የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሁም የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ምንም እንኳ የመንግስት ፖሊሲ ቀረፃ በምርምር ላይ እንዲመሰረት ሃሳብ የማመንጨት ተመሳሳይ ዓላማ ቢኖራቸውም ለዓመታት ተለያይተው ሰርተዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት ከአሥር ዓመት ባላነሰ ቆይታቸው ምን ያህል ለመንግስት ፖሊሲ ግብዓት የሚሆን አሳብ አቅርበዋል ወይም አመንጭተዋል? የሚለው ቢያጠያይቅም ተቋማቱ በአዲስ መልክ ተዋህደው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሚል ስም ከህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰሩ ታውጇል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ከሁለት ወደ አንድ የመጣው ተቋም ምን ላይ ደረሰ? በማለት በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ አህመድ አብተው ጋር የነበረንን ቆይታ እንሆ፡-
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ሶስት ወር አለፈ፡፡ ምን ሰራችሁ?
አቶ አህመድ፡- ድርጅቱ የተቋቋመበትን አዋጅ ተከትለን ደንብ አውጥተናል፡፡ ደንብ ከፀደቀ በኋላ የአዲሱን ተቋም መዋቅር እና የምርምር ዘርፎች እንዲሁም የጥቅማጥቅም ፓኬጆችን አዘጋጅተናል፡፡ በዋናው ሥራ በኩል አራት የምርምር ዘርፎችን አደራጅተናል፡፡ አንደኛው የማይክሮና ፋይናንስ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የባንክ ሁኔታን ጨምሮ አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማትን ይዳስሳል፡፡ በስሩ ሌላ አራት ዘርፎች አሉት፡፡ ሁለተኛው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ሲሆን፤ በስሩ የገጠር፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማትን ያካትታል፡፡
ሶስተኛው የድህነት ትንተና እና ማህበራዊ ልማት የፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ የሰው ሃይል ልማት ላይ ያተኩራል፡፡ የሰው ሃይል ልማት ከሥራ ስምሪት ጋር መናበቡን ያያል፡፡ በተጨማሪ የሰው ሃይል ልማት በፆታ እና በተለያየ ማህበራዊ ቡድን ያለውን ተሳታፊነት በመቃኘት የፖሊሲ ምክረሃሳብ ይሰጣል፡፡ በማህበራዊ ልማት ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸው በፍጥነት እንዲሻሻል ልዩ የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
የመጨረሻው የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ነው፡፡ አገሪቷ በምትከተለው የፌዴራል ስርዓት ውስጥ አሁን የሚታዩ በህብረተሰቡ ውስጥ አጀንዳ ሆነው የሚነሱ ጉዳዮች የፖሊሲ ክፍተታቸውን በማየት የፌዴራል ስርዓቱ እንዴት ሊበለፅግ ይችላል? የፌዴራል ተቋማት እንዴት ያድጋሉ? አሁን በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? የሚሉትን በማየት የፖሊሲ ክፍተቱን እያጠና ለመንግስት ያቀርባል በሚል እሳቤ አራት ዘርፎች ተደራጅተው በመጠናት ላይ ናቸው፡፡
መረጃዎችን (ዳታዎችን) ከዳታ ሰብሳቢ መስሪያቤቶች ጋር በመሆን ለተመራማሪዎች የማደራጀት እንደዚሁም ቀዳሚ መረጃ መሰብሰብ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰበስብ የሚመራ አንድ የተለየ ቢሮ እንዲቋቋም ለፕላን ኮሚሽን ተልኳል፡፡ ይህን ከመስራት ጎን ለጎን በሁለቱ ተቋማት ተይዞ የነበረውን ዕቅድ የማጣጣም ሥራ ተሰርቷል፡፡ መልሶ ማደራጀት ላይ መዋቅሩ ባይፀድቅም ሰራተኞቹን በጊዜያዊነት እያሰራ ነው፡፡ መዋቅሩ ሲፀድቅ ደግሞ ህጋዊ በሆነ መልኩ ሰራተኞቹን በቋሚነት በመመደብ ሃይልን አደራጅቶ የተያዘውን ዕቅድ ለመፈፀም እንሰራለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሁለቱ ተቋማት ከፀደቀው አዋጅ ባሻገር ተዋህደው እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ አህመድ፡- አዎ! ከአዋጁ ቀጥለን ወዲያው ደንብ በማዘጋጀት በህዳር ወር እንዲፀድቅ አድርገናል፡፡ ጎን ለጎን መዋቅር እየተሰራ ስለነበር ከህዳር 1 ቀን ጀምሮ ሰራተኞቹ በጊዜያዊነት እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡ መደበኛ ሥራው ምንም አልተስተጓጎለም፤ ሥራው በመሰራት ላይ ነው፡፡ በሁለቱም ተቋማት ቀድመው የታቀዱና የተጀመሩ ጥናቶችን በማጣጣም እየተሰራ ይገኛል፡፡ አዲስ የተጀመሩ ጥናቶችም አሉ:: በተለይ የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ከሌሎች ዓለም ዓቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር ውል በመግባት የሚፈፅማቸው የምርምር ሥራዎች አሉ፡፡ ኮንትራት የተገባባቸውን በመያዝ አሁን ካለው ጋር በማጣጣም እየታደሰና እየተሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ለመዋሃድ ፍቃደኛ አልነበሩም የሚል መረጃ አለ፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ አህመድ፡- በእርግጥ ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል ከውጪ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥናት ያካሂድ ነበር፡፡ ገቢውም በውጪ ፈንድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ አሰራሩም ለምርምር የሚመችና እንደውሉ ሁኔታ የሚቀያየር ነበር፡፡ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እንደገለፁት፤ አሁን ሙሉ ለሙሉ በመንግስት በጀት ከሚተዳደረው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጋር መዋሃዳቸው ነፃነታቸውን ይገፈዋል፡፡ በተቆላለፈው የመንግስት አሰራር ሳቢያ ምርምራቸውን በሚመች መልኩ ለማካሄድ አያስችልም የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ በዚህ በኩል ጠንካራ ጥያቄ ነበራቸው፡፡
ደንቡ ሲዘጋጅ ሁሉም ተመራማሪ እንዲገኝ ተደርጎ ለኢንስቲትዩቱ ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር እንዲሰራ የተሰጠው ስልጣን ተካቶ ተዘጋጅቷል፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ምርምር እንዲካሄድባቸው የሚፈልግባቸው ዘርፎችም እኩል ትኩረት አግኝተው መሰራት አለባቸው፡፡ አሠራሩ ላይ መመሪያ እየተዘጋጀ ሲሆን፤ በመንግስት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ምን ያህል ሽፋን ይኑራቸው? በውጪ ድጋፍ የሚሰሩትስ ምን ያህል ሽፋን ያግኙ? የሚለው በመመሪያ የሚመለስ ይሆናል፡፡ ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር የሚጠናው ጥናት ዋናው መስፈርት ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ምርምሩ ለአገሪቷ የሚጠቅም መሆን አለበት፡፡ በውጪ ድጋፍ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች ዓላማቸው የምርምር ወጪ በውጭ ይሸፈናል፡፡ የተመራማሪዎች ዓቅም ያድጋል፡፡ በዋናነት ግን ምርምሩ አገሪቷንም የሚጠቅም መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በውል የሚካሄዱ ጥናቶች ምን ያህል ለፖሊሲ ግብዓት ይሆናሉ? ወጪውን እነርሱ የሚሸፍኑ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ የጥናቱ ውጤትም ሆነ የተሰበሰቡ መረጃዎች ለኢትዮጵያ የማይተርፍበት ሁኔታ አለ ይባላል? ይህ ከሆነ አገሪቱ ምን ተጠቀማለች?
