በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች ይዘዋቸው ከወጡ ዘገባዎች የሰብሰብናቸውን ዘገባዎች ይዘን ቀርበናል፡፡ ያ ወቅት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሲያድባሬ በእብሪት ተነሳስቶ ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በነበረው ቅዠት የምስራቅ ኢትዮጵያን ሰፊ አካባቢዎች በወረራ የያዘበት፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በአንጻሩ ይህን የሶማሊያን ቅዠት ለማክሸፍ ርብርብ ሲያደርጉ የነበረበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አሁን ካለንበት ሀገራዊ ሁኔታ ጋር ብዙ መልኩ የሚመሳሰል በመሆኑ ነው ብታነቡት ብለን ይዘን መቅረባችን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ወደ ጦር ግንባር ለመዝመትብዙ ሺህ የመለዮ ለባሽ አባት ጦረኞች ተመዘገቡ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
ዕድሜያቸው ከ፷ ዓመት በታች የሆኑ የጦር ኃይል የመለዮ ለባሽ አባላት የነበሩ አባት ጦረኞችና አርበኞች ከመደበኛውና መለዮ ለባሹ ጦር ጎን ተሰልፈው የአገርን አብዮታዊና የቆየ ክብርና ህልውና ለማስከበርና የሰፊውን ሕዝብ አብዮት ከቅልበሳ ለመከላከል የትግሉ ተካፋይ እንዲሆኑ ከብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት ባለፈው እሁድ ሲመዘገቡ ውለዋል፡፡
በአንደኛው ክፍለጦር ቅጥር ጊቢ ውስጥ በተደረገው በዚሁ የምዝገባ ሥነሥርዓት ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባት ጦረኞችና አርበኞች በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት በመነሳሳት ከወራሪው የሲያድ ባሬ መደበኛ ጦር ጋር እስከ መጨረሻው ድል ለመዋጋት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር አነጋግሮ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያን ከግዛታቸው አንዲት ጋት እንኳን የማያስቆርሱ መሆናቸውን ከታሪክ ያልተረዳው የሞቃዲሾው ፕሬዚዳንት ሲያድ ባሬ በነፃ አውጪ ስም የአንድን ሕዝብ አስተያየት ለማወናበድ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እያሠራጨ ከወዲያ ወዲህ ቢራወጥም ከመደበኛና ከሚሊሻው ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈው ወራሪውን ኃይል ውርደት እንጎናጽፈዋለን ብለዋል፡፡
ከዚህም በማያያዝ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በጀግኖች ልጆችዋ ተከብሮ እንደኖረ ወደፊትም እንደ ተከበረ የሚኖር መሆኑን፣ ከደፈሩን ለማረጋገጥ አንድነታችንን በይበልጥ አስተባብረን ተነስተናል በማለት ለሀገራቸው መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጠዋል፡፡
(ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 1970 ዓ.ም)
መደበኛና ሚሊሺ ጦር የመከላከል ጦርነቱን ወደ አጥቂነት አሸጋገረየሰሜኑ ግንባር ጦር ተገንጣይን እያጠቃ የተዘጉ መንገዶች ከፈተ
(ከኢ-ዜ-አ-)
የአብዮታዊት ኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስና ሕልውናዋን ለማጥፋት የዓለምአቀፍ ኢምፔሪያሊዝም የአካባቢው አድኃሪያን ኃይሎች ከውስጥ ጠላቶች ጋር በመተባበር ያደረጉት ከበባ ወደ ግልፅ ወረራ ከተሸጋገረ ወዲህ ከጠላቶቹ ጋር በየግንባሩ በመዋደቅ ላይ ያለው የኢትዮጵያ መደበኛና ሚሊሺያ ጦር የመከላከል ጦርነቱን ወደ አጥቂነት በማሸጋገር በትናንቱ ዕለት ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ ውሏል፡፡
የብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ይህንኑ በማስታወቅ ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ የእናት አገሩን አንድነት አብዮትና የቆየ ክብር ለመጠበቅ ፍጹም በሆነ ወኔ የአገር ፍቅር ስሜትና አብዮታዊ ወኔ በምሥራቅና በሰሜን የተሰለፈው የኢትዮጵያ መደበኛና ሚሊሺያ ጦር የመከላከል ጦርነቱን ወደ አጥቂነት በማሸጋገር በሁለት ግንባሮች የተፋፋመ ውጊያና አሰሳ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለመውሰድ መደበኛ የጦር ኃይልን አሠልፎ በምሥራቅ በኩል የዕብሪት ወረራ የሚያካሂደው የሞቃዲሾው መንግሥት ያለ የሌለ ኃይሉን በማሰለፍ በተለይ በጅጅጋ ላይ በማተኮር ከኋላ ሆነው በሚገፉት ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች አይዞህ ባይነት የጅጅጋን ከተማ ለመያዝ ለሦስተኛ ጊዜ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ውጊያ መክፈቱን መረጃው ገልጧል፡፡
ይሁን እንጂ በጅጅጋ የተሠማራው የኢትዮጵያ መደበኛና ሚሊሺያ ጦር ወራሪው የሶማሊያ ጦር በትናንትናው ቀን በከፈተው እጅግ ከባድ ውጊያ ወደ አጠቂነት በማሸጋገር በሶማሊያ ታንኮችና ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ገልጧል፡፡
(መስከረም 1 ቀን 1970 ዓ.ም)
በማረቃ ወደ 300 አርሶ አደሮች በውትድርና ይሰለጥናሉ
ጅማ ፤(አ/ዜ/አ) አብዮታዊት ኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የተነሱባትን የውስጥ አድኃሪ ኃይሎችና የውጭ ወራሪዎች በመቋቋም አብዮቷን ጠብቃ ዳር ድንበር ለማስከበር እንደትችል የተደረገው ብሔራዊ የክተት ጥሪ በመቀበል በኩሎ አውራጃ በማረቃ ወረዳ ፫፻ አርሶ አደሮች ለመዝመት ተመዝግበው የውትድርና ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውን የአውራጃው አስተዳዳሪ ገለጡ፡፡
(መስከረም 11 ቀን 1970 የወጣው ዓ.ም)
«ግፋ» የተባለ ቲያትር በዲላና በይርጋጨፌ ታየ
ዲላ፤(ኢ.ዜ.አ) ገቢው የእናት አገር ዳር ድንበር በደሙና በአጥንቱ ለማስከበር በግንባር ቀደምትነት ለዘመተው ሚሊሺያ ጦር ስንቅ እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀው «ግፋ» የተባለ ቲያትር ሰሞኑን በዲላና በይርጋጨፌ ከተሞች ታይቶ 1950 ብር ተገኝቷል፡፡
በተመልካቹ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈው ይኸው ቲያትር ሁለት ጊዜ ለዲላ ከተማ ነዋሪዎች በቀረበባቸው ዕለታት 1ሺ187 ብር መገኘቱ ታውቋል፡፡
(መስከረም 15 ቀን 19 70 ዓ.ም)
አገር ወዳዱ መኰንን በጦርነቱ ለመሰለፍ መጡ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
አድኃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት መደበኛ የጦር ኃይሉን አሰልፎ በኢትዮጵያ ላይ የወረራ ጦርነት ማካሄድ ያስቆጣቸው በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባ የሆኑት ሻለቃ ባሻ ፅጌ ወልደመድህን ከመደበኛው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት ወደ አገራቸው መጥተዋል፡፡
በኤምባሲው በዘበኝነት የሚያገለግሉትና ቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባል የነበሩት እኝሁ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገራቸው በመመለስ ጠላትን ለመዋጋት ያነሳሳቸው ጓድ ሌተና ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ነሐሴ ፲፬ ቀን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረጉትን ብሔራዊ የክተት ጥሪ በጋዜጣ ላይ ከተመለከቱ በኋላ ነው፡፡
የሃምሳ ስድስት ዓመት አዛውንት የሆኑት ሻለቃ ባሻ ጽጌ ወልደመድኅን ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በኤምባሲው ውስጥ በዘበኝት ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በሌላም በኩል በፈረንሳይ የሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ስለአብዮታዊት እናት አገራቸው ጊዜያዊ ሁኔታ በቅርቡ በኤምባሲው ውስጥ ከተወያዩ በኋላ ፤ ለእናት አገር እርዳታ ለማድረግ መዋጮ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ኤምሴው ካስተላለፈው መልዕክት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014