ተዋናይ፣ኮሜዲያን፣ አዘጋጅ ሆኖ ለረዥም ዓመታት አገልግሏል። በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም ስራ እና በጋዜጠኝነት ሙያ ሠርቷል። የአፍሪካ የመድረክ ሙያተኞችን ማህበር በሊቀመንበርነት መርቷል፣ ቅንጅት የተሰኘው ፓርቲም ቃል አቀባይ ነበር። የዛሬው የዘመን እንግዳችን አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) ለታሪክ የሚተላለፉ ህያው ስራዎቹ ብዙ ናቸው። ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ በርካታ ሽልማትና እውቅናዎችን አግኝቷል። ከእነዚህም መካከል በአትላንታ ጆርጂያ ባበረከተው የሙያው ሥራ ኖቬምበር 24 ቀን በስሙ መሰየሙ ተጠቃሽ ነው። ከአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ጋር በተለየም በፖለቲካ ህይወቱ ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አሰናድተን አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣን ታነባለህ? ካነበብክ የትኛው አምድ ነው ትኩረትህን የሚስበው? አርቲስት ደበበ፡- እውነቱን እንድነግርሽ ነው የምትፈልጊው? አዲስ ዘመን፡- አዎ እውነቱን? አርቲስት ደበበ፡- አላነብም። ምክንያቱም አዲስ ዘመን ሁልጊዜ እኔን የሚሰድብ ጋዜጣ በመሆኑ ነው። ለመሰደብ ደግሞ አላነብም። አዲስ ዘመን፡- በየትኛው ዘመን ነው ይህ የሆነው? አርቲስት ደበበ፡- በኢህአዴግ ነዋ! ዶክተር አብይ ስልጣን እስከያዙበት ጊዜ ድረስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁልጊዜ ወንጀለኛ አድርጎ ነበር የሚያቀርበኝ።
በርዕሰ አንቀፃችሁም ሆነ በሌሎችም ገፆች እሰደብ ነበር። በዚህ ምክንያት ከአሳሪዎቹ ጋር የወገነ ጋዜጣ ነው። ርዕስ ባጡ ቁጥር እኔነበርኩ ርዕሳቸው የምሆነው። ፍርድቤት ሳይፈረድብኝ ቀድሞ የፈረደብኝ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመሆኑ ወገንተኛ ነው ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ አላነብም ነበር። አሁንም ገና እርግጠኛ አይደለሁም። ማንበብ አለብኝ ወይ ብዬ እያሰብኩ ነው። እኔን ፍለጋ እዚህ ድረስ መምጣታችሁ በጣም አስገርሞኛል፤ ምክንያቱም ይሄ ጊዜ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም ነበርና።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ሃሳባችን በነፃነት የምንገልፅበት ጊዜ በመፈጠሩ ያለምንም ስጋት የሚሰማህን መናገር ትችላለህ።
አርቲስት ደበበ፡- በወቅቱ እናንተ ስላልነበራችሁ ልትወቀሱ አይገባም። ለነገሩ ስድቡ በዛብኝ እንጂ በወቅቱ የነበሩትም ጋዜጠኞች ቢሆኑ ስራቸውን ነበር የሚሰሩት። ነገር ግን እነ አቶ በረከት ስምኦን የሚሰጧቸውን ፅሁፎች ዝም ብለው ከሚያወጡ እንደጋዜጠኛ የእኔንም ሃሳብ በማካተትና ሚዛናዊ ማድርግ ይገባቸው ነበር። በወቅቱ «ይሄ ነገር እውነት ነው ወይ?» ብለው ቢጠይቁኝ እኔ እነግራቸው ነበር። ግን እድሉንም አላገኘሁም። የሚገርመው ፎቶግራፌን እንኳ ሳይቀይሩ በተደጋጋሚ ያወጡት ስለነበር ቤተሰቦቼ በጣም ተሰላችተው ነበር። እኔ ጋዜጠኛ ሆኜ ሰርቻለሁ ስራውን አውቀዋለሁ፤ ሚዛናዊ መሆን ይቻላል። ይህን ስል ግን የግድ መመስገን ወይም መሞካሸት ነበረብን እያልኩ ግን አይደለም።ህፀፅ ሲኖርብን ህፀፃችንን ሲነግሩን የኛንም ወገን ሰምተው መሆን ነበረበት ነው እያልኩ ያለሁት።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካ የገባህበትን አጋጣሚ አጫውተኝ? አርቲስት ደበበ፡- ለምን ፖለቲካ ውስጥ ገባህ ብሎ ጥያቄ አይገባኝም። እዚህ አገር እየኖርኩ፤ የእዚህ አገር ዜጋ ሆኜ የህብረተሰቡ ችግር የእኔም ችግር መሆኑን እያወቅሁት፤ ለምንድነው ፖለቲካ ውስጥ የማልገባው? ባልገባም እኮ በግድ የፖለቲካው አካል መሆኔ አይቀርም ነበረ። ምክንያቱም የህብረተሰቡ ችግርም ሆነ ደስታ ተካፋይ በመሆኔ። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት አንዳንድ ሰዎች ለሀገሬ ስል ይላሉ። እኔ ፓለቲካ ውስጥ የገባሁት ለሀገርም ለህዝብም ስል አይደለም። ለራሴ ስል ነው የገባሁት። አዲስ ዘመን፡- እንዴት? አርቲስት ደበበ፡- በአንድ አጋጣሚ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት በሃሳቤ መጥቶ አላስተኛ አለኝ። ሁልጊዜ የጥበብ ሰዎች አንድ ችግር ሲፈጠር ይጠራሉ። የእናት አገር ጥሪ ሲባል እንጠራለን። ገንዘቡ ተሰብስቦ ለመንግስት ወይም ደግሞ ለሚመለከተው አካል ሲሰጥ ግን እገሌ የሚባለው ድርጅት ሰጠ ነው የሚባለው። የኪነጥበብ ባለሙያዎች ባበረከቱት አስተዋፅኦ አይባልም።
