ጀግንነት ግን ለኢትዮጵያውያን ዘረመላዊ ተፈጥሮ ሳይሆን ይቀራል? ባህላችን ራሱ እኮ በተዋጊነት፣ በገዳይነት፣ በአይሸነፌነት ላይ የተመሰረተ ነው። የአገር ቤት የባህል ዘፈን ውስጥ ‹‹አያ በለው በለው!›› የሚለው አዝማች የብዙ ዘፈኖች ማስጀመሪያ ነው። ለልጅ ስም ሲወጣም እንደዚሁ ነው፤ በለው፣ ደም መላሽ፣ አሸንፍ፣ አስጨንቅ፣ ቅጣው፣ አሳምነው…ብቻ የሆነ የተደባዳቢነት መልዕክት ያለው ስም ነው። የልጆች ጨዋታ ራሱ እንደዚሁ ነው።
በቃ ግንባር ፈጥሮ መጋጠም፤ አሸናፊው ቡድን ይጨፍራል ተሸናፊውም ይቆጫል። የሚገርመው እኮ ደግሞ ተሸናፊው ራሱ ተሸናፊ አይደለም፤ መልሶ መጋጠም ያምረዋል። ልጆች ገና እረኛ እያሉ ትግል ይገጥማሉ፤ በትግሉ የወደቀ ተነስቶ እንደገና ይይዛል። እንኳን ልጆቹ ራሳቸው የሚጠብቋቸውን ከብቶች ራሱ ማጋጠም የተለመደ ነው። በሬው ያሸነፈለት እረኛ ከጦር ሜዳ ድል ያደረገ ያህል ኩራት ይሰማዋል። የገና ጨዋታው፣ የኳስ ጨዋታው፣ የድብብቆሽ ጨዋታው፣ የዒላማ ጨዋታው ሁሉ ከአሸናፊነትና ተሸናፊነት ጋር የተያያዘ ነው። ዛሬ ዓድዋ በዓል ነው። መቼም ስለዓድዋ እኔ አልነግራችሁም።
ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ባህልና ወግ ከጀግንነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ማውራት ይሻላል። ይሄን ደግሞ እንደአንድ የገጠር ልጅ ምስክር ስለሆንኩ ነው። በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ምንሽር ከያዘው ወታደር እኩል ማሲንቆ የያዘ አዝማሪ ይሰለፍ ነበር አሉ። እንዲያውም የወታደሩ ወኔ አዝማሪው ነው። ይሄ ታሪክ ተጽፎ የምናነበው ታሪክ ነው። እኔ ደግሞ በአይኔ ያየሁትን በጀሮዬ የሰማሁትን ልናገር (የግድ ሽማግሌ መሆን አለብኝ እንዴ?) ገጠር ውስጥ እንደ ሰርግ የመሳሰሉ ድግስ የሚደገስባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ተሰባስቦ መጫወት የተለመደ ነው። ጨዋታ ማለት ታዲያ ቀረርቶና ፉከራው ነው።
በዚህ ቀረርቶና ፉከራ ውስጥ ነው እንግዲህ ተዓምር የሚታየው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አባቶች ቀረርቶና ፉከራውን ያስቆሙታል። በአካባቢው የተጣላ ሰው ካለ በአቅራሪነት የሚታወቁ ሰዎችን ቀደም ተብሎ ይነገራቸዋል። እገሌና እገሌ ተቀያይመዋልና የዚያን ዕለት አደራችሁን ምንም አይነት ቀረርቶ እንዳትጀምሩ ይሏቸዋል። ቀረርቶው ከተጀመረ ፉከራ አለ፤ ፉከራ ካለ እንግዲህ መሳሪያውን አቀባብሎ አለበለዚያም ዱላውን ይዞ ወደተጣላው ሰው መሮጥ ነው። እርግጠኛ ነኝ እዚህ ላይ አንድ ነገር ገምታችኋል። እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ መጠጥ ስላለ በስካር ተገፋፍተው ነው የሚል። ከገመታችሁ ትክክል ናችሁ፤ ስካርም አለ። ዳሩ ግን ከስካሩ በላይ ቀስቃሹ ቀረርቶና ፉከራው ነው። ይሄን ነገር ብዙ ሰው ልብ የሚለው አይመስለኝም።
