በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅናን አግኝተው ይንቀሳቀሳሉ። እነዚህ ፓርተዎች ለአገር ለወገን ይጠቅማል ያሉትንም ሁሉ ያንጸባርቃሉ። አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ አቋም ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲ ተከፋፍለን የምንታይበት ሳይሆን በአንድ የምንሰባሰብበት መሆኑን ቀድሞ ገብቷቸዋል። እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎችም ይህንን ጉዳይ ከግምት በማስገባት በጥምረታቸው አማካይነት በአንድነት ቆመው አገራቸውን ከችግር ለማውጣት የተለያዩ ተግባራትን እየከወኑም ነው።
ፓርቲዎቹ አመራሮቻቸውን ጦር ግንባር ላይ ከማሰለፍ ጀምሮ ለመከላከያው ደጀን በመሆን በሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ቀድመው በመገኘትም ወገናዊነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የእናት ፓርቲ አንዱ ነው። ፓርቲው መንግስት ያወጀውን የክተት ጥሪ ተቀብሎ አባላቱና ደጋፊዎቹን ወደ ጦር ግንባር ከመላክ ጀምሮ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሰባሰብ ደም በመለገስና ሙያዊ ድጋፍን እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አገራዊ ግዴታውን እየተወጣ ስለመሆኑ የፓርቲው ተጠባባቂ ፕሬዚደንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው ይገልጻሉ። እኛም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ ፓርቲያችሁ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ይመለከተዋል?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ከእለት ወደ እለት ጥሩ ነገር እየተመለከትን አይደለም ። ምናልባት የዛሬ ዓመት ላይ ሆነን በምንመለከትበት ጊዜ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት የነበረው ነገር ብዙ ያልጠራ ነበር፤ በኋላ ደግሞ በሰሜን እዝ ላይ ያንን መሰል ጥቃት ተፈጸመ ። ይህንን ተከትሎ በሽብር ቡድኑ በሕወሓት ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ ጠንከር ያለና ጎልቶ የሚታይ ነበር፤ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓም በኋላ ያሉት ነገሮች ግን ለኢትዮጵያ ጥሩ ካለመሆናቸውም በላይ ከዛ በኋላ በየአካበቢው ከፍተኛ የሆነ የጥቃት መስፋፋት እየታየ ነው። በዚህ ደግሞ አማራና አፋር አካባቢዎች ላይ በሰፊው ችግሮች እየተስተዋሉ ሰዎች እየሞቱ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ንብረት እየወደመ ያለበት ነገር አገራችን ጥሩ ሁኔታ ላይ አለመሆኗን የሚያሳይ ነው። ይህንን ተከትሎም መንግስት አጸፋዊ ምላሹን ለመስጠት ጥረት እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሃገር ከገባችበት የህልውና ስጋት እንድትወጣ እንደ ፓርቲ ያለው አማራጭ ምን ሊሆን ይገባል ትላላችሁ?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ አሁን አገር የህልውና ስጋት ተጋርጦባታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ስጋት እንዴት ነው መውጣት የሚቻለው የሚለውም አለ፤ አሁን ያለንበት የህልውና ስጋት ከመወጣት አንጻር የአገርን ህልውና ማንም ሊያስጠብቅ አይችልም፤ አገር በልጆቿ ክንድ ህልውናዋ ሊጠበቅ ሊከበር ይገባል። ይህ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት በተለያዩ መንገዶች መልዕክቶችና ጥሪዎችን ለዜጎች ሲያቀርብ ቆይቷል፤ በማቅረብ ላይም ነው። ዜጎችም ለዚህ በጎ ምላሽ ከመስጠትም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተመው የአገራቸውን ህልውና ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ነው።
