የአሸባሪው ህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ሳት ብሏቸው ይመስለኛል አንድ ምስጢር አውጥተዋል። ለነገሩ ገና ብዙ ያወጣሉ። በአንድ ወቅት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ሃላፊ ጋር ማውራታቸውን ተናገሩ፤ ሃላፊው መፈንቅለ መንግስት አታደርጉም ለምን ብለውኝ ነበር አሉን። መፈንቅለ መንግስት ህገወጥ ነው የሚለው ተቋም ሃላፊ ናቸው እንግዲህ ይህን ያሉዋቸው።
ይህ ነገር ዓለም አቀፉ ተቋም ምን ያህል በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ውስጥ ጣልቃ አንደገባ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ፣ እኛ ግን የለየለት ጣልቃ ገቢ ስለመሆኑ ሌሎች በርካታ መረጃዎችን መጥቀስ አንችላለን። ለማናቸውም አቶ ጌታቸው ሌላ አንድ ጥሩ መረጃ ሰጥተውናል።
እኛ ድርጅቱና የተለያዩ ተቋማቱ እንዲሁም አሜሪካን ጨምሮ አውሮፓውያኑ ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ በማድረግ ላይ ስለመሆናቸው ነጋሪም ሳንሻ አሳምረን እናውቃለን። ዛሬ አይደለም፤ ቡድኑ በህግ ማስከበሩ አከርካሪውን ከተመታ ጀምሮ ሲያደርጉ የነበረውን ሁሉ አሳምረን እናውቃለን። ቡድኑ ድል የቀናው ሲመስላቸው ጮቤ ሲረግጡ ሌላ ጊዜ ሲያደፍጡ፣ ሲመታ ወይም ሊመታ ሲል ደግሞ ያላዝናሉ፤ ያስፈራራሉ። የሚገርመው ደግሞ አብረው መጮሃቸው፤ ማስፈራራታቸው ነው።
ትኩስ ትኩሶቹን እንኳ ብንጠቅስ ሰሞኑንም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተለመደውን የተቀናጀ ዘመቻቸውን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተዋል። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በአሸባሪው ትህነግ ላይ መንግስት መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘረ ባለበት እና ይሰነዝራል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
እንደሚታወቀው አሸባሪው ትህነግ በወሎ ግንባር በደቡብ ወሎ እያካሄደ ያለውን ወረራ ለመቀልበስ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሺያ እንዲሁም ፋኖ በአሸባሪው ላይ የተቀናጀ ውጊያ እያካሄዱ ይገኛሉ። ይህ ውጊያ ተላላኪያቸውን ከተልእኮው ያስቀራል ብለው ሰግተው ነው ምዕራባውያኑ በየአቅጣጫው በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻቸውን የከፈቱት።
የአሜሪካ መንግስት ሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል በሚል በኢትዮጵያ ላይ የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብ ከትናንት በስቲያ መጣሉን አስታውቋል። ልብ በሉ አንግዲህ አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያና ዜጎቿ ላይ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘረ ባለበት በዚህ ወቅት ነው ማዕቀቡ የተጣለው። ቡድኑ ሰሞኑን በኮምቦልቻ ከ100 በላይ ወጣቶችን መጨፍጨፉ እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው እንግዲህ የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀቡ እንዲጣል የተደረገው።
ሀገሪቱ በዚህ ብቻ አላቆመችም፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገሮች ሰጥታው በነበረው ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜረካ ገበያ የማስገባት እድል/አጎአ/ ኢትዮጵያን ለሁለት ወራት ለሚሆን ጊዜ ማገዷንም ትናንት ይፋ አድርጋለች። ሀገሪቱ ህዝብን ሊጎዳ የሚችል እርምጃ አልወሰድም እያለች ነው ለበርካታ ሰራተኞች የስራ እድል በከፈተውና ለዚህ ገበያ ምርቶችን እያቀረበ ባለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል እገዳ የተጣለው።