አሸባሪው ሕወሓትን ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው …ይህ ሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው … እንዲህ አምርሮ የሚጠላቸው !? ለልጆቹ እንደሚሳሳ መልካም አባት ዊንጌት ቢሉ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ራሳቸውን እያሻሹ የሚበሉት፣ የሚጠጡትና የሚለብሱት ሳይጎድል ከቀዬያቸው አምጥተው ላስተማሯቸው ንጉስ ሀገርና ሕዝብ እንጥፍጣፌ ርህራሔና በጎነት እንዴት ያጣሉ። ውለታን ከማይረሳ ትግራዋይና ኢትዮጵያዊ አብራክ የተገኘ ስብስብ/ጉጅሌ /በዚህ ደረጃ ለምን አሪዎስ ሆነ ? ነው ከሌላ ፕላኔት የተገኘ ጉድ ነው ? አሸባሪውን ሕወሓት አይደለም በርዕዮተ አለምና በስልጣኔ/civilization /በአዘቦት ሰውነት እንኳን ለመገምገም ያስቸግራል ።
መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋልና ለ40 ዓመታት የዘለቀው ርዕዮተ አለም ላይ የተመሠረተው ቀዝቃዛው ጦርነት በአሜሪካና በአጋሮቿ አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላ አዲሱ ጎጆ ስልጣኔንና ባህልን/ሲቭላይዜሽን/ ዋልታ አርጎ እንደገና የተቀለሰ ነው ። ሀገራት በስልጣኔ ፣ በባህል፣ በእምነትና በቋንቋ ከሚመሳሰላቸው ሀገራት ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት ነው እንግዲህ ስልጣኔያዊ ትስስር የሚባለው። ከዚህ አኳያ አሜሪካና ምዕራባውያን በአንድ ረድፍ የሚሰለፉ ናቸው፤ ቻይናና እስያ በኮንፊሽየስና በቡድሀ ጥላ ሲሰባሰቡ፤ ራሽያ ደግሞ የኦርቶዶክስ አማኝ ሀገራትን አስከትላ በሌላ ረድፍ የምትሰለፍ ናት፤ ሱኒዎች ሳውዲ አረብያን ከፊት አድርገው ሲከተሉ፤ ሽያዎች ደግም ኢራንን አስቀድመው ይሰደራሉ። የሚገርመው ሀገራችን ኢትዮጵያ አልተጠቀመችበትም እንጂ በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት ከምዕራባውያን፣ ከራሽያና ከአረብ ሀገራትና ከኢራን ጋር ጠንካራ የስልጣኔ ግንኙነት መፍጠር ትችል ነበር። ምክንያቱም የሶስቱ አብርሀማዊ እምነቶች ማለትም የክርስትና፣ የአይሁድና የእስልምና ቀደምት መገኛ ታምረኛና ልዩ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር ጥንታዊውን ስልጣኔንም ስለምትጋራ ።
አሸባሪውና ፖለቲካዊ ድውዩ ሕወሓት ከስልጣኔ አኳያ በስነ ልቡና ፣ በእምነትና በቋንቋ ከተሳሰረው የኤርትራና የአማራ ሕዝብ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ሊኖረው ሲገባ የለየለት ጠላቱ አርጓቸው አረፈ። ይህ የፖለቲካዊ ድድብናው ጥሩ መገለጫ ነው ። በታሪኩ መርህ ሚባል ነገር ያልፈጠረበት አሸባሪዊ ሕወሓት ከአማራና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይልቅ ሱዳንና ግብፅ ይቀርቡኛል እስከማለት የደረሰ ጥልቀ ወመቀመቅ ወረደ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ።