አቶ አህመድ፡- ልክ ነው፡፡ የባለቤትነት ጉዳይን በተመለከተ ህዝባዊ ሲሆን ባለቤትነቱን ለእኛ ይሰጣሉ፡፡ በግል ሲያስጠኑ ግን ባለቤትነቱ ውላቸው ላይ ባለው መሰረት የእነርሱ ነው፡፡ ይህ አከራክሯል፡፡ ባለቤትነቱ የሁለታችንም መሆን አለበት፡፡ አሁንም በስራ ላይ ያሉት ማስተካከያ እየተደረገባቸው የምርምር አጀንዳዎች አሉ፡፡ ሁኔታውን በማሻሻል ባለቤትነቱን የኛ በማድረግ ላይ ነን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከእናንተ ተቋም ባሻገር ሌሎች ተቋማትንም ከሁለት ወደ አንድ ከማዋሃድ ባሻገር የታጠፉም አሉ፡፡ ይህ አደረጃጀት ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት አመቺ ነው? ይህንንስ አጥንታችሁታል?
አቶ አህመድ፡- በእርግጥ የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት በአዲሱ አደረጃት ላይ ጥናት አላካሄደም፡፡ ነገር ግን የመንግስት አደረጃጀት ብዙን ጊዜ የሚካሄዱት በአጭር ጊዜ ጥናት ነው፡፡ በየትኛው የዕድገት ደረጃ ምን ዓይነት የህዝብ ተቋም የስፈልጋል? የሚለው ሰፋ ያለ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ለአሁኑ ግን ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለመንግስት ቀርቦ ከተወሰነ በኋላ በአዲስ መልክ ተቋማቱ ተቋቁመዋል፡፡ እኔም የኮሚቴው አባል ነበርኩኝ ፡፡
ተቋማቱን መቀነስ ያስፈለገበት ምክንያት የአገሪቱ ሃብት ውስን በመሆኑ ነው፡፡ የሰው ሃይሉም የተወሰ ሲሆን፤ ተቋማቶች ደግሞ ባለሙያ የላቸውም ባዶ ናቸው፡፡ መስሪያ ቤቱ መቆሙ ለብቻው ለልማት የሚኖረው ፋይዳ አነስተኛ ነው፡፡ ለህብረተሰቡ የሚያስገኘው ጥቅም ጥቂት ነው፡፡ ስለዚህ ያለውን ውስን ሃብት ከመበተን ይልቅ የሚቀናጁ ስራዎችን አንድ ላይ በማድረግ የመፈፀም አቅማችን ከፍ ይላል፡፡ ተቋማቱም ውጤታማ ይሆናሉ የሚል መነሻ አለው፡፡
ሌላው እና ዋናው ፈተና የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ተለያይተው ቢቋቋሙም ግባቸው አንድ ነው፡፡ ሥራዎች ደግሞ ለየብቻ ይያዛሉ፡፡ ተደምሮ የሚመጣ ውጤት አልነበረም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የቅንጅት ሥራ ክፍተት ነበር፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ከኢንዱስትሪ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡ የሚሰለጥነው የሰው ሃይል ኢንዱስትሪው የሚፈልገው ካልሆነ ብክነት ነው፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪው ፍላጎት ምንድን ነው? በሚል የትምህርት አሰጣጡ እና የሰው ሃይል ስልጠናው ከኢንዱስትሪው መነሳት አለበት፡፡ ግብርናና ኢንዱስትሪም ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ይህ የቅንጅት ችግር በኢትዮጵያ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ መስሪያ ቤቶች በተበተኑ ቁጥር ችግሩ የባሰ ይገዝፋል፡፡ ስለዚህ ተቀራራቢ ስራዎች በአንድ ተቋም ውስጥ አንድ ላይ ተቀናጅተው ሲሄዱ ውጤቱም የተሻለ ይሆናል፡፡
በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡ ዘንድ በአገልግሎቶች አለመርካትና አለመረጋጋት ይታያል፡፡ ስለዚህ ተቋሞችም ከተነሱበት ፍልስፍናም ሆነ ካላቸው ዓላማ አንፃር መቀየር አለባቸው በማለት በአዲስ መልክ እንዲቋቋሙ ተወሰኗል፡፡ ከዛ እንፃር ይህኛው ከዚህኛው ጋር ቢዋቀር ጥሩ ነው በሚል አንዱን ከሌላው ጋር በማዋቀር ውጤታማ ሥራ እንስራለን በሚል መንግስት አምኖበት ተቋማቱ በአዲስ መልክ እንዲቋቋሙ ተወስኗል፡፡
ነገር ግን ለሶስተኛው የዕድገትና ትራንስፎር ሜሽን ዕቅድ ምን አይነት የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ያስፈልጋሉ? ብሎ ማጥናት ይቻላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ጥናት ዘርፍ አንዱ እንዲህ አይነት ነገሮችን ያያል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስከአሁን የተጠኑ ጥናቶች ምን ያህል ናቸው? ውጤት አምጥተናል ትላላችሁ?
