በዓለም ላይ ዘመናዊ የቅኝ ግዛት ታሪክ ስድስት ምዕተ አመታትን ወደኋላ ያስጉዘናል። በተለይ እአአ ከ1488 እስከ 1492 አውሮፓውያን የዓለምን በርካታ ክፍሎች ለመቆጣጠር የሄዱበት ወቅት ለቅኝ ግዛት መስፋፋት መሠረት የጣለበት ወቅት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በወቅቱ አፍሪካን ለመያዝ የተንቀሳቀሱት ምዕራባውያን በርካታ የአፍሪካ አካባቢዎችን መያዝ ችለው ነበር። በዚህ ወቅት የነበረው እንቅስቃሴ ደግሞ በቀጥታ በጦርነት ሳይሆን በተለይ የንግድ እንቅስቃሴን መሠረት ያደረገ ነበር። ይህ አካሄድ አሁን እየተሰሩ ካሉ የቅኝ ግዛት አካሄዶች ጋር በብዙ ነገር ይመሳሰላል። በወቅቱ በተለይ ፖርቹጋል፤ ግሪክ፤ ጥንታዊ ሮም እንዲሁም አፍሪካዊቷ ግብጽ ይህንን ካስፋፉ አገራት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
“Age of capital” በመባል በሚታወቀው በዚህ ዘመን ዋነኛ የቅኝ ግዛት ፍላጎት መንስኤ የንግድ እንቅስቃሴን የማስፋት እና ተጨማሪ ሃብት የማግኘት ፍላጎት ማደግ ነበር። በተለይ በወቅቱ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ከምዕራባውያን ወደአፍሪካና ሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚደረግ በመሆኑ ይህንን ተከትሎ ከነዚህ አገራት ሃብትን ወደአውሮፓ የመውሰድ እንቅስቃሴንም ያካተተ ነበር። ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ወደሃይል በመዞር በርካታ አገራት በምዕራባውያን ቁጥጥር ስር እንዲውሉና ሃብታቸው እንዲዘረፍ ምክንያት ሆኗል። በዚህም የተነሳ እአአ እስከ 1800 ድረስ አውሮፓውያን የዓለምን 35 ከመቶ ተቆጣጥረው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በኋላ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋት ይህንን የቅኝ ግዛት ፍላጎት ይበልጥ አስፋፋው። በዚህ ጊዜ ታዲያ ከተፈጥሮ ከሚገኝ ሃብት ባሻገር የሰው ልጅም ልክ እንደእቃ የዚህ ሰለባ የሆነበት ወቅት ነበር። በዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች በባርነት መያዝ የጀመሩበት ወቅት ነበር። ከዚህም አልፎ ምዕራባውያኑ የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴያቸውን ይበልጥ በማጠናከር አገራትን በሃይል ወደመያዝ የሄዱበት ወቅት ነበር።
አንደኛው የዓለም ጦርነት በሚነሳበት 1914 አካባቢ ምዕራባውያኑ የዓለምን 84 ከመቶ መቆጣጠር ችለው እንደነበርም ይነገራል። ይህ ታሪክ ሊቀየር የቻለው ታዲያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በርካታ አገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ አድርጓል። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት የተላቀቁትም ከዚህ ጦርነት በኋላ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷን ሚና ተጫውታለች።
አሁን አሁን የሚታየው የዓለም ሁኔታ ይህንን የቆየ የቅኝ ግዛት ታሪክ ለመመለስ በተለያዩ አግባቦች የሚደረጉ እቅስቃሴዎችና ጥረቶች ተጠናክረው እንደቀጠሉ አመላካች ነው ። በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ምዕራባውያኑ በቀዝቃዛው ጦርነት ዓለምን ዳግም በእጃቸው ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ አሜሪካ ሌላኛዋ ተባባሪ በመሆን ይህንን ቡድን ተቀላቅላለች። በዚህ ጽሑፍም በተለይ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫናና ርብርብ በጥቂቱ ለማስቃኘት እሞክራለሁ።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር ናት። ከዚህም አልፎ በአፍሪካ በታሪክም ሆነ በተፈጥሮ ሃብት ግዙፍ ከሚባሉ አገራት ስሟ በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ አገራ አንዷ ናት። በተለይ በመልከአ ምድራዊ አቀማመጧ በነዳጅ ከበለፀጉት የባህረ ሰላጤ አገራት ጋር በቀጥታ የምትገናኝ እና ለአውሮፓም መዳረሻ የሚሆነው አፍሪካ ቀንድ ማዕከል መሆኗ ተመራጭ አገር ያደርጋታል። ይህ ደግሞ የብዙዎች አይን እንዲያርፍባት አድርጓታል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ምዕራባውያን ለሚያስቡት ዳግም የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ የማይመች ታሪክ ያላት አገር ናት። ከዚህ ቀደም በቅኝ ግዛት ታሪክ ቅኝ ያልተገዛች እየተባለ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሳ መሆኑ እንዲሁም ለብዙ አፍሪካ አገራት የነፃነት ተምሳሌት የመሆኗ ታሪክ ከመዝገብ ላይ ካልተፋቀ ነገም በዚህ ታሪክ ተነሳስተው እምቢተኛ ለመሆን የሚንቀሳቀሱ አገራት መኖራቸው አይቀርም።