ስለዚህ ለእኛ ምንም አስተዋፅኦ አልተመዘገበልንም። ለምን ታዲያ የራሳችን አሻራ ያረፈበት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ተቋማትን አንገነባም ብዬ ብቻዬን ሳስብበበት ቆየሁ። በወቅቱ አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ስለነበርኩ እዛ ያሉ ሰዎችን ሳማክራቸው በሃሳቤ ተስማሙ። ነገር ግን ምንም ኮሚቴ አላደራጀሁም። ያለንን እውቅና በመጠቀም ባለሃብቶችን በምናነጋግርበት ጊዜም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሊሰጡን ቃል ገቡልን። የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሩንም በኤግዚቪሽን ማዕከል በነፃ ልናካሄድ በዝግጅት ላይ ሳለን በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ከነበሩት ከወይዘሮ ብስራት ጋሻው ጠና ቢሮ አንድ ስልክ ተደወለልኝ። ሚኒስትሯና አንድ ሌላ ሰው ያቋቋሙት ኮሚቴ አለና ትፈለጋለህ ተባልኩኝ። እኔ በመስተዳድሩ ስር ባለው አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነው የምሰራው የፌዴራል መንግስት አካል የሆነው ቢሮ እኔን ሊጠራኝ አይችልም የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው። በወቅቱ ለነበረው የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ ከፈለጉኝ በመጀመሪያ በመስተዳድሩ፤ ከዚያም ለቴአትር ቤቱ፤ ብሎም በአለቃዬ በኩል ነው ጥሪው መተላለፍ ያለበት አልኩት። በኋላም ያልኩትን ሂደት አልፎ ስብሰባው ላይ ተገኘሁ። ኮሚቴ ቀድመው አቋቁመው ኖሮ ሰብሳቢው ተቀመጥ ሲለኝ መጀመሪያ የተፈለግሁበትን ጉዳይ እንዲያሳውቀኝ ጠየኩት።
እርሱም እኛ የጀመርነውን አይነት ፕሮግራም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በማዕከል ስለጀመረ የእናንተን ትታችሁ እኛ ጋር ግቡ፤ እስካሁንም የተሰበሰበ ገንዘብ ካለ አምጡት አሉኝ። እኔ ግን ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለፅኩላቸውና ስብሰባውን ጥዬ ወጣሁ። ከዛ እንደወጣሁም ቃል ለገቡልኝ ድርጅቶች በሙሉ ደውዬ ላሳዩን ቀናነት አመስግኜ ፕሮግራሙ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ገለፅኩላቸው። ያን እለት ታዲያ የፓርቲ አባል መሆንን ተመኘሁ። የፓርቲ አባል ብሆን ኖሮ እኔም ዴሞክራሲያዊ መብቴን የሚያስጠብቅልኝ ይኖር ነበር ብዬ ተቆጨሁ። በዛው ስሜት ውስጥ ሆኜ ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሄድኩ። ያ የተቋቋመው ኮሚቴ ግን እንደተባለው መስቀል አደባባይ ዝግጅቱን አቀረበ። እኔ ውጭ እያለሁ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያዘጋጀው «ቀስተደመና» የሚል ማኑፌስቶ አገኘሁና ሳነበው ወደድኩት። ከዚያ በኋላም «ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ» የሚለውን የአንዳርጋቸውን መጽሐፍ አነበብኩ። ስለዚህ ራሴን ነፃ ማውጣት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ከዚያ በኋላ እንደመጣሁ መተዳደሪያ ደንባቸውን አነበብኩ። ያን ጊዜ ታዲያ ፓርቲ ሳይሆን እንደ ፕሮፈሰር መስፍን ያሉ እውቀትና ፍላጎት ያላቸው አንድ ላይ ሆነው የሚመክሩበት ስብስብ ነው። የግለሰብ ነፃነትን ለማስከበር የሚታገሉ በመሆናቸው አላማቸው አላማዬ ሆኖ ስላገኘሁት ቅፅ ሞልቼ ገባሁ። ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የገባሁት መብቴን ለማስከበር ስል ነው። አዲስ ዘመን፡- አንተ ይህንን ብትልም ሌሎች አርቲስቶች የኪነጥበብ ሰው ከፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም ብለው ይሟገታሉ? አርቲስት ደበበ፡- ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ስለሚፈሩ ነው! የኪነጥበብ ሰው ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል ሰው ፈሪ ነው ብዬ አስባለሁ።
