ታሪካዊ ዳራ
ዓለማችን ሩብ ክፍለ ዘመን በማይሞላ ጊዜያት ውስጥ ብቻ አውሮፓ ውስጥ ተቀስቅሰው መላ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍለው እርስ በእርስ ያጫረሱ ሁለት እጅግ አስከፊ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፡፡ ይህም ማህበራዊ ቀውሱንና ኢኮኖሚያዊ ውድመቱን ሳይጨምር ከመቶ ሃምሳ ሚሊዮን በላይ ክቡር ህይዎቶችን በመቅጠፍ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌም በክፉ ሲታወስ የሚኖር ጥቁር ጠባሳን ጥሎ አልፏል፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ መሰል ጦርነት ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል በማሰብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሃምሳ ሃገራትን በአባልነት አቅፎ እ.ኤ.አ በ1945 ተመሰረተ፡፡
የእኛዋ ኢትዮጵያም ከመስራቾቹ መካከል አንዷ ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት 153 አገራትን በአባልነት ያቀፈው ግዙፉ የዓለማችን ማሕበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሥሩ ልዩ ልዩ ዓላማ ያላቸው በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ ሲሆን፤ የጸጥታዉ ምክር ቤት አንዱ ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ እ.ኤ.አ በ1948 በቻርተር የተቋቋመና የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮችን የሚመለከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ነው፡፡
ለተቋቋመለት ዓላማ ያለመቆም ትችት
ታዲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮችን የሚመለከተው አካሉ የጸጥታው ምክር ቤት በ193ቱ አባል ሃገራት የዘር፣ የፆታ፣ የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለሁሉም አገራትና ለሁሉም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነፃነቶች ሊኖር እንደሚገው በመተዳደሪያ ቻርተራቸው ውስጥ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በሥሩ ያለው የጸጥታው ምክር ቤት በተለያዩ ጊዜያቶች ለአንዳንድ አባል ሃገራት፤ በተለይም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ለተሰጣቸው ኃያላኑ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ሲወግኑ በመታየታቸውና ሁሉንም ሃገራት በእኩል ዐይን ማየት ባለመቻላቸው የቆሙለትን ዓላማ ማሳካት አልቻሉም በሚል በተደጋጋሚ ሲተቹ ቆይተዋል፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅትና በጸጥታው ምክር ቤት አሠራር አድሏዊነት ላይ የሚቀርበው ቅሬታና ትችትም ከግል ጥቅም ወይም ፍላጎት የመነጨና የድርጅቶችን ሥም በከንቱ ለማጠልሸት የሚደረግ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሳይሆን በገሃዱ ዓለም የተከሰቱ ነባራዊ እውነታዎችን መሠረት ያደረገና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተፈጠሩ ሁነቶችን በማሳያነት የሚያቀርብ በተጨባጭ መረጃዎችና ማስረጃዎች የተደገፈ ነው። በዚህ ረገድ በጉልህ ከሚጠቀሱ ዋና ዋና ማሳያዎች መካከልም ከፍልስጤም እስከ እሥራኤል፣ ከሶሪያ እስከ የመን፣ ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሊቢያ እስከ ሶማሊያ በርካታ አገራትን መዘርዘር ይቻላል፡፡
በመሆኑም ድምፅን በድምፅ የመሻር ልዩ መብት የተሰጣቸው ኃያላኑ አባሎቹ፤ በተለይም አሜሪካና ምዕራባውያን በመተዳደሪያ ቻርተሩ የተቀመጠውን በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት ህግ ጥሰው በርካታ ሃገራትን ሲወሩና ሲያወድሙ የፀጥታው ምክር ቤት ሕገ ወጥ ድርጊታቸውን ሲቃወምም ሆነ ሲያስቆም አልተስተዋለም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ወንጀሎችን እንዲከላከልና የዓለምን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቅ በዓለም ሕዝብ ዘንድ የታወቀ፣ በሕግ የተደነገገ ስልጣን የተሰጠው አካል የፀጥታው ምክር ቤት የት ነበረ? ስንት ጊዜስ ጉባኤ ጠርቶ ተቀመጠ? እንዲያውስ በአገራቱ ሰላምና ደህንነት እንዲመለስና የሕዝብ ስቃይና መከራ እንዲያበቃ መደበኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት አባል አገራት በተደጋጋሚ የፀጥታው ምክር ቤትን ሲጠይቁ አንድም ምላሽ ሳይሰጥ ለጉዳዩ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሲቀር አልታየምን? በተቃራኒው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የፀጥታው ምክር ቤት ሾፋሪያቸውን አሜሪካን ተከትለው በኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር ላይ ሲጮሁ ዓለም ያላያቸውና ያልሰማቸው ይመስላቸዋልን?
