የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእነ ጀርመን ጣሊያንና ጃፓን ሽንፈት ፤ በእነ አሜሪካ እንግሊዝ ፈረንሳይ ሶቪየት ሕብረት አሸናፊነት ከተቋጨ በኋላ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዘለቀው የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጎራዎች የርዕዮተ ዓለም ውጊያ ቀረሽ ትንቅንቅ (የቀዝቃዛው ጦርነት) በሶቪየት ሕብረት መፈራረስ በጀርመን መዋሀድ (በበርሊን ግንብ መፍረስ) እንዲጠናቀቅ ካደረጉት አላባውያን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ። ሚዲያው በተለይ ሬዲዮ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን በፊት አውራሪነት መርቷል ።
ከዚያ ወዲህ እንደገና ባገረሸው ቀዝቃዛው ጦርነት በራሽያና በቻይና፣ በምዕራባውያንና በአሜሪካ መካከል መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም (ዌፐናይዝ) ማድረግ በስፋት ይስተዋላል።
ሀሰተኛ አሳሳችና የተዛባ መረጃ አንዱ የሌላውን ገጽታ ለማጠልሸት በመሳሪያነት አገልግሏል። በምዕራባውያንና በአሜሪካ ሚዲያዎች በዓለምአቀፍ ተቋማት በግብጽና በከሀዲውና አሸባሪው ሕወሓት በአገራችን ላይ የተከፈተብን ጦርነት ግን በቅድመም ሆነ በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት ከተስተዋለው የከፋና የመረረ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። ባለፈው አንድ ዓመት በተለይ ደግሞ ሰሞኑን እያወጧቸው ያሉት “ዘገባዎች” ሀሰተኛ (ፌክ) ፣ አሳሳች (ዲስ ኢንፎርሜሽን) እና ሆን ተብሎ የተዛባ (ሚስ ኢንፎርሜሽን) በመባል ብቻ የሚታለፉ ሳይሆን ፤ ምን ነካቸው ? ነካ ያደርጋቸዋል እንዴ ? ያማቸዋል እንዴ ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው።
“ከባዝማ እስከ ኢትዮጵያ” በሚለው ሚስጥራዊ ሰነድ የኢትዮጵያን መንግሥት አውርዶ ተላላኪያቸውን ወያኔ ወደሥልጣን በመመለስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር ቢማማሉም በዚህ ደረጃ ይሉኝታቸውንና “ክብራቸውን” ሽጠው ይወርዳሉ ብዬ አልጠበቅሁም ።
ጦርነቱን የዐቢይ መንግሥት ጀመረ ፤ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት እየፈጸመ ነው ፤ እረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው ፤ ምርጫው አወዛጋቢ ነው ፤ ወዘተረፈ በሚሉ በሬ ወለደ ነጫጭ ውሸታቸው ፤ ወያኔን ቅዱስ ፣ መንግሥትን እርኩስ ሲያደርጉ እያየን እየሰማንና እያነበብን እንደ የእጃችን መዳፍ ከምናውቀው እውነት ጋር እያመሳከርን በንዴት ጦፈን ሳናበቃ ሰሞኑን ደግሞ አዲስ አበባ በቅርብ እርቀት “በአማጽያኑ” ተከበበች ፤ አዲስ አበበ ደህንነቷ ያሰጋል ፤ ዜጎቻችን ወደ ኢትዮጵያ የመሔድ አሳባቸውን እንዲያጤኑ ፤ የዐቢይ መንግሥት አበቃለት ፤ ወዘተረፈ እያሉ ማሟረትን በጄ ብለው ተያይዘውታል ።
በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተጠናቀረውን የመጀመሪያ ረቂቅ ሪፖርት ግን ባላየ ባልሰማ አልፈውታል ። ጦርነቱን አሸባሪው ሕወሓት መጀመሩን፤ በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አለመፈጸሙን ፤ መንግስት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ አለመጠቀሙንና ሌሎችን የምርመራ ግኝቶች የውሾን ነገር ያነሳ በሚል ግብዝነት አልፈዋቸዋል ። ዓመቱን ሙሉ ሲነዟቸው ከከረሙ ውሸቶች ጋር ስለሚጣረሱ ጆሮ ነፍገዋቸዋል።
