መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ጉዳይ ዛሬ ከበይነ መረብና ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትና መጎልበት ጋር ተያይዞ ወደፊተኛው እረድፍ ቢመጣም ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ያደገና የጎለበተ ቤተኛ ነው። በአገራችን ወሬ ወይም መረጃ ከጦር በላይ ጉልበት እንዳለው የሚያስታውሰው ፤”ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው፤” የሚለው አባባል ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ። ከ2500 ዓመታት በፊት ታዋቂው የጦር ሊቅና ፈላስፋ ሰን ሱ “The art of war” በተሰኘው ዘመን ተሻጋሪ መጽሐፉ ፤ “ጠላትህን ያለ ውጊያ አንበርክክ” ማለቱ የመረጃ ኃያልነት ጥንትም እንደነበረ ያረጋግጣል ። ሆኖም ዓለማችን በሶሻሊስትና በካፒታሊስት ጎራዎች ስትከፈልና ቀዝቃዛው ጦርነት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሲዘልቅ ጦርነቱ በታንክ ፣ በጦር ጀት ፣ በቢኤም ወይም በመድፍ ሳይሆን በፕሮፓጋንዳ ፣ በርዕዮተ ዓለምና በመረጃ ነበር የተካሄደው ።
ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የምትዘውረው ጎራ በአሸናፊነት ቢወጣም በዘመነ በይነ መረብና ማሕበራዊ ሚዲያ አሰላለፉን ቀይሮ እንደ አዲስ ተከስቷል ። ሕልውናዋ በአሜሪካና በሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አደጋ እንደተደቀነባት የምታምነው ሩሲያ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙን ተክናበታለች ። እንደ ሕልውና ስጋት የምትቆጥራቸውን ሉላዊነት (Globalization ) ፣ የአውሮፓ ሕብረትና ኔቶን ከሚገዳደሩ አጋጣሚዎች ጎን ተሰልፋ ግዳይ ጥላላች ። የእንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት ሕብረቱን ያዳክመዋል ብላ ስለምታምን መነጠሉን ከሚያቀነቅነው ወግ አጥባቂ ቲዮሪ (Conservative ) ፓርቲ ጎን በሕዕቡ ቆማለች ፤ ሕብረቱን ከሚጠሉ የምዕራባውያን ሕዝበኛ (Populist) ፓርቲዎች ፤ ከአሜሪካ እሴቶች በተቃራኒው ቆመው የነበሩትን ኔቶንና ሕብረቱን ጠል ዶናልድ ትራምፕ ጎን በመቆም የ2016ቱን ምርጫ ውጤት እስከ መበየን ደርሳለች ።
የአሜሪካውን የ2020 ምርጫም በተመሳሳይ መንገድ ለመጫን ሞክራለች ። ዛሬም አሜሪካውያንን በዘር ለመከፋፈል ፤ በዴሞክራሲያዊና በመንግሥት ተቋማት እምነት እንዳይኖራቸው እስከ ማድረግ ደርሳለች ። የትራምፕ ደጋፊዎች የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ከማለት አልፈው እንደ የአሜሪካ የዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚታየውን ካፒቶል ሒል እስከ ማጥቃት ደርሰዋል። አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራባውያን የደህንነት ፣ የጸጥታና ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን የመረጃ ቋት በመስበር መረጃ በመበርበርና በመዝረፍ እየተከሰሰችና እየተወነጀለች ትገኛለች ። ሩሲያ ግን እንደ ሁልጊዜው በማስተባበሉ ገፍታበታለች ። ወደ ከሀዲው ትህነግ ሰሞነኛ የፕሮፓጋንዳና የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ ስንመጣ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን ጥርሱን ነቅሎበታል ቢባል ማጋነን አይሆንም ።
መረጃን የጦር መሳሪያ ማድረግ ፤ መረጃን እንደ ጉዳት ማድረሻ ፣ እንደ ግብ መምቻ መሳሪያ የመጠቀም ሒደት ነው ። ጥቃቱን የሚፈጽመው አካል እውቀትን፣ አስተሳሰብንና አመለካከትን ኢላማ አድርጎ በመስራት ስውር ዓላማን ዳር የማድረስ ሴራ ነው ። ፕሮፓጋንዳን ፣ የሴራ ኀልዮትን ፣ ማሕበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሀሰተኛ ወይም ሆን ተብሎ የተዛባና ሀሰተኛ መረጃን መንዛት እና እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም አውደ ውጊያ ነው። ከፍ ሲልም ኮምፒዩተርን ሰርስሮ መረጃን መመንተፍንና ከጥቅም ውጭ ማድረግን ያካትታል ።