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ ከትናንት በስቲያ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በደግ አልተመለከተውም። አዋጁ መንቀሳቀስ አያስችለንም አይነት አቋም እያንጸባረቀ ነው። የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ እዚህ ግባ የሚባል አቅም ለሌለው ለሸኔ ጦር አዲስ አበባ ከመክበብ አንዲቆጠብ በመጠየቅ የሌለውን አቅም እንዲያገኝ እያረገ ነው። እነ ቢቢሲም ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ አፍራሽ ዘገባዎችን እየሰሩ ናቸው። ይህ ሁሉ እርምጃ አሸባሪው ትህነግ አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያውያንን መጨፍጨፉን አጠናክሮ አንዲቀጥል፣ ኢትዮጵያ ሉኣለዊነቷ ተደፍሮ አንዲቆይ የሚያደርግ ነው።
እርምጃዎቹ አውሮፓውያኑ የተቀናጀ ዘመቻ ኢትዮጵያ ላይ መክፈታቸውን በሚገባ የሚያመለክቱ ሌሎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ቡድኑ ሲፈጠር አንስቶ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያለው መሆኑን የተረዱት ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት አንዳይኖራት ባላት ጽኑ ፍላጎት ለሰይጣንም ቢሆን ድጋፍ አንደምታደርግ ለትህነግ እያደረገች ካለችው ድጋፍ አሳምረን ተረድተናል። ኢትዮጵያውያንና መንግስታቸው እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ እያሉ ለአሜሪካና ለአጋሮቿ በተለያዩ መንገዶች ሲያስገነዝቡ የቆዩትም ከዚሁ በመነጨ ነው።
የአሁኖቹ እርምጃዎች አዲስ አይደሉም፤ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ጦርነት ቀጣይ ምዕራፎች ናቸው። ምዕራባውያኑ ለአሸባሪው ህወሓት በቀጥታ ስንቅ አልሰጡም፤ ቀለብ አልሰፈሩም፤ ወታደሮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ኢትዮጵያን አልወጉምም ለቡድኑ የጦር መሳሪያም፣ የሚገናኝበት ቴክኖሎጂም አልሰጠቱም የሚሉም ሊኖሩ ይችላሉ።
ህወሓት ግን እንደ እባብ አፈር ልሶ የተነሳው እነሱ በምንም በምንም አርገው የሰጡትን የእርዳታ ምግብና እየበላ፣ ከብስኩትና ስንዴ ጋር በገፍ የገባለትን የመገናኛ መሳሪያ ተጠቅሞ መሆኑን እኛ አሳምረን እናውቃለን። ለእዚህ ጠንቋይ መቀለብ ውስጥ አንገባም። የእርዳታውን ምግብ በተመለከተ የምናውቀው ሁሉ እንዳለ ሆኖ ያ የተማረከ ኮሎኔል እጅ የተመለከትነውና እሱም ስለብስኩቱ የተናገረው በቂ ማስረጃ ነው። ነፍስ የሚዘራ ብስኩት መሆኑን ተረድተናል።
አቤት ያን ሰሞን የሆነው። የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት ብስኩት በዚህ ታጣቂ እጅ ተገኘ መባሉን መገናኛ ብዙሃን ለጉድ ሲቀባበሉት የሰማው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሲ ተኝቶ አላደረም። እንደዚያን ጊዜ ለማስተባበያ ችኩሎ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ እርዳታው ተሰርቆ ይሆናል እንጂ ኤሜሪካ ይህን አታደርግም ሲል አስተባበለ። ምን አለ ዝም ቢል። የማርያምን መገበሪያ የበላ እንዲሁ ይለፈልፋል ነው የተባለው። የኤምባሲው ጉዳይም እንደዚያው ነው። እንዳልኩት እኛ እኮ ሁሉኑም ነገር እናውቃለን።
አንድ ነገር ወደ አእምሮዬ መጣ፤ ፈረንጆቹ የመከላከያ ሀይል ትግራይ እያሉ መንግስት ከ70 በመቶ በላይ የእርዳታ አቅርቦት ለህዝቡ እየሰጠ ባለበት ወቅት ለህዝቡ እርዳታ እየቀረበ አይደለም፤ እንዳውም ረሀብ ሊከሰት ይችላል እያሉ ይለፍፉ ነበር፤ ያሟርቱ ነበር ቢባል ይሻላል። ያልሆነውን፣ አንዳይሆን በሚገባ እየተሰራበት ያለውን ጉዳይ እያነሱ ጣሉ።
በተናጠል የተኩስ አቁሙ ወቅት ሰራዊቱ ከትግራይ ከወጣ በሁዋላ መንግስት የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲያስገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተከትሎ በአያሌ ከባድ መኪኖች እርዳታ ማስገባት ጀመሩ። ይህ ድጋፍ እየገባ ባለበት ወቅት ግን መኪኖቹ አይገቡም ብሎ ቡድኑ በአፋር ክልል ለቀናት አንዲቆሙ አረገ፤ ጥቃት የደረሰባቸውም ነበሩ።
