ወቅታዊው የሀገራችን የጦርነት ተጋድሎ ለየት ባሉ ቀለማት እየተጻፈ ያለ ይመስላል፡፡ እንዴታውን ላብራራ፡፡ ቀደምት የታሪኮቻችን ውርሶች ሲተረኩልን የኖሩትና ተመዝገበው የተላለፉልን በአብዛኛው በተመሳሳይ ባህርያትና አካሄድ እየተገለጹልን ነው። በጥቂቱ ጨልፈን እናስታውስ። የትኛውም ወራሪ ጠላት ድንበራችንን በጀብደኝነት ጥሶ “ሆ!” እያለ ገስግሶ ሲመጣ ጀግኖቹ አበውና እመው በጋለ ወኔ እየለበለቡ አንገቱን በማስደፋት ሲመልሱት መኖራቸው ለእኛ እንግዳ አይደለም፡፡ ክስተቱም በሺህ ዘመናት ውስጥ ሲፈጸም የኖረ “ሀገራዊ የጦርነቶቻችን የድል ባህል” ስለሆነ አስታዋሽ አያስፈልገውም፡፡
ጠላት የቱንም ያህል ግንባር ፈጥሮና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ተደራጅቶና ተኩራርቶ ቢመጣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ይፋለሙት የነበረው ጽኑ የኢትዮጵያዊነትን ዕቃ ጦር፣ የሚንበለበል የእምነት ሰይፍ፣ በነፃነት ክብር የበረታ “የራስ ቁር” በመታጠቅ ነበር፡፡ ለአካላዊ መፋለሚያ ሲያገለግሉ የኖሩት ሳንጃና ጦር፣ ጎራዴና ጋሻ፣ አረርና መድፍ የሚጠቀሱት በሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ የነባሩ ታሪካችንን የድል በድል ምሥጢር አድምቆ በክብር እንዲተላለፍልን ምክንያት የሆነው ዋነኛው ተጠቃሽ የጀግንነት ምሥጢር ይህ ነበር፡፡
መሠረታዊው እውነታ ይህን ይምሰል እንጂ በሀገራዊ የድሎቻችን ትረካ መካከል ለጠላት ያደሩ “ሆድ ተኮር” ከሀዲዎችና ባንዳዎች የጀርባ አጥቂ ጠላቶች አልነበሩም ማለት ግን አይደለም፡፡ በፍጹም። በጥቁር ጥብጣብ እየተከበበ እኩይ ድርጊታቸው በተጋድሎ ታሪኮቻችን ውስጥ ለዘለዓለም እንደ ጠቆረ ሲዘከር የሚኖረው አንዳች እርባና ስላለው ሳይሆን በግፍ የተጨማለቀው እጃቸው በትውልዶች ቅብብሎሽ መካከል ማስተማሪያ መሆን ስላለበት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ተጠቃሽ የጦር ሜዳ ውሎ ታሪክ ያለን አይመስልም፡፡
ዛሬ የተከፈተብን የጦርነትና የክህደት ክስተት ግን በባህርይውና በዓይነቱ ከቀደምት ታሪኮች የተለየ ነው የምንለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ እንኳንስ በነባሮቹ ታሪኮቻችን ውስጥ መፈጸሙን ለማስታወስ ቀርቶ በሌሎች ሀገራት የታሪክ መዛግብት ውስጥም ተፈልጎ ስለመገኘቱ እርግጠኛ ለመሆን ያዳግታል፡፡ እንዴታው ብዙ ቢያጽፍም አንዳንዱን የቅርብ ወራት የክህደት ዓይነት እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡
በአንድ የሉዓላዊነት ጥላ ሥር የተጠለለና “ለአንድ ክልል ሕዝብ ህጋዊ ውክልና ባለቤቱ እኔ ብቻ ነኝ” እያለ የሚያቅራራው ቡድን፣ ለሦስት አሠርት ዓመታት ያህል በፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን ሲፏልል የነበረ “ገዢ” ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን የመምራት፣ የማሠማራትና የመቆጣጠር ኃይልና ሥልጣን ጨብጦ የነበረና እንዳሻው የኢኮኖሚውንና የዲፕሎማሲውን መዘውር ጨብጦ “በስመ የመንግሥት መሪነት” ሲፋንን የኖረው የጥቂቶች ስብስብ ሲፈጽማቸው የኖረውን የክፋት ድርጊቶች መዘርዘሩ ለቀባሪ የማርዳትን ብሂል ያስታውሰናል፡፡
እንደ ባዕድ ኃይል በታላቋ ኢትዮጵያ ላይ የጥፋት ወረራ መፈጸሙም በታሪካችን ታይቶ የማያውቅ አዲስ ክስተት ነው ለመባል ቢያንስ እንጂ አይበዛትም፡፡ ያስተዳደራትን ሀገር ለማፈራረስ እየዛተ በአደባባይና በግላጭ በመሃላ ጭምር ሲያረጋግጥ አልፈራም ወይንም አላፈረም፡፡ የመራውን ሠራዊት ክህደት ፈጽሞበት ማዋረዱን የሚያውጀውም ታላቅ ጀብድ እንደፈጸመ ኃይል ራሱን በመቁጠር ነው፡፡
በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ንፁሐንን መጨፍጨፉ፣ ማፈናቀሉና ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸሙን በአደባባይ የሚተርከው የጽድቅ ያህል እየተመጻደቀ ነው፡፡ የግለሰቦችን፣ የተቋማትንና የሀገርን ሀብት ማውደሙና መዘርፉ ለእርሱና ለጀሌዎቹ የድላቸው ብሥራት አንዱ መገለጫ ነው። እኒህን መሰል የክፋት ድርጊቶቹን በቋንቋ ውስንነት ምክንያት በሚገባ ለመግለጽ በእጅጉ ይፈታተናል፡፡ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው በየትኛው ዘመንና በየትኞቹ ሀገራት ተፈጽሞ እንደነበር ለመመስከርም እንኳንስ ለእኛ ለተራ ዜጎች ቀርቶ ለታሪክ ተመራማሪ ምሁራንም ሳይቀር “ድፍን ዕንቁላል” ሆኖባቸው ግርምት ላይ ሳይጥላቸው እንደማይቀር እንገምታለን፡፡
ሌላውና የተለየው የዚህ እኩይ ቡድን የወረራ ስትራቴጂ የሚመራው በራሱ የጦር ጥማተኛ አበጋዞች ብቻ ሳይሆን በበርካታ ባዕዳን ሀገራት ሙሉ ድጋፍ ጭምር መሆኑ የዕንቆቅልሹን ክብደት አግዝፎታል፡፡ እጅግ የሚገርመው ደግሞ ተባባሪዎቹና ተሰላፊዎቹ የጎረቤት ሀገራት እሳት ጫሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በሺህዎች ማይል ርቀት ላይ የሚገኙና ባህርና የብስ በመካከላችን ገደብ የጣለባቸው “ስልጡንና የዲሞክራሲ ጠበቆች እኛ ብቻ ነን” የሚሉት አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት መሆናቸው ይበልጥ ለግርምት የሚዳርግ ነው፡፡ የየሀገራቱ ትውልዶችና ታሪክ ወደፊት ሴራው ተገላልጦ ይፋ ሲወጣ ምን ብለው ሲዘክሩት እንደሚኖሩ ለመተንበይ ግራ ያጋባል። ቢያንስ ቢያንስ ግን ከኩነኔ በስተቀር “አበጃችሁ!” ብሎ የሚያጨበጭብላቸው ዜጋ እንደማይኖራቸው ለማመን አይከበድም፡፡
የጦርነቱን ዙር አክርረው ኢትዮጵያ “እንድትበታተን” ለወራሪው የህወሓት ስብስብ በተለያዩ መልኮች አለኝታነታቸውን በመግለጽ ላይ ያሉት እነዚህ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ በእነርሱ የሚዘወሩት “የሰብዓዊ መብት ጠባቂና ጠበቆች ነን” የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና “የስንዴ ቀለብ ካልሰፈርንላችሁ” የሚሉ በተራድኦ ስም የሚንቀሳቀሱ አካላት ጭምር ናቸው፡፡
ስማቸው ገዝፎ ተግባራቸው የኮሰመነው የዓለማችን ግዙፍ የሚዲያ ተቋማትም ለአሸባሪው ቡድን በግላጭና በይፋ የውሸት አንደበቱ ማስተጋቢያ አፈ ቀላጤዎች መሆናቸው በእጅጉ ከማስገረም አልፎ እጅን በአፍ ላይ ያስጭናል፡፡ ምናልባትም የባንዳነት ትርጉሙ ከሀገራዊ ዐውድ ከፍ ብሎ ዓለማቀፋዊ ፍቺ መያዝ ካለበት እነዚህን መሰል ከሰብዓዊነትና ከኅሊናቸው ጋር የተጣሉ አካላትን ማካተት እንደሚኖርበት እናምናለን፡፡