ለመሆኑ የማንን ደመወዝ ነው የሚበሉት? ይህ ህዝብ የሚያዋጣውን ታክስ ተሰብስቦ አይደል የሚበሉት? ስለዚህ የፖለቲካው አካል የሚያደርገን አንዱ ነገር እርሱ ነው። በእርግጥ ወዴት ነው የምንወግነው? የትኛውን የፖለቲካ ድርጅት እንመርጣለን? የሚሉት ጉዳዮች የግል ምርጫችን ናቸው። ይሁንና ፖለቲካ ውስጥ ግን ጭራሹኑ መግባት የለብንም በሚለው ሀሳብ አልስማማም። በጣም የሚገርምሽ እኔ የታሰርኩት ሳልፈራ ያልታሰሩ ጓደኞቼ ለእኔ ይፈሩ ነበር። ለእኔ ለምን ይፈሩልኛል? እኔ የራሴ ፍርሃት አለኝ። ማንኛውም የጥበብ ባለሙያ የአገሩን የፖለቲካ ሁኔታ ሳያውቅ፣ የአገሩን ተጨባጭ የፖለቲካ ሂደት ሳይመረምርና ሳያገናዝብ ምንም አይነት ለህዝብ የሚጠቅም ስራ አይሰራም። የሚሰራው ነገር ቢኖር ለቆመለት ግለሰብም ሆነ ድርጅት ብቻ የሚያገለግል አሽከር መሆንን ነው። እኔ የኪነጥበብ ሰው በመሆኔ የአገሬን የፖለቲካ ሁኔታ ማወቅ አለብኝ ብዬ አምናለሁ።
ምክንያቱም እኔም አንድ የህብረተሰቡ አባል በመሆኔ። የኪነጥበብ ባለሙያ ስለተባለ እንደተለየ ነገር ሆኖ መቅረብ የለበትም። ሁላችንም የህዝቡ አካል ነን። ውሃ ሲጠፋ እኮ ይሄኛው ፖለቲካ ውስጥ ስላልገባ ለዚህኛው ይሰጠው፤ የገባው ግን አይሰጠው አይልም። ባንቧው ዝም ብሎ ነው የሚፈሰው፤ መብራቱም ዝም ብሎ ነው የሚመጣው። ግን የፖለቲካ አቅም አይደለም እንዴ እነዚህንስ ነገሮች የፈጠሩት? እንዳውም አጠቃቀማችንን ያለማወቅ ነው እንጂ የኪነጥበብ ሰው የአገሩን የፖለቲካ ሁኔታ የህብረተሰቡን ችግር አውቆ ነው ስራ መስራት ያለበት። ለዚህ እኮ ነው እስካሁን ከጥቂቶች በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ስራ መስራት ያልቻሉት። አሁን ደግሞ ዶክተር አብይ አህመድ ስርዓቱን እንደመሰለን እንድንተች እድል ፈጥረውልናል። ስለዚህ ለሁሉም ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ስለፖለቲካው ሳንፈራ እንፃፍ እንተች የሚል ነው። አዲስ ዘመን፡- በአንተ ዘመን የነበሩትን አርቲስቶች አሁን ካሉት ጋር አነጻጽረህ እንዴት ትገልፃቸዋል? አርቲስት ደበበ፡- አዎ የቀደሙት አርቲስቶች አመራሮችን በስራዎቻቸው በሚገባ ይተቹ፤ ህፀፃቸውን ይናገሩ ነበር።
ለምሳሌ «ሀ ሁ በስድስት ወርን»፣ «እናት አለም ጠኑን» እንዲሁም «ዋናው ተቆጣጣሪን» መጥቀስ ይቻላል። «የአዛውንቶች ክበብ» የሚለው ቴአትር እኮ በጡረተኞች ላይ የተመሰረተ እንዳይመስልሽ፤ ይልቁኑ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች በጡረታ ተገልለው ሳይሰሩ የተባረሩ ናቸው የሚል አቋም ያለው እንጂ። እነሱ ተሰብስበው ያመጡት ሃሳብ ወደ ተግባር ቢለወጥ ትልቅ ነገር ሊወጣው ይችላል በሚል ነው። አሁንም እኮ አልፎ አልፎም ቢሆን ደፈር ያሉ ስራዎችን አያለሁ። ለምሳሌ በቅርቡ የተሰራውና እኔ ልጫወተው የነበረው ቴአትር በኋላ በጤንነት ምክንያት ሳልጫወተው የቀረሁት «ባዶ እግር በአቴንስ» አጠቃላይ ይዘቱ ፖለቲካና ዴሞክራሲን የሚመለከት ነው። እንደዚህ አይነት ተውኔቶች በደርግ ግዜ በስፋት ይሰሩ ነበር። እንደውም አንድ ጊዜ ቴአትሩ ሁሉ ፖለቲካ ሆነ እና ተመልካቹ «ገንዘባችንን ከፍለን ጊዜያችንን ሰውተን ተቀምጠን ለመሰደብ ፈቃደኞች አይደለንም» እስከማለት ደርሶ እንደነበር አስታውሳለሁ። በአሁኑ ወቅት ፖለቲካውንና ፖለቲከኞችን የሚተቹ ቴአትሮች አናይም። በእኔ አምነት አሁን ያለው የአገራችን ፖለቲካ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። እኔ የመፃፍ ችሎታውና ትዕግስቱ ስለሌለኝ መፃፍ የሚችሉ ጓደኞቼን በተለይ ስለሜቴክ አሁን ፃፉ እያልኩ እየመከርኳቸው ነው።