ከአድሏዊነት ከራስ መተዳደሪያ በተቃራኒ እስከመቆም
እንደሚታወቀው የጸጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ውስጥ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን የማድረግ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ነው። ተቀዳሚ ተግባሩም የእያንዳንዱን አባል አገራትና በአጠቃላይ የዓለምን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህንን የዓለምን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን የሚያከናውነው ግን በአባል አገራቱ በግልጽ ተለይቶ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረትና ዝርዝር የአሠራር ሕግና ደንቦችን በመከተል ነው። ስለሆነም ምክር ቤቱ ሥራውን የሚያከናውንበት ራሱን የቻለ መተዳደሪያ ቻርተር አለው፡፡
ታዲያ የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ምክር ቤቱ የሚተዳደርበት ቻርተር እንደ ብሪታኒያ ሕገ መንግሥት ዜጎች በጊዜ ሂደት ለምደውትና ተላምደውት፣ በሕሊናቸው ቀርጸውት በቃላቸው ሸምድደው ይዘው በጋራ መግባባት ላይ ተመስርተው ወድደው የሚተዳደሩበት ረቂቅ ያልተጻፈ የሕሊና ሕግ አይደለም፡፡ በማያሻማ መንገድ በጽሑፍ ተብራርቶ የተቀመጠና አባል አገራት በሚፈልጉት ቋንቋ ተተርጉሞ በማንኛውም ሰዓት በሚፈለግበት ጊዜ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭና ማጣቀሸ ሆኖ የሚያገለግል፤ አጠቃላይ ስልጣንና ተግባራቸው የሚመራበትና የሚከናወንበት ሁሉም ተስማምቶ በሚገዛባቸው መሠረታዊ ዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ የተመሠረተ ቋሚ የጽሑፍ ሰነድ ነው፡፡
የዓለም አቀፍ ሕጎች ሁሉ መነሻና መድረሻ የሆነው ዋነኛው የሕግ ድንጋጌ ደግሞ “በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት” የሚለው ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የዓለምን ፀጥታና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል በመተዳደሪያ ቻርተሩ ላይ በግልጽ አስ ቀምጧል፡፡
ይሁን እንጅ የተባበሩት መግሥታት ድርጅትም የጸጥታው ምክር ቤት ሃገራትን በእኩል ዐይን ያለማየትና አድሏዊ አሠራር ብሎም ለዓላማቸው ተገዥ ያለመሆን ችግራቸው በየጊዜው እየባሰበት ጭራሽ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፡፡ በተለይም ተቋማቱ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያራመዱ ያሉት አቋም ድርጅቶቹ ከምንጊዜውም በላይ በግልጽ ከዓላማቸውና ከመተዳደሪያ ቻርተራቸው በተቃራኒው መቆማቸውን የሚያሳይ መሆኑን ዓለም ሁሉ እየመሰከረው ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በግልጽ አፈርስሻለሁ ብሎ ከተነሳ ጠላትና በመከላከያ ሠራዊቷ ላይ በይፋ ዘግናኝ ጥቃትን ከፈጸመ አሸባሪ ኃይል ጋር ራሷን ለመከላከልና እንደ ሃገር ሃገር ሆኖ ለመቀጠል ህልውናዋን ለማረጋገጥ ተገድዳ ከገባችበት የፍትህ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ የጸጥታው ምክር ቤት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አስራ ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጉባኤ መቀመጡ ነው፡፡
አሜሪካና የጥቅም ሸሪኮቿ ምዕራባውያን የምክር ቤቱን የመተዳደሪያ ቻርተር ጥሰው፣ በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው፣ የሉዓላዊ ሃገራትን ድንበር ጥሰው፣ ያውም አማፅያንን ደግፈው ሶሪያን ሲያወድሙ የፀጥታው ምክር ቤት አንድም ጉባኤ አልጠራም፣ አንድም ጊዜ ለስብሰባ አልተቀመጠም።አሜሪካ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰበብ በ2003 ኢራቅን በኃይል በመውረር ከአራት መቶ ሺ በላይ ኢራቃውያንን በግፍ ስትፈጅ፤ ሃገሪቱን እንዳልነበረች አድርጋ ስታፈርስ የፀጥታው ምክር ቤት ድምፁ አልተሰማም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በአሜሪካና የምዕራባውያን ሕገ ወጥ የጉልበት ጣልቃ ገብነት የመን ወደ ፍርስራሽነት ስትቀየር ዜጎቿ በግፍ ሲያልቁ፣ የቀሩት በዓለም ላይ እንደ ጨው ሲበተኑ፣ ሊቢያ የእርስ እርስ ጦርነት አውድማ ስትሆን፣ ንጹሐን በጥይት በጅምላ ሲያልቁ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን ሲሰቃዩ… የፀጥታው ምክር ቤት ምንም አላለም፡፡
ሴቭ ዘ-ችልድረን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ሰብዓዊ የተራድኦ ድርጅት በሶሪያ ለሰው ልጆች የተሻለ ህይወትን የመፍጠር ዓላማ ያላቸው ሰብዓዊ ተቋማት ትምህርት ቤቶች የሰው ልጆች የማሰቃያ ማዕከላት መሆናቸውንና፤ ሕፃናትና ልጆች ለጦርነት ዒላማ መለማመጃ መሆናቸውን የሚያሳይ በማስረጃ የተደገፈ ዘገባ ይዞ፤ “እባካችሁ በእነዚህ ልጆች ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ስቃይና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ዘግናኝ እውነታ እንዲያበቃ ኃላፊታችሁን ተወጡ” ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የፀጥታው ምክር ቤትን ሲማፀን ዓለም በአግራሞት ታዝቧል፡፡ ምንም አሳሳቢ ሁኔታ በሌለበት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ግን የተደበቀ ማንነቱን ግልጥልጥ አድርጎ በሚያሳይ ፍጹም አሳፋሪ ሁኔታ በአንድ ዓመት ውስጥ በተኩላ ተቆርቋሪነት የበግ ለምድ ለብሶ አስራ ሁለት ጊዜ ጉባኤ ተቀምጧል።
ለምን ኢትዮጵያ?
ታዲያ ለኢትዮጵያ ሲሆን ፍጹም በማይመለከተው ጉዳይ ላይ ያውም የራሱን መተዳደሪያ ቻርተር በግልጽ ጥሶ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አስራ ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መሰብሰብን ምን አመጣው? ምክንያቱም በመተዳደሪያ ቻርተሩ በግልጽ እንደተቀመጠው የፀጥታና የደህንነት ጉዳዮችን በሚመለከት ምክር ቤቱ ጉባኤ የሚጠራው በሁለት አገራት መካከል ጦርነት ሲካሄድና አስከፊ ድንበር ዘለል ግጭት ሲከሰት ብሎም ግጭቱ ከአገራቱ ቁጥጥር ውጪ ወጥተው ለዓለም ፀጥታና ደህንነት ስጋት ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ኢትዮጵያ አሁን ከአሸባሪውና ሃገር አፍራሹ ሕወሓት ጋር የገባችበት ጦርነት በመጀመሪያ የህልውና ነው፤ ሲቀጥል ጦርነቱ ከሌላ የውጭ ወራሪ ወይም ሃገር ጋር ሳይሆን ከራሷ የውስጥ ባንዳ ጋር ነው፤ እናም የውስጥ ጉዳይዋ ነው፣ ሲሰልስ ደግሞ ችግሩ ከቁጥጥሯ ውጪ አልወጣም ፣ አይደለምና ለዓለም ለጎረቤት ሃገራት ጸጥታና ደህንነት ስጋትም አልሆነም፡፡
እናም የፀጥታው ምክር ቤት ምንም በማይመለከተው የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሺ ጊዜ ጉባኤ የሚቀመጥበት ምክንያት አንድና አንድ ነው፤ እርሱም በሌሎች አገራት ላይ እንደለመደው የአዛዦቹን የአሜሪካና የምዕራባውንን ጥቅም በኢትዮጵያም ላይ ለማስፈጸም ነው፡፡ ሆኖም ይህ ፈጽሞ የማይሆንና መቸም ሊሳካ የማይችል፤ ብሎም ምዕራባዊ ውድቀትን ሊያመጣ የሚችል በራስ ላይ የተጠመደ አጉል ኢምፔሪያልስታዊ የጥፋት ህልም መሆኑን አውቆ ለራሱ ሲል በአስቸኳይ ከድርጊቱ እዲታቀብ ልናሳውቀው እንወዳለን፡፡
በሽንፈት የተደመደሙት ጣልቃ ገብነቶች
በአሜሪካና በምዕራባውያን የበላይነት የሚመራው የፀጥታው ምክር ቤትና በስሙ የሚነግዱት አሜሪካና ምዕራባውያን ምንም እንኳን የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ቻርተር በተደጋጋሚ በኃይል እየጣሱ በበርካታ አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ ብዙዎቹን ከሃገርነት ውጪ የሚያደርግ ውድመት የፈጸሙ ቢሆንም በጣልቃ ገብነት ያደረጉትን ወረራና ጦርነት ግን አንዱንም በድል አላጠናቀቁም፡፡ በአንጻሩ ሁሉንም ተሸንፈዋል፣ በብዙዎቹ የጣልቃ ገብነት ጦርነቶችም አሳፋሪ ሽንፈትና አሸማቃቂ ውርደትን ተከናንበዋል፡፡ ዓለም ላይ አሉ የተባሉ አሜሪካንን ያጠኑ ምሁራንም የሚያስረግጡት ይህንኑ ነው። የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነትና የጦርነት ታሪክ በጥልቀት ያጠኑት ታዋቂው የፖለቲካል ሳይንቲስት ዶሚኒክ ትሪየኒ አሜሪካንን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ዋና ሾፋሪና የምዕራባውያን መሪ አሜሪካ በሰብዓዊ መብት ማስከበርና ሽብርን በመከላከል ሽፋን የራሷንና የምዕራባውያንን ጥቅም ለማስከበር በተናጠልና በምክር ቤቱ ቡራኬ ጣልቃ ገብታ ባካሄደቻቸው የኃይል ወረራና ጦርነቶች አንዱንም በአሳማኝ ሁኔታ አላሸነፈችም፣ በተቃራኒው ሁሉንም ተሸንፋለች ማለት ይቻላል። በ1991 ያካሄደችው የባህረ ሰላጤው ጦርነት በጥቂቱም ቢሆን በአሸናፊነት የወጣችበት ቢሆንም ድሉ ግን በሁሉም ዘንድ እኩል ተቀባይነት ያገኘ አልነበረም፣ የኮሪያውም እንደዚሁ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ቬትናም ላይ በይፋ ከባድ ሽንፈትን አስተናግዳለች፡፡ ኢራቅ ላይም አልተሳካም፣ እዚያም የአሜሪካ ሽንፈት ነው አመዝኖ የተስተዋለው። በሊቢያ፣ በሶማሊያ በአጠቃላይ ጣልቃ ገብታ ጦርነት ባካሄደችባቸው ሃገራት በሁሉም ተሸንፋለች፡፡