አቶ አህመድ፡- በፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ሂደት እኛም ዘንድ የተመራማሪዎች ክርክር አለ፡፡ ራዕይ እና ተልዕኳችን ላይ ተመስርተን ምን ያህል እየሰራን ነው? የሚለው ተቋማቱ ከመዋሃዳቸውም በፊት ውይይት ይካሄድ ነበር፡፡ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል የጥናት ሰነዶችን አውጥቷል፡፡ በኢንዱስትሪም ሆነ በግብርናው መስክ ባጠናው ጥናት ፖሊሲዎችን ባያሻሽልም የፖሊሲ መሳሪያዎችን እያሻሻልን እየደገፍን መጥተናል፡፡ ትልቁ የግብርና ፖሊሲ እስካሁን በተካሄደው ጥናት አልተሻሻለም፡፡ ነገር ግን የፖሊሲ ሃሳቡን ወደ መሬት የሚቀይሩ የተለያዩ መሳሪያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የጎደላቸውን በማሟላት፤ ሌሎቹን ደግሞ በማሻሻል ትልቅ ስራ ሰርተናል፡፡
በኢንዲስትሪም የተነጠለ ጥናት በማጥናት ለተቋማት ገቢ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም፤ አገሪቷ ለዚህ ደርሳለች አልደረሰችም፤ የሚለው ተጠንቶ ለመንግስት እና ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገብቷል፡፡ ሌላም በቴክኖሎጂ ዙሪያ የነበረው የፖሊሲ ክፍተትም እንዲሁ ተጠንቷል፡፡ በከተማ ልማት የፖሊሲ ጥናት ተጠንቶ ገቢ ተደርጓል፡፡
የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ደግሞ በጣም ነጠላ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ጥናታቸው የችግሩን ባህሪ እና ጥልቀት ከነመፍትሄው የሚያመላክት ሲሆን፤ ፖሊሲ ልዩ ትኩረታቸው አይደለም፤ ይህ ተገምግሟል፡፡ በእርግጥ በሚሰሩት ጥናት በምርምር ዘርፉ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ የተሻለ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ እናም ዋነኞቹን እና ትልልቆቹን የፖሊሲ ሰነዶች በማሻሻል ሳይሆን፤ እነርሱን በመተግበር ዙሪያ ፖሊሲዎች ምን ያህል ዝርዝር እና ለመፈፀም ምቹ ናቸው? ተጨማሪ የፖሊሲ መሳሪያ ያስፋልጋል አያፈልግም የሚለው ሲጠና ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ያጠናችሁትን ጥናት መንግስት እየተጠቀመበት ነው?