ሜቴክ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ ግን ያልታወቀ አንድ ሰይጣናዊ ሃይል ያለው ተቋም በመሆኑ ብዙ ሊያሰራን ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ የምቀርባቸውን ሰዎች እስቲ የሜቴክ ምንጭ ማነው? ጄነራሉን ማን ሾመው? የሚል ቴአትር ፃፉ ብያቸዋለሁ። አንዳንድ ሰዎች እየሞከርን ነው ብለውኛል። አንድ ቀን እንደሚያስነብቡኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሂደትን እየተከተልን ህብረተሰቡን ማስተማር ይገባናል። መንግስት ሲሳሳት ተሳስተሃል ብለን መንገር አለብን። በእኛ አገር ቴሌቪዥን እኮ «የዚህ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄንን ስለተናገረ ትችት ወረደበት» ነው እንጂ የሚሉት ራሱን አይተቹም። በጣም የሚያሳዝነው የእኛ አገር ቴሌቪዥን የተስፋዬ ሳህሉን፣ የአውላቸው ደጀኔን፣ የወጋየሁ ንጋቱን ልደት በዚህ ቀን ነው ብሎ ተናግሮ አያውቅም። ሆሊውድ ያሉትን የፈረንጅ ተዋናይን ልደት ነው የሚነግሩን። የራሳችን የሆኑትን ክለቦች ጊዮርጊስ እና ቡናን ከቃላት ባለፈ በገንዘብ ደግፈን የትም አላደረስናቸውም።
የአርሴናልና ማንቸስተር ጫወታን ለማየት ግን ገንዘባችንን እንከሰክሳለን። ስለዚህ ኪነጥበባችንም እንዲህ አይነት የተዘበራረቀ ፍርሃት የነገሰበት ነው። አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑ በአንድ መድረክ ላይ አርቲስቶች እርስበርስ የፖለቲካ ወገንተኝነት ላይ ሲወቃቀሱ ነበር። አሁን ላይ መወቃቀሱ ትርፍ አለው ብለህ ታምናለህ? አርቲስት ደበበ፡- ይገርምሻል እኔም ነበርኩ በዚያ መድረክ ላይ። እኔ በበኩሌ እንዲህ አይነቱን ጭቅጭቅ አልደግፈውም። ዶክተር አብይ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥበብ ሰዎችን ሰብስበውን በነበረበት ጊዜ እንዲህ አይነት ጥያቄ ሳይነሳ ገና «ባለፈው ጊዜ እነእገሌ ይህንን አድርገዋል፤ አሁን ደግሞ እነሱ ዞር ይበሉልንና አሁን እኛ ደግሞ በተራችን እናድርግየሚል ጥያቄ እንዳታነሱ፤ አንድ ብለን ከዛሬ ጀምረን ወደ ፊት እንሂድ» የሚል ሃሳብ አንስተውልን ነበር። እኔም የምለው መጠቋቆሙ ምንም ዋጋ የለውም ነው። ሰራዊትና ሸዋፈራው ባይሰሩት ሌላ ሰው አይሰራውም ነበር? ሌላ ሰው ይህንን እድል ቢያገኝ አይጠቀምበትም ነበር? ህውሃት የታገለበትንስ ስፍራ ጎብኙ ተብለው በሄዱ ጊዜ ታሪካችሁን እንፃፈው ያሉ የሉም? እኔ እንኳ ስለማይወዱኝ አልጠሩኝም እንጂ ብሄድ ግን ደስ ይለኝ ነበር። በዚያ ወቅት ያወደሷቸው የሉም? እርግጥ ነው መወደስ ይገባቸዋል፤ ግን በአግባቡ ነው መሆን የሚገባው።
የበረከት ስምኦን መፅሐፍ የተመረቀ ጊዜ ሙሉዓለም ብቻ ነች እንዴ ግጥም ያነበበችው? ሌሎች ብዙ ሰዎች አላነበቡም? ያላነበብነው ደግሞ ለምን አላነበብንም ብለን አልተቆጨንም? ይህንን ከግንዛቤ ማስገባት የሚገባን ይመስለኛል። በእርግጥ እኔን አንብብልኝ ቢለኝም አላነብም ነበር። ምክንያቱም እሱ አቋሜን አይወድም፤ እኔም የሱን አቋም አልወደውም። ግን በፍፁም መኮራረፍ እንደማይገባን አምናለሁ።እኔ ቅንጅትነቴን እሱም ኢህአዴግነቱን ይዞ በምንተማመንባቸውና በምንግባባቸው ጉዳዮች አብረን መሄድ እንችላለን።
በሌሎቹም ላለመሰማማት ተስማምተን መቀጠል እንችላለን። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገር ሰብአዊ ግንኝነቶቻችንና የፖለቲካ አቋማችን ሊያበላሸው አይገባም። አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካ በተለወጠ ቁጥር ከየዘመኑ ፖለቲካ ጋር መለጠፉ ተገቢነው ብለህ ታምናለህ? አርቲስት ደበበ፡- እሱማ እነዚህን ልጆች ሰሩ ብለን እንወቅሳቸዋለን እንጂ እኛም እኮ ያ መንግስት የሚከፍለንን ደመወዝ እንወስዳለን። እኔ ልዩነቱ አይታየኝም። እኔ ጡረታዬን የማገኘው ከከፈልኩት ቢሆንም እንኳ መንግስት ሊያቆመው ይችላል እኮ። ግን አላቆመውም ልክ እንደሌሎቹ ጡረታዬን ቆጥሬ እቀበላለሁ። እርግጥ ነው እኔ የምቀበለው ጡረታና አሁን በኢህአዴግ ዘመን ያሉ ሰዎች የሚያገኙት ጡረታ አይመጣጠንም። በአንድ ሺ እጥፍ ይበልጠኛል።
ያ በመሆኑ ግን ቅር አላለኝም። እኔ በጊዜው የምከፍለውን ነው ያገኘሁት። ይሄ ነው መባል ያለበት። አንድ ግን የማምነው ነገር አለ፤ ሁሉም ሰው እንደራሱ ሆኖ ማሰብ መጀመር አለበት። ፕሬዚዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በእኔ በኩል ይህንን ያህል ሰው ሞቷል፤ በአንተ በኩል ደግሞ ይህንን ያህል ሰው ሞቷል ብለው ይቅርታ አልተጠያየቁም። ያ የተዘጋ ምዕራፍ ነው። ወደፊት ታሪክ ያነሳዋል። የዚያን ጊዜ ሁላችንም ጥፋታችንን ልንገነዘበውና ይቅርታ ልንጠያየቅ እንችላለን። አሁን ግን ከዛሬ ጀምረን ለህዝቦችና ለአገራችን ጥቅም ስንል አብረን እንቁም ብለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ያቃታቸውን አንድ ዶክተር አብይ ሄዶ ኢሳያስ አፈወርቂን አሳምኖ ሰላም መፍጠር ብቻ ሳይሆን ይዞት መጣ። ቀደም ባለው የኢህአዴግ አካሄድም እኮ ተሞክሮ አልተሳካም። ምክንያቱም አካሄዱን አላወቁበትም ነበር። ስለዚህ ቁርሾን ይዞ መታረቅ ለውጥ አያመጣም።
