መምሬ ካሳሁን እንግዳ ይባላሉ። የተወለዱት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳ፤ «ላይ ቤት ዋርኝ» ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው። ልዩ ስሙ «ኮሽም» ይባላል። ትምህርታቸውን በቤተክህነት ያጠናቀቁትም እዚያው አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። መምሬ ካሳሁን ባለቤታቸውን ወለተ ሚካኤልንና የመጀመሪያ ልጃቸውን ውብነሽን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ግቢ ገብርኤል አካባቢ ይኖሩ ነበር። ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ያገኟቸው በግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ እንደሆነም ይነገራል።
ንጉሱ የቅዱስ ጊዮርጊስን ፅላት አራዳ ላይ ሲተክሉ መምሬ ካሣሁን ተመርጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ ተደረገ። አፄ ምኒልክ የአድዋ ዘመቻን ሲያውጁም እዚያው ነበሩ። ባለበርኖሱ አዛውንት መምሬ ካሣሁን የጊዮርጊስን ታቦት ከተሸከሙት ውስጥ አንዱ ሆኑ። በባዶ እግራቸው ከዘማቾች ጋር እስከ አድዋ ድረስ ተጉዘዋል።
ከድል በኋላም ፅላቱን አዲስ አበባ ይዘው ተመለሱ። እስከ ዕለተ እረፍታቸው ጥቅምት 22 ቀን 1937 ዓ.ም ድረስም በዚያው ሲያገለግሉ እንደቆዩ ታሪካቸው ያስረዳል። ባለታሪኩ መምሬ ካሳሁን ህይወታቸው ሲያልፍ ሲጠቀሙባቸው የቆዩት እቃዎች ለገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ መዘክር እንዲቀመጥ ተደርጓል። 150 ዓመት ያስቆጠረ የብራና ዳዊታቸው፣ የዘመቻና የአቋቋም ስርዓቱን የሚያሳይ ፎቶቸውም በሙዚየሙ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት12/2011