ይህ የዜጎች ምላሽ አገርን ከችግር ከማውጣቱም በላይ ህልውናዋን ለማስከበር አይነተኛ ሚና እንዳለው ታውቆ መንግስት ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሊመራው ሊጠቀምበት ይገባል። መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ህዝቡ ይህ ችግር የአማራ ወይንም የአፋር አልያም የሌላ አካል ነው ሳይል ችግሩ የኢትዮጵያ ነው፤ የአገሬን ችግር ደግሞ የምወጣላት እኔ ነኝ፤ ብሎ በአራቱም መዓዘን ከጫፍ ጫፍ ተሟል፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ነገሮች በትክክል ተቀናጅተው ተደራጅተው ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ እየተደረገ ነውን? የሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ። ይህንን ያልኩት ደግሞ ይህንን የህዝብ ማዕበል በአግባቡ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ ስለማላስብ ነው።
በመሆኑም ይህንን የህልውና አደጋችንን አስወግደን የአገራችንን መጻኢ እድል ከማሳመር አኳያ መንግስት እጁ የገባውን ይህንን ህዝብ በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤት ማስመዝገብ መቻል ይገባል።
ወታደር ከውጪ አገር ቀጥረን የአገራችንን ዳር ድንበር ልናስከብር ወይንም ደግሞ ይህንን መሰሉን የከሃዲዎች ሴራ ልናከሽፍ የምንችልበት ሁኔታ የለም፤ የአገራችንን ህልውና መጠበቅ የኛ የዜጎች ሃላፊነት ነው፤ ዜጎች ደግሞ እናት አገር ያቀረበችላቸውን ጥሪ በአግባቡ ሰምተው ምላሽ ሰጥተዋል፤ ዜጋ ምላሽ ሰጠ ማለት ግን የአገር ህልውና ይረጋገጣል ማለት አይደለም፤ ዜጋውም እንደ ዜጋ መንግስትም እንደ መንግስት አቀናጅቶና በአግባቡ መርቶ አሰማርቶ ውጤት የማምጣት ሃላፊነት አለበት። ይህንንም በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል።
በዘለቄታው የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ እየታሰበ ያለው የብሔራዊ መግባባት ውይይት አይነተኛ ሚናን ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ “ሆ” ብሎ የወጣውን ህዝብ በአግባቡ መምራት አልተቻለም ብሎ ማለት ይቻላል?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ አዎ፤ በእኔ ፓርቲ እይታ፤ አሁን ወቅቱ የምንወቃቀስበትም የምንሞጋገስበትም ጊዜ አይደለም፤ ልንወቃቀስ ከፈለግን በጣም ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነኚህን ሁሉ ችግሮቻችንንና ተከትለውት የሚመጡትን ወቀሳዎች ኋላ ለታሪክ በመተው እንዴት ጉዳዮችን አስተባብሮ ወደፊት እናስኪደው ? ምን አይነት ውጤቶችን እናምጣ? የሚለውን ነገር በእርግጠኝነት ማየት ያስፈልጋል፤ ይህንን አድርገን አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከተሻገርን በኋላ ደግሞ ሌላውን ነገር ቀስ ብለን እንደርስበታለን።
አሁን ለጠፋው ነገር መወቃቀስ ትንሽ ለተሰራችው በጎ ነገር ደግሞ ልንሞጋገስ አይገባም ። በእኛ እይታ ይህንን ያህል ሰራዊት እንዲነሳሳ ተደርጎ የተለያዩ ክልሎች ልዩ ሃይሎቻቸውን አዋጥተው ሚሊሻው ፋኖው ተሰባስቦ ባለበት ሁኔታ ወራሪው ሃይል በትንሽ ሃይል እየገፋ እዚህ ሲደርስ የሆነ ቦታ ላይ ክፍተት የለም ለማለት እቸገራለሁ። ግን አጠናክሬ ለመናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር ይህንን ሁኔታ የምንቆጣጠርበትና የምንጠያየቅበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ፓርቲዬ እየሰራ ያለውን ነገር አውቃለሁ፤ መንግስትም በተመሳሳይ እየሰራ ያለውን ነገር ያውቃል፤ በመሆኑም ይህ ነገር በዚህ መልኩ ከሄደ የት ላይ ነው ፍጻሜው የሚለው ነገርም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ፈትሾ የእርምት እርምጃ በሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች ላይ ማረሚያ አድርጎ አስፈላጊውን ውጤት ለማምጣት አለማሰለስ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ነው መናገር የምችለው።
