ሐቅን እንደ መግቢያና መግባቢያ
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የአገርነትና መንግሥትነት ታሪክ ያላት ጥንታዊ አገር ፤ ከማንም ቀድማ ለዓለም የሥልጣኔ እርሾን የጣለች፣ የራሷ የሆነ ወግ፣ ባህልና ሥልጣኔ ያላት፤ በፍትሕና በእኩልነት የምታምን፣ ከሁሉም ጋር በመከባበርና በመተባበር መኖርን የምትመርጥ፣ በፍቅርና በትህትና እንጂ በእብሪት ተሸንፋ የማታውቅ አገር ናት፡፡ ብትጎለብት በኃይሏ የማትመካ፣ ደካማን ለማገዝ እንጅ ለማዘዝ ክንዷን የማታነሳ፣ አልፋ የማትነካ አልፎ ለመጣባት ደግሞ ክብሯን የማታስነካ፣ በኃይል ሌላውን ወርራ የማታውቅ ኃይል አለኝ ብሎ ሊወራት የመጣ ወራሪን ደግሞ አሸንፋ እንጅ ተሸንፋ የማታውቅ ታላቅ አገር ጭምር ናት ፡፡ በገዛ ክንዷ ነጻነቷን አስከብራ በክብር የኖረች፣ አብዛኛው ታሪኳ በአስደናቂ የጀግንነትና የክብር መዝገብ የተሞላ ነው።
ክብርና ዝና ተከፍሎበታል
ታዲያ ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም ዙሪያ እንዲህ በክብር፣ በኩራት፣ በጀግንነት መታወቅ የቻለው ከምን ተነስቶ ነው? ይህ ስምና ዝና እንዲሁ ዝም ተብሎ የተገኘ ነውን? እርሷ ስለፈለገች ነው በዚህ ስምና ዝና በዓለም ዙሪያ የታወቀችው? ወይንስ የዓለም ሕዝብ በችሮታ ሰጥቷት ይሆን? ሁሉም አይደለም፡፡ የክብር፣ የኩራት፣ የጀግንነት ስሟ ዝም ተብሎ የተገኘ አይደለም፣ የዓለም ሕዝብ በችሮታ የሰጣትም አይደለም፡፡ ይህ ስምና ዝና በምኞት ሳይሆን በሥራ የመጣ፣ በተግባር የተፈጸመ፣ በመፈለግ ሳይሆን በመሆን የተገኘ እውነተኛ ስም
ነው፡፡ ይህ ስምና ዝና፣ ይህ አኩሪ የጀግንነትና የክብር ታሪክ እንዲሁ በቀላል ሳይሆን ውድ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘ ነው፡፡
በአንድ ነገር ላይ ከራስ አልፎ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ድርጊቱ በተግባር ተደርጎ፣ አድራጊውም አስመስሎ ሳይሆን ድርጊቱን በተግባር ፈጽሞ፣ በሃሳብ ሳይሆን በተግባር ሆኖ መገኘት አለበትና፡፡ እናም የአገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ስምና ዝና የእኛም የልጆቿ የክብር፣ የኩራት፣ የጀግንነት ስማችን ዝም ተብሎ የተገኘ አይደለም፣ የዓለም ሕዝብ በችሮታ የሰጠንም
አይደለም፡፡ የምንኮራውና የምንከበረው በከንቱ መከበርና መወደስ ስለምንፈልግ አይደለም፡፡
ታላቋ አገራችን ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያውያን በጀግንነታችንና በኩሩነታችን በዓለም ሕዝብ ዘንድ የታወቅነው የጀግንነትን ጠባይ በገቢር ገልጠን፣ የሚያኮራ ምግባር ፈጽመን በእርግጥም ኩሩ ሆነን ስለተገኘን ነው፡፡ በምኞት ሳይሆን በተግባር አድርገው፣ ተመችቷቸውና ሁሉም አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ሳይሆን የሚገጥማቸውን ፈተና ሁሉ ፊት ለፊት በጽናት በመጋፈጥ በእሳት ተፈትነው አልፈው፣ ከሌላ አካል በመጠበቅ ሳይሆን እንዲሆንላቸውና እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ሁሉ በራሳቸው አድርገው፣ ከኋላ ሆኖ በመከላከል ሳይሆን ከፊት እየቀደሙ በመዋደቅ አባቶቻችንና እናቶቻችን በሠሩት አኩሪ ታሪክ ነው በታወቅንበት ስም መታወቅ የቻልነው፡፡