ኢትዮጵያን የከበባት የጦርነት ደመና ጠቁሮና ከብዶ በተቻለ ፍጥነት በአሸናፊነት እንዳትወጣ ምክንያት የሆኑት እነዚህን የመሳሰሉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ናቸው፡፡ በዐውደ ግንባሮችና በየጓዳው በማሴርም ባለ በሌለ ኃይላቸው እየተፋለሙን እንዳሉ ዕለት በዕለት እያስተዋልን ነው፡፡ በብዙ ማስረጃዎች እየተረጋገጠ ስለሆነም በነገው የታሪካችን ገበታ ላይ ተገቢውን ስፍራ እየተሰጠው ነው፡፡
ይህ ሁሉ የግፍ ወጨፎ ሀገሬን ያንገላታ ይምሰል እንጂ ያለምንም ጥርጥር አሸናፊዋ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ናቸው፡፡ የመከራ ጉም ይዋል ይደር እንጂ እያደር መቅለሉ ስለማይቀር ድሉ በቅርቡ እውን ሆኖ የሕዝባችን የሃሌሉያ ዝማሬ አየሩን እንደሚያውድ ኢምንት ጥርጣሬ አይኖረንም፡፡
ነጋችን እንዲሰምር ዛሬ ላይ እንምከር፤
ህወሓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወድቆ አፈር እንደሚልስ ምንም አያጠራጥርም፡፡ አዋራውን ልሶ ዳግም እንዳያንሰራራም አናቱ መቆረጥ ስለጀመረ ተዝረክርኮና ተበታትኖ በመክሰም ላይ ነው፡፡ እየባነነና እየተሹለከለከም ቢሆን ቀሪ ዘመኑን በመሳቀቅ ሊገፋ የሚችለው ጄሌውና ወዶ ገቡ ትርፍራፊ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህም እየተቀጠቀጠ ወደ ሙታን ጉባዔ በሚነዳው ወራሪና አሸባሪ ጉዳይ ላይ ጊዜንና ጉልበትን ከማባከን ይልቅ ስለ ነገው የድል ማግሥት ከወዲሁ ዝግጅት ቢጀመር የሚሻል እንደሆነ የጸሐፊው እምነት ስለሆነ ትኩረታችንን እርሱ ላይ ማድረጉ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ “በጦርነት ላይ ሆነን እንዴት ስለ ድል ማግሥት እንጨነቃለን?” ለሚሉ ወገኖች በየዋህነታቸው እናዝንላቸው ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
በድል ማግሥት በዋነኛነትና በተቀዳሚነት ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ብሔራዊ የሥነ ልቦና ተሐድሶ ስትራቴጂ ነድፎ መዘጋጀቱ ይዋል ይደር የማይባል የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ከመስዋዕትነቱና ከሀብት ውድመቱ ባልተናነሰ ወረራው ያናጋውና ያቆሰለው በርካታ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ጭምር ነው፡፡
በዐውደ ውጊያው የተሰዉ የጀግኖቻችን ቤተሰቦች ጉዳይ ከወዲሁ ሊታሰበብት ግድ ይሏል፡፡ ልጆቻቸው፣ የትዳር አጋሮቻቸውና መላው ቤተሰባቸው ስለሚጽናናበት ሁኔታም ከወዲሁ ዝግጅት ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህ የቤት ሥራ የመንግሥት ግዴታ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል፡፡
