የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት ምግብ፤ መጠለያ እና ልብስ ባልተናነሰ መልኩ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩለት ይሻል። ለዚህ እንደማሳያ እንዲሆነን የሩቁን ትተን ትውስታው ያልደበዘዘውን የአረቡን ዓለም አብዮት (Arab Spring) መለስ ብሎ መመልከት ይበጅ ይመስለኛል።
ቱኒዚያውያን፤ ሊቢያውያን፤ ግብጻውያን ለረጃጅም ዓመታት የገዟቸውን ሰዎች በቃችሁን ብለው በአደባባይ ትዕይንት ለመሞገት እና ኋላም ከሥልጣን ለማስወገድ ያስገደዳቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ብቻ አልነበረም። ሶሪያውያንም ቢሆኑ የበሽር አል አሳድን ከአባት የተወረሰ ስርወ መንግሥት በመቃወም ነፍጥ ሲያነሱ የዚያች አገር ዜጎች የኑሮ ይዞታ እና የድኅነት ሁኔታ እኛ ኢትዮጵያውያን እንገኝበት ከነበረው ደረጃ የተሻለ ሳይሆን ቀርቶ አልነበረም።
በኮሎኔል ሙዓመር አል ጋዳፊ የአርባ ሁለት ዓመታት አገዛዝ ሊቢያ አስደናቂ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ኑሮ እመርታ አስመዝግባለች። በ41 ቢሊየን ዶላር ወጪ ከደቡብ ክፍል ወንዝ በመጥለፍ ሰሜናዊውን የሊቢያ በረሃማ ምድር ማልማት ጋዳፊ ካከናወናቸው ተጠቃሽ ግዙፍ ተግባራት አንዱ ነው። አገዛዙ ለሊቢያውያን የትምህርት፤ የጤና፤ የመጓጓዣ አገልግሎቶች እና ሌሎችም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ ከማድረጉም በላይ እያንዳንዱ ሊቢያዊ ሥራ ሳይኖረው ጭምር የነፍስ ወከፍ የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያ ያገኝ ነበር። “ሰው በዳቦ ብቻ አይኖርም” እንዲል መጽሐፉ፤ ከአምባገነንነቱ ባሻገር የፈጸማቸው መልካም ተግባራት ሁሉ ተደምረው ጋዳፊን እና አስተዳደሩን ከአስከፊ ውድቀት ሊታደጓቸው አልቻሉም።
ዴሞክራሲን የማያውቅ አስተዳደር እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አክብሮ የማያስከብር መንግሥት ሽቅብ ከወጣበት ርቀት በላይ ቁልቁል ይፈጠፈጣል። መብት ሲመች የሚበረከት፤ ሳይመች የሚነፈግ የችሮታ ጉዳይ አይደለም። በስመ ዴሞክራሲ መነገድና ዴሞክራሲያዊ መሆን ደግሞ መንገዳቸው ለየቅል ነው። ሕገ መንግሥት አርቅቆ እና አጽድቆ ሲያበቃ ሕገ መንግሥታዊ መሆን ተስኖት አገራችንን ከአንዱ ቀውስ ወደ ሌላው እያሸጋገራት እንደሚገኘው አሸባሪው ሕወሓት ዓይነት።
ባላገርነትን ከእርሱ ውስጥ ማውጣት አንድን ሰው ከባላገር እንደ ማውጣት ቀላል እንደማይሆን ከበዓሉ ግርማ ድርሰቶች በአንዱ ውስጥ ያነበብኩት ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር። ደራሲው እውነት ብሏል። ማንነታችን የተወጠነበት ሰበዝ ሁሌም ወደዚያው እየሳበ ያበጀናል። ጠዋት የተበጀንበትን ማንነት ልንረሳው ይቅርና ከጠንካራ ጥንውቱ የተነሳ ሁለተኛ ተፈጥሯችን እስከ መምሰል ይዘልቃል። ከአንድ ወዳጄ ጋር ምሣ ላይ ሆነን የተጋራነው ወግ ትዝ አለኝ። ያው ከሊሕቅ እስከ ደቂቅ ያለው ኢትዮጵያዊ እንደሚያደርገው ሁሉ ርዕሰ ጉዳያችን ሕወሓት ሆነ። ድርጅቱንና መሪዎቹን በተመለከተ አያሌ ጉዳዮችን አንስተን ጣልን። የድርጅቱንና የአመራሩንም የወንጀል ዶሴዎች አብዝተን አገላበጥን። በተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ሁሉ ተስማማን። ለወጋችን እልባት ለማበጀት የመፍትሔ ሐሳቦችን መሰንዘር ያዝን። ወደ መፍትሔ ጥቁምታ ያደረግነው ጉዞ ግን ፍትጊያው የዋዛ አልነበረም።