በፈጸሙት አኩሪ የጀግንነት ገድል፣ በየዘርፉ ባስመዘገቡት ዘመን አይሽሬ ድል፣ በወርቅ ቀለም ጽፈው ባወረሱን ታሪክ የማይሽረው አኩሪ ጀግንነት፣ በሥራ ተጽፎ በድርጊት ታትሞ በተሰጠን ሕያው የታሪክ መጽሐፍ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በጀግንነትና በኩሩነት በዓለም ላይ ልንታወቅ የቻልነው፡፡ አባቶቻችንና እናቶቻችን በተግባር ሠርተው፣ ተከብረው ስላስከበሩን፣ ኮርተው ስላኮሩን ነው በታወቅንበት የክብርና የጀግንነት ስም መታወቅ የቻልነው፡፡
ጥበብን ከጀግንነት አዋህደው ታላቅ አገርን የፈጠሩ፣ የመሩና ያወረሱን ጀግኖች እናትና አባቶቻችን ጀግንነትን በተግባር ፈጽመው፣ ከማንም በላይ ተፈትነው ማንም የማይችለውን ችለው፣ በክብራቸውና በማንነታቸው የመጣባቸውን ሁሉ ድል አድርገው አሸንፈው፣ በእርግጥም የሚያስከብርና የሚያኮራ ታሪከ ሠርተው በማሳየታቸው ነው በክብርና በጀግንነት መታወቅ የቻልነው፡፡
ዛሬም እናሸንፋለን! ለምን?
መውደቅ መነሳት፣ ማግኘት ማጣት፣ መውጣት መውረድ፣ መብለጥ መመበለጥ፣ መቅደም መቅረት፣ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪይ ነው፡፡ ታሪክ ስንልም በዋነኝነት የሰው ልጆችን የሚመለከት ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ታሪክ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የሰው ልጆች በተለያዩ የዘመን ማእቀፎች ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የግሪክ ታሪክ፣ የአሜሪካ ታሪክ… ወዘተ ስንል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎች (የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ)፣ ግሪክ ውስጥ ያሉ ሰዎች (የግሪክ ሕዝብ ታሪክ)፣ የአሜሪካ ሰዎች (ሕዝብ) ታሪክ ማለታችን ነው፡፡ እናም መውጣትና መውረድ፣ መውደቅና መነሳት በግለሰብ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በአገራት ታሪክ ውስጥም አለ፡፡ በዚህም በአንድ የዘመን ክፈፍ ውስጥ ኃያል ይባል የነበረ አገር በሌላ ዘመን ተመልሶ ከተራ ተርታው አገራት ምድብ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የብዙ አገራት ታሪክ በአጠቃላይ የዓለም ታሪክ የሚነግረንም ይህንኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክም ከዚሁ የተለየ አይደለም፤ እርግጥ ነው እንደ ብዙዎቹ አገራት (ከብዙዎችም ቀድማ) ሥልጣኔን ጀምራ፣ በሥልጣኔ አብባና ጎምርታ፣ ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ብላ በእድገት ማማ ላይ በአሁኑ ዘመን ነባራዊ የእድገትና የልዕልና መለኪያ ስትመዘን በብዙ ወደኋላ መቅረቷ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ አገራት እንደ አገር፤ ሕዝባቸውም እንደ ሕዝብ በየትኛውም ዘመን ከከፍታቸው የማይወርዱበት የየራሳቸው ዘመን አይሽሬ የታላቅነት መገለጫ፤ የየግላቸው ተፈጥሯዊ የልእልና ሥሪት
አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ታሪኳን ስንመረምር በማንኛውም ዘመን የማያስሰው ተፈጥሯዊው የኢትዮጵያ ማንነታዊ ሥሪት ነጻነት ነው፡፡ ከዓለም ኃያላን መካከል አንደኛዋና ቀዳሚዋ በነበረችበት ጊዜ ያኔም፣ ከመጨረሻዎቹ መናኛዎቹ መካከል ተቀምጣ ዛሬም… ነገም ኢትዮጵያ በነጻነቷ ቅንጣት ከቦታዋ ተንሸራታ አታውቅም፡፡
