ቅድመ ታሪክ ልጅነቱን እንደ ዕድሜ እኩዮቹ አላሳለፈም። ገና የአንድ ዓመት ህጻን ሳለ ወላጅ አባቱን በሞት ተነጥቋል። የዛኔ የቤተሰቡ ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ። በቂ ገቢ ያልነበራቸው እናት የሙት ልጆችን በወጉ ለማሳደግ አቅም አነሳቸው። አባቱን በማለዳው ያጣው ታዳጊም ህይወት ፈተና ሆነችበት። ራሱን ለመቻልና ቤተሰቡን ለመደጎም ከአቅሙ በላይ መልፋት ግዴታው ሆነ። አብዲ መንሱር የአባት ፍቅር ይሉት ነገር አያውቅም። አላለለትም እንጂ ሁሌም እንደ እኩዮቹ «አባዬ» የሚለው አባት ቢኖረው ይሻል። እንደ ባልንጀሮቹም እጁን ይዞት ትምህርት ቤት ወስዶ ቢመልሰው ይወዳል።
ይህ ሁሉ ግን ለትንሹ አብዲ እውን የማይሆን ህልም ነበር። እርሱ አባት የለውም። ምኞትና ሀሳቡም ከዳር አይደርስም። እናም ህይወቱን ለመቀየር ጠንክሮ መማር ይኖርበታል። በችግርና መከራ የተዋዛው ህይወት ቀጥሏል። አብዲ በትምህርቱ ገፍቶ ዘጠነኛ ክፍል ደርሷል። ይህ መሆኑ ነገን ለሚያልመው ታዳጊ ታላቅ ተስፋ ነው። ትላንትን በችግር ያሳለፈው ቤተሰብ በእርሱ ተምሮ መለወጥ ኑሮውን ሊቀይር ይችላል። ያለአባወራ የኖረው ጎጆም አንድ ቀን ሙሉ ይሆናል። ይህ ሁሉ ሀሳብ ግን እንደታሰበው አልዘለቀም።
አንድ ቀን አብዲ ልክ እንደአባቱ ወላጅ እናቱንም ሞት ነጠቀው። ይህ አጋጣሚ ደግሞ የወጣቱን የህይወት መንገድ ለመቀየር ምክንያት ሆነ። አብዲ ከእናቱ ሞት በኋላ ዳግመኛ ስለትምህርት አላነሳም። እንደቀድሞ ማልዶ ትምህርት ቤት መገስገስን እርግፍ አድርጎ ተወው። ደብተሩን አስቀምጦም ስራ ፍለጋ ባዘነ። በወቅቱ ለእሱ የሚመጥን ውሎ የቀን ስራ ብቻ ሆነ። በጉልበቱ ከማደር ሌላ ምርጫ ያልነበረው አብዲ በአንድ ፋብሪካ ተቀጥሮ የዕለት ጉርሱን ማግኘት ጀመረ። አሁን በሚከፈለው ደመወዝ አቅሙን መደገፍ ይቻለዋል።
ለቤተሰቡም ቢሆን ጥቂት ድጎማን አያጣም። ይህ የተስፋ ጊዜ ግን ከአንድ ዓመት በላይ አልተሻገረም። በጊዜያዊነት የቀጠረው ፋብሪካ ቀን ጠብቆ «በዚህ ይብቃህ» ሲል አሰናበተው። ስራ በማግኘቱ የተደሰተው አብዲ ድንገት እንጀራውን ማጣቱ ከልብ አስከፋው። ሰርቶ ካላደረ እንደሚቸገር ያውቃል።
ችግሮቹ ከተደገሙ ደግሞ ህይወት መልሶ ይከብደዋል። ስራ ፈላጊው ስለራሱ ደጋግሞ አሰበ። አሁንም በጉልበቱ ከማደር ሌላ ምርጫ የለውም። ጥቂት ጊዜያትን በቀን ስራ እንደገፋ አንድ ጭምጭምታ ለጆሮው ደረሰ። ወቅቱ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የተፋፋመበት ነው። ይህን ተከትሎም በመላው ሀገሪቱ የወታደሮች ምልመላ ይካሄዳል። እሱን መሰል ወጣቶች ደግሞ በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ለውትድርና ይታጫሉ።