አንዳንዶችም ከሪፖርቱ መንፈስ በተቃራኒ ለመዘገብ ተላልጠዋል ። በአንጻሩ በebs የ” Tech Talk With Solomon “ አዘጋጅ” እና “የግርምተ ሳይቴክ” ደራሲ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በቲዊተሩ እንዳጋራን ፤ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ ፣ አልጀዚራ ፣ አሶሼትድ ፕሬስና ፍራንስ 24 በአራት ቀናት ብቻ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን ለማሸበር ፤ ሀሰተኛ ትርክት ለማንበር ፤ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ለመፍጠር ፤ አገራችንን ለማፍረስ 72 ሀሰተኛ ዘገባዎችን ሰርተዋል ። እየሰሩም ይገኛል ።
በአንጻሩ ታዋቂ የአፍሪካና የምዕራባውያን ጋዜጠኞች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የእነዚህ እኩይ ሚዲያዎችን ሴራና ሸፍጥ በማጋለጥ ከኢትዮጵያ ጎን ቆመዋል ። የሲቢኤስ ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ፤ የኡጋንዳው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሉታያ ፤ ፒርስ ሞርጋን ፤ አና ጎሜዝ ፤ ቲቦር ናዥ እና ሌሎች ይሄን የምዕራባውያንንና የወያኔን ሴራ ለዓለም በማጋለጥ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።
አሁን ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለ ትግል እንደ ዓድዋ ለአፍሪካዊ እህት ወንድሞቿ ጭምር ነውና አፍሪካውያን ከጎኗ ሊቆሙ ይገባል ያሉም አሉ። በአጠቃላይ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ተረክንና ትርክትን ከመቆጣጠር አጀንዳ ከመቅረጽና ከመስጠት ባሻገር ከወያኔና ከሸኔ ጋር ግንባር ፈጥረው አገራችንን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየኳተኑ ነው።
በታሪክ ሀሰተኛ መረጃን እንደ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጦር መሳሪያ ያደረገ /ዌፐናይዝ/ ርዕዮተዓለም ድርጅትም ሆነ አገር የለም ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በሶቪየት ሕብረትና በአሜሪካ መርነት በሶሻሊዝምና በኢምፔሪያሊዝም በተካሄደው ወጊያ ቀረሽ የርዕዮተ ዓለም ጦርነት እንኳ የአሸባሪውን ሕወሓት ያህል መረጃ የጦር መሳሪያ አልሆነም ።
የቀዝቃዛው ጦርነት በአሜሪካው ጎራ በአሸናፊነት ከተቋጨ በኋላ በዓለማችን እንደ ራሽያው የስለላ ተቋም (ኤፍኤስቢ) መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ የተጠቀመ ወይም የሚጠቀም የለም ቢባልም የትህነግ ርዝራዥና የዲያስፖራ ጭፍራ ግን በገገማነትና በገልጃጃነት አሳምሮ ይበልጠዋል ።
ላለፉት 47 ዓመታት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃን ከክላሹ መሳ ለመሳ በስፋት ተጠቅሟል ። እንደሸሚዝ ከሚቀያይረው ርዕዮተ ዓለም እና ከታጠቀው ነፍጥ ይልቅ ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም ለፈጠራ ትርክት መታመን ይቀለዋል ። በውንብድናውም ሆነ በአገዛዙ ጥሩ አርጎ ያረጋገጠልን ይሄን እኩይ ማንነቱን ነው ።
በሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻውም ሆነ በኋላ ሆን ተብሎ በተዛባና በሀሰተኛ መረጃ የጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳና የማጠልሸት ዘመቻውን በመደበኛና በማሕበራዊ ሚዲያው እያፈራረቀና እያጃመለ ተያይዞታል ። መደበኛውም ሆነ ማሕበራዊ ሚዲያው በአገር ቤትም ሆነ በውጭ በተጠና ፣ በተቃናጀ ፣ በተናበበና በተመጋገበ አግባብ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ይመራል ።