መረጃ እንደ ጦር መሳሪያ ያገለግል ዘንድ ተደራሲና ታዳሚ ያስፈልገዋል። ለዛውም አንብቦ ፣ አድምጦና ተመልክቶ ለታለመለት ድርጊት የሚቀባበልና የሚተኮስ። ለሰሞነኛው የትህነግ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ዘመቻ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ፣ ዓለምአቀፉ ሚዲያና ምዕራባውያን እንደ ጠብ መንጃ ቃታ በሀሰተኛ መረጃ ተቀባብለው ተተኩሰዋል ። በዚህ የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዘው የተለያየ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀሳቸው ዘመቻው ጊዜያዊ “ድል” እንዳስመዘገበ አንዱ ማሳያ ነው ።
ላለፉት ሶስት ዓመታት በተለይ ደግሞ ሰሞኑን እነ CNN BBC FRANCE 24 AP ALJAZEERA REUTERS BLOOMBERG The Economist New York Times Guardian ወዘተረፈ አዲስ አበባ በአሸባሪው ሕወሓትና በእነ ኦነግ ሸኔ እንደተከበበች ውዥንብር በመንዛት የኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና ለመስለብ ፤ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ የሆኑ አህጉራዊ ዓለምአቀፋዊ ተቋማት የዲፕሎማሲው ማሕበረሰብ አባላት ከአዲስ አበባ ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ሽብር ለመንዛት ያልተሳካ ጥረት አድርገዋል ።
ይህ አልበቃ ብሎ በፌስቡክ በዩቲውብ በቲዊተርና በሌሎች ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ድምጽ እንዳይሰማ ጫና ማድረግና እንቅፋት መሆን ጀምረዋል። ከአገራቸውና ከመንግሥታቸው ጎን የቆሙ አንቂዎችና ተሟጋቾች ቲዊተር ፌስቡክ ዩቲውብ ድረ ገጾችና ሌሎች ማሕበራዊ መድረኮች እንዲወርዱና እንዲዘጉ እየተደረገ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ መልዕክት ከፌስቡክ ተነስቷል። ለዚህ ነው ድምጻችንን የምናሰማበት የራሳችን የሆነ መደበኛ ዓለምአቀፍ ሚዲያ እና ማሕበራዊ ሚዲያዎችን ከሌሎች ወንድም የአፍሪካ አገራት ጋር ለማቋቋም አበክረን መንቀሳቀስና ከምዕራባውያን የሚዲያ ጥገኝነት ነጻ መውጣት ግድ የሚለው ።
በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ፋና ወጊ በመሆን ለነጻነት ካበቃቻቸው አገራት አንዷ የሆነችው ዛምቢያ ካለምንም ማጋነን ከዋና ከተማዋ ሉሳካ በአስር እጥፍ የተረጋጋችውን አዲስ አበባ በሀሰተኛ መረጃ የተነዛን ሟርት በማመን እንደ ስጋት በማየት የኤምባሲዋን አባላት ከአዲስ አበባ ለቀው እንዲወጡ አድርጋለች ። ለዚህ ወረታዋ ይመስላል ከጋላቢዋ አሜሪካ የ30 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ያገኘችው። ኬነት ካውንዳን በመሰለ የአፍሪካ ኩራት በሆነ መሪ ስትተዳደር የነበረች ዛምቢያ ሀኪያንዴ ሒቺሌማ በሚባል የእነ አሜሪካ ተላላኪ እጅ መውደቋ በፓን አፍሪካኒዝም እንደሚያምን ኢትዮጵያዊ በጣም አሳዝኖኛል ።
ይሄን መጣጥፍ እየጫጫርሁ ሳለ በግብጽ ሳንባ የምትተነፍሰው ሱዳንም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት መፈንቅለ መንግሥት ማስተናገዷንና ካርቱምን ጨምሮ ጎዳናዎቿ በሕዝባዊ አመጽ መናጣቸውን ዘንግታ የዛምቢያን መንገድ ለመከተል መወሰኗን ስሰማ መንገዱ ጨርቅ ያርግልሽ ብያለሁ። በሱዳን ከጀርባ መወጋትና መከዳት ዛሬ ስላልተጀመረ አይደንቅም ። የእኛዋ አዲስማ ከካርቱም ከጌታዋ የፈርኦን ከተማ ካይሮ በላይ ሰላሟ የተረጋገጠ ነው ።
አሸባሪው ሕወሓትና ጋላቢዎቹ የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰቡም ሆነ ሌላው የውጭ ሀገር ዜጋ እነሱ በተመኙትና በሸፈጡት ልክ ከአዲስ አበባ አልወጣ ሲላቸው የሽብር ሀይሉ ከኢትዮጵያ ጋር የሚሰራ የውጭ ሀገር ዜጋ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር የሚያስጠነቅቅ መግለጫ ባለፈው ሀሙስ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን በአሸባሪነት እንደፈረጀው ግብሩ እንዲህ ጮሆ እየተናገረ ነው ። ሆኖም የተወሰኑ አፍሪካውያን ዛሬም ከዚያ ሁሉ ህልቆ መሳፍርት ከሌለው የምዕራባውያን ሸፍጥና ሴራ በኋላም በጉዳይ አስፈጻሚነት ሲንቀሳቀሱ ማየት ያሳፍራል።