የገጠር ነዋሪዎች በስካር ከሚነሳሱት ይልቅ በቀረርቶ የሚነሳሱት ነው የሚበልጠው። በነገራችን ላይ የገጠር ነዋሪ ሁሉ የሚጠጣ እንዳይመስላችሁ፤ መጠጥ በሄደበት የማይሄዱ አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ግን ቀረርቶና ፉከራ ሲነሳ ሳግ እየተናነቃቸው ይፎክራሉ። እንዲያውም ተቃራኒውን ልንገራችሁ። እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይጥንብዝ ብሎ የሰከረ ሰው ሊያቅራራም ሊፎክርም አይችልም። ዝም ብሎ ይዘባርቃል እንጂ ወኔ ቀስቃሽ ግጥም ሊናገር አይችልም። እንዲህ አይነት አጋጣሚ ለገጠሩ ነዋሪ እንደነፃ ፕሬስ ያገለግላል።
የልባቸውን የሚናገሩት፣ በነገር የሚወጋጉበት ነው። ለዚያውም በቅኔ ነዋ! እስኪ አንዳንዶቹን እንያቸው (መቼስ ዓድዋም አይደል?) የተጣላን ሰው ማስታረቅ የተለመደ ነው። ታዲያ በእርቁ ያልተስማማ ወይም እርቁን ማፍረስ የፈለገ ብሶተኛ ለተቀናቃኙ እንዲህ ይላል። «ውሽልሽል ነው አልጠበቀም እርቁ አውድማው ይለቅለቅ በሮችም አይራቁ» ይላል።
ሁለቱም ተቀናቃኞች ነገረኛ ከሆኑና ጠቡ የማይቀር መሆኑን ለመግለጽ ይመስላል ሌላ (ሦስተኛ ወገን) ደግሞ ለሽማግሌዎች መልዕክት ይሆን ዘንድ እንዲህ ይላል። «አንድ መልክ በሮች ከዳገት ጠምዳችሁ ኋላ መመለሻው እንዳይቸግራችሁ!» በእንዲህ አይነት ጉዳይ ነው የተከፋን ሰው ከሚናገረው ግጥሞች መረዳት ይችላሉ።
ገና አዲስ ጠብ ለመጀመር ያሰበ ራሱ ያስታውቃል። ከሰው ተጣልቶ ቤቴን፣ ልጆቼንና ንብረቴን ያለ ሰው ደግሞ እንዲህ ሊል ይችላል። «ጓዜን ጠቅለል ጠቅለል፤ ከብቴን ነዳ ነዳ ምናልባት ሰው ሆኜ ጠላቴን ብጎዳ» ብዙ ጊዜ በጠብአጫሪነት የሚታወቁት ደግሞ ብዙም ሀብትና ንብረት የሌላቸው ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጓዝና ሀብት ባላቸው ደግሞ እንደ ጀግና ሳይሆን እንደቦዘኔም ይታያሉ።
‹‹ማረስና ሀብት ማፍራት ሲያቅተው›› እያሉ በነገር ጎሸም ያደርጉታል። እሱም ደግሞ ይሄን ቦዘኔነቱን እንደ ጀብዱ ነው የሚቆጥረው። ከአንድ ሀብታም ጋር ቢጣላ እንዲህ ሊል ይችላል።
«አትንኳት ጎጆዬን በአንድ እግሯ ቆማለች ትልቁን አዳራሽ ይዛው ትጓዛለች!» የውስጡ ወኔ አላስቀምጥ አላስተኛው ይለውና ዳሩ ግን የልጆቹ፣ የቤቱና የቤተሰቡ መጉላላትን ሲያስበው ደግሞ ግራ ይጋባል።
ጓዝና ቤት ያለው እንዲህ አይነቱ ሰው ደግሞ እንዲህ ይላል። «ላሚት እሳት ወልዳ፣ እንዳትልሰው ፈጃት፣ እንዳተወው ቆጫት፣ የማይረባ ኑሮ ያደርጋል እመጫት!» እንግዲህ የሚረባ ኑሮ ማለት ለእርሱ ክላሽ ይዞ ሰውን ማስፈራራት ነው ማለት ነው። ኧረ ወዲያ! በጣም አበዙት እኮ! እንዲያው ዕለቱ ዓድዋ ስለሆነ እነዚህን ስነ ቃሎች ተጠቅምን እንጂ በዚህ ዘመንስ ደግም አይደል! ዳሩ ግን አንድ ነገር ያሳየናል። ጀግንነት የኢትዮጵያውያን የደም አይነት ሆኗል። እነዚህን ስነ ቃሎች ያስፈጠራቸው የውስጥ ወኔያቸው ነው። እነዚህ ገበሬዎች የዓድዋን ታሪክ ላያውቁት ሁሉ ይችላሉ። ጀግና ያደረጋቸው የምንም ነገር ተፅዕኖ አይደለም ለማለት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
በዋለልኝ አየለ