ስለዚህ ይህንን “ኢትዮጵያ” የሚል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ የሆነ መጠሪያ በቅድሚያ ማጥፋት ዋነኛው የምዕራባውያን ፍላጎት ነው። በዚህ የተነሳ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ለማጥፋት ገና ከቅኝ ግዛት ማግስት የጀመረው በብሔር የመከፋፈል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
እንግሊዞች ከጣልያን ወረራ ማግስት በኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው እንቅስቃሴ ካስቀመጧቸው የቤት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያን በብሔር በመከፋፈል አሻራ ማኖር አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት አገራት ጋር ስትወዛገብ እንድትኖር የሚያስችል ግልጽነት የሚጎድለው ድንበር ማበጀት ሌላኛው የረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ ነው። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ካለፈው አንድ ምዕተ አመት ወዲህ አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጎረቤት አገራት ጋር በሚነሱ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብ ውስጥ እንድትገባ ተደርጓል።
በዚህም የተነሳ አንዴ ከሱዳን፤ ሌላ ጊዜ ከሶማሊያ ጦርነት እንዲካሄድ ተደርጓል። ከዚህም አልፎ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትለይ ተደርጓል። በዚህ ብቻ አላበቃም። ዛሬም ውዝግቡ ብሔርን መሠረት እያደረገ እነሆ የቤት ሥራችን ከብዶ የኢትዮጵያ የእድገት ሾተላይ ዛሬም ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ሌላው ቢቀር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ እንኳን ለምን ማደግ አቃታት የሚለው ጥያቄ የብዙዎች መልስ የሌለው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ላለፉት መቶ አመታት ከውጭ ያስገባቻቸው የጦር መሳሪያዎች ከሌሎች ሃብቶች ይልቅ በብዙ እጥፍ የሚበልጡ ናቸው። ይህ ዘላቂ እንዲሆን በብዙ መልኩ የሚፈለግ ነው።
ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ አመታት በፊት ከነበረችበት የስልጣኔ ማማ ወርዳ ታች ከተገኘች በኋላ ዳግም ማንሰራራት ያልቻለችው ለምን ይሆን የሚለው ዛሬም መልስ ያላገኝ ጥያቄ ነው። ትላንት ከኋላዋ ተነስተው ከቅኝ ግዛት የተላቀቁ የአፍሪካ አገራት ጭምር ከኋላዋ እየተነሱ ሲቀድሟ ከእንቅልፏ መንቃት ያልቻለችው ለምንድነው ሲባል ይኸው የቆየው የምዕራባውያን ሴራና አሻጥር መልስ ሆኖ እናገኘዋለን።
እስኪ የቆየውን ታሪክ እናቆየውና ካለፈው ግማሽ ምዕተአመት ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ እናንሳ። አምሳ አመት ለአንዳንድ አገራት ከድህነት ወደ ሃብታምነት መለወጥ የቻሉበት በቂ ጊዜ ነው። እነኮርያና ቻይና ደግሞ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው። ኢትዮጵያም ባለፉት አምሳ አመታት በአብዛኛው ያሳለፈችው በጦርነትና እርስ በርስ ግጭት በኋላም በሕወሓት የሴራ አገዛዝ ሥር ነው።
በመጀመሪያዎቹ አካባቢ ሕወሓት ለ17 አመታት ኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ከሞላ ጎደል በብዙ መልኩ እንዲወድም ተደርጓል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ያተረፈችው ነገር ቢኖር የድርቅ፣ የረሃብ እና የጦርነት ተምሳሌት መሆንን ብቻ ነበር። በዚያን ጊዜ አሜሪካ ከሞላ ጎደል ሕወሓትን ትደግፍ ነበር። ዛሬ ዳግም ኢትዮጵያ ምድረበዳ ለማድረግ እየታተረ ያለው አሸባሪው ሕወሓት ለስልጣን ሲበቃ አሜሪካ ከጎኑ ነበረች። በ1983 ዓ.ም ወደዙፋን ሲወጣም አሜሪካ ሚዜ ከወንበሩ ላይ አኑራዋለች።
የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ቡድን ለ27 አመታት ኢትዮጵያ ወደኋላ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግና ህዝቦቿንም በቤታቸው ሲኦል ሲያደርግባቸው በአብዛኛው ከጥቂት የውሸት ማስፈራሪያዎች ውጭ አንዳችም ጫና ለማድረግ አልሞከረችም ነበር። በአብዛኛው ይህ ቡድን ብዙዎችን በየእስር ቤቱ እያጎረ ሲያሰቃይ አይታ እንዳላየ በመሆን ከማለፍ ውጭ አንዳችም ጥረት አላደረገችም።
ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ አዲስ ፀሃይ መውጣት ስትጀምር አሜሪካ ይህ ብዙም አልተዋጠላትም። ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህንን ለውጥ ለማበረታታት የሄዱበት ርቀት እምብዛም ነበር። በተለይ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እየተጠናከረ ሲሄድ ብዙም ያላማራቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ ማሴር ጀምረዋል። አሜሪካም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ብዙ እየጣረች ነው። ለዚህ በዋናነት የተጠቀመችው ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ ግብጽ የጀመረችውን ጥረት በመደገፍ ኢትዮጵን ማዳከም ነበር።
በወቅቱ አሜሪካ ታዛቢ በሚል ሰበብ ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የሶስትዮሽ ውይይት በመጥለፍ ለግብፅ የወገነ አቅጣጫ በመንደፍ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት አድርጋለች። በዚህም የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ግብጽ ግድቡን በቦምብ እንድትመታ ጭምር የሚያነሳሳ ንግግር በማድረግ አሳፋሪ የወገንተኝነት ተግባር ፈጽመዋል።
አሜሪካ በዚህ ብቻ አላበቃችም። በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና በማጠናከር ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጭምር በመጨመር ጫናውን ለማጠናከር ብዙ ጥራለች። ለዚህ ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት አንዱ ነው። ይህ ምክር ቤት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመሰረተበት አላማ ውጭ በውሃ ጉዳይ የተሰበሰብ ምክር ቤት ነው። ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ጉዳይ እሱና መሰሎቹ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 11 ጊዜ በመሰብሰብ ታሪክ ሰርተዋል። ይህ ለምን ሆነ? ያልተመሰለ ጥያቄ ነው።
ሌላው የአሜሪካ አድሎአዊነት መገለጫ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የምትወስናቸው ውሳኔዎች ናቸው። አጎዋ አንድ ማሳያ ነው። አጎዋ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የሰጠችው ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት እድል ነው። ይህ እድል የተሰጠው ደግሞ በተለይ የአፍሪካ ምርቶች በአሜሪካ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግና በአፍሪካ የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ነው።
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተከፍተው ወደስራ ገብተዋል። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሙት የአጎዋን ገበያ ነው። በዚህም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል እንዲያገኙ ተደርጓል። ይሁን እንጂ አሜሪካ ይህንን እድል በዚህ ወቅት ለመከልከል መነሳቷ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማድረግ አሸባሪውን ቡድን ለመታደግ ነው።
የሚገርመው ነገር ደግሞ አሜሪካ ይህንን ማዕቀብ የጣለችበት ጊዜ ነው። አሜሪካ የአጎዋ ተጠቃሚነትን ክልከላ ያደረገችበት እለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የተፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ያካሄደውን ጥናት ይፋ ለማድረግ ሰዓታት ብቻ ሲቀሩት የተጣለ መሆኑ ነው። አሜሪካ ለዚህ ውሳኔ የቸኮለችበት ምክንያትም ሪፖርቱ በአብዛኛው ኢትዮጵን ነፃ የሚያወጣ በመሆኑ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ምክንያት የሚያሳጣ መሆኑ ነው። ስለዚህ ከሪፖርቱ በፊት ማዕቀብ መጣሏ ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም ከጦርነቱ ጋር የተገናኘ ሳይሆን የሽብር ቡድኑን የመደገፍና ዳግም ወደሥልጣን የመመለስ ጥረት መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
