የጀግናው ደም ጥሪ፤
“እጅ ስጥ አለኝ ፈረንጅ፣
እጅ ተይዞ ሊወሰድ፤
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ፣
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ።”
እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ስንኞች በአንጋፋው ብዕረኛ በጸጋዬ ገ/መድኅን የተቀመሩት በ1957 ዓ.ም ደሴ ላይ ነበር። “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ዘለግ ያለ ግጥም የጀግናውን ንጉሥ የመጨረሻውን የጣር ሰዓታት በሚገባ መግለጽ ብቻም ሳይሆን ልክ እንደ ተዋጣለት ሥዕል በምናባችን ውስጥ ምስል የመከሰት አቅሙ ከፍ ያለ ነው።
የግጥሙ ትኩረት በዋነኛነት በንጉሡ ላይ ያተኮረ ይሁን እንጂ መታሰቢያ የተደረገው “ተከታታይ ትውልዶችን ይወክላል” ተብሎ ለተገመተውና አባቱ ያንን መራራ ጽዋ ሲጎነጩ የሰባት ዓመት ታዳጊ ለነበረው ለልጃቸው ለደጃዝማች ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ስለመሆኑ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ሰፍሯል።
“የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ” በሚል ርዕስ ግርማ ኪዳኔ የተባሉ ተመራማሪ ከዛሬ ሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዓለም አቀፍ ጉባዔ ካቀረቡት ጽሑፍ ውስጥ ጥቂት ዐረፍተ ነገሮችን እንጥቀስ። “የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ወደማቆሙ ተቃረበ። የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በየአቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ።”
“ከቀኑ ዐሥር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ያሰማራቸው ሁለት የአይሪሽ ወታደሮች የተኩስ ድምጽ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደ ደረሱ ‹አንድ ጀግና በራሱ ላይ የሽጉጥ ቃታ ስቦ› ወድቆ አገኙት። …የአፄ ቴዎድሮስ መሞት በይፋ እንደታወቀ የእንግሊዝ ወታደሮች ደስታ በተመላበት ሁኔታ ባንዲራቸውን በማውለብለብ በመቅደላ ተራራ ላይ ጩኸታቸውን አስተጋቡ። ብሔራዊ መዝሙራቸውንም አሰሙ።”
ይህ ጀግና የአገር ዋልታ ነፍሱን በእጁ ቆርጦ ለአገሩ የሉዓላዊነት ክብር ከወደቀ እነሆ 154 ዓመታት አስቆጥሯል። ጸጋዬ ገ/መድኅን ያልኖረበትን ዘመን ከኖረበት ዘመን በተሻለ ገለጻ በጥበበ ቃላት ቀምሮ ካስተላለፈልን ደግሞ ዘመኑ ወደ ስድስት ዐሠርት ዓመታት እየገሠገሠ ነው። “ገጣሚው እምባውንና የብዕሩን ቀለም አዋህዶ” የቃተተው ሥጋው ደሴ ላይ ሆኖ መንፈሱ ግን መቅደላ አምባ ላይ ገዝፋ ተነስታ እየተንቀሳቀሰች እንደነበር መገመት አይከብድም። ይህንኑ ግጥም ነፍሰ ሄር አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም በአስደናቂ አቀራረብ ተውኖት እንደነበርም አይዘነጋም።
የጀግናው ንጉሥ የአፄ ቴዎድሮስ የደም ጥሪ ዛሬም በዚያው በደሴና በዙሪያው ከአረመኔው አሸባሪ ወራሪ ጋር እየተካሄደ ባለው የፍልሚያ ጎራ እየተዋደቀ ላለው የዘመኔ ጀግና “ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ” የሚለው መልዕክት ወቅታዊ ስለሆነ እነሆ መልዕክቱን አስታውሰን እናልፋለን።