ስለዚህ “ሆ“ ብሎ አገሩን ከጥፋት ለማዳን የተመመውን ሃይል በአግባቡ መምራት ካልቻልን መላው የአገሪቱ ህዝብ “ሆ” ብሎ ቢወጣ የሚያቀናጀው ውጤት በሚያመጣ መልኩ የሚያሰልፈው አካል እስካላገኘ ድረስ የህዝብ ብዛት ውጤት እያመጣም እንደውም ኪሳራ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራቡ ዓለም ለአሸባሪው ሕወሓት እድሜ ለመግዛት እያደረጉ ያለውን ሁለንተናዊ ዘመቻ እንዴት አገኙት?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ አሜሪካንም ሆነች አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በተለይም የተለየ ፍላጎት ያላቸው በአንድ ድምጽ አገራችንን እያጠቁ ስለመሆኑ እየታየ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን እንጂ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ ወይም የሌላው አይደለም፤ ኢትዮጵያን ሊያድንም ሊያጠፋም ሊታደጋትም የሚችለው ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው።
የትኛውም ጥግ ላይ የሚነሳ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሁሉ አስቀድሞ የሚመለከተው እኛን ነው፤ እነሱ ባዕዳን ናቸው፤ ነገር ግን በሰብዓዊ መብት ሽፋን ይመጣሉ፤ እኛም እንቀበላለን ምናልባት እርዳታ ሰጪዎቻችን ስለሆኑ፣ አጉራሾቻችን በመሆናቸው የሆነ ነገር እያነሱ በእኛ ጉዳይ ጥልቅ ሊሉ ይችላሉ እንጂ ስለእኛ እኛው እንበቃለን የእነሱን ሞግዚትነት አንፈልግም ይህንንም ሊረዱ ይገባል።
እነሱ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እንደውም ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካውያን ላይ ያሳደረችውን ነገር አለም ያውቀዋል፤ እኛ ጣልያንን ተዋግተን በመግፋታችንና በማሸነፋችን የፈጠረው ነገር ግልጽ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው ውጊያ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ዱር ለዱር ሲዘዋወሩ በነበሩ ልጆቿ ምን እንደፈጠረች ዓለም ያውቀዋል፤ በጠቅላላው አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ከማላቀቅ አንጻር ጠንካራዋ ኢትዮጵያ የተጫወተችውን ሚና ያውቃሉ።
እነሱ እስከአሁንም ድረስ በአንዳንድ አገሮች ላይ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ላይ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንድ ታዳጊ አገሮች እንደውም በእነሱ ፍቃድ ስር ያሉ ናቸው፤ በመሆኑም ቀና ብላ የምትሄድ ኢትዮጵያ ለእነሱ ስጋት ናት፤ በተቻለ መጠን አገሪቱ ቀና እንዳትል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
ለእኔ የእነዚህ አገራት ሴራ ሕወሓትን መታደግ አንድ ጉዳያቸው ሆኖ ሳለ ፍላጎታቸው ግን ከዛም በላይ ነው። በመሆኑም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እጃቸውን አስገብተው የኢትዮጵያን ጉዳይ ማመስ ላይ የሚሰንፉ አይደሉም።
በነገራችን ላይ የሁሉም ዜጋ አሻራ ያለበትን የህዳሴ ግድባችንን ብንመለከት እንኳን በጣም ብዙ እጅ ነው እየገባበት ለማደናቀፍ እየጣረ ያለው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እያደገች ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ በአንድ ልብ መካሪ በአንድ ቃል ተናጋሪ እየሆነ በሄደ ቁጥር ምን ሊፈጠር እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። በመሆኑም በተቻለ መጠን እጃቸውን አስገብተው ማመስን እንደ አማራጭ ይዘውታል።
