አሁን በአገራችን በጣም ፈታኝ ጊዜ እየኖርን ያለንበት ጊዜ ነው። በተለያዩ መሰናክሎች ፊት ቀርበን የዴሞክራሲ፣ የልማትና የፍትህ ጉዞአችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈተነ ነው። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በመካከላችን ቀላል የማይባሉ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነቶችን በመቅበር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን እና ህብረታችንን በማጠናከር በመንግስት እየተመራን ለአንድ አላማ መንቀሳቀስ አለብን።
ሀገሪቱ ዋነኛ ጠላቷ ከሆነው አሸባሪው ህወሓት እና ሸኔ ጋር እየተፋለመች ያለችበት ወቅት በመሆኑና ሀገር ለማፍረስ ጦርነቱን ወደ አማራ እና አፋር ክልል በማራዘም መቃብሩን እየቆፈረ ያለበት ሁኔታ በመኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያንም ከምን ጊዜም በበለጠ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ አቋም ይዞ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። በዚህም ጠላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል በማድረግ ሀገሪቱን ከውርደትና ማለቂያ ከሌለው ስቃይ ማዳን ያስፈልጋል።
በአሸባሪው ህወሓትና አጋሮቹ ፋሽስታዊ ተግባር የደረሰብንን እጅግ አሳዛኝ አደጋ ማንም አቅልሎ ሊመለከተው አይችልም። ከዚህ ጦርነት ጎን ለጎን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ።
የመጀመሪያው አሸባሪው ህወሓትን ማሸነፍ፣ መደምሰስ እና መቅበር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ደጋግሞ እንደተናገረው ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነው።
እዚህ ላይ አሸባሪው ህወሓት በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የሹፌርነቱን ቦታ ካልያዘ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ሲዘጋጅ የኖረ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ቡድኑ ሀገሪቱን ካላስተዳደረ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ሲሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲዝቱ ሰምተናል። ይህም በተዘዋዋሪ አገሪቷን እኛ ካልመራናት እንበትናታለን ብሎ ማስፈራራቱ ነበር።
ለሚጠፋው የሰው ህይወት ፍፁም ደንታ የሌላቸው የአሸባሪው ህወሓት መሪዎች ህዝቡን በተለያየ መንገድና በሀሰት ትርክቶች ህዝቡን ለጦርነት ሲያዘጋጁ ቆይተዋል።
በእርግጥ ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት ወታደራዊ ትጥቆችን ሲያከማች፣ ከህዝብ በዘረፈው በሀገር ውስጥና ውጪ ባከማቸው ገንዘብ ለዚሁ እኩይ አላማ ሲዘጋጅ እንደነበር ማስረጃዎቹ ይመሰክራሉ። ይሄንንም በተጨባጭ አይተና፤ ሰምተናል። ለዚህም ዓላማ መሳካት አጋዥ የሆኑት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በውጭ ሀገር ያሉ የፖለቲካ ሰዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ የባንዳ ሚና የሚጫወቱትን ሁሉ ከጎኑ አሰልፎ መንቀሳቀሱና እየተንቀሳቀሰ እንዳለም ይታወቃል።
በአሁኑ ጊዜ ለቡድኑ አላማ መሳካት ከጎኑ የተሰለፉ አለም አቀፍ ተቋማትና አመራሮቻቸው ግልጽ በሆነ መንገድ የቡድኑን አላማ ደግፈው በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ሲንቀሳቀሱ እየታየ ነው።
የቡድኑ መሪዎች በስልጣን በቆዩባቸው 27 ዓመታት የሀገር እና ሕዝብ ሀብት ከመዝረፍ ባለፈ ለኢትዮጵያ ሆነ እወክለዋለሁ ለሚሉት የትግራይ ህዝብ ብልፅግና የሠሩት አንዳች ነገር የለም። ከዛ ይልቅ በተለያዩ ክልሎች ሆን ብለው በፈጠሩት የብሄር ልዩነት በህዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲፈጠር ሲተጉ ቆይተዋል።
የቡድኑ አመራሮች ታሪካዊ ስህተት ኢትዮጵያን በመሰላቸው አካሄድ ብቻ መግዛት አልያም መበታተን የሚለውን የተሳሳተ ስሌት ቀምረው መነሳታቸው ነው። ለ27 ዓመታት ህዝብን በብሄሩና በሀይማኖቱ እየከፋፈሉ ሲያጋጩ ቆይተዋል። ዛሬም ያዳፈኑትን እሳት እየገላለጡ አንዱን ብሄር በሌላው ላይ ለማነሳሳት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ከኢትጵያና ከህዝቧ ላይ የገፈፈቱን ሀብት እየረጩና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ዛሬም በአንድ ብሄር ዘር ማጥፋት ተግባር ላይ ዘምተዋል። ሲያሻቸው በራሳቸው አልሆነ ሲላቸው በቀላሉ የሚጋልቡትን ሸኔን ጃስ እያሉ ህይወት የማጥፋት ንብረት የማውደም