አሸባሪው ሕወሓት ሸፋጭ ድርጅት ነው። ከሸፍጥና ከሴራ ውጭ ሕልውና የለውም። በሸፍጥ ተፈጥሮ፤ ሸፍጥ ሲጎነጉን እና ሌላ ሸፋጭ እንዳይነሳበት በሸፍጥ እያደባየ የዘለቀ ድርጅት ከሸፍጥ ውጭ ለማሰብ ስለማይችል በምንም ሁኔታ ሴራ ከመሸረብ እና አሽክላ ከማጥመድ ባነሰ ሁኔታ ውስጥ መኖር አይቻለውም። መሪዎቹም ቢሆኑ የፈጸሙት ሸፍጥ የመንፈስ ሠላም ስለሚነሳቸው ጭር ሲል ደስ አይላቸውም። የንጹሐን ደም ጭምር አዕምሯቸው ውስጥ አዘውትሮ ስለሚጮኽ ጥፋትን በሌላ ጥፋት፤ በደልንም በሌላ በደል ለማስታገስ ከመሞከር ያለፈ የተሻለና ዘላቂ መፍትሔ ለማመንጨት የታደሉ አይደሉም።
የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሕልውና የሚረጋገጠው በግጭት ውስጥ ስለሚሆን ሠላም አይስማማቸውም። ሸፍጠኞችን ከጦርነት ይልቅ የሐሳብ ብዝሐነት ያስፈራቸዋል። እንቅልፍ ይነሳቸዋል። አንድም አይቀሬው ሞት ካልገላገላቸው ወይም ከፍትሕ አደባባይ ቀርበው በካቴና ካልተቆራኙ በስተቀር በሸፍጥ ተፈጥሮ፤ በሸፍጥ የኖረ አዕምሮ ከሸፍጥ ወደ ሸፍጥ ከመንሸራተት በቀር ምንም ዓይነት ጤናማ መንገድ አይታየውም።
እንዲህ ዓይነት ድርጅቶችም ሆኑ መሪዎቻቸው ከአቅማቸው በላይ ስለሚንጠራሩ እነርሱ ከሌሉ በስተቀር ጀምበር እንደማትሠርቅ ብትሠርቅም እንደማትጠልቅ ሊነግሩን ይከጅላቸዋል። የቀንና የሌሊት ፍርርቅ ከእነርሱ በፊት የነበረ እና ከእነርሱም በኋላ የሚቀጥል የተፈጥሮ ሒደት መሆኑን ሊነግራቸው የሚሞክር ካለ እርሱ እንደ ቀንደኛ ጠላት ይቆጠርና “ለምሣ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ዓይነት ዘመቻ ይጧጧፍበታል። ሸፍጠኞች ሠማዩን እንደ ባላ ደግፈው እንደያዙትና ከለቀቁትም እንደሚደረመስብን እየነገሩ ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ። ሕወሓቶችም ሲያደርጉ የዘለቁት ይህንኑ ስለመሆኑ አሌ የሚል ይኖር አይመስለኝም፤ ከራሳቸው ከሕወሓት ሰዎች በስተቀር።
አሸባሪው ሕወሓት በአማጺነት 17 ዓመት አስቆጥሯል። የማዕከላዊውን መንግሥት መንበር በአምባገነናዊ ፈላጭ ቆራጭነት፤ በሿሚና ሻሪነት ለ28 ዓመታት ተቆጣጥሮታል። ከመጋቢት 2010 ዓ.ም በኋላ ደግሞ በለየለት ሽፍትነት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ በማጎሳቆል ላይ ይገኛል። ሕወሓት የፖለቲካ ሕይወቱን በደደቢት በረሃ በሽፍትነት ጀመረ። አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ሲገባም ከደደቢት እንጂ ከሽፍትነት አልተላቀቀም። እነሆ ዛሬም ሽፍትነቱን ቀጥሎ ግድያውን፤ ዘረፋውን፤ ማፈናቀሉን፤ የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት እና ንብረት ማውደሙን በስፋት ተያይዞታል። ሕወሓት ከጫካ ቢወጣም የጫካው አስተሳሰብ ከሕወሓት አልወጣ ስለነበር ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖም ሸማቂነቱ አልተላቀቀውም።