ፈሊጡን ለባለ ሊጡ፤
“እጅ ስጡ!” ወይንም “እጁን ሰጠ!” የሚሉት አገላለጾች አንድም ተፈላጊ ወንጀለኛ ወይንም አጥፊ ከተሸሸገበት ወጥቶ ለፍትህ ተጠሪ ቡድኖች ወይንም ተቋማት ራሱን ለቅጣት ሲያቀርብ ወይንም እንዲያቀርብ የሚጠየቅበት ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። በሌላ ትርጉሙም በጦር ሜዳ ፍልሚያ የጠላት ወገን እንዲማረክ ሲፈለግ “እጅህን ስጥ!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ይተላለፍለታል። በወዶ ገብነት ወይንም በተሸናፊነት እጁን አሳልፎ ለመስጠት ምርጫውን ያደረገ “ድፍን ቅል ፈሪ” ከሆነም “እጅህን ስጥ!” ሲባል ሱሪው ከስር እየረጠበ እጁን ለሠንሠለት፤ እግሩን ለእግር ብረት ተሽቀዳድሞ ለሽልማት ያቀርባል።
አሸባሪው፣ ጨካኙና ወራሪው ኃይል “እጃችሁን ስጡ!” እያለ በጀግኖቹ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ላይ መሳለቅ ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህ እጀ መርዝ ቂመኛ ወራሪ በትዕቢት አብጦና በእብሪት ሰክሮ “እጅህን ስጥ!” በማለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ክህደት የፈጸመበት የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከጉዳቱ በፍጥነት አገግሞ እያርበደበደ መሪዎቹንና ጀሌዎቹን እንደምን ወደ ትቢያ እንደለወጣቸው እነርሱ ለእውነት ጆሯቸውን ቢደፍኑም የኢትዮጵያ ሕዝብና ታሪክ ግን ሕያው ምስክሮች ናቸው።
እፍኝ የማይሞሉት አሸባሪዎች ከመቶ ዐሥር ሚሊዮን የሚበልጠውን ሕዝብ “እጅህን ስጥ!” ብለው ሲያቅራሩ አለማፈራቸው የልባቸውን ቁርበት ድንዳኔ በሚገባ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጣቸው መልስ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ጀግናው ቴዎድሮስ “ተናገረ” ተብሎ ብዕረኛው ጸጋዬ ገ/መድኅን የተቀኘው ሃሳብ ነው። “ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ፤ አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ” – ከገባቸው መልሱ ይሄ ነው።
ይልቅዬ “እጁን ይዘው ያስገቡት እጁን ተይዞ ይወጣል!” እንዲል የአበው ብሂል፤ ከአዝመራ እስከ ዐውድማ፣ ከባንክ እስከ ኪዮስክ፣ ከወጥ እስከ ሊጥ፣ ከመቀነት እስከ እንስሳት እንደ አንበጣ እየወረረ ግለሰቦችን፣ ተቋማትንና አገርን የዘረፈውና የሚዘርፈው ከሃዲ ኃይል ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተላለፍለት ቁርጥ ያለ መልስ እርሱ ራሱ በደም የጨቀየ እጁን እንዲሰጥ ሳይሆን ትቢያ ሆኖ እንደሚቀበር በአዋጅም ሆነ በሹክሹክታ እየተነገረው ስለሆነ ቀኑን እየቆጠረና መቃብሩን እየቆፈረ ቢሰነብት ይበጀዋል።
የህሊና ጉንድሾቹ የ“እጅ ስጡ!” ፌዝ፤