ሥነ ልቦናቸው የተቃወሰ፣ ሀብታቸው የተዘረፈና የወደመ፣ በገፍና በግፍ የተገደሉና የቆሰሉ ወገኖቻችን ቤተሰቦች በሙሉ የተሰበረው መንፈሳቸው ስለሚጠገንበት ሁኔታ በሚገባ ሊታሰብበት የሚገባው ዛሬ ነው፡፡ ይህ ሥራ ለነገ የሚሸጋገር መሆን የለበትም። ከእርሻው፣ ከንግዱ ወይንም ከመንግሥት ተቋማት መደበኛ ስራው “እምቢኝ ለሀገሬና ለክብሬ” ብሎ የዘመተው ጀግና ተመልሶ ወደ መደበኛ ስራው ለመሰማራት ጊዜና ተሃድሶ ያስፈልገዋል፡፡ ሌላው የድህረ ድል ሀገራዊ የቤት ሥራችን አንዱ ኃላፊነት ይህ ስለሆነ በአተገባበሩ ላይ ከወዲሁ መመካከር መጀመር ይኖርብናል፡፡
“የራሴ” የሚላቸው እኩያን ልጆቹ በጫሩት ጦርነት ምክንያት ንፁሐንን የሰዋው፣ ንብረቱ የወደመበትና በፍቃዱም ሀብቱንና ልጆቹን ለወረራ የገበረውና በሥነ ልቦናው ላይ ከፍተኛ ቁስለት ሲደርስ ልጆቹን ከመገሰጽ ይልቅ በዝምታ እየቆዘመ ያለው አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ፈቃደኛ ከሆነ ራሱን ለተሃድሶ ከወዲሁ ማዘጋጀት ያለበት ይመስለናል። ደም ካቃቡት ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋርም ቁርሾው እንዲጠግግ አጥብቆ ሊያስብበት ይገባል፡፡
የክልሉ የእምነት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ጨክነው ስለ ዘላቂው አብሮነት ቢመክሩ አይከፋም፡፡ በማእከላዊ መንግሥት በኩልም ጥበብ የታከለበት ስልት ሊቀየስ ይገባል ባይ ነን። ይህ የቤት ስራ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ስለሚችል ምክክሩና ዕቅዱ ምናልባትም ረዘም ያሉ ጊዜያት ሊወስድ ስለሚችል ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላው የድል ማግሥት ፈተና በመንግሥት አማካይነት ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው ዕውቅናና ሽልማቶች ጋር የሚያያዝ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም፡፡ ምንም እንኳን ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት መክፈል የዜጎች ሁሉ ግዴታ መሆኑ ባይካድም ለሀገር ለተከፈለ የደምና የላብ ክብር ጀግኖችንና የክፉ ቀን ፈጥኖ ደራሽ ዜጎችን ከጦርነት ማግሥት ማመስገን ያለና የነበረ ባህል ነው፡፡ ጀግናን በአደባባይ ማመስገን፣ በተለያዩ ዘርፎች ለሀገራዊ ድሎች መገኘት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለውለታዎች ዕውቅና መስጠቱ ተገቢ ስለሆነ ከወዲሁ ሃሳቡን ማብላላቱ ክፋት ያለው አይመስልም፡፡
ምናልባትም ዕውቅናና ሽልማቱ ሲተገበር፤ ምንም እንኳን ሁሉንም ሊያረካ ይችላል ተብሎ ባይገመትም፤ ከወዲሁ መዘጋጀቱ ግን ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር ጉዳት የለውም፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በሀገራችን የተፈጸሙ አንዳንድ ማስተማሪያ ክስተቶችን ፈትሾ ትምህርት መውሰዱ ብልህነት ነው፡፡ ለመነሻ እንዲያግዝ አንድ የሀገራችንን የጦርነት ማግሥት ተግዳሮት እናስታውስ፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ድል ተመትቶ በተባረረ ማግሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በጦርነቱ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ለነበራቸው አርበኞችና ዜጎች ሜዳሊያና ሽልማት ስለሚሰጥበት ሁኔታ ተጠንቶ እንዲቀርብላቸው “የእኔ ለሚሏቸው” ሹማምንት ኃላፊነቱን ሰጥተው እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ሥራው በአጭር ጊዜ ተሰርቶ ወደ ትግበራ ሊገባ ሲል ያልተጠበቀ አደገኛ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡
አጥኚዎቹ ተመስጋኞቹንና ተሸላሚዎቹን ያቀረቡት ከአንድ እስከ ሦስት በደረጃ መድበው ነበር። በአንደኛ ደረጃ ተሸላሚ እንዲሆኑ የተመረጡት ንጉሡና ከእርሳቸው ጋር በስደት የኖሩት ሹማምንት ሲሆኑ፤ በሁለተኛነት ደግሞ በጦር ሜዳ ፍልሚያው ለሕይወታቸው ሳይሳሱ የተሰለፉትና ለድሉ መገኘት ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ዋነኞቹ አርበኞች ነበሩ። በሦስተኛነት ደግሞ በውስጥ አርበኝነት ያገለገሉ ዜጎች ተመደቡ፡፡
ይህ ምደባ በተለይም ዋናዎቹን አርበኞች እጅግ አበሳጭቶ “ስደተኞቹ” እንዴት ተቀዳሚ ጀግኖች ሊሆኑ በቁ የሚል አመጽ ተቀሰቀሰ፡፡ ይህንን ያስተዋሉት ንጉሡ ቅደም ተከተሉ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ተደርጎ ዋናዎቹ አርበኞች ተቀዳሚ፣ “ስደተኞቹ” ተከታይ፣ ሦስተኞቹ እንደነበሩ ሆነው እንዲሸለሙ በመወሰኑ የተቀጣጠለው አመጽ በቀላሉ ሊረግብ እንደቻለ ታሪክ ያስታውሰናል፡፡
“እኛስ ከማን አንስን” ያሉ ባንዳዎችም ተቀላቅለው ገብተው ትልቅ ሀገራዊ ስህተት እንደተፈጸመ በበርካታ የታሪክ ሰነዶች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ “ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ…” እንጉርጉሮ የተዜመው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ከአሸባሪዎቹ ጋር የተካሄደው ጦርነት ተጠናቆ ድሉ ሲዘመር ሊፈጸሙ የሚችሉ መሰል ስህተቶች እንዳይስተዋሉ ከወዲሁ ይህንን ታሪክ ማስታወሱ ሊጠቅም ይችላል፡፡
በብቃት ሳይሆን “በእከክልኝ ልክክልህ” ሲፈጸሙ እያየናቸው ያሉ ዓይን ያወጡ መጠቃቀሞች በድል ማግሥትም በተዘረጋው ቻናል እየፈሰሱ ሕዝቡን እንዳያስቀይሙ በእጅጉ ሊመከርበትና ሊዘከርበት ይገባል፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን፣ የዲፕሎማሲ አገነባባችን፣ የሚዲያ አደረጃጀታችን ወዘተ. ሁሉ ጥሞናን ሰብስቦ ሥር ነቀል ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ በስተቀር ወረራውን ቀልብሰን ድል ሲዘመር ነገሮች ባሉበት እንዲሄዱ መፍቀድ ሌላ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ የድሉን ማግሥት በጥንቃቄ ልንቀበለው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ያለጥርጥር ታሸንፋለች፡፡
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014