ለዚህም ነው ሸፍቶ መንግሥትነት እና መንግሥታዊ ሽፍትነት በሕወሓት እንዲያበቃ የሚፈለገው። ሐሳቤን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ሲባል የሸፍቶ መንግሥትነትን እና መንግሥታዊ ሽፍትነትን ጽንሰ ሐሳብ በጥቂቱ በሚከተለው አኳኋን ለማብራራት ልሞክር።
ሸፍቶ መንግሥትነት
ሽፍትነት ብዙ ገጽታዎች አሉት። የሽፍትነት አንዱ መነሻ የሚሆነው በደል እና የፍትሕ መጓደል እንደሆነ የአገሬ ሰው እንዲህ ሲል ይገልጸዋል “ዝንጀሮ ተው ሲሉት ይጠጋል ከገደል፤ ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል”። በደልን እና የፍትሕ እጦትን መታገስ ይከብዳል። ስለዚህ ሰው ከውርደት እና ከጥቃት ራሱን ለመከላከል እንዲሁም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ተስፋ ሲቆርጥ ሽፍትነትን እንደ አማራጭ አድርጎ ሊወስድ ይገደድ ይሆናል። እንደ ከዳተኛው መስፍን እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሣ ያሉት ደግሞ ጦራቸውን አስከትለው ከጠላት ጋር በማበር ወንድሞቻቸው ግንባር ላይ አነጣጥረውቃታ ሊስቡ እና አገራቸውን ሊወጉ ይሸፍታሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ በሥልጣን ጥም የታወሩ ከመሆናቸው የተነሳ
ከሚቋምጡለት ዙፋን ውጭ የአገር ክብር እና የሕዝብ ፍቅር አይታያቸውም። ሌላኛው ሽፍትነት ደግሞ የግል ጥቅምን በእምቢታ ለማስጠበቅ ሲባል የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። በየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም የገጠር መሬት አዋጅን ተከትሎ አዋጁ ጥቅማቸውን የነካባቸው የመሬት ከበርቴዎች መውዜራቸውን ወልውለው እና ዝናራቸውን ታጥቀው ጫካ ገብተው ነበር።
የአገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እና ዳር ድንበሯን ላለማስደፈርም ይሸፈታል። የአምስቱን ዓመት የጣሊያንን ወረራ እዚህ ላይ ማስታወስ ይበጃል። ያኔ ማዕከላዊው ዕዝ ፈርሷል። ንጉሠ ነገሥቱም በአገር አልነበሩም። ኢትዮጵያ ግን ነበረች። ለኢትዮጵያ መኖር ደግሞ ምክንያት የነበሩት በዱር በገደሉ ተሰማርተው ግንባራቸውን ለአረር፤ ደረታቸውን ለጦር ያልሰሰቱት የአገር ባለውለታ ትንታግ አርበኞቿ ናቸው። ጣሊያን በኢትዮጵያ ግዛት እንዳይደላደል እና አገራችንም ከቅኝ ተገዥዎች ተርታ እንዳትገባ ያደረጋት የነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፤ ደጃዝማች አሞራው ውብነህ፤ ራስ አበበ አረጋይ፤ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር፤ ልጅ ኃይለማርያም ማሞ፤ ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፤ ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ፤ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፤ ፊታውራሪ ገረሱ ዱኪ፤ እና ሌሎችም ዘርዝሬ የማልዘልቃቸው ጀግኖች አርበኞች የፈጸሙት የነጻነትን ገድል ነበር።