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ መዘርጋት” (መዝሙር 68፡31) ካልሆነ በስተቀር ለተገዳዳሪዎቿና ለጠላቶቿ በታሪኳ ውስጥ “እጅ ሰጥታ” አታውቅም። ከሃዲውን አሸባሪ ቡድን “አለንልህ” የሚሉት ፌዘኞቹ የውጭ ኃይላት በአባሪ ተባባሪነት “ኢትዮጵያን እጅ ካላሰጠን” ብለው ሌት ተቀን መትጋታቸው የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የህሊናቸውን ድንክነት የሚያመለክት ጭምር ነው።
በተለያዩ የዓለም አገራት ዜጎች ስብጥር (Melting Pot) አገራቸውንና “ታላቅነታቸውን” የገነቡትና የሌሎችን ሉዓላዊ አገራት ለማፈራረስ እንቅልፍ በዓይናቸው ዞሮ የማያውቀው ያኒኪዎቹን መሰል አገራት “የማዕቀብ” ጩኸት ሌላው የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ “እጃችሁን ስጡ!” የፌዝ ተረት ተረት ነው። አጯጯኺዎቹ ገባቸውም አልገባቸው “ቅኔው” ለአገሬ የተሰወረ አይደለም።
በያ ሰሞን “የጉዞ ማዕቀባችንን ልናዘገይ የምንችለው በእኛ ምክረ ሃሳብና ምክረ ተግባር ተማርካችሁ እጃችሁን ከሰጣችሁን ብቻ ነው” በማለት ሀገሬን መሞገታቸው አይዘነጋም። አስከትለውም የዓለም መንግሥታቱን የፀጥታ ምክር ቤት ፋታ ነስተው “እጅ ለማሰጠት” ደጋግመው ቢሞክሩም ኢትዮጵያዬ አልተበገረችላቸውም። ይልቁንስ የዐረብ አገራትን ነባር ብሂል ተውሳ “ውሾች ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ይጓዛሉ” በማለት መልስ መስጠቷ ይታወሳል። ለእነዚህ መሰል ዕብሪት ላሰከራቸው አገራት “የሕሊና ጨርቃችሁን አውልቃችሁ የፖለቲካ እርቃናችሁን አታጋልጡ” ብለው ከጎናችን ለተሰለፉት ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድና መሰል ወዳጆቻችን ምስጋና ይድረሳቸው።
የሰሞኑ “የእጅ ስጡ!” የነጠላ ዜማቸው ቅኝት ደግሞ “ከወራሪዎቹ ጋር ካልተደራደራችሁ” የአጎዋ ኢንሼቲቭ (Tariff-free; African Growth and Opportunity Act, AGOA) የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነታችሁን እንነፍጋለን በማለት በግልጽ ቋንቋ ነግረውናል። በመሠረቱ ውሳኔው ኢፍትሐዊ መሆኑ ብቻም ሳይሆን በኢኮኖሚያችን ላይ መጠነኛ ጉዳት ማስከተሉና በተወሰኑ ሠራተኞች ሕይወት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ እንገነዘባለን። በዚሁ ጋዜጣ የበቀደም ዕትም ላይ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፤ “አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማገዷ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ነው” ማለታቸውን ይህ ጸሐፊ በፍጹም አይስማማበትም። አጎዋን በተመለከተ ከአሁን ቀደም በታተመ አንድ ጽሑፌ ከጅማሬው እስከ ዛሬ ያለውን ሂደት በመቃኘት ዘርዘር ያለ ሃሳብ ማቅረቤ አይዘነጋም።
ፈራ ተባ በማለት በቀዳሚው ጽሑፌ ያልጠቀስኩትን አንድ የልዩነት ሃሳቤን ገልጬ ባልፍ ፍርሃቱን ያመጣጥን ይመስለኛል። ለመሆኑ የቀረጥ ነፃ ዕድል የሚጠቀሙትና እፍኝ የማይሞላ ዶላር ወደ ሀገራችን በማስገባት በእነርሱ ካዝና ውስጥ ግን እያፈሱ የሚቆልሉት የውጭ አገራት ኩባንያዎች ምንጫቸውና ባለቤቶቻቸው እነማን ናቸው? ከዚያው “በልፅገናል፣ አድገናል” እያሉ በኢኮኖሚ ጡንቻቸው ዓለምን ካላሽከረከርን ከሚሉት አገራት የተገኙ ባለ ብራንድ ኩባንያዎች አይደሉም?