ይህ ጸረ ኢትዮጵያ ፣ ጸረ እውነትና ጸረ ፍትሕ የፕሮፓጋንዳና የሚዲያ ከፍ ሲልም የዲፕሎማሲ ደባና ሻጥር በአገር ውስጥ በጌታቸው ረዳ ይመራል። ይሄን አውደ ውጊያ በበላይነት የሚዘውረውና የሚያሽከረክረው በምንደኛውና ጥቅሙ በተነካበት እብሪተኛና ማንአህሎተኛ /chauvinist / የትህነግ ርዝራዥና ጭፍራ ዲያስፓራ ነው ። ለዚህ እንዲያግዘው ደግሞ ፤” የትግራይ ወዳጅነት አገናኝ ቢሮ “(Tigray Friendship Liaison Office ) በተሰኘ ተቋም አማካኝነት በቀድሞው ዲፕሎማት ወንድሙ አሳምነው እንደሚመራ መስፍን አማን የተባሉ ጸሐፊ በፍት_ሕ መጽሔት ፤ 3ኛ አመት ፣ ቁ111 ፣ ታህሳስ እትም ላይ ፤” ከወታደራዊ ሽንፈት ወደ ዲፕሎማሳያዊ ትንቅንቅ “ በሚል ርዕስ ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ተረድተናል ።
በመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በጀኔቭ በመንግሥታቱ ድርጅት ሕዝብ ልማት ፈንድ ባልደረባው ዶ/ር ኪዳኔ አብርሃ ከአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀናጀት የአውሮፓውን የዲፕሎማሲና የዓለምአቀፍ ሚዲያውን እጅ ለመጠምዘዝ በተደረገው ርብርብ የአንበሳውን ደርሻ ወስደዋል ። ከአትላንቲክ ማዶ በአሜሪካ ያለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለአምባሳደር ፍስሐ አስግዶም በአደራ መሰጠቱን እኚሁ ጸሐፊ ጠቁመዋል ። የቀድሞው ታጋይ ሙሉጌታ ገብረህይወት ( ጫልቱ ) ከመለስ ዜናዊ ወዳጅ አሌክስ ዲወል ጋር በመሆን የትህነግን ተስካር ለማሳመር እየባዘኑ ነው ።
የኦባማ የብሔራዊ ደህንነት የቀድሞ አማካሪና የአዲሱ የባይደን አስተዳደር ተሿሚ ሱዛን ራይስ ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ ፣ የሒውማን ራይትስ ዋች ኃላፊ ኬኔትስ ሮዝ ከእነ የማነ ኪዳኔ (ጀማይካ ) ጋር በመሆን ዓለምአቀፍ ሚዲያውንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስራ ተጠምደዋል። በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጋር ለማጣረስ እየኳተነ ያለው ሌላው ከሀዲ ዶ/ር መሀሪ ታደለ ነው ።
በዚያ ሰሞን በመደበኛውና በማሕበራዊ ሚዲያው ስለወሬሳው ትህነግ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረው ማርቲን ፕላውት ፤ የቢቢሲ የአፍሪካ አርታኢ ዊል ሮስ ቢቢሲ አማርኛንና ትግርኛን በትህነግ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በመሙላት እና ኖርዌያዊው ሸተል ትሮንቮል እንደነ ቢቢሲ ባሉ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ ለከሀዲው ትህነግ በመወገን የተዛባና የሐሰት መረጃ በመንዛት ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል ።
ምዕራባውያን አሜሪካና ዓለምአቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ መንግሥት የማያባራና ፋታ የማይሰጥ ጫና እንዲያደርጉ ሰበብ በመሆን አገልግለዋል ። የሕልውና እና የሕግ የበላይነት ዘመቻውን 15 ቀናት ባልሞላ ጊዜ በአንጸባራቂ ድል ያጠናቀቀውን ፍትሐዊ ወታደራዊ ዘመቻ በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ውርጅብኝ ዳር ሳያደርስ ቀርቷል ።
በሌለ ጥሪት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለትግራይ መልሶ ግንባታ ገፍግፎ ፤ በስንት መስዋዕትነት ያስመዘገበውን ድል ፤ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በተቀናጀና በተናበበ የሌት ተቀን ሀሰተኛ ፣ ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ፣ በዲፕሎማሲና የፖለቲካ ዘመቻ ጫና እና ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት እንዲሁም ወቅቱ የእርሻ ወቅት ስለነበር የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከስምንት ወራት የሕግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻ በኋላ ባለፈው ሰኔ 21 ቀን 2013 ትግራይን ለቆ መውጣቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወረራውን ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች አስፋፍቷል ።