መደረግ ያለበት ነገር ግን አለ። በስራው ሂደት አንዳንድ የተከፉ የህብረተሰብ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይገባል። ምክንያቱም ከህዝብ የሚበልጥ ማንም የለም። እኛ ለህዝብ አይደለም እንዴ የምንሰራው? ያ ህዝብ አይደለም እንዴ መጥቶ የሚያየን እኛን? ስለዚህ ያንን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልግም?። ደግሞም «ኩራዝ ወደ ሙዚየም ይገባል፤ ሻማ ለልደት ይሆናል» ብለን ኩራዝም ሆነ ሻማ ማብራታችን አልቀረም መብራትም መጥፋቱን አላቆመም። ይህ አባባል አስከፍቷቸው ሊሆን ስለሚችል የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይገባል። እኛም ደግሞ ያደረጉትን ጥሩ ነገር መካድ የለብንም። እነዚህ ልጆች እኮ ብዙ አድርገዋል፤ አልተናገሩም እንጂ። አሁን የነገሩንን እውነታ ተቀብለን ይቅር ልንላቸው ይገባል። አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ አሁን ካለው የፖለቲካ እንቅሳቃሴ ምን ትታዘባለህ? ምን ተለውጧል? ምንስ ይቀራል? አርቲስት ደበበ፡- እንግዲህ ይሆናል ብለን ያልገመትነውና ያላሰብነው ነገር ነው እየሆነ ያለው። እኔ በበኩሌ እንኳን ላልመው ይቅርና አልቃዠውም።
ነገር ግን ሆነ። የእውነት ሲሆን ደንግጫለሁ።ብዙግፍ ደርሶብናል። እንደሰው ብዙ መከራ አይተናል። በኢህአዴግ ጊዜ ከአቅማችን በላይ የሆነ ችግር ደርሶብናል። ይሁንና ያንን እያስታወስን መኖር አይገባንም። የመጣው ለውጥ ፈር ይዞ እንዲሄድ ማገዝ ይገባናል። ምክንያቱም ዶክተር አብይም ሆነ የሱ ካቢኔ አባላት ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። እነዚህ ሰዎች መረዳትና መታገዝ አለባቸው። ስናግዛቸው ደግሞ ለለውጡ ቀጣይነት በሚጠቅም ጎኑ መሆን ይገባል። ሰላማዊ ሰልፍና ህዝብ በመጥራት አይደለም። ወጣቱን በክፉ ነገር ማሰማራትም አይገባም። ደግሞም በአመፅ የሚፈጠር ጥሩ ነገር አለ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም አስር ጊዜ ብትወለውይውና ብታሽሞነሙኚው ከጠብመንጃ አፍ የሚወጣው ጥይት ነው። ያ ደግሞ ገዳይ ነው። እና መጥፎ ነገር በማሰብ የምናደርገው ነገር ለዚህች አገር ምንም የሚጠቅም ነገር የለም። አንዳንዶቹ ከውጭ የመጡት መንገዱ ግራ የገባቸው ይመስለኛል።
አንድ ቦታ ላይ ሆነሽ እድሜ ሲበዛ ሌላ ነገር መመልከት ያቅትሻል። እንደዚያ ይመስለኛል አሁን ያለው ችግር። ቦታው ላይ ብዙ ቆዩበትና እኛ ለቀን ማን ሊወስድብን ነው? የተለፋው እኮ ህዝብ እንዲያልፍለት እንጂ ህዝብ መከራ ውስጥ እንዲገባ አይደለም።እርግጥ ነው ለፍተዋል፤ እናመሰግናቸዋለን፤ አሁን ደግሞ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው። ትውልዱ በአዲስ አይንና አመለካከት ሊመራው ይገባል። ፖለቲካ ማለት ጭፍን መሆን አይደለም። ክፍት ቦታ አለው። ክፍተቱ ግን መሞላት ያለበት በጥሩ ሃሳቦች ነው። ፖለቲካ ውስጥ መጥፎ ነገር አለ ብለሽ መጥፎ ነገር ስትጨምሪበት አጥፊና ጎጂ ነው የሚሆነው። ይህንን ማሰብ መቻል አለብን። እኛ እኮ የደረሰብንን ችግር እያነሳን እዚያ ላይ ስንቆዝም እኮ ነው ሌላ ችግር ተፈጥሮ የሚያድረው። ሁላችንም በአካባቢያችን ያለውን ሁኔታ ማጤን ይገባናል። ድሮ ቀበሌዎች ብቻቸውን ነበር የሚሰሩት። አሁን ህብረተሰቡን እየጠሩ አማክሩን ይላሉ። ስለዚህ መደገፍ ይገባናል። ሁላችንም የዚህች አገር ተጠሪዎች እንደመሆናችን ስለሰላም ማወጅና መዝፈን አለብን። አሁን ደግሞ አፋችንን ሞልተን ያለምንም ችግር ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራበት እድል ተፈጥሮልናል። ስለዚህ በጎሳ በነገድ መከፋፈሉ ይቅርና ኢትዮጵያዊ ሆነን አገራችንን እናልማት።
አዲስ ዘመን፡- በዚሁ አያይዘህ ስለአገር አንድነት ያለህን አመለካከት ንገረን? አርቲስት ደበበ፡- እኔ የተቆራረሰች አገር ውስጥ መኖር አልፈልግም። አዲስ ዘመን፡- ምን ማለት ነው? ይብራራ?
