ባሳለፍነው ሳምንት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ባለፉት ስድስት ወራት የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ዘርፉ ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለፉት ዓመታት እያደገ መምጣቱን ተናግረው ነበር፡፡
በተለይ ከ1996 እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በአማካይ አስር ነጥብ ሁለት በመቶ እድገት ሲመዘገብ ቆይቷል፡፡ ከዚያ በኋላ በ2008 ዓ.ም ሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲጀመር በወቅቱ የድርቅ ሁኔታም ስለነበረ እድገት ቢኖርም ከታሰበው 11 በመቶ ወደ አንድ አሃዝ ዝቅ ብሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም ምጣኔ ሀብቱ በመጠኑ የማገገም ሁኔታ አሳይቶ አስር ነጥብ ሁለት በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡ ባሳለፍነው 2010 ዓ.ም ደግሞ ሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ 2008 ዓ.ም በፊት የነበረው የእድገት ምጣኔ በየአመቱ ጭማሪ የሚታይበት ነበር፡፡ ከ 2008 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስም እድገት አለ፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀነስና የመዋዠቅ ሁኔታ የታየባቸው ዓመታት ናቸው፡፡
ይህ ዕድገት በመኖሩ ምክንያት ባለፉት ዓመታት በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት ፣በጤናና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ለውጦቹ በቂ ናቸው አይደሉም የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ እነዚህ ለውጦች በዕድገቱ ምክንያት የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ምጣኔ ሀብቱ ምንም አይነት ችግርና ስጋት የለበትም ማለት አይደለም፡፡ ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ በተከተለቻቸው አንዳንድ አሰራሮችና በተለይም ከወጪ ንግድ ጋር በተገናኘ ይሰራሉ ተብለው ባልተሰሩ ስራዎች ምክንያት ምጣኔ ሀብቱ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ስጋቶች ተደቅነውበታል፡፡
ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት ባለፉት አራት ዓመታት የወጪ ንግዱ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ የወጪ ንግዱ የተቀዛቀዘው በዋናነት የአምራች ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ልክ ባለመንቀሳቀሱና ከማዕድንና ግብርና ዘርፍ የተጠበቀውን ያህል ገቢ ባለመገኘቱ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በአማካይ 30 በመቶ የወጪ ንግድ ዕድገት ይኖራል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም የወጪ ንግዱ እንደታሰበው 30 በመቶ መድረስ አልቻለም፡፡ ይህም የሆነው የአምራች ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ባለማቅረቡና የማዕድንና የእርሻ ምርቶች በጥራትም በመጠንም በሚፈለገው ደረጃ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው እንዲሁም የዓለም ገበያ ባለመረጋጋቱና የዓለም ምጣኔ ሀብት፣ በተለይም የቻይና ምጣኔ ሀብት በመቀዛቀዙ ነው፡፡
የወጪ ንግዱ በመቀዛቀዙ ምክንያት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙን የገለጹት ዶክተር ይናገር ደሴ በማዕድን ዘርፍም የወጪ ንግዱ አሽቆልቁሏል ብለዋል፡፡ በተለይም ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ የኮንትሮባንድ ሰለባ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል፡፡ በ2006 ዓ.ም 430 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው የወርቅ ማዕድን ባለፈው ዓመት 32 ሚሊዮን ዶላር ብቻ አስገኝቷል፡፡
የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ በቀጥታ የሚያያዘው “ሪል ሴክተርስ” ከምንላቸው ከግብርና ፣ ከማዕድንና ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በተገናኘ ነው የሚሉት የባንኩ ገዢ ፣ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አወቃቀር ከ73 በመቶ በላይ ቡና ፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከመሳሰሉት የግብርና ምርቶች የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከፍተኛው የወጪ ንግድ ግኝት የሚገኘው ከግብርናው ነው፡፡ የአምራች ዘርፉ በየጊዜው ድርሻውን እያሳደገ ቢመጣም አሁንም ግን ዝቀተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የወጪ ንግዱ ተቀዛቅዟል ስንል በቀጥታ የሚያያዘው ከግብርና ዘርፉ እድገት ጋር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ ችግር ስለሆነ ዋናው መፍትሄ የአቅርቦቱን ችግር መፍታት ነው፡፡
እንደ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለፃ ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ግብዓት ከውጭ ለማስገባትና ምጣኔ ሀብቱን ለማስቀጠል ዘላቂ መፍትሄው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ማሻሻል ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የወጪ ንግዱን በጥንቃቄ በመምራት ነው፡፡ የወጪ ንግዱ በታቀደው መልኩ ካልተፈጸመ ሄዶ ሄዶ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡
ዶክተሩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ሲጠቁሙም “አንድ ሀገር የውጭ ምንዛሬ የሚያገኘው ከወጪ ንግድ ብቻ አይደለም፤ ከተለያዩ ምንጮችም ይገኛል፡፡ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በብድርና እርዳታ የውጭ ምንዛሬ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ምንጮች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የተጠቀሱት በወጪ ንግድ ከሚገኘው ምንዛሬ ጋር የሚስተካከሉ አይደሉም፤ ተጨማሪ አማራጮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የወጪ ንግዱን ከሚገኝበት የመቀዛቀዝ ሁኔታ አውጥቶ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ብለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ ሰለባ ያልሆነ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርት አለመኖሩን በተመለከተም፤ የቁም እንስሳት፣ወርቅና ቡና በብዛት በኮንትሮባንድ ንግድ ከሀገር እንደሚወጡ፣ ኮንትሮባንድ የወጪ ንግዱን አዳክሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን እንዳባባሰው፣ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር መንግሥት እየሠራ መሆኑን፣በአጠቃላይ የወጪ ንግዱን የሚጎዱ የተለያዩ ተግባራትን ለመከላከል የመፍትሔ ሃሳቦች ቀርበው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳለ ዶክተር ይናገር ደሴ ይጠቅሳሉ፡፡
ዶክተር ይናገር ደሴ እንደሚገልጹት በተጠቃሚው ዘንድ ያለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ በመሆኑና በባንኮች እጅ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ አነስተኛ በመሆኑ ሁሉንም ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ አቅም የሁሉንም ፍላጎት ማሟላት ስለማይቻል ያለው ምርጫ መሠረታዊ ለሚባሉ ዕቃዎች ብቻ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ ነው፡፡ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ከፍተኛ ክፍተት በመፈጠሩ ባንኮች በእጃቸው ያለውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ምጣኔ ሀብቱ ላይ እንዲያውሉ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ማህበር ጋር እየሰራ ነው፡፡
በመግለጫው መንግሥት በተለይ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመተግበር መቆጠቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳለና የያዝነው ዓመት በጀት ሲጸድቅ ለተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ለተወሰኑ የመንገድ ሥራዎች ብቻ በጀት መመደቡንና በጀት ይፈልጉ የነበሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መተላለፋቸው ተነግሯል፡፡
«ለአንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዋነኛው የወጪ ንግድ ነው፡፡ የምንዛሪው እጥረት የውጭ ዕዳ ክፍያ ላይም ተፅዕኖ እንዳሳደረ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሀገሪቱ ብድር ስትበደር መቆየቷና አሁን ደግሞ አጋጣሚ ሆኖ ብድሩ የሚመለስበት ወቅት በመሆኑ የብድር ክፍያው የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይ ተፅእኖ አሳርፏል፡፡ ብድሩ ሲወሰድ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የአገሪቱ የወጪ ንግድ አማካይ ዕድገት 30 በመቶ ደርሷል፡፡ ብድር የመክፈል አቅማችንም በዚያው ልክ ያድጋል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ነበር ፡፡ የውጭ ዕዳን ለማቃለል ዋነኛው መንገድ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ዕዳን የመክፈል አቅም ለማሳደግ በወጪ ንግዱ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል» ሲሉም ዶክተር ይናገር ደሴ ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጻ፣ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሀገሪቱ ዋነኛ አበዳሪ በመሆን 85 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ብድር ካቀረበችው ቻይና ጋር በተደረገ ድርድር የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘምና የወለድ መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለመደገፍ ፍቃደኛ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ከዓለም ባንክ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከሳዑዲ አረቢያ 500 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ሀገሪቱ በወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያት የገጠማትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ ትልቅ ዕገዛ አድርጓል፡፡
የብድር ጫናውን ለመቀነስ ሌሎች እርምጃዎችም እየተወሰዱ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተሩ የሀገሪቱ የብድር ሁኔታ በዚህ መልኩ ሊቀጥል ስለማይገባ አሁን ያለው የብድር ጫና እስኪቃለል ድረስ መንግሥት በአጭር ጊዜ የሚከፈልና ከፍተኛ ወለድ ያለው ብድር መበደር ማቆሙን ዶክተር ይናገር ደሴ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉና በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የወጪ ንግዱ በየ15 ቀኑ እየተገመገመ መሆኑ ተነግሯል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በየትናየት ፈሩ