ከጥንት ጀምሮ እስከ ቅርብ የአድዋና የፋሽስት ወረራ ድረስ በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ የተደጋገሙ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። በዚህም ጠላቶቻችን ያተረፉት ሽንፈት፣ ውርደትና ውድቀት ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጣሊያንም ሆነ አስራ ስድስት ጊዜ ሞክራ አስራ ስድስት ጊዜ በተሸነፈችው ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ፣ በኦቶማን ቱርክም ሆነ በዚያድባሬዋ ሶማሊያ… ክብሯንና ነጻነቷን ለመድፈር በሞከረ ማንኛውም ኃያል ነኝ ባይ ወይንም እብሪተኛ ምድራዊ ኃይል ኢትዮጵያ በታሪኳ ተሸንፋ አታውቅም፡ ፡ ክብርና ነጻነት ለኢትዮጵያ ሲመቻት የምታጠልቀው ሲቸግራት የምታወልቀው የጌጥ እቃዋ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ በየትኛውም ሁኔታ ለድርድር የማታቀርበው፣ እንደ ዓይኗ ብሌን ሁል ጊዜ የምትጠብቀው የማያልቅ የማያረጅ ውድ የዘወትር ልብሷ ነው!፡፡
እኛም ዛሬ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ስንል ከገዛ ማህፀኗ ተወልዶ “ክብሯን ረግጬ በኃይል አንበርክኬ እኔ ብቻ እገዛታለሁ፣ ካልሆነ አፈርሳታለሁ” ብሎ እየወጋን እንዳለው አሁናዊው ጠላታችን እንደ አሸባሪው ሕወሓት እና ሌሎችም እንደሚሉት ከአጉል እብሪትና ከተራ ጉራ ተነስተን ሳይሆን ደግመን ደጋግመን በተግባር ካደረግነው የራሳችን የአሸናፊነት ታሪክ ተነስተን ነው፡፡ ምክንያቱም አላዋቂዎችና የትንሽነትና ታህተ ሰብዓዊነት፣ የአጥንት ቆጠራና የኢምክንያታዊና ግዑዛዊ ፖለቲካ መስራችና አቀንቃኝ የሆኑት ትሕነግና መሰሎቻቸው እንደሚሉት ታሪክ ተራ ተረት ተረት ሳይሆን የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር ሆነውና ችለው ያረጋገጡበት፣ ዛሬን ከትናንትናና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ፣ የአሁኑና መጪው ትውልድም መሆንና ማድረግ እንደሚቻል በወሬ ሳይሆን በድርጊት የሚማርበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነው።
ታሪክን በትክክል ያጠኑ እውነተኛ አዋቂዎችና ታላላቆቹ የዘርፉ ሊቃውንት የሚሉትም ይህንኑ ነው፡፡ “ታሪክ ማለት የሰው ልጅ ስለ ራሱ የሚያውቅበት ግላዊ ዕውቀት ነው… ሰዎች ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ለማወቅ የሚያስችለው ብቸኛው ፍንጭ ሰዎች ከዚህ ቀደም የሠሩት ሥራ ነው፡፡
የታሪክ ዋነኛው ፋይዳ ̔ሰው ምን ሠራ?҆የሚለውን ለእኛ ለሰው ልጆች ማስተማርና በዚህም ‛ሰው ምንድነውዕዕ የሚለውን እንድናውቅ ማድረግ ነው” ይለናል አር. ጂ. ኮሊንግውድ፡፡ እናማ ታሪክ አሸናፊነትን በተግባር የምንማርበት የመቻል ቤተ ሙከራ ነውና፣ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ማድረግ የቻሉትን እኛም ማድረግ እንችላለንና ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች! እናማ የአሸናፊነት፣ የነጻነትና የጀግንነት አኩሪ ታሪካችን ሁለ ነገራችን የተመሰረተበት፣ ማንነታችን የተገነባበት ሥጋና ደማችን፣ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን አጠቃላይ ሕዝባዊ ሥነ ልቦናችን የተሠራበት፣ በየትኛውም ጊዜ የማይለወጥ፣ በማንኛውም ጊዜ የማያስስ የታላቋ አገራችን የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ሥሪት ነውና እኛም አሁን ማሸነፍ እንችላለን፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች! ማለት ስለሆነ ከምንም በላይ ታሪክ ሥነ ልቦና ነው፡፡