ኢትዮጵያነት ተንከሲስ ማንነት ነው ሲል ዜግነትን የሚራገምና አምርሮ የሚጠላ የመጀመሪያ ድርጅት ሆነ። እያየሁ ኢትዮጵያ ስትፈርስ በማየቴ እድለኛ ነኝ አለ። የሚጠላትን ስሟን መጥራት የሚጠየፋትን ሀገር የገዛ የመጀመሪያው ድርጅት ነው። የእሱ እድል በሌላው መፍረስ የተመሠረተ ነውና። ጉጅሌው በድምሰሳው ከሰብዓዊነት ይልቅ ለጭራቅ ወይም ለዙምቢ ይቀርባል። በዚህ አውድ ሆኖ አሸባሪው ሕወሓትን ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው …ይህ እሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው … እንዲህ አምርሮ የሚጠላቸው በሚል የሚነሳው ጥያቄ የእኔም ፣ የትውልዴም፣ የትውልዶችም፣ የታሪክም ጥያቄ ሆኖ ይኖራል።
ከባዕድ ወራሪ፣ ከደመኛ ፣ ከአባት ገዳይ በላይ አምርሮ የሚጠላቸው፤ ከጀርባ እንዲህ ደጋግሞ የሚወጋቸው ፣ ጥፋታቸውን ውድቀታቸውን የሚመኘው ፤ በቁማቸው መቃብር የሚምሰው ፤ ጥላቻን ፣ ግጭትን 24 ሰዓት የሚቀፈቅፈው ፤ በሴራና በደባ ፖለቲካ ጠልፎ ለመጣል ሌት ተቀን የሚታትረው፤ ትንሳያቸውን ለማብሰር ሳይሆን ቀውሳቸውን ለማርዳት በጥፍሩ የቆመው፤ ይቺ ሀገር፣ ይህ ሕዝብ ምን ቢያጠፉ ነው እንደ ወገቡ ቅ** ጠምዶ የያዛቸው !? ይቺ ሀገርስ በየትኛው እዳዋ ነው እንድትፈርስ ያለ እረፍት መሰረቷን የሚነቀንቀው !? የሚያናጋው !? እነዚህን ጥያቄዎች የማዥጎደጉደው በታሪክ ሀገርና ሕዝብ ማንንም በድለው፣ አስከፍተው እንደማያውቁ በተቃራኒው አገዛዝና ገዥዎች ሕዝብንም ሀገርንም እንደሚበድሉና እንደሚያጎሳቁሉ ዘንግቸው አይደለም። አሸባሪው ትህነግ ለሀገርና ለሕዝብ እንዲህ የመረረ ጥላቻ ያደረበት ምክንያት ግራ ቢያጋባኝና አልገለጥ ቢለኝ እንጂ።
አሸባሪው ሕወሓት ያለፉት 30 ዓመታት ግፍና በደል አልበቃ ብሎት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱን ወደ ለየለት የርስ በርስ ግጭት ለመክተት፣ ለማተራመስ ያልወጣው አቀበት፣ ያለወረደው ቁልቁለት የለም። ይህ እንዳሰበው ሳይሳካለት ሲቀር ደግሞ ትውልድም ታሪክም ይቅር የማይለውን ክህደት በሀገርና በሕዝብ ላይ ፈጸመ። ቀድሞ በታቀደ፣ በተጠና፣ ዝግጅት በተደረገበት በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ በሰሜን ዕዝ መዋቅሮች ላይ ከ40 በላይ ጥቃቶችን ከፈተ። ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት የቀን ጽሐይ የሌሊት ቁር ሳይበግረው፤ የእድሜውን ሲሶ በቀበሮ ጉድጓድ በምሽግ ሰውቶ፤ ከገበሬው ጋር እያረሰ፣ እየዘራ፣ እያረመ፣ እያጨደ፣ እያበራየ፤ አንበጣ ሲከሰት እየተከላከለ፤ በሌለ አቅሙ ከቤተሰቦቹ ጉሮሮ ቀምቶ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ የገነባ፤ አረጋውያንን የሚጦር ወላጅ አልባ ወይም ችግረኛ ህጻናትን የሚያሳድግ፤ ከትግራዋይ ጋር የተጋባ የተዋለደ፤ አበልጅ የተናሳ ሰራዊት፤ በአንድ ኮዳና ጋቤጣ በጠጡ በአንድ ማዕድ በቆረሱ ከሀዲ የአሸባሪው ሕወሓት ጀሌዎች ለመስማት የሚሰቀጥጥ ለማየት የሚዘገንን አረመኔአዊ ግፍ ተፈጸመበት።
ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ የሰራዊት አባላት ተጨፈጨፉ። ተገደሉ። ዕዙ የታጠቀው ከነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ መሳሪያ ዘረፈ። ከሀገሪቱ መከላከያ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው ኃይሉ ተጠቃ። የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ –ወዘተ ደርሰው ሰራዊቱ መልሶ እንዲደራጅና ከከበባና ከጥቃት ሰብሮ እንዲወጣ ወሳኝ ሚና ባይጫወቱ ኑሮ፤ የአሸባሪው ሕወሓት ቅዠት ቢቻል በቀናት አዲስ አበባን መቆጣጠር ካልሆነ ጎንደርና ጎጃምን ተቆጣጥሮ የለውጥ ኃይሉን እጅ ጠምዝዞ ወደቀደመ የበላይነቱ መመለስ፤ በኤርትራም የመንግስት ለውጥ ከማምጣት ባሻገር እጩ ፕሬዝዳንት እስከማዘጋጀት ደርሶ ነበር። ደግነቱ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሜ ደምስሸዋለሁ ያለው ሰራዊት በአጭር ጊዜ በጀግንነት፣ በእልህና በቁጭት መልሶ ተደራጅቶ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ብትንትኑን አወጣው። በአሸዋ ላይ እንደተቀለሰ ሰቀላ በቁሙ ፈረሰ። ይሄን ተአምር በአሰብሁ ቁጥር የመታበይና የእብሪት መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ፈርኦንን ያስታውሰኛል።
ከሴራዎቹ ሁሉ አረመኔያዊና ዘግናኝ የሆነው ይህ ክህደቱ ሲከሽፍበትና ሲባርቅበት ነጮች ፕላን ቢ ወደሚሉት አይነት ቀጣይ ሴራውና ዘመቻው ፊቱን አዞረ። ከድሀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተዘርፎ በየሀገራቱ የሸሸውን ዶላር፤ በየዓለማቀፍ ተቋማቱና ሚዲያው የተሰገሰጉ ጭፍራዎቹን፤ አራጋቢዎችን/lobbyist/ በመቅጠር፣ ዲጅታል ወያኔንና እንደ ትግራይ ሚዲያ ሀውስ ያሉ ብዙኅን መገናኛዎችን፤ እንደ ሱዛን ራይስ ያሉ የመለስ ዜናዊ ታማኝ ወዳጆችንና ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖምን አናቦ በማቀናጀት በጦር ሜዳ የተከናነበውን የውርደት
ማቅ በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነቱ ጊዜያዊ ድል ነጠላ ለመቀየር ሌት ተቀን ማሰነ። የእኛ ተቋማዊና መዋቅራዊ ዳተኝነትና እንዝህላልነት ተጨምሮበት ጊዜያዊ ቢሆንም በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ግዳይ ጣለ። በአሜሪካ ማዕቀብ እስከማስጣል፤ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከሰው እስከ ማቆም፤ በአውሮፓ ሕብረት በጥርጣሬ እንድትታይ፤ በአሜሪካ ሰኔት ባልዋለችበት እንድትከሰስ፤ ገጽታው እንዲጠለሽ በማድረግ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ለታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ጥቃት፤ ለሱዳን ወረራ አመቻቻት። ዛሬ ሀገራችን የምዕራባውያን ሚዲያ አፍ ማሟሻ እስከመሆነ ደርሳለች። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን ቀርተናል። ምንም እንኳ የማታ ማታ እውነት ማሸነፉ ባይቀርም።
እንደ መውጫ
