የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብዙ አነጋጋሪም አደናጋሪም ጉዳዮችን የተሸከመ ነው፡፡ የቀጣናው አገራት በሃብታቸው ከሚጠቀሙበት በበለጠ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ እጀ ረጃጅሞች የበለጠውን ተጠቃሚ የሆኑበት መሆኑ ዓለም ያወቀው እውነታ ሆኗል፡፡ አብነት ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ 90 ከመቶ የሚሆነውን የዓባይ የውሃ ድርሻ የምትሸፍነው ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች ሆና ምንም የውሃ ድርሻ የሌላት ግብጽ በልጽጋበት የሃብት ማማ ላይ ደርሳለች፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የተፋሰሱ አገራት ጉዳዩ አያገባችሁም ተብለው ተገልለው ኖረዋል፡፡ ከግብፅ ወሰን የለሽ ፍላጎትና ጭካኔ በስተጀርባ ደግሞ ፍትሐዊነትና እኩልነት መገለጫችን ነው የሚሉ አገራት ደግሞ ይህን ኢ-ፍትሐዊ አካሄድ በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡
አሸባሪዎች የሚፈለፈሉበት በሚልም ቀጣናውን የጦር አውድማ ተድርጓል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ሆኖ ሳለ አሸባሪ በሚል ሽፋን በአካባቢው የሚገኘውን ትልቅ ሀብትና የተፈጥሮ ፀጋን ለመቀራመት ያመች ዘንድም የምዕራባውያን የግብረ ሠናይ ድርጅቶች መናኸሪያ ሆኗል፡፡
ቀጣናው በዚህ ብቻ ጫናው የሚያበቃ አይደለም። በተደጋጋሚ የተፈጥሮና አደጋዎች የሚጎበኙት ሲሆን በተለይም ድርቅ ዋንኛ መለያው እስከመሆን ደርሷል፡፡ በዚህም የረድዔት ድርጅቶች በቀጣናው ለመፈንጨት ሰፊ ዕድል አግኝተዋል፡፡
በሌላው ገፅ ቀጣናው 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የያዘ ሲሆን ከበርካታ ቁልፍ የዓለም ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ማዕበልን በሰፊው የሚንጠው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀይ ባህር ከጎረቤት አገር ኤርትራ ተነስቶ በርካታ ዓረብ ሊግ አገራትን በማካለል የበርካቶችን ትኩረት የያዘ ነው፡፡
አካባቢው የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመታደልም የሚስተካከለው ቀጣና የለም የሚባልለት ነው፡፡ የተለያዩ መልክዓ ምድሮች፣ ተስማሚ የሚባል የአየር ፀባይና በተፈጥሮ ሚዛን በብዙ መንገድ የሚፈልግ ነው፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን የዓለም ዋነኛ የንግድ መስመሮች መገኛ ብሎም የሌሎች የንግድ መስመሮችን ለማገናኛትም የሚስተካከለውም ሆነ የሚገዳደረው መስመር የለም። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ኃያላን የሚባሉ አገራት የጦር ሰፈራቸውን በስፋትና በብዛት የመሰረቱበት ቀጣና ነው ። ይህም ምሥራቅ አፍሪካ ለዓለም ፖለቲካ ያለውን ቅርበትና አስፈላጊነት በሚገባ የሚያሳይ ነው፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በብዙ ስሌቶች የዓለም ፖለቲካ መቀየር ዕድሉ ሰፊ ስለመሆኑም በታሪክ ውስጥ ያለፉትን ክስተቶችንም ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ በዓለም ላይ ጎልተው በተፃፉ ታሪኮች ውስጥም ምሥራቅ አፍሪካ በደማቁ ያልተፃፈበት መጽሐፍ ወይንም ትንታኔዎችን አለማግኘት አይቻልም፡፡
ታዲያ በዚህ ቀጣና የበላይ ለመሆን የዓለም ኃያላን አገራት ትኩረታቸው ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ በቀጭን ትዕዛዝ ቀጣናውን ማናወጥ ይፈልጋሉ፤ ይሞክራሉም ሞክረውም የተሳካላቸው ክስተቶች አሉ፡፡ ሶማሊያን ያልተረጋጋች አገር ለዓመታትም መንግስት አልባ አድርገው አስቀምጠዋታል፡፡ በጎሳ ተቧድነውም እርስ በእርስ እየተጠዛጠዙ እንዲቀጥሉም ጠባሳ አሳርፈው ሴራቸውን ጎንጉነው ከዳር ሆነው እየተሳለቁ ነው፡፡
ኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀብ በመጣል እንዳሰቡት የተሳካላቸው ባይሆንም በኢኮኖሚ የተዳከመች አገር አድርገዋታል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአጎራባች አገራት ጋር ሰላም እንዳትፈጥር አጀንዳ ሰጥተው ሲንጧት ቆይተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ጋርም በጎሪጥ ይተያዩ ዘንድ ሴራ ጎንጉነው ዛሬም ድረስ ከዚያ ጉስቁልና እንዳትወጣ አድርገዋታል፤ ከኢትዮጵያ ጋር ከፈጠረችው መልካም ግንኙነት በስተቀር፡፡