ሴራቸውን እያከናወኑ ናቸው። ይህን አላማቸውን ለማሳካትም የውስጥ ባንዳዎች ጨምሮ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀንን ከጎናቸው አሰልፈው የእናት ጡት ነካሽነታቸውን ደግመው ደጋግመው በተግባራቸው አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለነበራቸው እኩይ አላማ እስካገዛቸው እና የኢትዮጵያን ስም ከዓለም ካርታ ላይ እስካጠፋላቸው ድረስ ራሳቸው ዲያብሎስ ሆነው <<ከዲያብሎስ ጋርም ቢሆን እንሰራለን>> ብለው ሲናገሩም በአደባባይ ተደምጠዋል። እንዳሉትም ኢትዮጵያን በጠላትነት ከሚያዩና የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ጥንካሬ ስጋት ከሚፈጥርባቸው አካላት ጋር ተጣምረው ሲሰሩ አይተን ታዝበናል ።
አሳፋሪው ነገር ከፍ ያሉ የሰብአዊ እሴቶች ባለቤት ናቸው የሚባሉ አንዳንድ ሀገራት ድጋፋቸውን ለአሸባሪው ህወሓት ማሳየታቸው ነው። በእነሱ የሚዘወሩት እንደ ተመድ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ለቡድኑ አቅም የመሆናቸው እውነታ ድርጅቶቹ የቱን ያህል ከመርህ ወጥተው በአደባባይ በተሳሳተ መንገድ ላይ እየተጓዙ እንደሆነ ያመለክታል።
እነዚህ አካላት የአሸባሪ ቡድን የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ዓላማዎች በውል አልተረዱትም የሚባል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ የቱን ያህል የስጋት ምንጭ እንደሆነባቸው የሚያሳይ ነው።
ለዚህም አንዱ ማሳያ የሚሆነው አሜሪካና ምዕራባውያን በሚያስተዳድሯቸው የመገናኛ ብዙሃን ተቋሞቻቸው ሳይቀር በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ዘመቻ አሻባሪው ህወሓት እራሱ የቱን ያህል ለነሱ አላማ የታጨ አህያ እንደሆነ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።
አሸባሪው ህወሓት ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የደርግን መንግስት ከስልጣን ለማስወገድ ባደረጉት የትጥቅ ትግል ወቅት ሆነም አሁን እየሆነ ካለው በብዙ የተለየ አይደለም፤ አሁንም በዛው መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነው።
ምዕራቡ አለምና የነሱ አስተሳሰብ ተሸካሚ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ የቡድኑን የሽብር ተግባሮች ከማውገዝ ይልቅ ዝምታን መርጠዋል። ቡድኑ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ገብቶ በየአካባቢው እያደረገ ያለውን ግድያና ዘረፋ ለማውገዝ ፈቃደኛ አልሆኑም።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ህፃናትን ለወታደር ሲመለምል፤ የእርዳታ አቅርቦቶች ችግር ውስጥ ላለው የትግራይ ህዝብ እንዳይቀርብ መሰናክል ሲሆን ዝምታን መርጠዋል። ይህም በአሸባሪው ሕወሓትና በምዕራባውያን አጋሮቹ መካከል ግልጽ የሆነ የዓላማ አንድነት መኖሩ ያመለክታል።
ለዚህም ነው ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በመወያየት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር በብዙ የመከረው። በገሀድ በታየው ብቻ በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ 10 ጊዜ ስብሰባ ተቀምጧል። ይሄ ዛሬ የታዘብነው ነገ ታሪክ የሚጽፈው መጥፎው ታሪካቸው ነው። መቼም አንረሳውም።
ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ የቅኝ አገዛዝ ፍላጎት ካላቸው የውጭ ሀገር መንግስታትና ሀይሎች ጋር መሆኑን ነው። መላው ህዝባችን ይህንን አሁናዊ እውነታ በአግባቡ በመረዳት በብሄር፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሳይከፋፈል ኢትዮጵያን ለማዳን “ሆ’ ብሎ በመነሳት በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጭ ወረራ መመከት ይኖርበታል።
ኢትዮጵያን አሁን ካጋጠማት የህልውና አደጋ በአሸናፊነት ለመወጣት ዜጎች የማይበገር የአትንኩኝ ባይነት አስተሳሰብ አንግበውና የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰንቀው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የተጀመረው የህልውና ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆንም በግንባርም ሆነ በደጀንነት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው በመቀጠል ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
ከዘላለም
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014