በዚህ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ እነ ሞገስ አስገዶምን፤ አብርሃ ደቦጭን፤ ዘርዓይ ድረስን፤ ኮሎኔል አብዲሣ አጋን እና ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌን ጨምሮ ሌሎች በቅጡ ያልተዘመረላቸውን አርበኞች አለመዘከር አይቻልም። እነዚህ ዕንቁ አበው አገራቸውን ሞተው ሊያኖሯት ሸፈቱ። የቅኝ ገዥ አጀንዳ አስቀጣዮች ደግሞ በፊናቸው በጀግኖች አርበኞች ክቡር መስዋዕትነት የቆመን የአገር ሉዓላዊነት እና በደም እና አጥንት የጸናን የግዛት አንድነት ለማፍረስ ጫካ ገቡ።
ለሽፍትነት ለሽፍትነቱማ የአጥቢያው ኮከብ፤ ስመ ጥር ጀግና መይሣው ካሣ (ኋላ ዐጼ ቴዎድሮስ) ሽፍታ ነበሩ። የዐጼ ቴዎድሮስ ሽፍትነት ዓላማና ግብ ግን በዘረፋ የግል ሀብት ለማጋበስ፤ ሥልጣን ለማካበት፤ አገርን መቅኖ ለመንሳት አልነበረም። ይልቁንም ከሀብታም የተገኘን ጥሪት ለደሃ በማካፈል በዘመነ መሣፍንት ተበታትና የተጎሳቆለችን አገር ዝና እና ክብር ዳግም ከፍ ብሎ እንዲታይ ለማስቻል እንጂ። ዐጼ ቴዎድሮስ መቅደላ አምባ ላይ ሽንፈትን ተጠይፈው፤ የሚወዷትን ኢትዮጵያ ክብር ጠብቀው የጀግና ስንብት ሲያደርጉ እርሳቸውን ሊወጋ የመጣውን የናፒሪን ጦር መንገድ በመምራት፤ ከአጋሰስ የተረፈውን የወራሪውን ጦር ጓዝ በጫንቃ ሸክም በማጓጓዝ እና በአገር ቅርስ ምዝበራውም ጭምር ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ባንዳዎችንም ታሪክ በጥቁር መዝገቡ ሲዘክራቸው ይኖራል።
ዐጼ ቴዎድሮስ በተከታዮቻቸው እና በወታደሮቻቸው ብቻ ሳይሆን በገዛ ራሳቸው መስዋዕትነት ጭምር አንድነቷን ለማስጠበቅ ሲደክሙ በክብር ከወደቁ በ106ኛው ዓመት ወደ ደደቢት ያቀናው እና በለስ ቀንቶት ከመይሣው እረፍት በ123ኛው ዓመት በኋላ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የመጣው ሕወሓት አገራችንን እንደምን ላለው ጉስቁልና እንደዳረጋት ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም። አሸባሪው ሕወሓት ወደ ጫካ ሲያመራ የአንድን ብሔረሰብ የበላይነት ለማስፈን ከመሻት ያለፈ ሌላ ምክንያት አልነበረውም። አገርን ከወረራ ለመከላከል እንዳይባል በየካቲት 1967 ዓ.ም የተከሰተ የጠላት ወረራ አልነበረም። ይልቁንም በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከወረረው የሶማሊያ ጦር ጎን ቆሞ ቡድኑ አገርን የማፍረስ ውጉዝ ተግባር መፈጸሙም እርግጥ ነው። የአስተዳደር በደልን ሰበብ እንዳያደርግም በቂ መነሻ አልነበረውም።
አሸባሪው ሕወሓት ለሽምቅ ውጊያ በረሃ የገባው ለዘመናት አገሪቱን ይገዛ የነበረው ንጉሣዊ አስተዳደር ከሥልጣን ከተወገደ ገና በአንድ ዓመት ቆይታ ውስጥ መሆኑንም ልብ ይሏል። ቡድኑ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ቢኖረው ኖሮ ለመቶ ሺህዎች ሞት እና ስፍር ቁጥር ለሌለው ቁሳዊ ውድመት ለዳረገን የእርስ በእርስ ጦርነት ክተት ከማወጅ ይልቅ በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ሁነኛ ቦታ በመያዝ ለአገረ መንግሥት ግንባታው አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ በቻለ ነበር። አገር ለመሰብሰብም አገር ለመበተንም ይሸፍቷል ማለት እንዲህ መሆኑም አይደል?
