሪም ግጭቶችን በማስወገድ ሂደት ውስጥ በየሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ፤ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። አተገባበሩም የማይሸራረፍ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ አንጎላ በነፃነት ማግስት ከገጠማት ተግዳሮት ሀገራት ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል። አፍሪካውያን ለነፃነታቸው የከፈሉትን ዋጋ ያህል ለግዛት አንድነታቸው እለት እለት መትጋት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ የነበራትን ሚና እንዴት ይገልፁታል?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡– እንደእኔ እምነት ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እና ቁልፍ ሚና የተጫወተች ሀገር ናት። በተለይም ለአፍሪካ ህብረት መመስረት የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር እሙን ነው። እንደኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራና ጥቂት የአፍሪካ አገራት ብርቱ ትግል ነው አህጉሪቱ አሁን ላይ ያላትን ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ማግኘት የቻለችው። በተለይም ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ቅኝ ግዛት ወራሪን እምቢኝ ብለው ባደረጉት ተጋድሎ የመጣባቸውን የነጭ ወራሪ ድል መንሳታቸውና ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር መቻላቸው ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በጭቆና ላይ ለነበሩ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት መሆን ችለዋል። ይህም ነው ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ የነፃነት አርማና ተምሳሌት ሆነው በዓለም ላይ እንዲጠሩ ያደረጋቸው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ 46ኛውን የአንጎላን የነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- እንደ ሀገር ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጣንበት ቀን ልዩና ወሳኝ እለት ነው። ይህንን ልዩ በዓል ስናከበር ግን ሁሉ ለነፃነት የከፈልነውን ዋጋ ምንጊዜም ቢሆን ልንዘነጋ አይገባም። በተለይም ሁሉም አፍሪካዊ ሀገር የግዛት አንድነቱንና ሉዓላዊነቱን አስጠብቆ በማቆየት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋም ለሀገሩ እድገትና ብሔራዊ ጥቅም መከበር የየበኩሉን ሚና መጫወትም አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ እንዳለ አገር ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለን መልካም ግንኙነት በማሳደግ በትብብር መስራት ይጠበቅብናል። በተለይም በአጀንዳ 2063 ለመተግበር የታቀዱ የልማት መርሐ ግብሮች ስኬት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተን መስራት ይገባናል።
በሌላ በኩል እያንዳንዱ አፍሪካው ሀገር ዜጎቹ በተሻለ ደረጃ የልማትና የዲሞክራሲ ተጠቃሚ እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት ይገባል የሚል ሃሳብ አለኝ። በተለይም በየሀገራችን ውስጥ ያሉ አለመግባባቶችን በማስወገድ ለኑሮ ምቹ፤ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት አፍሪካ በመፍጠሩ ሂደት ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ራሱን ቆም ብሎ መፈተሽና ለዚህም በትጋት ሊሰራ ይገባል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር ዳ ክሩዥ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014