እርዳታ በፍጥነት ካልገባ ረሀብ ብዙዎችን ይፈጃል ሲል የነበረው ይህ ሞርቱ ቡድን፣ የእርዳታ አቅርቦቱ አንደ ልብ መግባትም አመመው። ምክንያቱም የረሀብ ንግዱ ሊበላሽ ሆነ፤ ረሀብ እንዲከሰት ይፈልጋልና ጥጋብ ሊሆን ነው ብሎ አሰበ። እናም የእርዳታው መጉረፍ በእድሜዬ ላይ ችግር ያስከትላል በሚል ስጋት ማጓጓዙን አስተጓጎለው።
ምን ይህ ብቻ፤ እርዳታ ጭነው ትግራይ ከገቡ ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ /ፊት 400 ከሚሆኑት ውስጥ ሰላሳ የማይሞሉት/ሲመለሱ የተቀሩት እዚያው ሰምጠው ቀርተው ነበር። ሁኔታው ኢትዮጵያውያንን በሰፊው አነጋገረ። ያኔ ያሟርቱ የነበሩት ግን የመኪኖቹ ትግራይ ገብቶ መቅረት አላሳሰባቸውም።
በቅርቡ የአሜሪካ ኮንግሬስ አንዳንድ አባላት ቡድኑ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን ከማሳለፋቸው በቀር፣ ፈረንጆቹ ቡድኑ እርዳታ አንዳይገባ ሲከለክል፣ እርዳታ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎችን ለታጣቂዎች ማመላለሻ አድርጓል ሲባል ፈጥነው ያሉት አይደለም፣ ዘግይተውም ያሉት ብዙም የለም።
ቡድኑ አውቆ ያረገው በመሆኑ ጉዳዩ ሊያሳስበው አይገባም፤ አላሳሰበውምም። መኪኖቹ የመመለሻ ነዳጃቸውን ጨርሰው ቆመዋል ተባለ። በሁዋላ ግን ቡድኑ መኪኖቹ ነዳጅ መጨረሳቸውን አርጋግጧል። ምን አርገውበት ጨረሱት? ብሎ የጠየቀ የመኪኖቹ ባለቤትም ሆነ አስተዳዳሪ ሲጠይቅ አልተሰማም። አሽከርካሪዎችም በማጓጓዝ ወቅት እንግልት ደርሶብናል ወደ መሀል አገር አንመለስም ብለዋልም ተባለ፤ የተባለው በአሸባሪው ነው።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች አንደሚያመለክቱት፤ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ከገቡ ከአንድ ሺ 100 በላይ ከባድ መኪኖች መካከል የተመለሰቱት ከሁለት መቶ ብዙም አይዘሉም። አለመመለሳቸው ብቻ አይደለም የሚያጠያይቀው፤ የመኪኖቹ ባለቤት ተብዬም/ የዓለም ምግብ ፕሮግራም/ የት ደረሱ ብሎ አልጠየቀም፤ ይቺ ናት ሰብአዊ አገልግሎት!
የሚገርመው ግን ተጨማሪ ኮሪደር ካልተከፈተ በስተቀር ለትግራይ ህዝብ የሚቀርበውን ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ አይቻልም ሲሉ የነበሩት እነዚህ አካላት ያሰማሯቸው ከአንድ ሺ የማያንሱ ተሽከርካሪዎች የቁራ መልዕክተኛ ሆነው ሲቀሩ አላሳሰባቸውም። አውቆ የሞተ ቢቀሰቅሱት አይሠማም ነው ነገሩ።
እንደጠቀስኩት መኪኖቹ ወደ ሀገር ውስጥ ከመጡበት አላማ ውጪ ታጣቂዎች እያመላለሱ ስለመሆናቸው ይጠረጠራል። አንዳንዶች ደግሞ መኪኖቹ ሳይሆኑ ነዳጃቸው ነው ይበልጥ የሚጠቅመው ይላሉ። መኪኖቹ ነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ሆነዋል ማለት ነው። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ መኪኖቹ በመስፍን ኢንዱስትሪያል ቀለማቸው እየተቀየረ ለጦርነቱ አገልግሎት ውለዋል ይሉም ነበር። ሁለቱም ህገወጥ ድርጊት ነው።
ምዕራባውያኑ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ይህን ድርጊት አለማውገዛቸው እኛን ገረመን እንጂ፣ እነሱ ይህ ሊሆን አንደሚችል አያውቁም ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም እነዚህ አካላት ቡድኑን ከመደገፍ በላይ በጦርነቱ በግልጽ ተሳትፈዋል ቢባል ስህተት ሊሆን አይችልም። እኛስ መኪኖቹ በትግራይ ክልል ለጦርነቱ አላማ እንዲውሉ ታስቦ የገቡ ናቸው ብለን ብንገምት ስህተት የሚሆን አይመስለኝም።
አዎን ቡድኑን በብዙ መልኩ እየደገፉት ናቸው። በሰብአዊ አገልግሎት ስም የሳተለይት መገናኛ መሳሪያዎችን በገፍ በማቅረብ ግብአተ መሬቱን ሲጠበቅ የነበረውን ቡድን ነፍስ ዘርተውበታል። በጦርነቱ ለሰብአዊ ድጋፍ ለተዳረጉ በሚል ያስገቡትን ስንዴ ብቻ ሳይሆን ብስኩቱን በገፍ አቅርበውለታል። ስንቅ አቅርበውለታል ማለት ነው።