አሁን የምንገኘው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ከብሉይ ዘመን የአስተዳደር እሳቤ ጋር ካልቆረብን በስተቀር የአመራር ጥበቡም፤ የአኗኗር ሥርዓቱም ሌላው ቀርቶ የጦርነት ብልሃቱም እጅጉን ተለውጠዋል። የዘመናዊው ዘመን ሕዝባዊ አስተዳደር በሐሳብ ፍጭት እንጂ በጡንቻ ግጭት ላይ እንዲንጠለጠል አይጠበቅም። ብረት ነካሽነት የዘመኑ ተመራጭ መስመር አይደለም። ሸፍቶ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው ሕወሓት ተጀምሮ እስከሚጨረስ ራሱንና ጉልበቱን ብቻ ሲያመልክ እንጂ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ እና ለኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ግድ ሲለው አላየንም። እንዲያውም የሚጠላትን አገር የመግዛት ዕድል ከማግኘቱ የተነሳ በዕለት ተዕለት ክዋኔዎቹ አገራችንን ትንሽ በትንሹ ሲያፈርሳት ዘልቋል። ከዚህ በኋላ ግን የሚያዋጣ ሐሳብ ያለው ሁሉ በሕዝቡ እየተዳኘ እና ይሁንታ እያገኘ እንጂ ማንኛውም ቡድን በሽፍትነት እና በሸፋጭነት የመንግሥትን ሥልጣን የሚቆጣጠርበት በር ጨርሶ መዘጋት ይኖርበታል።
መንግሥታዊ ሽፍትነት
ሸፍቶ መንግሥትነት መገታት አለበት ሲባል መንግሥታዊ ሽፍትነትንም ባለመዘንጋት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባናል። እንዲያውም፤ መንግሥታዊ ሽፍትነት የሸፍቶ መንግሥትነት ማቀጣጠያ ነዳጅ እንደሆነ ልንገነዘብ የግድ ይለናል። አሸባሪው ሕወሓት በሽፍትነት ወደ ሥልጣን መምጣቱ ሳያንሰው፤ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑን ያለ ተቀናቃኝ ከተቆጣጠረ በኋላም ቢሆን ከሽፍታ ባሕርያቱ እና የሽፍትነት ተግባራቱ አልታቀበም። መንግሥት ሆኖ አገር እንዲመራ በታሪክ አጋጣሚ እጁ ላይ የሆነውን ኃላፊነት ጨርሶ በመዘንጋት ወረዳ ወርዶ ታክሲ ላይ ፈንጂ የሚያጠምድ ተራ አሸባሪ ሆኖ ታገኘዋለህ።
በመንግሥትነት ፍትሕ ርትዕ እንዲያሰፍን የተጣለበትን ኃላፊነት እርግፍ አድርጎ በመተው በሐሰት ውንጀላ፤ በተቀነባበር ክስ እና በሐሰት ምስክር የፍትሕ ውርጃ ሲፈጽም ታየዋለህ። ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል የመሆናቸውን መርህ እንዲያስፈጽም በተሰየመበት መንበር ላይ ተመቻችቶ ተኮፍሶ ሲያበቃ በአፍራሻው ዜጎችን “ወርቅ እና ጨርቅ” እያለ ሲፈርጅ ትሰማዋለህ። ለመላ አገሪቱ አመራር እንዲሰጥበት በተደራጀ ቢሮ ውስጥ የአንድን አካባቢ ኢንዳስትራሊዜሽን ፖሊሲ በማርቀቅ ሥራ ላይ ተጠምዶ ታገኘዋለህ። መንግሥታዊ ሽፍትነት ይሉሃል ይኼ ነው።
የአገሩን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር በየትኛውም መስፈርት በዜጎች መካከል እና በመኖሪያ አካባቢም ጭምር ምንም ዓይነት ማበላለጥ እና አድሎ ሳይፈጽም አገር እንዲያለማ የተጣለበትን መንግሥታዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ሕወሓት አገርንና ሕዝብን እየዘረፈ ሀብት በማሸሽ ላይ ተጠምዶ ከርሟል። ምዝበራ እና ብልሹ አሠራር ተቀናቃኞችን ለመምታት ካልሆነ በስተቀር በግብረ አበሮች ሲፈጸሙ እንደ ጽድቅ ሲቆጠሩ ዘልቀዋል። ዓይን ያወጣ ዘረፋ መዋቅራዊ መልክ እንዲይዝ ተደርጓል። ለሕጋዊ ሕገ ወጥነት መንሰራፋትም ጥርጊያ መንገድ አበጅቷል። ጠንካራ አገር ያለ ጠንካራ መንግሥት፤ ጠንካራ መንግሥትም ያለ ጠንካራ ተቋማት እንደማይኖሩ እየታወቀ አሸባሪ ሕወሓት መንግሥታዊ ሥልጣኑን በመጠቀም የአገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ተቋማት ከጎጥና ከጎሣ ያለፈ ትልቁን ምስል ማየት የሚያስችል ቁመና እንዳይኖራቸው ተደርገው እንዲዋቀሩ አድርጓል። በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ብቻም ሳይሆን የጥቃቱ አቀናባሪዎች እና ፈጻሚዎች የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት የመምራት አደራ የተጣለባቸው የሕወሓት ሰዎች መሆናቸውን ከመጥቀስ ያለፈ ለዚህ የሚሆን ማስረጃ እያፈላለጉ መድከም ያሻኝ አይመስለኝም።
አሸባሪው ሕወሓት ከውስጡ ፈጽሞ ሊያወጣው ያልቻለውን ሽፍትነት ለመቀጠል ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ለዳግም ኩብለላ ጓዙን ሲሸክፍ በተሳሳተ ስሌት ላይ ከጣሉት ጉዳዮች አንዱ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን በማፍረስ እና ትጥቁን በመውረስ እንደገና አገር የማተራመስ ዕድል በእጁ ማስገባት የመቻል ምኞቱ ነበር። በመሆኑም በልዩ ኃይል ሽፋን አንድም መድፍ፤ አንድም ታንክ ወይም የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሳይታጠቅ ነገር ግን ሜካናይዝድ ጦር አሰልጥኖ አዘጋጅቷል። ይህም የሆነው በሰሜን ዕዝ ይዞታ ስር የሚገኙትን ሚሳኤሎች ጨምሮ ሁሉንም ከባድ መሣሪያዎችን ወርሶ ባሰበው ፍጥነት አልበታተን ብላ ያስቸገረችውን ኢትዮጵያን ለመውጋት ነው።
ወደ ባሕር ዳር እና ጎንደር ባስወነጨፋቸው የረዥም ርቀት ሮኬቶች እና ባደረሱትም ጉዳት በጥቂቱም ቢሆን ዕቅዱን ወደ ድርጊት መንዝሮ አሳይቶናል። ከዚህም ባሻገር 1.8 ሚሊየን የትግራይ ነዋሪ ከድኅነት ወለል በታች እየኖረ በሴፍቲ ኔት የዕለት ጉርሱን እና የዓመት ልብሱን ሊያገኝ በሚጣጣርበት ክልል የክልሉ አስተዳደር በኮንክሪት ምሽግ ግንባታ ሥራ ተጠምዶ ኖሯል። እህል ይቀብራል፤ የጦር መሣሪያ ከነተተኳሹ ይቀብራል፤ ነዳጅ ይቀብራል፤ ተሽከርካሪ ይቀብራል። ከዚህ ያለፈ እና የገዘፈ መንግሥታዊ ሽፍትነት ይኖር እንደሆነ እኔ እርግጠኛ አይደለሁም።
የመንግሥት ኃላፊነት ቅራኔዎችን ማርገብ እና በዜጎች መካከል መግባባትን ማጎልበት መሆኑ ማንም በቀላሉ የሚገነዘበው እውነታ እንደሆነ አምናለሁ። ሕወሓት በጫካ ሳለ ያደረገውን ለጊዜው እንተወውና የአዲስ አበባውን ቤተመንግሥት በእገታው ስር ካዋለ ማግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን መካከል የፈጠራ ቅራኔዎችን ለመቀፍቀፍ እና ለማዛመት ሲደክም ሰንብቷል። ሊያስገብሩን የቋመጡት አውሮፓውያን ከፋፍለው ሊገዙን የነደፉትን በነገድ እና በቋንቋ የተሸነሸነ አስተዳደር እውን በማድረግ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት እና ሁለተኛ ዜግነት እንዲሰማቸው አድርጓል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሱማሌ ክልል፤ ሌሎች በሚሊየን የሚገመቱ የጌዴኦ ተወላጆች