በስመ ባለ ብራንድነት (Branded Companies) ከዘርፉ የሚሰጣቸውን ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ እያጋበሱ ያሉትስ እነርሱው አይደሉም? እውነቱን እናፍርጠው ካልንስ እነዚህ ኩባንያዎች ከሚያመርቷቸው አልባሳትና ጫማዎች መካከል ቆንጥረው ለአገር ውስጥ ገበያ ያቃምሳሉን? አይመስለኝም። በዚህ ጉዳይ ላይ የስጋታችንን ክንብንብ ገላልጠን በጉዳዩ ላይ በግልጽነት መነጋገር ያለብን ይመስለኛል።
ይህ ጸሐፊ በአገሪቱ የሚገኙትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ ታሪካቸውን በዶኪዩመንት ለማስቀረት ከባልደረቦቹ ጋር ባደረጋቸው የሥራ ስምሪቶች አንድም ሳይቀር ጎብኝቷቸው ስለነበር በድፍረት ለሚገልጻቸው እውነታዎች አይሸማቀቅም። የአጎዋ ዕድል ተነፈግን ማለት ሌሎች የገበያ ዕድሎች አይኖሩም ማለት አይደለም። “ያስጨነቅኸኝ ለመልካም ሆነልኝ” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፤ የንግድ አቅጣጫዎቻችንን ወደ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያና የዐረብ አገራት ወዘተ. ማድረጉ ወቅቱም ሁኔታውም ግድ ይለናል። ስለዚህም ከአጎዋ ተጠቃሚነት “ፊት ተነሳን” ብለን ፊታችንን ብናጠቁር ምንም እርባና ስለማይኖረው ፖሊሲ አመንጭዎቻችንና አስፈጻሚ አካላት ሊበረቱ ይገባል እንጂ አገሬ ጥቅሙ ቀረብኝ በማለት እጇን ለምርኮ አትሰጥም።
ወራሪውን አሸባሪ ኃይል የደገፉ መስሏቸው እጃችንን ለምርኮ እንድንዘረጋ ከሚጎመጁ ቡድኖች መካከል በስማቸው ገዝፈው በተግባራቸው የኮሰመኑ አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት፣ በሰብዓዊ ድጋፍና እርዳታ ስም ስንዴ እንስፈርላችሁ የሚሉ የተራድኦ ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ መብቶችና የዲሞክራሲ አዋላጆች ነን የሚሉ ተቋማት፣ የማደራደርና የማቀራረብ ብልሃቱን ተክነናል ባይ “አሸማጋይ ተብዬዎች” ወዘተ. ሁሉም እየተረባረቡ የአገሬን ጆሮ በጩኸታቸው የሚያደነቁሩት “ወይ ከአሸባሪው ጋር ተደራደሩ ወይ ለምርኮ እጅ ስጡ” በማለት ነው።
እውነት ነው አገራዊ ችግሮቻችን ውስብስቦች ናቸው። የውስጥ ጉዶችና የውጭ ኃይላትም ፈተናችንን እንዳከበዱ አልጠፋንም። ቢሆንም ግን የዶላሩም ሆነ የአረር ግዢ ፍላጎታችንን ዋጥ አድርገን እንችለዋለን እንጂ “እጅ ስጡ!” ለሚለው መደራደሪያቸው የቀደምት ታሪኮቻችንን ዱካ ደልዘን ለውርደት አንበረከክም። በፌዝ ስላቃቸው ተማርከንም አንማልልም። የሚሰሙን ከሆነም ነፍሳችንን ለሉዓላዊነታችን መገበሩ ከሁሉም አማራጮች ቀዳሚ መሆኑንም አስረግጠን እንነግራቸዋለን።
“እጅ መስጠት” የከሀዲያን “ጀብድ” ነው። ለተገዳዳሪዎቻችን በሙሉ ይህ መልዕክት ይድረስልን። እንኳንም ለውስጥ ከሀዲዎችና ባንዳዎች ቀርቶ ባህር አቋርጠውና በውቂያኖስ ላይ ቀዝፈው ለመጡ ወራሪዎች አገሬ እጇን ሰጥታ አልተዋረደችም። እንኳንስ እጆቿን ጠፍረው ሊማረኳት ቀርቶ እጃቸውን ዘርግተውም ቢሆን ሊዳብሷት አልሞከሩም።
“እጅግ ተታለዋል ጠላቶቿ ሁሉ፣
ሲያወሩ ሰማሁኝ ሞታለች እያሉ”
በማለት አቅራራ ይባላል የአገሬ “ደም መላሽ” ጀግና። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014