ዋ …. ያቺ አድዋ
ዓድዋ ሩቋ
የአለት ምሶሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስ
ዓድዋ ….
የካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ክስተቶችን በማስተናገድ ከተቀሩት ወራት ተወዳዳሪ አይገኝለትም፡፡ በወሩ ከተከናወኑት አበይት ክስተቶች አንዱና ዋነኛው ደግሞ የዓድዋ ድል ነው፡፡
አጼ ምኒልክ ሀገራችንን ጠላት እንዳይደፍራት ኢትዮጵያውያንን በጥበብ አንቀሳቅሰው በጀግንነት መክተው መልሰዋል:: እኔ በግሌ ስለ ዓድዋ ድል በተነሳ ቁጥር የምደመመው አባቶቻችን ጣሊያኖችን ካሸነፉ በኋላ ለምርኮኞቹ ምህረት አድርገው ‹‹እነሱም እኮ እናት አላቸው›› ብለው ራርተው ወደ ወገናቸው በመሸኘታቸው ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለጠላት እንኳን አንጀታቸው ይንሰፈሰፍ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እኛ ጠላት ሳይኖረን በአንድነት መቆም አቅቶን እርስ በርሳችን በጠላትነት እየተያየን ነው፡፡
ታሪክ ሰርተው ቀና ብለን እንድንራመድ ያደረጉንን አባቶች ማብጠልጠል አርበኝነት ሆኗል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የቀደሙት መሪዎቻችን የሚያስወቅሳቸውን ተግባር ፈጽመው ያለፉ ቢሆን እንኳን መልካም ስራቸውን ጥላሸት መቀባት አያስፈልግም፡፡ መላ ኢትዮጵያውያንን አስከትለው ጠላትን ድባቅ የመቱና ለሀገራችን ህዝብ መኪና፣ ስልክ፣ የቧንቧ ውሃ፣ ባቡር፣ መብራት ፣ ወፍጮ፣ ሲኒማ፣ ሆቴል፣ ብስክሌትና ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች ያስተዋወቁ መሪን መጥፎ አድርጎ መሳል የቅናት በሽታ ነው፡፡ ስህተት ፈላጊዎች ከበጎነት ውስጥም ግድፈት ከመፈለግ ወደኋላ አይሉም ያለው ማን ነበር ?
ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል በአንድ ግጥማቸው እንዲህ ብለው ነበር፡-
የቅናት በሽታ ህመሙ የከፋ፤
የህሊናን ዓይኖች ጨርሶ የሚያጠፋ፤
በዚህ ክፉ ደዌ የሰው ልጅ ሲለከፍ፤
የተጣራው ነገር ይመስለዋል ሰፈፍ፤
ልቡም እያደላ ወደ ክፋት ወገን ፤
መሞትን ይመርጣል ሰውን ከማመስገን፤
ዓድዋ የጋራ ድል ነው፡፡
ግራዚያኒ በሶስት ቀን ውስጥ ብቻ ከ 30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የፈጀበት የካቲት 12 ሲታሰብ የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ ከመታሰቢያ ሀውልቱ በቅርብ ርቀት በሚገኘው የካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ ስለ ዕለቱ የሚያውቁትን እንዲነግሩት ተማሪዎችን ጠይቆ ነበር፡፡
ከአንድ ተማሪ በስተቀር የተቀሩት ተጠያቂዎች በዕለቱ ስለተፈጸመው ፍጅትና ትምህርት ቤታቸው ለምን የካቲት 12 ተብሎ እንደተሰየመ እንደ ማያውቁ ተናግረዋል፡፡
አሁን እየመጣ ያለው ትውልድ ለታሪክ ግድ ስለሌለው በታሪካዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤው ደካማ ነው፡፡ ለመዘባረቅም ቢሆን እኮ ትንሽ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ባለፉት ዓመታት በመጀመሪያ ዲግሪ ታሪክን የሚያጠኑ ተማሪዎች ማግኘት አለመቻሉን ተናግሮ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በመሪዎች አንደበት ‹‹ታሪክ ዳቦ አይሆንም›› በሚባልበት ሀገር ታሪክን እንደመማር የሚሰቀጥጥ ምን ነገር አለ? በታሪክ ትምህርት ተመርቆ ስራ ከመያዝ በምህንድስና ተመርቆ ቁጭ ማለትን የሚመርጥ ትውልድ አፍርተናል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ በግጥሙ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ሀገሬ አርማ ነው የነጻነት ዋንጫ፤
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ቢጫ፤
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ፤
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፤ የሚል ትውልድ ይኖር ይሆን ?እንጃ …
ዋ …. ያቺ አድዋ
ዓድዋ ሩቋ
የአለት ምሶሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ ….
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2011
በየትናየት ፈሩ