አሜሪካና አጋሮቿ የሚደርጉት ርብርብ በብዙ መልኩ የሚገለፅ ነው። በተለይ ሚዲያዎቻቸው የውሸት መረጃዎችን ጭምር በመፈብረክና በማሰራጨት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ብዙ ጥረዋል፤ ለምሳሌ በቅርቡ እንኳን የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ጥምር ግብረ ሃይሉ ያወጣውን ሪፖርት በተሳሳተ መንገድ ለመተርጎም የሄደበት ርቀት ሌላው ማሳያ ነው። በዚህ ላይ እነሮይተርስ በተለይ የጦርነቱን አጀማመር በተመለከተ ራሱ የሽብር ቡድኑ አምኖ ተቀብሎ እያለ እና በሪፖርቱም በግልጽ ተመላክቶ የተቀመጠን ጉዳይ ለመቀልበስ የሚሄዱበት መንገድ ሲታይ ሚዛናዊነት የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደማይታሰብ ያመላክታል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቷ ይታወሳል። ይህ አዋጅ ወደህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት ግን አሜሪካ በዚህ ህግ ላይ ቅሬታዋን ለማቅረብ የቀደማት አልነበረም። ገና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ረቂቁን ማቅረቡን ተከትሎ አሜሪካ መንቀሳቀስ አልቻልኩም በሚል ይህንን ውሳኔ ለመቀልበስ የሄዱበት መንገድ ምን ያህል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው እንደሚፈተፍቱ ትልቅ ማሳያ ነው። የአሜሪካ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለው ጫና በአጠቃላይ ሲታይ በእጅ አዙር የሚደረግ የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ነው። በኔ ስር ሆናችሁ እና እኔ የምላችሁን ብቻ ተግባራዊ ካላደረጋችሁ አጠፋችኋለሁ የሚል እብሪት ነው።
ለአሜሪካ አሸባሪነት የሚለው ፅንሰ ሀሳብ እንኳን የተለየ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ለነሱ ሲሆን አሸባሪነትም ሆነ አሸባሪዎች ፈጽሞ ለድርድር የሚያበቃ ስብእና የላቸውም። ስለዚህ በአሸባሪዎች ላይ የሚወሰደው ማንኛውም እርምጃ ትክክል ነው። ለዚህ ደግሞ በአፍጋኒስታን ላይ ያደረጉት የ20 አመታት ወረራ ማሳያ ነው። አሜሪካ አፍጋኒስታንን ወርራ ለ20 አመታት ስትገዛት የኖረችው ቢንላደን ጎድቶኛል በሚል መነሻ ነው። ከዚያ በኋላም ይህንን የአሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በብዙ ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተዋል። ብዙ ጉድጓድ ምሰዋል፤ ብዙ አገራት ላይ ጫና አሳድረዋል። በዚህ ጊዜ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ሁሉ ያለምህረት እርምጃ ሲወሰድበት ኖሯል። ሌላ ሶስተኛ አማራጭ የሚል እድልም አልነበረም።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ከአሸባሪም በላይ የሆነባት ሕወሓት በዚህ መልኩ ብዙ ጫና ሲፈጥር አሜሪካ አይታ እንዳላየ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ከጎኑ ቆማ ዳግም ልታድነው መነሳቷ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሚያስብል ነው። ሽብር ለአሜሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ ያው ሽብር ነው። እዚያ ወንጀል፣ እዚህ ሕልውና የሚሆንበት ምንም አይነት ምክንያት የለም።
በአጠቃላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለው ጫና በጫካ ውስጥ የሚደረግ የእንስሳት የአኗኗር ዘይቤን ያስታውሰናል። በሴሬንጊቱ ጫካ ውስጥ በርካታ እንስሳት አብረው ይኖራሉ። አንበሳ፣ ጎሽ፣ ሚዳቋ፣ ጅብ፣ ወዘተ። በዚህ ግዛት ታዲያ ሕግ የሚባል ነገር የለም። ሕጋቸው ጉልበት ነው። የነዚህ ሁሉ ንጉስ ደግሞ አንበሳ ነው። አንበሳ ሰነፍ እንስሳ ነው። ሥራው መተኛትና ሲነሳ ያገኘውን መብላት ነው። ተኝቶ ሲነሳ ከፊቱ ያገኘውን ጎሽም ሆነ ሚዳቋ አሳዶ ይይዛል፤ ይበላል።
ተበይዎቹ እንስሳት ካንተ ጋር ምን አገናኘን፤ ምንህን ነካን ብለው ሊከራከሩ አይችሉም፤ ከመበላት ውጭ። ነገር ግን አልፎ አልፎ ጎሾቹ ሲተባበሩ እነዚህን አንበሶች እስከማጥቃት የሚሄዱበት ሂደት አለ። ዓለማችንም ልክ እንዲሁ እየሆነች ነው። ጉልበተኞች የሚኖሩባት፤ ጉልበት የሌላቸው ደግሞ የሚጠቁበት፤ ስለዚህ ዋነኛው መፍትሄ መተባበርና የራስን አቅም ማጎልበት ብቻ ነው።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2014