አርቲስት ደበበ፡- ሰፊውን አገር ይዤ እዛ ውስጥ እንደፈለግሁ እየዘለልኩና እየተደሰትኩበት ነው መኖር የምፈልገው። አገር ተከፋፈለች ማለት ጠፋን ማለት ነው። ግንኙነታችን ተቆራረጠ ማለት ነው። አገር ተከፋፈለ ማለት መተሳሰብና ወዳጅነት ቀረ ማለት ነው። በርቀት መተያየት እንጀምራለን። የዚያን ጊዜ ትንሽ እየሆንን ነው የምንሄደው። ሌላው አለም እኮ ይህንን አልፎ ለድንበርነት የተሰራን ግንብ እየናደ አንድ ለመሆን እየጣረ ነው። እኛ ደግሞ አንድነትን ትተን እንበጣጠስ ነው የምንለው። የመበታተንና የመከፋፈልን ውጤት ለማወቅ የዶሮን መገነጣጠል ማየት ይሻላል። ዶሮ ስትገነጣጠል እያንዳንዳችን አንድ አንዷን ክፍል በልተን እንጨርሳታለን።
ተመልሳ አትገጣጠምም። ዶሮዋ ግን ብትቆይ እንቁላል ትጥልልናለች። ልጆች ታፈራለች።ብዙ ዶሮዎች ትሆናለች። እንደዛ ከመሆን ያውጣን ነው የሚባለው። ደግሞስ እንዴት አድርገን ነው ይህንን ትልቅ ህዝብ በትንሹ የምንከፋፍለው? ትንንሽ መንደሮች ሆነን መጠሪያችንስ ማን ሊሆን ነው?። እኔ በምሄድባቸው አገራት ሁሉ ይዤ የምዞረው የኢትዮጵያን ፓስፖርት ነው እንጂ የተወለድኩበትን አካባቢ መታወቂያ አይደለም። እንደዛ ካልሆነ ደግሞ የወሎ ፓስፖርት፣ የጎንደር ፓስፖርት፣ የትግራይ ፓስፖርት እየተባለ ትንንሽ የፓስፖርት ቢሮዎች ልንከፍት ነው ማለት ነው።
ከዚሁ ሁሉ ጣጣ ሁሉንም ትተን ብዙዎች ነን አንድ ሆነን ልዩነታችን ውበታችን ነው ብለን መነሳት አለብን የሚል አቋም አለኝ። አንዱ ለሌላው ማሰብ እንጂ አንዱ ሌላውን መፍራት የለበትም። እኔ መርጬ አይደለም ወሎ የተወለድኩት። የእኔ ልጆች ደግሞ አዲስ አበባ ነውየተወለዱት። ስለዚህ እኔና እነሱ የሁለት አገር ሰዎች ልንሆን ነው ማለት ነው? ለእኔ አንድነት ማለት የህዝብ፣ የአገር፣ የኑሮ፣ የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ስለዚህ የሚያዋጣን ሁላችንም በጎሳና በነገድ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነታችንን አስጠብቀን መኖራችን ነው። አሁን ደግሞ ሁላችንም ነፃነታችን ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ተከብረው የምንኖርበት እድል ተፈጥሮልናል። ለዚህም ኢህአዴግ ዶክተር አብይንና ቲም ለማን ስላመጣልን ማመስገን ይገባናል የሚል እምነት አለኝ። ኢህአዴግ ባይኖር ኖሮ ዶክተር አብይን ከየት እናመጣው ነበር።
ኢህአዴጎች እንደሚቀበሉት ባላውቅም በዚህ መመስገን አለበት የሚል ፅኑ አቋም አለኝ። አዲስ ዘመን፡- የቅንጅት የህዝብ ግንኙነት በነበርክበት ጊዜ ቀድሞ የነበረህ እውቅና ለፓርቲው ተወዳጅነትና ተቀባይነት የጎላ ሚና ተጫውቷል ብለህ ታምናለህ? አርቲስት ደበበ፡- እውነት ነው፤ በወቅቱ የእኔ ስራ የነበረው ቀስተደመና እንዲወደድ ማድረግ ነው። ሌላው ነገር በቴሌቪዥን ላይ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ተመልካች እንዲያገኙ ማድረግ ነበር። ብዙ ሰዎች ያንንም ሚናህን ተወጥተሃል ብለውኛል፤ በዚያም ደስተኛ ነኝ። ለዚያ ደግሞ በዚያን ጊዜ በማቀርባቸው ፕሮግራሞች የመንግስት ባለስልጣናትም ተባብረውኝም ነው ውጤታማ መሆን የቻልነው። ስለዚህ ባለውለታዬ ናቸው ብዬ አምናለሁ። መጀመሪያ ላይ የተወራብንን ነገር የማስተባበል ስራ ነበር የምንሰራው በኋላ ግን እነዚያ ባለስልጣናት ሚስጥራቸውን ይነግሩኝ ስለነበር ስትራቴጂያችንን ለውጠን ሚስጥር ስናገኝ ሚስጥሩን ማውጣት ጀመርን። እነሱም በተራቸው ሚስጥሩን ማፍረስ ጀመሩ። ያን ጊዜ አልፈናቸው ሄድን፤ ከጠበቅነው በላይ አባላት መሰብሰብ ቻልን።
አዲስ ዘመን፡- ለቅንጅት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ማግኘት የአንተ ሚና እንዳለ ሆኖ ለመፍረሱ ማነው ተጠያቂ መሆን የሚገባው ትላለህ? ይህንን ብናደርግ ኖሮ ብለህ ተቆጭተህ አታውቅም?