ይህን የሰማው አብዲ በመከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን ጊዜ አልፈጀም። «ማቄን ጨርቄን» ሳይል አካባቢውን ለቆ ወደ ማሰልጠኛ አመራ። የውትድርና ስልጠናውን አጠናቆ የሰራዊቱ አባል መሆኑን ሲያረጋግጥ ሙሉነት ይሰማው ያዘ። ከዚህ በኋላ በስራና ገንዘብ እጦት አይንገላታም። ለራሱ የሚለው መተዳደሪያን ይዟልና የሚያሰጋው ችግር አይኖርም። አሁን ወር ጠብቆ ብር የሚቆጥር ደመወዝተኛ ሆኗል። ባሻው ጊዜም የፈለገውን ማድረግ ይቻለዋል። ይህ ስሜት ያደረበት አብዲ ዋል አደር ሲል የትላንቱን ችግር ረሳ። ያለበትን ስፍራዘንግቶም የቆመበትን አላማ ሳተ። ባልተገባ ባህሪው የለዩት አለቆቹ ደጋግመው ምክር ለገሱት።
ከሚኖርበት ካምፕ እየወጣ አድሮ መመለሱን ሲያውቁም በማስጠንቀቂያ አለፉት። አንድ ቀን ግን የሁሉ ነገር መጨረሻ ሆነ። ትዕግስቱ ያለቀባቸው አዛዦች ውሳኔያቸውን በማባረር አጸኑት። አብዲ አምስት ዓመታት ካገለገለበት መከላከያ ሰራዊት ከተባረረ በኋላ ወደትውልድ ቦታው አዲስ አበባ ሊመለስ ግድ ሆነበት ። አሁን ወጣቱ በዕድሜው በስሏል። ከቤተሰቦቹ ግቢ የራሱን ጎጆ ቀልሷል። ይህ መሆኑ ብቻ እፎይታን አልሰጠውም። መልሶ «ስራ ፈት» መባሉ እያስጨነቀው ነው። ለዓመታት ደመወዝ መቁጠሩና በራሱ ጥፋት ከስራው መባረሩ አመል ነስቶታል። ኑሮውን ከታናሽ እህቱ ጋር ቢቀጥልም በቀላሉ ደስታን ማግኘት አልቻለም። ወቅቱ 1997ዓ.ም ነው።
በአዲስ አበበ ከተማ ከምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ ረብሻና ብጥብጥ ሰፍኗል። መንግስትን የሚቃወሙና ተይዘው የሚታሰሩ ወጣቶች ቁጥር በርክቷል። አብዲም ቢሆን ከዚህ ማዕበል አልወጣም። በእርሱ ዕድሜ ካሉ እኩዮቹ ጋር በማበር በረብሻው መሳተፉን ቀጥሏል። መንግስት በአደገኛ ቦዘኔነት ፈርጆ የጠረጠራቸውን ወጣቶች እየያዘ ወደ እስር ቤት እየላከ ነው። አብዲም ከነዚህ ወጣቶች መሀል አንዱ ሆኗልና በዚህ መንገድ ሊያልፍ ግድ ብሏል። በተከሰሰበት መዝገብ የአንድ ዓመት እስር የተወሰነበት ፍርደኛ ጸጉሩን ተላጭቶ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ተልኳል። ለእርሱ ደግሞ ታስሮ መፈታት ብርቁ ሆኖ አያውቅም። ከዚህ በፊትም በፈጸመው የስርቆት ወንጀል ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቆይቷል። አንድ ዓመት በእስር አሳልፎ ከተለቀቀ በኋላ ተመልሶ አዲስ አበባ ገባ። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ብዙ ያየበት የቃሊቲው «አረብ ሰፈር» ለእርሱ ሁለመናው ነው። በዚህ መንደር አፈር ፈጭቶ አድጓል።
ሰርቶ ማግኘትንና ሰርቆ መታሰርን በየፈርጃቸው አጣጥሟቸዋል። አሁን ደግሞ ህይወትን በአዲስ ሊጀምር በመንገድ ላይ ነው። አብዲ በቅርቡ የተዋወቃት ወጣት ልቡን ማርካዋለች። ስለእርሷም ማሰብ ከጀመረ ውሎ አድሯል። የሁለቱ ቅርበት አይሎ በአንድ መዋል ሲጀምሩ ቁምነገር ማውራት ይዘዋል። አብረው ለመኖርና ልጅ ወልደው ለመሳም ያላቸውጉጉት በትዳር እንዲጣመር እያሰቡ ነው። ይህን ለማድረግ ግን አንድ ግድግዳ መሀላቸው ቆሟል። አብዲ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ነው። ሄለን ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያን። የጥንዶቹ ሀይማኖት መለያየት በጋራ ለመኖር አያስችልም። ሁለቱን በአንድ የሚያጣምር ዕምነት ከሌለ ትዳር ይሉት ጉዳይ አይታሰብም።