እኛም አባቶቻችን አሸናፊዎች እንደነበሩ፣ በዚህም በዓለም ላይ ተከብረው እንደኖሩ እኛንም አስከብረውና አኩርተው እንዳኖሩን እኛም ከሃዲውንና ዋናውን አሁናዊ የህልውና ጠላታችን ጨምሮ የክብራችንና የነጻነታችን ጠላት የሆኑ ማናቸውንም የዘመናችንን ጠላቶች ማሸነፍ እንችላለን፤ ኢትዮጵያም ዛሬም ጠላቶቿን አሸንፋ በክብርና በነጻነት ከፍ ብላ ትኖራለች!
እንዴትና በምን?
ኢትዮጵያ ዛሬም እንደምታሸንፍ ከተግባባን በዛሬው ዘመን ላይ የምንኖር እኛ አሁኖቹ ኢትዮጵያውያን እንዴትና በምን ነው እንደ አባቶቻችንና እናቶቻችን የገጠመንን ክፉ የህልውና ጠላት አሸንፈን በክብርና በነጻነት መቀጠል የምንችለው የሚለውን በጣም በጥቂቱ ለማመላከት እሞክራለሁ፡፡
እጅግ የቅርቡንና በዓለም ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ልጅ ፍጡር ዘንድ እንድንከበርና እንድንኮራ ያደረገንን አንዱንና ዋነኛውን የነጻነትና የክብር ታሪካችን በማሳየነት በማንሳት ልጀምር፡፡ እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ህዝብ “ምንጊዜም የበላይ ነን” ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፍንና እናም ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ታሪክ የሠራነው አድዋ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን! በዚህም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው የሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር የተገኙ ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ምክንያት፣ ድል አመላካች፣ የአሸናፊነት ምልክት የሆንንን ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያውን ነን! ታዲያ ይህን እንዴት ልናደርገው ቻልን? አጭርና ግልጽ መልሱ፡- በተባበረ ክንዳችንና በአንበሳ ልባችን ነው፡፡
እንዴት ለሚለው፤ በአሁኗ ኢትየጵያ የምንገኝ እኔና የእኔ ትውልድ ጀግንነታችንና ኩሩነታችንን አስጠብቀን ለመቀጠል እንደ አባቶቻችን በአንድነት መመከትና በጀግንነት ዋጋ በመክፈል የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኚስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት፤ ይህንን የምናደርገውና እንደ አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ መስራት የምንችለው “በፌስቡክና በወሬ” ሳይሆን በሥራና በተግባር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ እንደ አባቶቻችን በጀግንነት ታግለን በድል መወጣት ስንችል ነው እኛም በኩራት ኢትዮጵያም በክብር መኖር የምትችለው፡፡
ትውልዱ እንደቀደምቶቹ አባቶቹና እናቶቹ ጀግና ነኝ ለማለትና ኩሩ ሆኖ ለመገኘት በምኞት ሳይሆን በተግባር ማድረግ የሚገባውን አድርጎ መገኘት፤ የራሱን ዘመን ሥራ ሠርቶ ጀግንነትን ፈጽሞ እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ፣ እንደ እናት አባቶቹ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ በኩራት በክብር ለመኖር የሚያስችለውን ታሪክ አድርጎና ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ዛሬም ታሸንፋለች፤ ለዘላለምም በክብር ትኖራለች!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014