አቶ አህመድ ፡- አንዳንዶቹ ጥናቶች ወዲያው ወደ አፈፃፀም ለመግባት የሚያዳግቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት እና ጥራት ያለውን ምርት ወደ ውጭ ለመላክ የማሸጊያ ምርት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ አዋጪ ነው፡፡ ከምርት ሂደት አንፃር አዋጪ ቢሆንም ወደ ተግባር አልተገባም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ምክር ሃሳቦች ወዲያው ወደ አፈፃፀም አይገቡም፤ ዝግጅት ይጠይቃሉ፡፡ የሚፈልገው ኢንቨስትመንትም ትልቅ ነው፡፡ የነበሩ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ እና የብድር ጫናቸው ሳይቀንስ ወደ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት መግባት ነገሩን ያወሳስበዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን መንግስት አልተገበረውም የሚያስብል አይደለም፡፡ ሁኔታው ራሱ በማስገደዱ ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
ሌሎቹ ግን ከዕለት ዕለት አፈፃፀም ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው አልተተገበሩም የሚባሉ አይደሉም፡፡ በአብዛኛው በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ተቋማትም የተሳቱበት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ለአብነት ትልልቆቹ የስኳር ፕሮጀክቶች ከሌሎች ጋር እንዴት ይቀናጃሉ? ለምሳሌ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራኖችን በማሳተፍም ሰፊ የጥናት ውጤት ቀርቧል፤ ውይይት ተደርጓል፡፡ አንዳንዶቹ ስምምነት ተደርጎባቸው ምቹ ሁኔታ እየተጠበቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መንግስት ሳያየው የተቀመጠ ጥናት የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በትክክል በኛ ጥናት ይህ ተሰርቷል ብለው የሚጠቅሱልኝን ውጤት ይግለፁልኝ፡፡
አቶ አህመድ ፡- አሁን ያለውን የግብርና ፖሊሲ ብንቀይረው የጥናቱ ውጤት ነው አይደለም ብሎ መግለፅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲውን ለማቃናት የተሰራውን ጥናትና ያስገኘውን ውጤት መለካት ከባድ ነው፡፡ ከጥናት ሰነዱ የወጡ ምክረ ሃሳቦች አንዳንዶቹ ጊዜ እየጠየቁ ነው፡፡ በአብዛኛው ግን አፈፃፀም ላይ የገቡ እንጂ ሼልፍ ላይ የቀሩ አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቂ ተመራማሪዎች አላችሁ?
አቶ አህመድ ፡- 40 ተመራማሪዎች አሉን፡፡ አብዛኞቹ ሶስተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ 31ዱ ቋሚ ሆነው እየሰሩ ናቸው፡፡ዘጠኙ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እያጠኑ ናቸው፡፡ ለአንዳንድ ጥናቶች በኮንትራት የምንቀጥርበት ሁኔታም አለ፡፡ የሰው ሃይልን ለማሟላት መንግስትም ያግዛል፡፡ ተቋሙም ለማብቃት እየተሰራ ነው፡፡
መንግስት እንደማንኛውም ተቋም በቂ በጀት ይመድባል፡፡ ነገር ግን አጠቃቀሙ ላይ የሚወጡ መመሪያዎች ለሁሉም ተመሳሳይ ስለሚሆን እና የተቋሙ ባህሪ ግምት ውስጥ ስለማይገባ ችግር ተፈጥሮብናል፡፡ ስለዚህ በጀቱ ብዙ ይተርፋል፡፡ ነገር ግን እንደምንፈልገው እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እናንተ መንግስት እንደሚፈልገው ሃሳብ ማመንጨት አልቻላችሁም? መንግስት መርካት ያልቻለው ለዚህ ነው?