ይህን እውነት ውስጣቸው አሳምሮ ያውቃል። ከሁለቱ አንዳቸው ክርስቲያን አልያም ሙስሊም ሊሆኑ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በጋራ መወሰን አለባቸው። ወራትን በፍቅር እንደገፉ ሄለን ስታስበው በከረመችው ጉዳይ ከውሳኔ ደረሰች። አብዲን ታምናበታለች፤ ለትዳር አጋር መርጣዋለች። ከእሱ ጋርም ጎጆ ቀልሳ መኖርን ትሻለች። እናም ክርስቲያን መሆኗን ትታ የእስልምና ሀይማኖትን ስትቀበል ደጋግማ አላሰበችም። የቀደመ ስሟን ቀይራ ፋጡማ ስትባልም ያለምንም ቅሬታ ነበር። አሁን አብዲና ፋጡማ የትዳር ህይወት ጀምረዋል። ቤተሰቦቹ ግቢ ከሰራው ቤት ይዟት መግባቱ ለቤት ኪራይ እንዳያስቡ ረድቷቸዋል። እርሷ ዘወትር ስለጓዳዋ ሙላት ታስባለች።
የጎደለውን ለማከል፣ ያለውንም ወር ለማድረስ እንደባዘነች ነው። የእርሱ ታናሽ እህት ዘሀራ እምነቷን ቀይራ ቤተኛ በሆነችው እንግዳ ደስተኛ አልሆነችም። በወጣች በገባች ቁጥር በክፉ ዓይን ታያታለች። ይህ ስሜቷ ደግሞ ከፋጡማ ጋር አላግባባቸውም። ከሰላምታ ይልቅ ግልምጫ፣ ከፍቅር ይበልጥ ጥላቻ ገዝፎ በጠበኝነት ዘልቀዋል። ከወራት በኋላ የጥንዶቹን ጎጆ አንድ ጨቅላ ተቀላቀለ። ለሁለቱ አብሮነት ማሰሪያ የሆነው ህጻንም ስያሜ ተችሮት፣ አብሯቸው መኖርን ቀጠለ። ከዚህ በኋላ ግን የሁለቱ ፍቅር እንደወትሮው ላይሆን ቀዘቀዘ። አብዲ በባለቤቱ ላይ ያደረበት ቅናትና ያልተገባ ጥርጣሬ የቤቱን ሰላም ያናጋው ያዘ።
ፋጡማ ዕቃ ለመግዛት ሱቅ ስትወጣና ጥቂት ዘግይታ ስትመለስ በውሀ ቀጠነ ሰበብ ዱላ ማንሳቱ ተለመደ። በሰላምታ የቀረበቻቸውን ወንዶች ሁሉ እየጠረጠረም ጭቅጭቅና ንዝንዙን አጧጧፈው። አንዳንዴ ፋጡማ በደሉ ሲበዛባት ቤቱን ትታለት ትወጣለች። የልጇ ነገር ሲያሳስባትና ሰላም ያመጣች ሲመስላት ደግሞ ተመልሳ ትገባለች። ይህ መሆኑ ግን የአባወራውን ልብ ማዋዛት አልቻለም። በግቢው ውስጥ የተከራየውን ወንደላጤ መጠርጠርጀምሯል። ወንደላጤው ተከራይ በፋጡማ ላይ የሚሆነውን ሁሉ ይመለከታል። እስከዛሬም የእርሷ በደልና ትካዜ ከልብ ሲያሳዝነው ቆይቷል። አንድ ቀን ተከራዩ ፋጡማ ከውጭ ውሀ ቀድታ ስትመለስ ያገኛታል።
ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር መሆኗን ያውቃልና የተሸከመችውን ተቀብሎ እስከ ቤቷ ያደርሳል። ይህኔ አብዲ ከውጭ እየመጣ ያየዋል። እሱን ከሚስቱ ኋላ ሲያገኘው በንዴት ይጦፋል። ቤት እንደገባ ያለምንም ጥያቄ በሚስቱ ፊት ላይ ጠንካራ ቦክስ ያሳርፋል።
ይህን መቋቋም ያልቻለችው ፋጡማ በኡኡታ «ድረሱልኝ» ስትል ትጮሃለች። ከዚህ ቀን በኋላ በቤቱ የሰላም ርጋፊ ጠፋ፣ በጭቅጭቅ ውሎ በእሪታ የሚያመሸው ጎጆም ለቅሶና ሀዘን ማስተናገዱ ተለመደ። በየጊዜው የተከራዩን ስም እያነሳ ነገር የሚመዘው አብዲ ለነፍሰጡር ሚስቱ የሚራራ አልሆነም። በሚያገኘው ዱላና በሚሰነዝረው ቡጢ ፋጡማን ማሰቃየቱን ቀጠለ። የወንድሟ ዛቻና ማስፈራሪያ ያሳሰባት ዘሀራ ነገር ለማብረድና ላከራየችው ወንደላጤ በማሰብ ከቤቱ እንዲለቅ አደረገች። ይህን ያወቀው ወንድሟ ውስጡ በጥርጣሬ በመመረዙ በሰውዬው ለቆ መሄድ መረጋጋት ተሳነው። አንድ ቀን ዱላ የበዛባት ፋጡማ ድንገት ቤቱን ትታ ሄደች።
