ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መላው ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ፣ ያስገረመ፣ ያሳዘነ በጠቅላላው ጉድ ያሰኘ የክህደት ጥግ የታየበት ቀን ሆኖ ተመዝግቧል:: ይህ እለት የብዙዎችን ልብ የሰበረ እለትም ሆኖ እልፏል::
“ታሪክ ሠሪዎቿን ትመስላለች “እንደሚባለው ሁሉ መልካም ነገር ያደረጉ ሰዎች በመልካምነታቸው ታሪክ እንደማይዝነጋቸው ሁሉ እቡያንና እኩያንም በዚያው በምግባራቸው ልክ ታሪክ ሲያስታውሳቸው መኖሩ አይቀሬ ነው:: ለእውነት የቆሙና ከግል ጥቅማቸው ይልቅ አገርን ያስቀደሙት ደግሞ በዚያው ልክ ታሪክም ህዝብም ሲያመሰግናቸው፣ አገርም በሠሩላት ሥራ ቀና ስትልባቸው ትኖራለች::
በተለይም እቡያንና እኩያን የታሪክ ስንክሳር የሆኑት ከዚህ ቀደምም ባለው ሁኔታ አገራቸውን ከድተዋል ፤ለግል ጥቅማቸው ብለው ባንዳ ሆነዋል ፤አገራቸውን ወግተዋል፤ የእናታቸውን ጡት ነክሰዋል፤ ህዝብን አስጨርሰዋል፣ አሳዝነዋል፣ አስለቅሰዋል:: ከዘመናችን የክህደት ጥጎች መካከል ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተፈፀመውን አይነት ክህደት የሚመስል የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም ::
ይህች እለት ለአገር ዳር ድንበር መከበር ለመሰዋት የቆመው ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በራሱ ወገኖች ከጀርባው የተወጋባት እለት በመሆኗም በታሪክ ጠባሳነት ሁሌም ስንዘክራት እንኖራለን::
አበው እንዲህ ያለው የግፍ ግፍ ሲገጥማቸው “ሁለተኛ ግፌ ጫንቃ ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ” ይላሉ፤በመከላከያችን ላይም የሆነው ይኸው ነበር:: በግፍ ላይ ግፍ በበደል ላይ በደል ከሁሉም በላይ የሚያመው ደግሞ ግፉ የተፈጸመው ህልውናቸውን ለመጠበቅ ከ20 ዓመት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ በቆየላቸው ወገናቸው ላይ መሆኑ ሲታሰብ ነው::
በሌላ በኩልም ድርጊቱ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ በኖረች አገርና በውስጧ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን ያዋረደ መሆኑም ነው:: የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ይህችን እለት ሲያስታውሱ ለህልውና ዘመቻው የራሳቸውን ድርሻ እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ከማሰብ ጀምሮ በርካታ ነገሮችን በማድረግ ነው::
ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋት ሁሉንም እንደየአመጣጣቸው በመቀበል በድል አጠናቃለች:: በዚህም ዘመናትን ተሻግራለች:: ዛሬም የከዳተኞችን የእናት ጡት ነካሾችን ቅስም ሰብረን አገራችንን ወደአዲስ ምዕራፍ ለማሻገር ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ መስክ የአገራችን ወታደር ልንሆን ይገባል::
የከዳተኞች ጀንበር ጠልቃ እውነት ደምቃና ፈክታ የድል ጮራ በመላው አገሪቱ እስከሚወጣ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ እንደ አንድ ልብ መካሪ በአንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን አሸባሪውንና ወራሪውን የጁንታ ቡድን ልንዋጋ ይገባል::
በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሽንፈቱ የተነሳ በረዘመው ምላሱ የሚረጨውን ፕሮፖጋንዳ ወደጎን በማለትም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተባብሮና ተፈቃቅሮ እንዲሁም በአንድነት ቆሞ ለመከላከያ ሠራዊቱ ደጀንነቱን ከማረጋገጥ ባሻገር ጤና ያለው ዕድሜው የሚፈቅድለት ሁሉ ወደጦር ግንባር በመሄድ አገሩን ከዚህ ባንዳ እጅ ማውጣትም አለበት::
ልክ የዛሬ ዓመት በዚህች ቀን የተለኮሰችው እሳት እስከ አሁን አልበርድ ከማለቷም በላይ የበርካታ ንጹሐን ዜጎችን ህይወት እየበላች ብዙሃኑንም ለስደት እየዳረገች ነው፤ እኛም ከሁኔታው አጀማመር ጀምሮ አሁን ያለበትን ደረጃ ብሎም ወደፊት ሊሆን ስለሚገባው ከቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉበርሃን ኃይሌ ጋር ቆይታን አድርገናል::
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ሕወሓት በሃገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት አንድ ዓመት ሆኖታል፤ ለመሆኑ ቡድኑ በመጀመርያ ይህንን ከመፈፀሙ በፊት ሲያደርጋቸው የነበሩ ዝግጅቶች ምን ይመስሉ እንደነበር ቢያስታውሱን፤
አቶ ሙሉብርሃን፦ ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥትነቱ ከተነሳ በኋላ በርካታ ሴራዎችን ሲሠራ ነበር፤ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲም ይህንን እኩይ ተግባሩን እግር በእግር እየተከታተለ የማጋለጥ ሥራን አከናውኗል:: ቡድኑ እየሄደበት ያለው መንገድ እጅግ አደገኛ በመሆኑም ይህንን ሴራ የሚያከሽፍ ሥራ ከሥር ከሥር እንዲሠራ እንደ ፓርቲ መንግሥትና ሕዝብን ስናሳስብ ነበር::
ምንም እንኳን እኛ ለተናገርናቸው ነገሮች ፈጣን ምላሽ ባይሰጥም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሆነው ሁሉ ሆነ መከላከያችንም ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ደረሰበት::
መከላከያ ማለት የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ዘብ አጥር ማለት ነው:: ይህንን መከላከያ መንካት አገርን ማፍረስ እንደሆነ እነሱም ያውቃሉ በዚያ መንገድም መሄድ ስለፈለጉ ነው ያንን ያደረጉት::
ይህ ቡድን ግን አገር በመራበት ጊዜ እንኳን አፋኝ አምባገንን ከፋፍሎ የሚገዛ በኢትዮጵያ አንድነት የማያምን ነው:: በዚህ ምክንያት ደግሞ ለአንድነታችንም ጠንቅ ሆኖ የቆየ ነው:: ከዛሬ ዓመት ጀምሮም ይህንን እኩይ ተግባሩን ገሃድ በማውጣትና በሕዝቦች ላይ የመጨረሻ የጭካኔ ጥጉን በማሳየት ብዙሐን እንዲቸገሩ እንዲጨነቁ ሕይወታቸውን እንዲያጡ ከቤት ንብረታቸው እንዲገፈናቀሉ እያደረገም ነው::
አዲስ ዘመን፦ ቡድኑ በተለይ በጥቃቱ ወቅት በሠራዊቱ ላይ የተጠቀመው ስትራቴጂ ከውስጥ ሆኖ በመውጋት ነበር፤ በተለይ ለአንድ ዓላማ የተሰለፉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በራሳቸው ወንድም ሠራዊት ላይ ያደረሱት ጥቃት ቡድኑ ምን ያህል ሴረኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው የሚሉ አሉ፤ ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ምን ያመለክታሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፦ እውነት ነው በአገር መከላከያ ላይ የተፈጸመው ያን ዓይነት ክህደት እጅግ የሚያሳዝን ከህሊና የማይጠፋ መጥፎ ታሪካችን ነው:: የመከላከያ ውለታም በዚያ መልኩ አልነበረም መከፈል የነበረበት:: መከላከያው ለ20 ዓመት ዳር ድንበርን በተለይም ደግሞ ትግራዋይን ሲጠብቅ ደመወዙን አዋጥቶ መሰረተ ልማት ሲያሠራ ትምህርት ቤት ጤና ኬላ ሲገነባ ነበር ፤ የደረሰ ሰብል በማጨድ አቅመ ደካሞችን ሲደግፍ ነበር ፤ ነገር ግን ውለታው የተመለሰለት ጥቂት ለሆዳቸው ያደሩ ግብረ አበሮቻቸውን ይዘው አብረውት እየዋሉ እያደሩ እርሱን እራሱን እየሰለሉት ይህንን መሰሉን እኩይ ተግባራቸውን ፈጽመውበታል::
በተለይ ይህ ሁኔታ ከትግራዋይ ስነ ልቦናና ባህል አንጻር እጅግ አጸያፊና አንገት የሚያስደፋ ነው:: ይህንን አጸያፊ ተግባር የፈጸሙበት ዋና ምክንያት ግን የስልጣን ፍቅራቸውና ተመልሰው በስልጣን ላይ ቁጭ ብለው የጀመሩትን አገር የማፍረስ ስትራቴጂ ለመጨረስ ነው::
በግልጽ እኛ የማንመራት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለዋል፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ነገር ግን አልተሳካላቸውም፤ ነገም አይሳካላቸውም:: ምክንያቱም ሕወሓት ማለት በኢትዮጵያ ህዝብ ተፈትኖ የወደቀ ነው:: ስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ህዝቡን ሲያሰቃዩ ፍትህን ሲነፍጉ ከፋፋይ ሆነው አይቷቸዋል፤ በመሆኑም አሁንም ይህንን ኃይል መታገል ብቻ ነው የሚያዋጣው::
አዲስ ዘመን ፦ በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የሃገር መከላከያ ሠራዊቱ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ መበተን ችሎ ነበር፤ ሆኖም ቡድኑ ዳግም እንዲያንሰራራ የሆነው በተሠሩ ሴራዎች ነው የሚሉ አሉ፤ በተለይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕወሓት መልሶ እንዲያንሰራራ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል የሚሉ አሉ፤ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፦ ይህንን እንግዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ያልነው ጉዳይ ነው:: ነገር ግን እኛ እንናገር እንጂ በአንጻሩ ደግሞ ሰሚም አልነበረም:: ከዛሬ ዓመት ጥቅምት 24 ጥቃት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ጦርነቱ የተጠናቀቀው በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው:: ነገር ግን ካለቀ በኋላ ሕወሓት ተመልሶ አንሰራርቷል ፤ለዚህ ደግሞ በወቅቱ የተሠሩ በርካታ ሴራዎችን አንደ ምክንያት ማንሳት ይቻላል:: በተለይም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጀምሮ በፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ውስጥ ያሉ ሆድ አደር አመራሮች ለዚህ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፤ ይህ ደግሞ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው:: አሁን በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ውስጥም እንኳን ያሉ 27 ዓመት ሙሉ ከኢህአዴግ ጋር ሲሠሩ ሲዘርፉ ህዝብ ሲበድሉ የነበሩ ጀሌዎቹ አሉ ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በሁለት ቢላ እየበሉ ሴራ እየሸረቡ ሕወሓት አፈር ልሶ እንዲነሳ አድርገው እዚህ ደረጃ ላይ አድርሰውናል::