አለማወቅ የሽንፈት ምንጭ
“አሜሪካን ለዚህ ሁሉ አሳፋሪ ሽንፈት የዳረጋት ምንድነው?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ የአሜሪካ የጦርነት ታሪክ አጥኝውና የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ሲመልሱ፤ “የሽንፈቷ ዋነኛ ምከንያት አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ጦርነት የምትገጥመውን ሃገርና ሕዝብ ማንነትና ታሪክ አለማወቋ ነው የሽንፈቷና የውርደቷ ዋነኛ መንስኤው” ይላሉ፡፡ ድፍን ሃያ ዓመታትን ጨርሶ በአፍጋኒስታንና በሕዝቦቿ ላይ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሎ፤ አፍጋኒስታውያንን ብቻ ሳይሆን አሜሪካውያንም ጭምር ከፍተኛ መስዋዕትነትን አስከፍሎና አሜሪካን እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ አክስሮ በመጨረሻም በሳፋሪ ሽንፈት የተደመደመውን የቅርቡን የአፍጋኒስታንን ጦርነት በማሳያነት ያነሳሉ፡፡
“የቅርብ ጊዜውን የአፍጋኒስታንን ጦርነት ብንወስድ እንኳን አሜሪካ ስለ አፍጋኒስታን ታሪክ፣ ሕዝብ፣ ማንነት ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም” ይላሉ፡፡ “ፕሬዚዳንት ቡሽና ጦር አዛዣቸው ዶናልድ ራምስፊልድ በ2001 አፍጋኒስታን ሲገቡ ትክክለኛው የአገሪቱ ካርታ እንኳን አልነበራቸውም፣ በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውንና ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተለወጠውን የድሮውን የአፍጋኒስታን ካርታ ይዘው ነበር እርግጠኛ ሆነው በዚያ እየተመሩ ወደ አፍጋኒስታን የገቡት” በማለት የአሜሪካን የውርደት መንስኤ ምን እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
እኛም እንላችኋለን፤ አፍጋኒስታንን አለማወቃችሁ አሁን ሽንፈትና ውርደትን አምጥቶባችኋል ኢትዮጵያን አለማወቅ ደግሞ ከሽንፈትም በላይ የመጨረሻ ውድቀትን ያመጣልና እባካችሁ ቢያንስ አሁን እንኳን እወቁ፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየገባችሁ የማይመለከታችሁን እየፈተፈታችሁ ባለማወቅ ውድቀታችሁን ከምትጠሩ፣ ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ዕወቁ፡፡ የምታደርጉትን እያደረጋችሁት ያላችሁት እኛ መሳሪያ አለን፣ እኛ ቴክኖሎጂ አለን፣ እኛ የበላይ ነን በሚል ከሆነም ያኔ ከመቶ ሃያ አምስት ዓመት በፊት ልክ አሁን እናንተን እንደሚያደርጋችሁ ሲያደርገው የነበረው እብሪት መጨረሻውን ያገኘው በማን እንደሆነና ውድቀቱም የት እንደነበረ አያቶቻችሁን ጠይቁ!::
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014