ከምዕራብ ጉጂ አካባቢ ዕድሜ ልክ ያፈሩትን ሀብት እና ንብረት አጥተው ለሞት፤ ለስደት እና ተመጽዋችነት የተዳረጉት ከዚሁ እቡይ የአገዛዝ ዘይቤ የተነሳ ነው። በተለይም ድርጅቱ በማኒፌስቶው ጥርሱን የነከሰበትን የአማራ ማኅበረሰብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እና በየትኛውም መልኩ ሕልውናው አደጋ ላይ እንዲወድቅ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ከአርባ ጉጉ፤ ከበደኖ፤ ከወተር፤ ከአሰቦት ገዳም አንስቶ፤ ጊዳ ኪራሙን ይዞ በሌሎች የምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ክፍሎች፤ በጉራ ፈርዳ፤ እንዲሁም በአሶሳ እና መተከል በአማራ ንጹሐን ደም ያልጨቀየ ምድር የለም። አሁንም እልቂትና መፈናቀሉ ጋብ አላለም።
ይህ ሁሉ በመንግሥታዊ ሽፍትነት ዘመን የተዘራ የክፋት ቡቃያ መሆኑን ማንም አይዘነጋውም። በእጅ አዙር ይመራው የነበረው የዘር ፍጅት አልበቃ ብሎት ሕወሓት በአሁኑ ሰዓት ጭምር በአማራው ሕዝብ ላይ የጅምላ ግድያ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በቀጥታ እየፈጸመበት ይገኛል። እዚህ ላይ በኢትዮጵያዊነቱ ፈጽሞ ድርድር የማያውቀው የአፋር ሕዝብ እየተቀበለ የሚገኘው መከራ ለጥቂት እንኳን ሊዘነጋ የተገባው አለመሆኑን ልብ ይሏል። ይህ ድርጊትስ ቢሆን መንግሥታዊ ሽፍትነት ካልተባለ በስተቀር ሌላ ምንድን ሊሆን ይችላል?
እኔ መንግሥታዊ ሽፍትነት የምለው የመንግሥትን መዋቅር ተገን አድርጎ የሚፈጸም ማንኛውንም አድሎአዊነት፤ ኢፍትሐዊነት፤ ከአገር ይልቅ የግል እና የቡድን ፍላጎትን ማስቀደምን ነው። አጋጣሚ አገኘሁ ብሎ ፍትሕን ማጓደል፤ ደሃን መበደል መንግሥታዊ ሽፍትነት ነው። የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሽፍቶች ሕገ ወጥ ድርጊታቸውን ለመፈጸም ከጫካው ይልቅ በደራው ከተማ የሚገኙትን የመንግሥት መዋቅሮችን ይመርጣሉ። መንግሥትን ከውጭ ወደ ውስጥ ከመግፋት ይልቅ ከውስጥ ሆኖ መገዝገዝ ይበልጥ ውጤታማው ስልት እንደሆነ ያምናሉ። በሸንጋይ አንደበት መንግሥትን ተጠግተው ሲያበቃ ሕዝብን በማማረር በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደርጋሉ።
እነዚህ መንግሥታዊ ሽፍቶች ፍትሕን በማዛባት፤ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመርገጥ፤ በነጻነት የመኖርን እና ሐሳብን የመግለጽ መብትን በማፈን፤ ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እና ከበሬታ በመንፈግ፤ ጉቦኝነትና ንቅዘትን በማስፈን ሥርዓቱን እንደ ጥንጣን ቀስ በቀስ ይቦረቡሩታል። ቆይቶም ተመልሶ ሊቆም በማይችልበት አኳኋን ይደረምሱታል። መንግሥት መንግሥታዊ ሽፍቶችን ከእቅፉ ውስጥ መንጭቆ የማውጣት ፈቃደኝነት እና አቅም የማይኖረው ከሆነ ሕልሞቹም ትልሞቹም ዳር የማይደርሱበትን እውነታ ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ይገደዳል።
ከዚህ በመነሳት ነው፤ ሸፍቶ መንግሥትነት እና መንግሥታዊ ሽፍትነት ይብቃን የምለው።
ዓለማየሁ ደበበ (ፒ.ኤች.ዲ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2014