አሁንም መንግሥት ለውጡን ለማስቀጠል ከሆነ ፍላጎቱ እነዚህን ሴረኛ የሕወሓት ቅጥረኛ የሆኑ አመራሮችን ነቅሶ በማውጣት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ አለበት:: ምክንያቱም ትልቁ የለውጡ መሪ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደመሆኑ ይህ ሕዝብ ደግሞ ከዚህ በኋላ ጭቆናን አይቀበልም ፤ አንድነትን እኩልነትን ይፈልጋል፣ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልም ምኞቱ ነው፤ በመሆኑም የዚህ ለውጥ ባለቤት የሆነን ሕዝብ በማክበር የለውጡ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም መያዝ አለበት::
ሁላችንም ታግለን ለውጥ አምጥተናል፤ ከዚህ በኋላ ባለው ሁኔታም ቢሆን ለዚህ ጁንታ ቡድን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ባለመንበርከክ ለውጡን ማስቀጠልም ከመንግሥት ቀጥሎ የሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነት ነው::
አዲስ ዘመን ፦አሸባሪው ሕወሓት ከማይካድራ ጀምሮ በርካታ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ማድረሱ ይታወቃል፤ በሌላ በኩል እኔ የቆምኩት ህዝብን ነፃ ለማድረግ ነው ይላል፤ ለመሆኑ ቡድኑ በዚህ መልኩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ጭፍጨፋ ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ሙሉብርሃን፦ ይህ ነው በጣም የሚያሳፍረው:: ሕወሓት ማጥቃት ሲፈልግ ዘር ሃይማኖት ብሔር አይመርጥም፤ እራሱ ማስቀጠል የሚፈልገው ዓላማና መደብ አለው ፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በተቃራኒው የቆመን ማንኛውንም ኃይል ያጠቃል:: ይጨፈጭፋል፤ እስከ አሁንም እየጨፈጨፈ ነው :: ወደፊትም በሕይወት እስካለ ድረስ ጭፍጨፋውን አያቆምም:: ምክንያቱም በባህሪው ዴሞክራቲክ አይደለም፤ አፋኝ ነው߹ አምባገነን ነው፤ አሰላለፉ ራሱ ጠላትና ወዳጅ ብሎ ነው::
ወዳጅ የሚለው ከእኩይ ተግባሩ ጎን የተሰለፈን ማንኛውንም አካል ሲሆን፤ ጠላት የሚለው ደግሞ እውነትን ይዘው በሃሳቡ አንስማማም ያሉ ማንኛውንም አካል ነው:: ጠላት ብሎ ካስቀመጠ ደግሞ ይጨፈጭፋል፤ ያስራል፤ ያንገላታል:: በመሆኑም ይህ ሁኔታ ባህርይው ከመሆኑም በላይ የሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ የሚላት ነገር ደግሞ ሽፋኑ ናት::
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ዓይነት የጥላቻ ሁኔታና ጭፍጨፋ እንዲሁም ጦርነት ወደስልጣን መመለስ ይቻላል?
አቶ ሙሉብርሃን፦ አይቻልም:: ሕወሓት ከዚህ በኋላ እንኳን አገር መንደር መምራት አይችልም:: ተፈትኖ የወደቀ ኃይል ነው:: ማወክ፣ ማሸበር፣ መዝረፍ ብቻ ነው የሚችለው:: በመሆኑም ሕወሓት እንደ ቡድን እራሱን ለማቆየት የፈለገው በጦርነት በሽብር ተግባር በዘረፋ ውስጥ ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቡድን እዚህም እዚያም ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን እሳት በመጫር አገር ወደ ጀመረችው የብልጽግና ጉዞ እንዳትሄድ እድገቷ እንዲዘገይ ያደርግ ይሆናል እንጂ ዳግም ተመልሶ አገር ይመራል ማለት ከባድ ነው:: ነገር ግን መንግሥት አካሄዱን በደንብ መፈተሽ በትልልቅ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ሆነው ሕወሓታዊነት የሚታይባቸው አሉና እነሱ ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል:: ነገር ግን ሕወሓት ይመጣል ብለው የሚያስቡ ካሉ ህልም ነው የሚሆንባቸው::