አብዲ ግን የእርሷን ርቆ መሄድ ከተከራዩ መውጣት ጋር አያይዞታል። በዚህም ሳቢያ ቅናቱ ጫፍ ደርሶ እንቅልፍ ካጣ ሰንብቷል። አየለን ፈልጎና ከሶ ለማስቀጣት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይህ እንዳልሆነ ቢገባው ሚስቱን ካለችበት አጠያይቆና፣ በይቅርታ አሳምኖ ከቤት መመለስ እንዳለበት አምኗል። አሁን ልበ ሩህሩኋ ወይዘሮ በባለቤቷ ምልጃና ይቅርታ ከቤቷ ተመልሳለች።እንደወትሮዋም የጎደለ ጎጆዋን ልትሞላ ፍቅር የራቀው ልጇን ልትንከባከብ ደፋ ቀና እያለች ነው። የአብዲ ልብ ግን ዛሬም እንደጎሸ ነው። ገና ሲያያት ደሙ ይፈላል፣ በየምክንያቱ ይናደዳል፣ አሁንም አየለን ፈጽሞ መርሳት አልቻለም። እሱን እያሰበ ሚስቱን ያስተውላል። የሆነ ያለውን እያስታወሰም በንዴት ይበግናል።
የካቲት 14ቀን 2005 ማለዳ፦
የባልና ሚስቱ ጎጆ በከሰል ፍም ግሟል። ትንሹ ልጃቸውና እናቱ በፍቅር እየተጨዋወቱ ነው። የአባወራው ስሜት ግን ከምንግዜውም የተለየ ሆኗል። በየሰበቡ የሚያነሳውን የአየለን ስም ዛሬ በተለየ ብሽቀት እየደጋገመ ይጠራል። «በእመኚልኝ አላምንም» ሰበብ የተነሳው ውዝግብ ከመቼውም በላይ መካረሩ ህጻኑን ሰይድ እያስጨነቀው ነው። አባወራው ያሰበውን ከማድረግ አልዘገየም። አጠገቡ ያስቀመጠውን የብረት ዘነዘና አንስቶ የፋጡማን ሁለት እግሮች ሰበራቸው። በዚህ ብቻ አልበቃውም። የግራ እጅዋን ቀጥቅጦና ሰብሮ አይኗን በመሸፈን ከወለሉ ላይ ወደተዘረጋው ፍራሽ ወረወራት።
ስቃዩ የበዛበት ፋጡማ በአሳዛኝ ድምጽ ‹‹የሰው ያለህ» ስትል ጮኸች። ጩኸቷን የሰሙ የግቢው ሰዎች ጆሯቸውን ጣሉ። እንደሰሙት ግን ፈጥነው አልገቡም። ለባይተዋሯ ነፍሰጡር ሊደርሱላት አልፈቀዱም። አብዲ ስራውን አልጨረሰም። በጋመው የከሰል ምድጃ የሻጣቸውን ሶስት ቢላዎች ተራ በተራ እያነሳ ወደ ፋጡማ ቀረበ። አሁንም እየጮኸች ደጋግማ ተማጸነችው። የቅናት ዛር የተቆጣጠረው ልቡ ፈጽሞ አልራራም። የጋለውን ቢላዋ በፊቷ ላይ አጋደመው። ወዲያው በተቃጠለ የቆዳ ሽታና ጭስ ቤቱ ታጠነ።
ሰውዬው ያነሳውን ቢላዋ ከምድጃው መልሶ ሌላ የጋለ ቢላዋ ቀየረ። ቢላዎቹን በመላ ሰውነቷ እያመላለሰም እንዳሻው አቃጠላት፣ ለበለባት። ድርጊቱን የሚያየው የአምስት ዓመት ህጻን ዕንባው በጉንጩ እየወረደ በፍርሀት ራደ። አሁን ከቀኑ ሰባት ሰአት ሆኗል። ሚስቱን በማሰቃየት ድካም የተሰማው አብዲ ወጣ ብሎ ምሳ መብላት ፈልጓል። ከምሳ መልስ ቀሪ ስራ አለበት። የጀመረውን ሊጨርስ ከራሱ ጋር ተቃጥሯል። ከቆይታው መልስ ለልጁ የገዛውን ምግብ ወርውሮ ጅምሩን ቀጠለ። የጠፋውን ከሰል አያይዞ ቢላዎቹን እያጋለ ማቃጠል መለብለቡን አጠናቀቀ። በመጨረሻም በአንዱ ቢላዋ ፊቷን እየቆራረጠ አፌዘባት። አሁን እስትንፋስ እንደሌላት አውቋል። የልቡን አድርሶም ስራውን ፈጽሟል። አስር ሰአት ሆኖ ከቤቱ ሲወጣ ልጁን ለእህቱ ማስረከብን አልረሳም። እርሷ ገንዘብ ሰጥታ ስትሸኘው ሚስቱን በጭካኔ እንደገደለ ነግሯት