ይህ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ አይደለም፤እንደዚህ አይነት ብዙ ችግሮችንም አልፋለች፡፡ ይህ አሁን ያለንበት ሁኔታም የመጨረሻችን ይሆናል ብዬ አላምንም፤ ይህንንም ተሻግረነው ደግሞ በሌላ ምዕራፍ እንደምንገናኝ በበኩሌ ይሰማኛል። ግን ደግሞ የውጭ ጠላቶቻችን ሺ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት እና ሊዘውሩን ቢሞክሩም እኛ ጠንካራ ህዝቦች በመሆናችን የአሁኑንም ጫናቸውን እንሻገረዋለን። ኢትዮጵያም ትቀጥላለች።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ምዕራባውያን ግን የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቦና በቅጡ አውቀውታል ይላሉ?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ ፈረንጆቹ ስነ ልቦናችንን የተረዱት አይመስለኝም። ሕወሓት ባለፉት 30 ዓመታት በተጠና መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ ፖለቲካን በደንብ አድርጎ ስር ሰዶ እንዲቆም አድርጓል። ከዚህም ባሻገር ህዝብን ለመከፋፈል የተዋጣለት የሚባል ሥራንም ሠርቷል። ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ባለፉት 30 ዓመታት አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች በማሳነስ የሚለያዩንን ጉዳዮች እጅግ አድርጎ በማግዘፍ ተሰርቷል። ሕወሓት ለውጥ አሻፈረኝ ብሎ መቀሌ ሲገባና ከዛም ይህ ጦርነት ሲቀሰቀስ የሁሉም በተለይም የውጭ መንግስታት የተገነዘቡት በቃ አገሪቱ በጎሳ ፖለቲካ ተከፋፍላለች አንድ ሆናም ተነጋግራ የመጣበትን ነገር መቋቋም የማትችል አድርገው ነበር የተረዱት። ይህ እንግዲህ ስነ ልቦናችንን አለማወቃቸውን የሚያሳይ ነው።
በነገራችን ላይ ይህ ጦርነት ስውር በረከትን ይዞ መጥቷል የሚል እይታ አለኝ ፤ይህንን ያልኩበት ዋና ምክንያት ደግሞ ተለያይተዋል የተባልን ህዝቦች ልክ የአገራችን ህልውና ሲነካ ፣ የሆነ ነገር ሲጋረጥና የተጋረጠውም ነገር እውን ሆኖ በሚታይበት ጊዜ እንደተገመተው የተለያየን አለመሆናችንን ነው ለዓለም ያሳየነው። በወረራው ማግስት የሁሉም ክልሎች አስተዳዳሪዎች የሰጡት ምላሽ ከሁሉም አካባቢ ቅሌን ጨርቄን ሳይል ችግሩ ወደተፈጠረበት ቦታ የተመመው ህዝብን በምንመለከትበት ጊዜ ጠንካራውን ስነ ልቦናችንን አልበገር ባይነታችንን ብሎም ልዩነታችንን ወደጎን ጥለን ለአገራችን በአንድ መቆም እንደምናውቅበት የታየበት ነው።
ከዚህ ቀደምም ቢሆን ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳችን እንዋጋለን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በህልውናዋ ላይ የተቃጣ ነገር በሚነሳበት ጊዜ ህዝቡ እንደ አንድ መቆምን የሚያውቅበት ነው። ይህንን ስነ ልቦናችንን በተለይም ምዕራባውያኑ አልተረዱትም፤ ምናልባትም ባለፉት 30 ዓመታት በተሰራው ከፋፋይ ሥራ አንድነታቸው ጠፍቷል የሚል እሳቤንም ይዘዋል። እኛ እንደ ህዝብ የተለያየ ቋንቋ ሀይማኖት ባህል ሊኖረን ይችላል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት በደማችን ውስጥ ያለ ነገር መሆኑን አልተረዱንም።
አዲስ ዘመን፦ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በአገራችን ላይ የጀመሩት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ አላማው ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ እነሱም እኮ የመንግስቶቻቸውን አስተሳሰብ ነው የሚያንጸባርቁት፤ እነ ሲኤን ኤን እኮ የአሜሪካን መንግስት የሚለውን ነገር አግዘው የሚወጡት፤ እኛ ደግሞ እነሱ የሚያራግቡትን የሃሰት ዘገባ ሊደመስስ የሚችል እውነት በደንብ አድርገን አጉልተን በሚረዱት መልኩ ማቅረብ ላይ ምንም አልሰራንም። እውነት አለን፤ በእጃችን ይህንን እውነት ምናልባት መንግስት በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እንዲደርሳቸው ያደርግ ይሆናል፤ ነገር ግን እነሱ የሃሰት ዘገባቸውን በሚያስኬዱበት መጠን ልክ እንደ አገር እውነታችንን መግለጽ ይገባናል።
እንዲህ አይነት ነገሮች ምናልባት በአንድ ሌሊት ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም፤ ተቋማዊ መልክ ይዞ በተከታታይ በተጠና መልኩ መስራትን ይፈልጋል። እንደ አለመታደል ሆኖ ባለፉት 30 ዓመታት እንደዚህ አይነት ተቋም ሳንገነባ ቀርተናል። ነገር ግን አሁን ችግሩ ሁሉ አፍጦ የመጣበት ጊዜ በመሆኑ በራሳችን መገናኛ ብዙሃን እንኳን መስራት ቢሳነን በመላው ዓለም ያሉ እድሉ አጋጣሚው የተመቻቸላቸው ለአገራቸው መስራት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ተጠቅሞ መስራት ግን ያስፈልጋል።