አዲስ ዘመን፦ ቡድኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፈፀማቸው ግፎችና ጭፍጨፋዎች ባሻገር በእንስሳት እና በሰብል እንዲሁም በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ይታያል፤ ለመሆኑ ይህንን የሚያደርገው ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ሙሉብርሃን፦ ቡድኑ በአገዛዝ ዘመኑም ቢሆን ልማታዊ መንግሥት ነኝ ይላል እንጂ እራሱን ብቻ የሚያለማ መንግሥት ነበር:: ይህ ቡድን በለውጡ መንግሥት ተገፍቶ ወደ መቀሌ ከሄደ በኋላም በግል የተናገረው ነገር ኢትዮጵያን እኛ የማንመራት ከሆነ ትፈርሳለች ነበር ያሉት፤ አዎ በዚህ መልኩ የተለፋበትን እህል በማቃጠል መሰረተ ልማት በማውደም ኢኮኖሚውን በማናጋት ኅብረተሰቡን ለችግር በመዳረግ አገርን የማፍረስ ሥራቸውን ቀጥለውበታል:: በተለይም አሁን ላይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለው ኃይል በርካታ ተከታዮች ያሉት ሽፍታ አሸባሪ ነው፤ እስከ አሁንም እንዳየነው ኃላፊነት የማይሰማው የሚገድል የሚዘርፍና የሚያዘርፍ ነው:: ሕወሓትም እነዚህ ባህርይዎች በሙሉ ያሉበት በመሆኑ እነዚህ እስካሉ ድረስ ችግሩ የማያባራ በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ማስቆም መቻል ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን ፦ ቡድኑ በተለይ የአማራን ሕዝብ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ የሚያደርገው የጥፋት ሥራ እርስዎ እንዴት ያዩታል፤
አቶ ሙሉብርሃን፦ ሕወሓት በመጀመሪያ ከፋፋይ ነው፤ በቋንቋ ይከፋፍላል፤ በተለይም የአማራና የትግራይ ህዝብ በጥላቻ እንዲተያይ ሠርቷል:: ነገር ግን ይህ ሕዝብ አንድ ዓይነት በታሪክም ተጣልቶ የማያውቅ ለብዙ ዘመናት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ባህላዊ ወገቹን አብሮ ሲፈጽም የኖረ ሕዝብ ነው:: ይህንን ሕዝብ ለማጣላት ነው ሕወሓት ደፋ ቀና የሚለው ነገር ግን ህዝቡ ታሪክን ወደኋላ ሄዶ በማየት በጋራ በመሆን ሕወሓት ጥላቱ መሆኑን ተገንዝቦ መመከት እንጂ በእሱ የውሸት ፕሮፖጋንዳ መታለል የለበትም::
ሕዝቡ ሊረዳው የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ሕወሓት ራሱን ሊያቆይ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን ነው:: ሕወሓት ከአማራ ህዝብ በላይ የትግራይን ህዝብ እየተበቀለ ያለ ይመስላል፤ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ አሁንም ሆነ ከዚህ ቀደም ከሕወሓት ያገኘው ነገር የለም ከዚያ ይልቅ ቡድኑ ሕዝቡ እንዲዋረድ እንዲጠፋ እያደረገ ነው:: ሕፃናትን ሳይቀር ትርጉም ለሌለውና የራሱን የስልጣን ጥም ለማርካት ሲል ጦርነት ላይ እየማገደ ነው:: በመሆኑም ህዝቡ ቡድኑ የማንም ወዳጅ አለመሆኑን በመረዳት እኩይ ተግባሩን ማክሸፍ ይገባል:: በእርግጥ ቡድኑ ሕዝባዊ ነኝ ይላል፤ ነገር ግን ሕዝባዊነቱን በተግባር