ሰሞኑን በሕዝባዊ ማዕበል ፣ በሰርጎ ገቦችና ቀድሞ በሚነዛው ሽብር ያገኘውን ጊዜያዊ ድል ጭፍራዎቹን እልል በቅምጤ አስብሏል ። ምንም እንኳ የመጨረሻው ሳቅና ሀሴት የኢትዮጵያውያን መሆኑ ባያጠራጥርም ።
የቀድሞው ፓትሪያሪክ የአቡነ ጳውሎስ ልዩ ረዳት ስታሊን ገብረስላሴ (ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ ፤ ጆሴፍ ስታሊን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቪየት ዜጎችን የጨፈጨፈ ሰው በላ ገዥ ነው፤ ) ፣ አሉላ ሰለሞንና ዳንኤል ብርሃኔና ሌሎች የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ሰዎች ደግሞ የአገር ቤቱንና የውጭውን የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ማሽን መካኒኮች ናቸው ። የትግራይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው ።
ትግራዋይ ሁሉ ትህነግ ነው ሲሉ ካለማፈራቸው ባሻገር በአገሪቱ ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጃቸው አለበት። ከፍ ብየ የጠቃቀስኋቸው የቀድሞ ታጋዮች ፣ አምባሳደሮች፣ በዓለምአቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ፣ የውጭ አገር ዜጎች ፣ አክቲቪስቶች በመማጸኛ ከተማው መሽጎ ከነበረው ከሀዲው የትህነግ ስብስብ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ካሰማራቸው ጭፍራዎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ የፈጠራ ትርክታቸውን ከመለፈፋቸው ባሻገር የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በመንዛት ሀገራችንን በጦር መፍታት ቢሳናቸው በወሬ ለመፍታት ሌት ተቀን እየተረባረቡ ነው ።
በዋናነት ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH ) ፣ ትግራይ ፈርስት ፣ አይጋ ፎረም፣ ትግራይ ፕሬስ ፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ ፣ ትግራይ ኦን ላይንና ሰሞኑን ደግሞ እንደአሸን የፈሉ ድረ ገጾችና ዩቲውቦች ሀሰተኛ መረጃውን ሌት ተቀን ያንበለብላሉ። እንደ ኦኤምኤን ያሉ የአጋሮቻቸውን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተውሶ ይጠቀማሉ ።
ማሕበራዊ ሚዲያዎችን አቀናጅቶ የሚጠቀመው በተለምዶ ዲጂታል ወያኔ በመባል የሚታወቀው የከሀዲው ትህነግ ጭፍራ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር የፌስ ቡክ ፣ የቲዊተር ፣ የቴሌግራም፣ የኢንስታግራምና የዩቲውብ ሀሰተኛ አካውንት በመክፈት ጥላቻን ፣ ልዩነትን ፣ ዘረኝነትንና ልዩነትን የሚያቀነቅኑ የፈጠራ መረጃዎችን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለረፍት ሌት ተቀን ይነዛሉ ። ጊዜያዊና መናኛ ግዳይ ቢጥሉም የመጨረሻውን ሳቅ በሀሴት የምንፈነድቀው እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን ።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በክልሎች ደግሞ 30 ሚሊዮን ሕዝብ በነቂስ አደባባይ በመውጣት የአሸባሪዎችን ጋላቢዎች በአገራችን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አንደራደርም ተላላኪ መንግሥት አንቀበልም በማለት ምዕራባውያንን እርማችሁን አውጡ የሚል ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በእውነተኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሕዳር 2/2014