ከሰሞኑ አንኳን የምንመለከታት የሲቢኤስ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ እንዴት አድርጋ የአገሯን እውነት ለመላው ዓለም ለማስረዳት እንደምትጣጣር እያየን ነው፤ እሷን መሰል ብዙ አገር ወዳድ ዜጎች በመላው ዓለም አሉና መንግስት በገንዘብ ባይደግፋቸው የተጣራ እውነትን የሚያጎላ መረጃን በአግባቡና በተደራጀ መንገድ እየሰጠ አገራችን ላይ እየዘመቱ ያሉትን የሃሰት ወሬ ፈብሪካዎች መዋጋት መቻል አለብን።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያውያን ሆነው በተለያዩ ዓለም አገራት እየኖሩ ዜግነታቸውን የቀየሩ አካላትን መጠቀም ያስፈልጋል፤ እርግጠኛ ነኝ በእዚህ ወሳኝ ጊዜ ላይ እነሱም አገራቸውን ለመታደግ አይሰንፉም፡፡ በመሆኑም ባላቸው ግንኙነቶች ባሉበት አገር ላይ ሆነው የአገራቸውን እውነት ለመላው ዓለም እንዲያወጡ በባትሪ ፈልጎ ማሠራት ይገባል። አሁን እውነትን ብንይዝም መግለጽ ስላልቻልን አሳምነው እየተናገሩት ባሉት ውሸታሞች እውነታችን እየተቀማ ነው። እየሆነብን ያለው ነገር ይህ ነው።
ጠቅለል ስናደርገው ያለውን እውነት በአንድ ጀንበር መቀየር ላንችል እንችላለን፡፡ ነገር ግን እውነት ገብቶ ቶሎ ብለን መነሳት አለብን፤ ዝም ብለን ቁጭ ባልን መጠን አሁን ካለንበት የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ልንገባ እንችላለን በመሆኑም ለአገራችን ልንጮህላት ከቻልን ያንን ማድረግ ያለብን ዛሬ ነው፤ ነገ ከነገወዲያ ብለን የምናቆየው ነገር ሊኖር አይገባም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ይህንን ጊዜ በእርግጠኝነት ትሻገረዋለች።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ተልዕኮ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር ሰይፈስላሴ ፦ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ተራ ዜጋም ማንም ሊኖር የሚችለው አገር ሰላም ስትሆን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። አገር የምትባለው ሰብሳቢ እናት ችግር ላይ ከወደቀችና ከሌለች ፖለቲካ ፓርቲም ይሁን ምንም ይሁን ምን መኖር አይቻልም። እንደውም ባንጻሩ ስደተኛ መሆን ነው የሚመጣው። ስደት እንኳን ቢቀር በአምባገነኖች እጅ ገብቶ እያለቀሱ መኖር ነው የሚፈጠረው። በመሆኑም የእኔን ፓርቲ ጨምሮ ግንባር ቀደም ስራችን ሊሆን ይገባል ብዬ የማስበው የአገር ህልውና በምን ዓይነት መልኩ ልንታደግ እንችላለን የሚለውን ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ መሰናክሎችን አልፋለች፤ ልክ እንደ መሰናክል ሯጮች ከፊቷ የሚደቀኑ መከራዎች አሉ፤ ከዚህ በፊትም አሁንም ወደፊትም መሰል ችግሮችን ትሻገራለች። በመሆኑም ከእኛ የሚጠበቀው ልክ እንደ ህዝቦቿ አንድነትን ፈጥረው መንቀሳቀስ ነው የሚፈለግባቸው። በእርግጥ አሁን ላይ የአንድነቱ አስፈላጊነት በትክክል የገባን ጊዜም ላይ ነን። ምክንያቱም አገር ካልኖረች ተቃዋሚ፤ ደጋፊ፤ ገዢ ብለን ብንተራመስ ሁላችንም ጠፊ ስለምንሆን አሁን የቅድሚያ ቅድሚያ ስራችን ሊሆን የሚገባው አገራችንን ከገባችበት ችግር ማውጣት ብቻ ነው።
የራሴን ፖለቲካ ፓርቲ ለመጥቀስ ብሞክር ወቅታዊውን ሁኔታ ከስር ከስር ከመከታተል ጀምሮ አገር ድጋፋችንን በምትሻው ልክም የምንችለውን እያደረግን ነው። ከዛም ባሻገር ደግሞ ሁላችንንም በአንድ በሚያስተዳድረን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ውስጥም ጥሩ ተሳትፎ እያደረግን ነው። ይህንን ነገር ደግሞ አጠናክሮ መሄድ ላይ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ መንግስት ላወጀው የክተት አዋጅ ፓርቲያችሁ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው ? በቀጣይስ ምን ለማድረግ አቅዷል?