አቶ አህመድ፡- የኢኮኖሚ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት በነጠላ የፖሊሲ ሃሳቦች ላይ ጥናት ወደ ማድረግ በማጋደሉ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በእርሱ ላይ ተደርቦ ተቋቋመ፡፡ ሁለቱም የሚፈለገውን ውጤት ባለማምጣታቸው ይቀናጁ እና አንደኛው ስራ ቢሰራ ይሻላል የተባለው ለዚያ ነው፡፡ መንግስት ውጤታማ ሥራ እየተሰራ እና እየረካ ቢሆን ተቋማቱን አያጥፋቸውም ነበር፡፡ ይልቁኑ ይጠብቃቸው ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ከዚህ ተቋም ብዙ ይጠበቃል፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከግቡ በጣም የራቀ ነው፡፡ ውጤታማነታችንን ከራሳችን ዕቅድ ጋር ስናነፃፅረው ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህ ለምን ብለን ስንጠይቅ፤ መጀመሪያ ታሳቢ ያደረግናቸው ነገሮች ለምን አልሰሩም? እንደርስበታለን ብለን ባሰብነው ላይ ለምን አልደረስንም? የሚል ጥያቄ ይጭራል፡፡ እይታ ላይ ተመስርቶ መገመት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የችግሩን መንስኤ ለማወቅ መጠናት አለበት፡፡ ይሄንን መንግስት ይፈልጋል ስለዚህ በዛ ላይ ይሰራል፡፡
የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጊዜ እያለቀ ሶስተኛው እየተያዘ ነው፡፡ በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንፈጥራለን የሚል ግብ ተቀምጧል፡፡ የቀረው 5 ዓመት ነው፡፡ ይህን ለማሳካት በተለይ ትልልቆቹ ስትራቴጂዎች ረዥም ዓመት የሰሩ በመሆናቸው መከለስ አለባቸው፡፡ አሁን ካለንበት ተነስተን ነገ እንደርስበታለን ካልንበት ግብ አንፃር በደንብ መረጃ ላይ ተመስርተን ማሻሻል ይጠበቅብናል፡፡ ውሳኔ የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው መንግስት ከዚህ ተቋም ብዙ ይፈልጋል፡፡ ይህን ለመስራት ተቋሙ በአዲስ መልክ ተቋቁሟል፡፡ ያለውን የሰው ሃይል ተጠቅሞ እና ሌሎቹንም አንቀሳቅሶ የቤት ስራውን ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ትልልቅ ውሳኔዎችን መወሰን ያስፈልገዋል ሲሉ በምን በምን ጉዳዮች ላይ እስኪ ቢያብራሩልኝ፡፡
አቶ አህመድ፡- እስከ አሁን ግብርናው ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ኢንድስትሪ እንሸጋገራለን ሲባል ነበር፡፡ በዛ ጊዜ ይህ የተባለበት ምክንያት በወቅቱ ያለው የመወዳደር አቅም ግብርና ላይ ዘመቻ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ተብሎ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰለጠነው የሰው ሃይል፤ የቁጠባው መጠን፤ የህዝቡ ቁጥር እና የቴክኖሎጂው አቅም እንደአሁኑ አልነበረም፡፡ በእነዚህ ዓመታት ዕድገቱ ጨምሯል፡፡ አሁን ኢንዱስትሪውን መሪ አድርጎ ለመሄድ ጊዜው ነው ወይስ አሁንም ያላሟላናቸው ኢንዱስትሪውን መሪ የሚያደርጉ ሁኔታዎች የሉም? ብሎ ያንን በማወቅ ትልልቅ ውሳኔዎችን መወሰን ያስፈልጋል፡፡
ከአሁን በኋላ የኢንዱስትሪ ዕድገቱንና ያለውን ፍላጎት መሰረት አድርገን መነሳት እንችላለን? ወይስ ሌላ ኢንዱስትሪ እንድናቋቁም አሁን ያለው አቅም ይፈቅድልናል? ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው በዓለም ዓቀፍ ገበያ ላይ ተወዳደድረው የውጪ ምንዛሬ ችግራችንን ሊቀርፉ በሚችሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ርብርብ ማድረግ ጊዜው ነው አይደለም? በሚለው ላይ መንግስት አቋም መያዝ አለበት፡፡ በእዚህ መሰረት የሦስተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድና ግብ ይወስናል፡፡ በተነፃፃሪነት በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሃብት ብለን የለየነው የተፈጥሮ ሃብቱ፣ ጉልበት፣ መሬትና ውሃን በመጠቀም ፈጣን ልማት ማምጣት ዋነኛው ሃሳብ ነበር፡፡ አሁን የፈጠርናቸው ደግሞ ፈጣን ልማት ማምጫ አማራጮች አሉ፡፡ የተፈጥሮ ሃብቱን አልምተን ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንችላለን? በእርግጥ አቅም ፈጥረናል፡፡ አቅማችን ተቀይሯል? ይህ ከሆነ ተነፃፃሪ የፖሊሲ ሃሳቦች በምርምር ተደግፈው መቅረብ አለባቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ክርክር ተደርጎባቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተወስነው የሶስተኛውን ዕቅድ ማቀድ ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ
አቶ አህመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2011
በምህረት ሞገስ