አስመስክሮ አያውቅም:: ይህንን መረዳት ደግሞ በጣም ጠቃሚ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ከላይ እርስዎም እንዳነሱት ሕወሓት የትግራይን ህዝብ በጦርነት አዘቅት ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ ሰብዓዊ ድጋፎች እንኳን በአግባቡና በወቅቱ እንዳይደርሱለት እንቅፋት ሆኖ ነው ያለው፤ በአንጻሩ ግን ሕዝቡ በተሰጠው የጥሞና ጊዜ ተጠቅሞ ወደራሱ መመለስና የዚህ እኩይ ተግባር ተባባሪ ላለመሆን ያደረገው ጥረት እምብዛም ነው የሚሉ አሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፦ አንደኛ የትግራይ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት በአፈና ውስጥ የቆየ ነው:: አሁን ደግሞ ቡድኑ በተለይም በፈጸመው እኩይ ተግባር በመንግሥት እርምጃ ተወስዶበት በጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካይነት ለውጥ ሊያይ ነው ሲባል እነዚሁ ሴረኞች በአስተዳደሩ ውስጥ ሰርገው በመግባት የትግራይ ህዝብ ችግር እንዲባባስ አልፎ ተርፎም የእነሱ ጦስ ለእነርሱም እንዲተርፈውና እንዲመቱ አድርጓል:: የትግራይ ህዝብ ከዚህ ቀደምም አንድ ቀን ሳይደላው ነበር የኖረው፤ አሁን ደግሞ ወደባሰ ችግር ውስጥ እንዲገባ ሆኗል:: በመሆኑም ህዝቡ የማሰቢያም ሆነ የሚበጀውን መምረጫ እድል አላገኘም::
በሌላ በኩል ደግሞ ከጥንት ጀምሮ በተሠራበት ፕሮፖጋንዳ ህልውናው በሕወሓት ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዲመስለው ሆኗል:: በመሆኑም በዚህ ተደናግሮ በርካታ ህዝብ ወጣት ከአሸባሪው ቡድን ጎን እንዲሰለፍ ሆኗል::
ይህንን መቀየር ላይ መንግሥትም ሆነ እኛ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የነበርን አመራሮች ከፍተኛ የሆነ ድክመት አሳይተናል ብዬ ነው የማስበው:: በተለይም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወቅት ህዝቡ ከአፈና እንደወጣ እንዲሰማው ማድረግ ብሎም ከነበረው አስተዳደር የተሻለ ነገር እንዲያገኝ ሊሆን ይገባ ነበር:: ነገር ግን አልተሠራል::
በወቅቱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥቱ መዋቅር ውስጥ የገቡ ሰዎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት በተቃራኒው በመቆም ህዝቡን ተስፋ አስቆረጡት:: በመሆኑም ለውጡ መሬት እንዳይነካ ህዝቡ ጋር እንዳይደርስ ሆነ::
ሕወሓት እንዲጠፋ መንግሥትን ጨምሮ ሁላችንም እንፈልጋለን ፤ነገር ግን እንዴት? ባለው መንገድ ነው የሚጠፋው የሚለውን ማሰብ ደግሞ ከሁላችንም የሚጠበቅ ይመስለኛል:: ለምሳሌ እኛ እንደ ፓርቲ ሕወሓት የሚጠፋው ከትግራይ ሕዝብ ላይ ሲነጠል ነው ብለን እናምናለን:: የትግራይ ሕዝብና ሕወሓትን የመለየት ሥራው ግን በጣም ፈታኝ ብዙ ጊዜና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ነው:: በመሆኑም ይህንን የሚመጥን የፖለቲካ ሥራ መሥራት ደግሞ ከገዢው መንግሥት የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው::
በጠቅላላው ሕወሓት የትግራይን ህዝብ ያዋረደ አንገት ያስደፋ ነው እንጂ ለጥቅሙ ለነፃነቱ የቆመ አለመሆኑን ህዝቡም ያውቃል፤ ዓለምም ሊገነዘበው ይገባል:: በመሆኑም ይህንን የሚመጥን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል:: አሁን ላይ ሁላችንም ልንረዳው የሚገባው ነገር ሕወሓትና የትግራይ ህዝብ ፍጹም የተለያዩ መሆናቸውን ነው:: በቀጣይ ደግሞ ሁለቱን ውሃና ዘይት የሆኑ ነገሮችን መለየት ነው::