ሱዳን በመከፋፈል አንድ የነበረ አገርን ሁለት ሕዝብ ሁለት አገር የተለያዩ አስተሳሰብ የነገሰበት አገር ፈጥረው ነጋ ጠባ በአፈ-ሙዝ እየተፋለሙ ይገኛሉ። ታዲያ ካርቱም ሆነች ጁባ አንድም ቀን ንጹህ አየር መተንፈስ ያቃታቸው ዜጎቻቸውን ይዘው ከድጡ ወደ ማጡ እየተጓዙ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋነኛ መነሻ እና የፀቡ ጠንሳሽ ሁለቱ ሱዳኖች ፈልገው ያመጡት ሳይሆን ምዕራባውያን ሃብት ለመቀራመትና ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት በማሰብ የመጣ ነው፡፡ ዑጋንዳንም ቢሆን ከሚፈልጉት ቅርፅና ተክለ ቁመና በተጨማሪ አንድም ስንዝር ከፍ ወይንም ዝቅ እንዳትል አድርገው ጠፍጥፈው ሰርተዋታል፡፡
የዴሞክራሲ ቁንጮ ነኝ የምትለው አሜሪካና ምዕራባውያን በሚዲያ ዲስኩራቸው እና ዋሾ በሆነ አንደበታቸው በተደጋጋሚ ስለሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ላንቃቸው እስኪላጥ ድረስ ይናገሩ እንጂ እነዚህ አገራት በዓለም ላይ በየትኛውም አቅጣጫ ለሚገኘው ማኅበረሰብ ሰብዓዊነት ወይንም ዴሞክራሲ ተጨንቀው አያውቁም፤ ወደፊትም የሚጨነቁ አለመሆናቸው ለዘመናት ከመጡበትና ከፈጠሩት ትርክትና ታሪክ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በዚህ ተለዋዋጭ ፍላጎትና ውስብስብ ቀጣናዊ ባህሪ በመነሳት ኢትዮጵያ አያሌ የቤት ሥራዎች ይጠበቁባታል። በተለይም ደግሞ ቀጣናውን የጦር አውድማ በማድረግ የግል ፍላጎታቸውን ለማጋበስ የሚንጠራሩ አካላትና አገራትን ፍላጎት ጠንቅቆ መገንዘብና ቢሆኖችን በሙሉ በመገመትና በመተንተን ለምላሹ መዘጋጀት ግድ ይላታል፡፡ በቀጣናው ያላትን አሁናዊ ተሰሚነት በማጉላትም ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ አገር መሆኗን ተፈላጊነቷን በብዙዎች ዘንድ እንዲጨምር መሥራት ግድ ይላታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ዕድገት ቀጣናውን ብሎም አህጉሪቱን በማነቃቃትና በማነሳሳት ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህን እጥፍ ድርብ ኃላፊነት ለመወጣት በትጋት መሥራት ይገባታል። የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም ብቻም ሳይሆን ሌሎች መልካም አጋጣሚዎች የሚፈጠሩበትን ዕድል ማመቻቸትም የኢትዮጵያ ኃላፊነት ነው፡፡ በቀጣናውም አጀንዳ ተቀባይ ከመሆን በማለፍ ለሌሎች አካላት አጀንዳ ሰጪ ሆኖ መቀጠል የሚገባ በመሆኑ ሊታሰብበት የሚገባው አንገብጋቢና በስፋት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ምሥራቅ አፍሪካ በአሁናዊ ገፅታው እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቃሚታው አኳያ በማናቸውም መስፈርት ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ለአብነትም ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ ባለቤት ነች። በርካታ ወንዞቿ ወደ ሁሉም ጎረቤት አገራት ይፈሳሉ፤ ከጎረቤት አገራቱም ጋር በማይነጣጠል ዕድልና የተፈጥሮ ፀጋ የተሳሰረች ናት ።
በአህጉሪቱ ሰላም አስከባሪዎችን በስፋትና በብዛት በማሰማራት ቀዳሚ አገር መሆኗ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር የምንጋራቸው ባህል፣ ቋንቋ ዕምነት መኖሩን በማጤን ትርፍና ኪሣራውን ማስላት ብሎም ለጎረቤት አገራት ሊቀርቡ የሚችሉ በርካታ ትሩፋቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ መሥራት ይኖርባታል ፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ሊያሳድጉ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ በአንክሮ መከታተልና ሁኔታዎችን ፈር ማስያዝ ይጠበቅባታል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ አገርም ሆነ እንደ አህጉር ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉባት አገር ናት ፡፡ ከዚህ የተነሳም ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ፤ ሳይንሳዊ ጥበብን የተላበሰ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርባታል ፡፡ ቀጣናው ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ በሚሉ ተፈጥሯዊ ቀመሮች በማስላት ብቻ የሚመራ ሳይሆን ከዚህ በላቀ መልኩ ትኩረት በመስጠት መሥራት የሚጠይቅ ሁለንተናው ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል ፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው እናትም አናታም ሆኖ መቀጠሏ ተጠባቂና አይቀሬ ነው ። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወቅታዊ ፈተናዎችን በማለፍ ታሪካዊ ድሎችን አስጠብቆና ጠብቆ መሻገር ይጠበቅበታል፡ ፡ በቀጭን ትዕዛዝ ቀጣናውን የሚረብሹትንም ኢትዮጵያ መፈንጫቸው እንዳልሆነች በሚገባ ማሳየት ይገባል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014