ሌላው ሁል ጊዜ እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ አሜሪካ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ እየተናጠች እና ዋጋ እየከፈለች የዲጂታል ወያኔ ሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ ሰለባና መጠቀሚያ መሆኗ ለማመን የሚቸግር ወለፈንዲ ነገር ነው ።
ይባስ ብላ እንደ CNN ባሉ ሚዲያዎቿና በዓለምአቀፍ ተቋማቷ ኢትዮጵያንና መንግሥቷን በሀሰተኛ መረጃ ለማጠልሸት በግልጽ ከአሸባሪው ሕወሓት ጎን መቆሟ የሁለቱ አገራትን የቆየ ወዳጅነት አደጋ ላይ ጥሎታል። የባይደን አስተዳደርም ሀሰተኛ ፣ ሆን ተብሎ የተዛባንና የተሳሳተ መረጃን እያፈራረቀና በአንድ ላይ እየተጠቀመ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተናበበና ተልዕኮ እየተለዋወጠ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ጦርነቱን እያካሄደብን ነው።
እንደ መውጫ
በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነት ሥራው ዳተኛና ደካማ መሆናችን ፍትሕንና እውነትን ይዘን ተከላካይ ሆነናል። ውሸትን ፣ ሆን ተብሎ የተዛባንና የተሳሳተ መረጃ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የከሀዲው ትህነግ ርዝራዥና ዲያስፖራ ጭፍራ ጊዜያዊ ድል አስመዝግቧል። ዓለምአቀፍ ማሕበረሰቡን ፣ ሚዲያውንና ምዕራባውያንን አሳስተው ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል ። ምንም እንኳ አንድ ጊዜ የጎደፈን ስም የጠለሸን ገጽታ ለማደስ አስቸጋሪ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እውነቱ ሲታወቅ በተወሰነ ደረጃ መስተካከሉ አይቀርም ።
ሰሞነኛው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመንግሥታቱ ድርጅት የጋራ ሪፖርት በ16 አገራት ተቀባይነት ማግኘቱ ፤ አመነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው እሮብ አሸባሪው ሕወሓት በወረራ ይዟቸው በነበረ አካባቢዎች በቡድን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የፈጸማቸውን ዘግናኝ ግፎች ቆንጦሮ ማሳየቱ ፤ አፍሪካውያን እህት ወንድሞቻችንና ሌሎች እንደ ቦብ ሼልቨር ያሉ የውጭ ዜጎች በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በዋሽንግተን ዲሲ በቀጣይ በሎስ አንጀለስ ፣ በላስቬጋስ፣ በብራስልስ ፣ በጄኔቫ ፣ በካናዳ ፣ በለንደን ፣ በፓሪስ፣ በበርሊን ፣ ወዘተረፈ የሚካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች የፖለቲካዊ ዲፕሎማሲው ነፍስ አድንና ወሳኝ መታጠፊያ ናቸው ።
ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣይ ግን ዲፕሎማሲውና የመረጃ ተደራሽነቱ ፍጹም ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል። ሚዲያዎቻችን ከአረጠ ጋዜጠኝነት ማለትም ሁነት ፣ ስብሰባ ፣ ፕሮቶኮልና አኃዝ ከማሳደድ ወጥተው አጀንዳ ቀራጭ ፣ ተንታኝና ተርጓሚ ሆነው ከፊት በመሆን አገርንና ሕዝብን መምራት ይጠበቅባቸዋል። አድማጭ ተመልካች የሚፈልገውን ከማቅረብ ይልቅ የሚገባውን ማቀበል ያሻል። ገና ድራማ ስፖርትና ሙዚቃ ይወዳል ተብሎ አየር ሰዓቱ በእነሱ መያዝና መሞላት የለበትም። ከፊት ሆኖ መምራት ያለበት አድማጭ ፣ ተመልካችና አንባቢ ሳይሆን ሚዲያው ነው።
በተለይ እንደ ኢቲቪ ያለ የሕዝብ ቴሌቪዥን ጭራ ሳይሆን መሪ ነው መሆን ያለበት ። ህጸጽን የሚያርም ፣ የተንጋደደ ሃሳብን የሚያርቅና ሕዝብንና እውነትን የሚያስቀድም ሊሆን ይገባል። እንደ ኢቲቪ ፣ ኢዜአና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሉት ደግሞ መረጃን የሚያበጥሩበት ፣ የሚያጠሩበትና የሚያረጋግጡበት ራሱን የቻለ የ (fact cheker) አደረጃጀትና አሰራር እንዲዘረጉ ዘመኑ ያስገድዳል ። ከሁሉም በላይ ተናበውና ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ። ከዚህ ጎን ለጎን ዜጋው ስለሚዲያ አጠቃቀምና አመራረጥ ግንዛቤ (media literacy ) እንዲኖረውና እንክርዳዱን ከስንዴው የመለየት አቅም እንዲያጎለብት አበክሮ መስራት ይጠይቃል ።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በእውነተኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014