አዲስ ዘመን፦ ይህንን አሸባሪ ቡድን ከትግራይ ሕዝብ ላይ መነጠል ግን ቀላል ሊሆን ይችላል ይላሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፦ በጣም ቃላል ነው:: ይህንን የምለው ደግሞ ለምሳሌ እኔ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ገብቼ ሦስት ወራትን ሠርቻለሁ:: በርካታ መድረኮችንም ከህዝቡ ጋር አካሂጃለሁ:: በ45 ዓመት ጉዞ የትግራይ ህዝብ ከሕወሓት ምን አገኘ የሚለውን ስንነጋገር ምንም ነበር መልሱ፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሕዝቡ ሰልችቶታል በየአስር ዓመቱም ልጆቹን መገበር በጦርነት እሳት መለብለብ አይፈልግም:: እኛም እዚያ በነበርንበት ጊዜ የተረዳነው ይህንን ነው::
ሕወሓት እኮ እንኳን ለመላው የትግራይ ሕዝብ ይቅርና 17 ዓመት አብረውት የታገሉ ሰዎችን ያለጡረታ ነው ጎዳና ላይ የበተናቸው፤ ነገር ግን ቡድኑ በጣም ሴረኛ በመሆኑ ሕዝቡን ቁስሉን በመቀስቀስ እናትህ ሞተች፣ አባትህ ተገደለ፣ እህት ወንድሞችህ እንዲህ ሆኑ ፣እያለ ነው ልቡን የሚበላውና እንዲደግፉት የሚያደርገው በመሆኑም እኛ ደግሞ ይህንን ገልብጠን ውጤታማ ኪሱ የሚገባ ሊበላው ሊጠጣው የሚችል ውጤትን አመጥተን ካሳየነው ከሕወሓት ምን አለው ያን ጊዜ ይነቃል የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል::
በሌላ በኩልም ትግራዋይ ለአገሩ ብዙ መስዋዕትነትን እየከፈለ እነ አጼ ዮሐንስ መተማ ላይ አንገታቸውን ሰጥተው እያለ ፤ ዘመቻ ሲሄዱም ሆነ ሕዝቡ እንዲከተላቸው ሲያደርጉ ኢትዮጵያ እናትህ ሚስትህ ርስትህ መቀበሪያህ ናት እያሉ በሄዱበት አገር ከላይ እርሱ ትግራዋያን በሙሉ ኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ሠርቷል:: ” አንተ ትግራዋይ ነህ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የሚል ትርክት ፈጥሯል:: ይህንን በቶሎ መቀየር ያስፈልጋል:: ይህንን እውነት ማስረዳትም ይገባል:: ያን ጊዜ ሕወሓት የመሰሪዎችና የነፍሰ በላዎች ሰብስብ መሆኑን ይረዳል::
አዲስ ዘመን፦ ይህ ቡድን አሁን ላይ አማራ ክልልን በሰፊው እያጠቃ በሰዎች ላይም ፍርሐትና መረበሽ እንዲሆን እያደረገ ነውና እንደው ሕዝቡ ከመረበሽና ከስጋት ወጥቶ ለመከላከያው ደጀን በመሆንና የሚችለውን በማድረግ በኩል እንዴት ይሳተፍ ይላሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፦ ይህ ዘራፊ የወንበዴዎች ስብስብ በአማራ፣ አፋር ክልል እንዲሁም በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: በመሆኑም በቃ ሊባል ይገባል:: ለዚህ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሆኖ መነሳቱ የግድ ነው:: በመንግሥት በኩልም እንዳለፉት ጊዜያት የመዘናጋት ችላ የማለትና የማቅለል ሁኔታ ውስጥ ከገባ ቡድኑ ወደከፍተኛ ችግር ውስጥ የማይከተን ምክንያት የለውም:: በመሆኑም በጋራ አገራችንን ማዳንና የለውጥ ጉዟችንም እንዳይደናቀፍ ማድረግ ይገባል::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ ሙሉብርሃን፦ እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014