አንጋፋው፣ ሁለገቡና ስመጥሩ የጥበብ ሰው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ያረፉት ከ13 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም) ነው፡፡
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ሁለገብ የጥበብ ሰዎች መካከል በቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡት ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ በመላው ዓለም ሳይቀር ተደናቂነትና ከበሬታ ያላቸው ድንቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው ናቸው፡፡ ጸጋዬ የተወለዱት በ1929 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በተጀመረ በስድስተኛው ወር ነው። የትውልዳቸው ቦታ ከአምቦ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቦዳ አቦ በመባል የምትጠራው ስፍራ ናት፡፡ ቦዳ ተራራ ግርጌ የሚገኘው የአባታቸው ቤት ሲቃጠል እናታቸውና እህታቸው ከወራሪው ጦርና ከባንዳ ጋር ተታኩሰው በአርበኞች እርዳታ ሕይወታቸውን ካተረፉ በኋላ ወደ እናታቸው የትውልድ ስፋራ ተሰደዱ፡፡
በግዕዝ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ እየተማሩ ያደጉት ጸጋዬ፣ የኋላ ኋላ ዓለም ያደነቃቸው ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ ሆኑ፡፡ ከግጥም ስራዎቻቸው መካከል ‹‹እሳት ወይ አበባ›› ተጠቃሽ ነው፡፡ ከተውኔቶቻቸው መካከል ደግሞ ‹‹የዳኒሲዩስ ዳኝነት››፣ ‹‹በልግ››፣ ‹‹የደም አዝመራ››፣ ‹‹እኔም እኮ ሰው ነኝ››፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹የእሾህ አክሊል››፣ ‹‹ቴዎድሮስ››፣ ‹‹ምኒልክ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹ዘርዓይ ደረስ››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹መልእክተ ወዛደር›› ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››፣ ‹‹አፅም በየገጹ›› ‹‹ትንሣኤ ሰንደቅ ዓላማ›› እና ‹‹የመቅደላ ስንብት›› ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የተለየና ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ካልተዘመረላቸው የሀገራችን ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰጣቸው ክብርና አድናቆት ይልቅ በውጭ አገራት የተሰጣቸው ክብር የተሻለ እንደነበርም ይገለፃል፡፡
ከጥበባዊ እውቀታቸው ባሻገር፣ ሰሚ አላገኙም እንጂ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦችንም በተደጋጋሚ ሰንዝረው ነበር፡፡ በርካታ አንጋፋ የሀገር ውስጥና የውጭ ጸሐፍትና ባለሙያዎች በብዕሮቻቸው ያሞገሷቸውና የመሰከሩላቸው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ከፍተኛውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስነ-ጽሑፍ ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም አሜሪካ ውስጥ አርፈው አስክሬናቸው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን አርፏል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2011
በአንተነህ ቸሬ