አርቲስት ደበበ፡- ስለእሱ ጉዳይ በሚመለከት መፅሃፌን ብታነቢው ኖሮ ታውቂው ነበር። በዚያ ድርጅት ውስጥ ቅንጅት ተብለው አንድ ላይየተጣመሩት ፓርቲዎች አራት ናቸው። እንግዲህ ምርጫ ሲመጣ ብዙ ሰው የአንድ ድርጅት መሪ ለመሆን ይመኛል። ጠቅላላ ጉባኤ የሚፈልገው ግን አንድ ሰው ብቻ ነው። ለዚያ ደግሞ በዋናነት ለመሪነት የሚመረጠው ሰው ታዓማኒነት፣ ግልፅነት የዴሞክራሲን አመለካከትና የሰብአዊ መብትን ለህዝቡ ሊያረጋግጥ ይችላል ወይ? ብሎ መርምሮ ነው። በዚህ መሰረት በተደረገው ምርጫው ላይ እንግዲህ ብርቱካን ሚደቅሳ አሸነፈች። ምርጫው ነፃና ግልፅ በሆነ መንገድ ቢካሄድም ብርቱካን በመመረጧ ደስ ያላላቸው ሰዎች ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ ቅንጅት በመፈጠሩ ፓርቲያችን ሞተብን ብለው ያሰቡም ሰዎች ነበሩ። በተጨማሪም በስምምነቱ መሰረት ሁሉም ፍቃዳቸውን መልሰው በቅንጅት ስር አንድ መሆን፤ እያንዳንዱ ፓርቲ ፋይናንሱን ኦዲት አድርጎ ማቅረብ ሲኖርባቸው ያንን ያላደረጉ ፓርቲዎች ነበሩ። ስለዚህ እነዚህ ትንንሽ የማይባሉ የፓርቲውን ግንባታ ሊያጠነክሩ ይችላሉ ተብለው ግምት የተሰጣቸው ባለመሆናቸው ለገዢው መንግስት እኛን ለመበታተን ጥሩ መንገድ ከፈተለት፤ እናም በታተነን። እንዳንስማማ አደረገን። ያም ሆኖ ግን እዚያ ጋር መቆም ሲገባ አልቆመም፤ ምርጫ 97 ሲመጣ ቅንጅት በከፍተኛ ድምፅ ተመረጠ። መጀመሪያ ላይ ሁሉም የኢህአዴግ ሰዎች መሸነፉን አምነው ነበር። በኋላ ግን ተኝተው ሲነሱ ተሸንፈናል ብለው ስልጣን ማስረከባቸው ስጋት ፈጠረባቸው። ስለዚህ ምርጫው ተጭበርብሯል አሉ። እነዚህ አራት ድርጅቶች ጦር ወይም ደህንነት እንዲሁም የያዙትና የሚያስተዳድሩት ቀበሌ ሳይኖራቸው በምንድን ነው የሚያጭበረብሩት?። የኢህአዴግ ጠባቂዎች አይናቸውን አፍጥጠው በሚጠብቁበት ሁኔታ ኮሮጆ መገልበጥስ ይችሉስ ነበር?። እውነታው ግን ቅንጅት ማሸነፉን መቀበል ባለመቻላቸው ያቀረቡት ሰበብ ነው።
በተለይም አዲስ አበባ ላይ ኢህአዴጎች ከአንድ ድምፅ በላይ ባለማግኘታቸው ከተማዋን ለቅንጅት አስረክቡ ሲባሉ አሻፈረኝ አሉ። አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን በወቅቱ ቅንጅት አልረከብም እንዳለ ነው ሲገለፅ የነበረው? አርቲስት ደበበ፡- በፍጹም አልረከብም አላለም። ሊረከብማ ነው ተወካዮች ልኮ የነበረው። ነገር ግን በወቅቱ የአዲስ አበበ ከንቲባ የነበረው አርከበ እቁባይ ፓርላማ መግባታችሁን ስታረጋግጡ ብቻ ነው የምናስረክባችሁ የሚል ምላሽ የሰጠው። ከዚያ ቀጠለናም አቶ መለስ ደግሞ ላስራችሁ እችላለሁ አለን። እንዳለውም ደህንነት መጥቶ ከየቤታችን እየለቀመ ወሰደን። እኔ የማውቀው እውነታ ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለእስር ቤት ቆይታ ትንሽ እናውራ? ለእስር የሚያበቃ ተጨባጭ ማስረጃ ተገኝቶብህ ነበር?
አርቲስት ደበበ፡- ምንም ማስረጃ አልተገኘብኝም። የቅንጅት አባል መሆኔ የአደባበይ ሚስጥር ነው። ተደብቄ አልነበረም እየሰራሁ ነበርኩ። ስለዚህ ሚስጥር የሆነ ነገር ማስረጃ ምንድን ነው የሚፈልጉት። ይልቁንም «ህፀፅ የሌለበት ነፃ ምርጫ ነው የምናካሂደው» በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎክረው እንዳልነበር ሲሸነፉ ህገመንግስቱን ለመናድ፣ አገር ለመናድ ሞክረዋል ተብለን ነው የታሰርነው። ከታሰርንም በኋላ ከማዕከላዊ ጀምሮ ሁሉም የኢህአዴግ አባሎች በመሆናቸው እኛን ወንጀለኛ አድርገው ደምድመው ስለነበር በተቻለ መጠን እኛ ምቾት እንዳይሰማን ያደርጉ ነበር። በሳምንት ለ20 ደቂቃ ፀሃይ መሞቅ የቻልነው ለፍርድቤት ባቀረብነው አቤቱታ ነው። የሚገርመው በአስገድዶ መድፈር ስርቆት ግድያ የታሰሩ ሰዎች ጥሩ አያያዝ ነው ያላቸው። የሚጠይቁት ነገር ሁሉ ይፈፀምላቸዋል። ትምህርት ይማራሉ ሃኪም ቤት በፈለጉበት ጊዜ ይሄዳሉ። የኛ አባላት እኮ በተልዕኮ እንኳ ለመማር ተከልክለዋል።በተጨማሪም ባልሰራነው ስራ እንደሰራን አድርገን በራሳችን ላይ እንድንመሰክር ጫና ያደርጉብን ነበር። እምቢ ስንላቸው የጸሃይ ብርሃን እንዳናይ አድረገው ያስቀምጡን ነበር።
ይህም ሰዎቹ ምንያህል ኢ-ሰብአዊ ፍጡር እንደነበሩ የሚያሳይ ነው። ለመሆኑ እንዴት አድርገው ቢመለምሏቸውና ቢያሰባስቧቸው ነው ሁሉም አንድ አይነት ጨካኝ፤ አንድ አይነት ግፍ ሰሪ ሆነው የተገኙት? ይሄ ሁኔታ እንደዜጋ ያሳዝነኝ ነበር። ወደ ወህኒ ቤት ስንወርድ የት እንኳን እንደምንሄድ ለቤተሰቦቻችን አልተነገረም። እርግጥ ነው ህገመንግስቱ አንድ ተጠርጣሪ እስር ቤት በሚቆይበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ወንጀለኝነቱን እስካላረጋገጠ ጊዜ ድረስ ነፃነቱ የተጠበቀ መሆኑን ደንግጓል። ይሄ በፍፁም ተግባራዊ አልሆነም። በተለይም እኛ ላይ ከፍተኛ ጫና ይደረግብን ነበር። አብረን ቁጭ ብለን እንድናወራ እንኳ አይፈለግም ነበር። ቤተመፅሃፍት ቢኖርም ለኛ ግን አይፈቀድልንም ነበር። ይሁንና ውስጥ ስለሚገባልን እየተዋዋስን እናነብ ነበር። ይህንን ሲያውቁ ደግሞ መፅሃፍ እንዳይገባ አደረጉ። አጠቃላይ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈፀመው በደል በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር እንደነበር ማንሳት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከተፈታህ በኋላስ በምን ምክንያት ዳግመኛ ታሰርክ?