ሀሰተኛ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞ ሀገራችንን በማጠልሸቱ ረገድ ቢቀናውም የለውጥ ኃይሉ ከሙት መንፈስና ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር አልደራደርም በሚለው አቋሙ መጽናቱና አለማቀፋ ማህበረሰቡ የሰላም ማስከበር ጦር እንዲያስገባ ከተቻለም ጣልቃ እንዲገባ ያደረገው ውትወታና ተማጽኖ እንደማይሰምር ቁርጡን ሲያውቅ ደግሞ ሌላ ሀገርን ብሎም ቀጣናውን ለማተራመስ ያዘጋጀውን የሽብር እቅድ ዙም በተሰኘ ኮቪድ አመጣሽ የበይነ መረብ መገናኛ ዘዴ ከጀሌዎቹ ጋር የመከረበትና የዘከረበት ሰነድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደርሶት ይፋ በመሆኑ በዚያ ሰሞን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ሽብር ጠማቂ በሆነው በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት በማስነሳት ትግራይን እንደ ሀገር ለመመስረት ያስችላሉ ብሎ ያስተላለፋቸውን 19 ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ስትራቴጅያዊ ውሳኔዎችን፤ እኔ የቀን ቅዠት ያልኋቸውን ተመለከትኋቸው።
እውነት ለመናገር አሸባሪው ሕወሓት ለዚች ሀገርና ሕዝብ ያለው የመረረ ጥላቸው እስከመጨረሻዋ ህቅታ እንደሚቀጥል ከማረጋገጡ ባሻገር ዛሬም መጨረሻዋ ጣዕረ ሞት ላይ ሆኖ ከሽብር፣ ከደባ፣ ከጭካኔና ከአሬዎስነቱ እንደማይላቀቅ፤ ለዚች ሀገርና ሕዝብ አንድ አሙስ ቀርቶትም እንደማይተኛ ያረጋገጠበት ሰነድ ነው። የዚህ ጉጅሌ የሽብርና የጥላቻ ጥግ የት ድረስ እንደሆነ፤ ከተጨባጭ ሁኔታው አፈንግጦ ራሱ በፈጠረው የቅዠት አለም እየባተለ መሆኑን፤ ያጣውን የበላይነት አገዛዝ ለማስመለስ አይደለም ኢትዮጵያና ቀጣናው ዓለም ብትጠፋ ወደ ምድራዊ ሲኦልነት ብትቀየር ጉዳዩ እንዳልሆነ ዳግም አረጋግጧል።
ይህም ያልጨረስነው ወዝፈን የተውነው የቤት ስራ እንዳለብን ያሳያል። የዚህን አሸባሪ ጉጅሌ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ተግባቦታዊ የመጨረሻ ምሽግ መደምሰስ ላይ መረባረብ ይጠይቃል። ከዚህ ጎን ባጠረ ጊዜ በወረራ ከያዛቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ጠራርጎ ማስወጣትና የገባበት ገብቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ አለበት። የደሴና የኮምቦልቻ መወረር ጋላቢዎቹን ስላስደሰተ እንዴት ባለ በሌለ አቅማቸው ለመደገፍ የሄዱበትን እርቀት ተመልክተናል።
ሌላ እድል ፈንታና ግዳይ እንዲጥል በፈቀድንለት ቁጥር ጫናውና የሀሰተኛ መረጃና የዲፕሎማሲው ዘመቻ እንዴት ተናቦና ተቀናጅቶ እንደሚካሄድብን አይተናል። ስለሆነም ባጠረ ጊዜ ጦርነቱን በአንጸባራቂ ድል ለመቋጨት የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ። በጦር ግንባር ድል ማዕረግ በራሱ ሙሉኡና የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን አረጋግጠናልና። ደጋግሜ እንዳሳሰብሁት የትግራዋይን ልብና ልቦና/mind/ስለማሸነፍ አበክሮ መስራት፤ የተነጠቅነውን የዲፕሎማሲና የሕዝብ ግንኙነት የበላይነትን ለማስመለስም ጎን ለጎን መጣር ይጠበቅብናል።
የሆነው ሆነና፣ አሸባሪው ሕወሓት ይቺ ሀገር ምን ብትበድለው … ይህ ሩህሩህና ደግ ሕዝብስ በምን እዳው ነው … እንዲህ ሊያጠፋቸው ቀን ከሌት የሚታትረው !? የሚለው ጥያቄ፣ እኔን ጨምሮ ትውልዶች መልስ ያጡለት ጥያቄ እንደሆነ ይዘልቃል።
አሸባሪው ሕወሓት ይውደም !
ኢትዮጵያ ትቅደም !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014