ነበር። የፖሊስ ምርመራ፦ ፖሊስ ግድያ መፈጸሙን እንደሰማ ፈጥኖ በቦታው ደረሰ። የተዘጋውን በር ከፍቶ ሲገባም በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ወይዘሮ አስከሬን አገኘ። በስፍራው የተገኙ የወንጀል ፍሬዎችን በጥንቃቄ በማንሳት መረጃዎችን አሰባስቦም ተጠርጣሪውን ለመያዝ የምርምራ ቡድን አዋቀረ። በመርማሪ ፖሊስ ምክትል ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የሚመራው ቡድን የሲቪል ክትትሎችን በማሰማራት ወንጀል ፈጻሚው ይገኝባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ሁሉ ፍለጋውን ቀጠለ። በመዝገብ ቁጥር 660/2005 የተከፈተው ፋይል በየጊዜው የዕለት ሁኔታ ይሰፍርበታል። አሁን አሳሽ ቡድኑ ሌት ተቀን ዕንቅልፍ የለውም። መረጃዎችን ያነፈንፋል። ይበጁኛል የሚላቸውን ሁሉ እየጠራ ቃል ይቀበላል። በተባባሪነት የጠረጠራቸውንና ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን እየያዘም በምርመራ ያጣድፋል። በዚህ መሀል አንድ መረጃ ለፖሊስ ጆሮ ደረሰ። ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ እጁን ለመስጠት ፈቅዷል የሚል መረጃ። ይህን ያወቀው ፖሊስ አብዲ ተደብቆበታል በተባለ አንዲት ሴት መኖሪያ ደርሶ ፍለጋውን ጀመረ። ሁሉም ግን እንደታሰበው አልሆነም። ሰውዬው በቤቱ አልነበረም። የክትትል አባላቱ ሌሎች በርካታ መረጃዎችን አገኙ።
የሚሰሙትን ሳይንቁ፣ የተባለውን ሳይተዉ ፍለጋውን ተያያዙት። ድንገት ደግሞ ሌላ አዲስ መረጃ ከፖሊስ ዘንድ ደረሰ። ተጠርጣሪው ከአዲስ አበባ ርቆ ዲላ ከተማ እንደሚገኝ ተሰማ። ይህ እንደታወቀ ፖሊስ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ተጣደፈ። ለጉዞው በሚዘጋጅበት አጋጣሚ ግን ሌላ አዲስ መረጃ ደረሰው። ግለሰቡን ቃሊቲ አካባቢ ከሰዎች ጋር በድብቅ ሲያወራ ተመልከተናል ያሉ ያዩትን መጥተው ተናገሩ። ይህ መረጃ በርካታ ምልክቶችን ጠቆመ። ታይቶበታል በተባለ ስፍራ አግኝቶ ለመያዝ ፖሊስ ሰአት እየለየ፣ ቦታ እየቀየረ፣ ማንነቱን እየለወጠ ሌት ተቀን አደፈጠ። የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ግን የፍለጋው ወጥመድ ፍሬ ያዘለት። አብዲ ሃና ማርያም በተባለ የጎዳና ማደሪያው አካባቢ ሲዘዋወር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። የዕምነት ክህደት ቃሉን በመቀበል ድርጊቱ በበቂ ምስክርና ማስረጃዎች የተረጋገጠበት አብዲ መንሱር በግድያ ወንጀል ተከሶ ፍርድቤት ቀረበ። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ሃያኛ የወንጀል ችሎት ግለሰቡ በፈጸመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት «ይገባዋል» ያለውን የሞት ፍርድ ወሰነበት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2019
በመልካምስራ አፈወርቅ