ፊትም ይጠረጠር የነበረ ከመረጃ ጋር የተያያዘ አንድ ነገር አለ፤ በቅርቡ በወጡ መረጃዎች እውነት ሆኗል፤ ቡድኑ ወደ ህንድ ውቂያኖስ አካባቢ ካሉ የጦር መርከቦች የሳተላይት መረጃ እየደረሰው ነው። የቡድኑ ታጣቂዎች ሊያልፉ የሚችሉባቸውን ኮሪደሮች፣ የመንግስት ጠንካራና ደካማ ይዞታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እያደረሱት ስለመሆኑ ከተጠለፈ የሳተላይት መረጃ መረዳት ተችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከአሸባሪው ጋር እየተካሄደ ባለው ውጊያ የውጪ ወታደሮች በግንባር ጭምር እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እነዚህ መረጃዎች አሁንም ምዕራባውያኑ በግልጽ እየወጉን መሆኑን ያመለክታሉ።
በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ ጦርነቱ የውክልና ጦርነት ነው። በየጊዜው ከሚገኙ መረጃዎች መረዳት አንደሚቻለው ግን የህወሓት ውክልና እስከ አሁን ከምናውቀው የውክልና ትርጉምም በላይ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ምዕራባውያኑ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብናል። እየወጉን ናቸው። ነጭ ወታደር ስላልተመለከትን እነሱ አይደሉም አሸባሪው ትህነግ ነው እየወጋን ያለው የምንል ካለን ስህተት ውስጥ መሆናቸውን አንረዳ።
ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን በመጉዳት ቡድኑን ለመጠቀም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ወደ አስሬ ከሰው ስብስባ አስጠሩ፣ የኢትዮጵያን እውነት ገፍተው፣ የአሸባሪውን ሀሰት እውነታቸው አርገው ተከራከሩ። ምስጋና ለእውነተኞቹ የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉም ውድቅ ተደረጉ።
ምዕራባውያኑ በተመድ ያልቻሉትን በየራሳቸውና በየቡድናቸው እያደረጉ ናቸው። አስጠነቀቁን አስፈራሩን፣ ጫና አሳደሩብን። በሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል ብድር እርዳታና ድጋፍን ቀነሱ፤ ከለከሉ። በምንገዛው በምንሸጠው ላይ መጡ። ባዶ እጃቸውን ምን ይፈጥራሉ ብለው አሰቡ።
ኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩ ያሉት ጫና፣ ለትህነግ እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ከውክልና ጦርነትም በላይ ጦርነት አንደከፈቱብን ያመለክታል። አዎን ምዕራባውያኑ በግልጽ ጦርነት ከፍተውብናል። አሸባሪው ትህነግ ደግሞ ታጣቂያቸው ጦራቸው ነው። ቅጥረኛ ጦር።
የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ምላሽም ይህን የምዕራባውያኑን ዘመቻ የሚመጥን መሆን አለበት። አሸባሪውን ህወሓትንማ በ17 ቀናት ውስጥ ድል አርገን የተፈጠረበት ዋሻ ከተነዋል። አሁን የተከፈተብን ጦርነት ከህወሓት ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም፤ የውክልና ጦርነት ብቻም አይደለም፤ ከምዕራባውያኑ ጋር የተቀናጀ ጦርነት ነው የተከፈተብን።
ጦርነቱን በድል ለመውጣት ይህን ሊመጥን የሚችል ዝግጁነት በሁሉም መስኩ አርጎ መፋለም ይጠበቅብናል። ጠላቶቻችን ብዙ ናቸው፤ የተቀናጀ ዘመቻ ነው የተከፈተብን፤ ይህን የሚመጥን ዘመቻ በማድረግ ሀገራችንን መታደግ ይኖርብናል። የሀገረ ሉአላዊነትን ለተዳፈረ ምላሹ መሆን ያለበት ይሄው ነው። ለእዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ይገባል።
ማዕቀቦች ሊጎዱን ይችላሉ፤ ይጎዱናል ብለን ግን ሉአላዊነታችንን አሳልፈን መስጠት የለብንም። ለማዕቀቦች በጭራሽ መንበርከክ የለብንም። መውጫውን ማሰብ ነው ያለብን። አሜሪካ በወሳኝ ወቅት እንዲህ እንደ አሁኑ በ”1969 የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅትም የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብ እንዲጣልባት አድርጋለች። ይህንና ኢትዮጵያ ግን ጦርነቱን በድል ተወጥታለች። ዛሬም የተከፈተብንን የተቀናጀ ጦርነት እሱን የሚመጥን ምላሽ በመስጠት በድል አንወጣለን።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014