አርቲስት ደበበ፡- ድጋሚ የታሰርኩት የግንቦት ሰባት መልማይ ነህ ተብዬ ነው። እነሱ የሚፈልጉት እነ እገሌና እገሌ የግንቦት ሰባት አባል በልልን አሉኝ እኔ ግን አልልም አልኳቸው።በዚህ ምክንያት ለሶስት ወር አቆይተውኛል። አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ ልትጠቅስልን ትችላለህ? አርቲስት ደበበ፡- ለምሳሌ አንዷለም አራጌን፣ እስክንድር ነጋንና ከወታደሮችም የማላውቃቸውን ሰዎች ስምዝርዝር እየጠሩ የግንቦት ሰባት አባል ናቸው በልልን ይሉኝ ነበር። አዲስ ዘመን፡- አንተ ግን ከግንቦት ሰባት ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረህም? አርቲስት ደበበ፡- እኔ የግንቦት ሰባት አባልም ሆነ መልማይ አልነበርኩም። ግንቦት ሰባትም እኔን አያውቀኝም። ግንቦት ሰባት ከተባለ በኋላ ከእኔ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም። ሶስት ወር ካሰሩኝ በኋላ ደግሞ እቃህን ጠቅልል ውጣ ነው የተባልኩት።
አዲስ ዘመን፡- በማንም ላይ ሳትመሰክር ነው የተፈታኸው?
አርቲስት ደበበ፡- በማንም ላይ አልመሰከርኩም፤ የማላውቀውን ነገር ምን ብዬ ነው የምመሰክረው? ለምሳሌ አንዷለም ጋር ቅንጅት ውስጥ አብረን ነበርን፤ እስክንድርም ጋር እስርቤት ነው የተገናኘነው እንጂ የፓርቲ አባልም አልነበረም። የሚጠሩልኝ ወታደሮችና መኮንኖችንም አላውቃቸውም ነበር። እና በምን ታዓምር ነው ልመሰክርባቸው የምችለው። ግን ያልሆነውና የማላውቀውን ነገር እንድናገር ብዙ ነገር ነው ያደረጉኝ። ሶስት ወር ሙሉ አንድም ቀን ጸሃይ ሞቄ አላውቅም፤ በጣም አነስተኛ ቀዳዳ ባላትና በጣም ጠባብ በሆነች ክፍል ውስጥ ሆኔ ምግብ ከሚያቀርብልኝ ወታደር በስተቀር ሰው አይቼም አላውቅም። ሌላው ቢቀር ከጎኔ የታሰሩትን ሰዎች አላውቃቸውም ነበር። መፀዳጃ እንኳን የምሄደው ሰው ከተኛ በኋላ ነው። ይህም ካልሆነ ክፍሌ ውስጥ ባልዲ ያመጡልኛል። እሱንም ደግሞ አንዳንድ ቀን አያወጡልኝም ነበር። ስለዚህ እንዳይሸተኝ አንድ እስር ቤት የተማርኩት ዘዴ የጥርስ ሳሙና በጥብጦ እዛ ውስጥ መጨመር ነበር። በዚህ መልኩ ሽታውን ለመቀነስ እሞክር ነበር። በአጠቃላይ ያደረጉኝን ሁሉ መናገር አልፈልግም፤ ምክንያቱም ያመኛል። እኩይ የሆኑ ሰዎች የተሰበሰቡበት ቦታ መሆኑን ግን መግለፅ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁንስ ፓለቲካ ውስጥ የመግባት ፍላጎቱ አለህ? አርቲስት ደበበ፡- አልገባም፤ አባል አልሆንም፤ ግን ፖለቲካው የእኔም መብት በመሆኑ ያለበትን ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ። አዲስ ዘመን፡- በሚቀጥለው ጊዜ በኪነጥበብ ስራዎች ዙሪያ ደግመን እንገናኛለን፤ ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ ስም አመሰግንሃለሁ። አርቲስት ደበበ፡- እኔም እዚህ ድርስ መጥታችሁ ከእኔ ጋር ቆይታ በማድረጋችሁ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት23/2011
በማህሌት አብዱል