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ የአማራ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ መግለጫ ካወጣ በኋላ እኛም መግለጫ አውጥተናል። በዚህም አገር የገባችበትን ችግር በዋናነት እየተጋፈጡ ያሉት አማራና አፋር ክልሎች ናቸው፤ ነገር ግን ይህ የሁለቱ ክልሎች ችግር ብቻ ካለመሆኑም በላይ ጥቃቱም የኢትዮጵያ ነው፤ የኢትዮጵያ ጥቃት ሊመለስ የሚገባው ደግሞ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ነው። በመሆኑም እናት ፓርቲ አገር አቀፍ ፓርቲ ነው፡፡ ደጋፊዎቹም በመላው አገሪቱ ያሉና በርካታ ናቸው፤ ከዚህም በላይ በትምህርት ደረጃም ከፍ ያሉና በትላልቅ ተቋማት ላይም በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያሉ ናቸው፤ በመሆኑም በዚህ ደረጃ ከፓርቲያችን የሚጠበቅ ነገር እንዳለ እናምናለን፡፡ አገር የምትጣራው እናት ፓርቲንም ጭምር ነው፡፡ አገር የምትሰጠው ምላሽም እናት ፓርቲ የምትሰጠው ምላሽ ነውና የፓርቲያችን አባላት አገር የምትፈልግባቸውን ምላሽ በአግባቡ እንዲሰጡ እኛም ጥሪያችንን አስተላልፈናል።
በሌላ በኩል ከአባላቶቻችን መካከል ጦር ሜዳ ድረስ የሄዱ አሉ፣ ደም ልገሳ ላይ በነቂስ ወጥተው ይሳተፋሉ፣ የተለየዩ አልባሳትና ቁሳቁሶችን እያሰባሰብን ለተጎዱ ወገኖቻችን እንዲደርሱ እያደረግን ነው፣ የህክምና ባለሙያዎች የሆኑ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ለጦር ቁስለኞች ቦታው ላይ በመሄድ የነጻ ህክምና እርዳታ እንዲያደርጉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ነን።
ሁሉም ወታደር መሆን ሲገባው ወታደር ነው፤ ነገር ግን መቶ አስር ሚሊየኖች ጦር ሜዳ ላይ ስላልሆንን ከአውደ ውጊያው ባልተናነሰ መልኩ በተሠማራንበት የሥራ መስክ አገር የምትጠብቅብንን ነገር አግባብ ባለው ሁኔታ መወጣት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ አባላትና ደጋፊዎቻችን በዚህ መንገድ እንዲሄዱም ጥሪያችንን አስተላልፈናል።
አዲስ ዘመን ፦ መላው ህዝባችን ይህንን ፈተና ለመሻገር ምን ማድረግ ይኖርበታል ይላሉ?
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ ኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ነች። ይህንን ደግሞ ዓለምም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ይህንን ሁሉ ዘመን ስታሳልፍ ግን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖላት አይደለም። እጅግ በጣም ብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋለች። ፈተና ማለፍ ደግሞ ያበረታል፣ ያጠነክራል። ፈተና ለምን አጋጠመንም አንልም፤ ምክንያቱም ፈተና መማሪያም ስለሆነ፤ እኔ በግሌ እንደ መልካም አሳቢ ዜጋ ኢትዮጵያ ዛሬ የገባችበት ችግር በቶሎም እያለፈችበት ያለው አይነት ፈተና ውስጥ ባትገባ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምክንቱም ይህ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ብዙ የተደከመበትን ሃብት እያጠፋ ያለ ብዙዎችን አካለ ጎዶሎ እያደረገ እያፈናቀለ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ጥሩ ነበር። ግን ደግሞ ሆነ አሁን ማድረግ ያለብን ታሪካችንን ወደኋላ መለስ ብለን በማየት ኢትዮጵያ በታሪኳ ካሉ አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱ እንደሆነና እየተሻገረች መሆኑን አውቀን እንደ ህዝብ በጽናት አብረን መቆም ያስፈልገናል።
አገሬን መታደግና ህልውናዋን መጠበቅ እንደ ዜጋ የእኔ ሃላፊነት ነው ብሎ ማሰብና በጽናት መቆም፤ ከዛ እንደምንሻገረውም እምነት ማሳደር፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስና የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን ማምጣት አለብን።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሰይፈስላሴ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014