በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እግር እስኪቀጥን ቢታሰስ እንደ ትህነግ/ሕወሓት ጁንታና ጉጀሌ ያለ አሪዮስና አረመኔ የፖለቲካ ቡድን የለም።
በዚህ ጊዜ በዓለማችን የትኛውም ክፍል እንደ ትህነግ ያለ እፉኝት የፖለቲካ ስብስብ በዲያጎን ፋኖስ እንኳ ቢፈለግ አይገኝም። በአፍሪካም ሆነ በላቲን አሜሪካ አልያም በእስያ ከትህነግ ጋር በዘመነ ጓዴነት ( ኮንቴምፓራሪስ) ሊነጻጸር የሚችል ምንም ዓይነት እኩይ ኃይል የለም። በዚህ አንድ ዓመት ያረጋገጥነው ይሄን ሐቅ ነው።
ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቁት እኩይ ተግባሮቹ እንዳሉ ሆነው። ገና ከምስረታው እንደሱ የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ ለመታገል ጫካ የገቡትን እንደ ኢህአፓ ፣ ኢዲዩና የትግራይ ድርጅቶችን እንደራደር ፣ ልዩነታችንን በውይይት እንፍታ እያለ እያግባባ እውነት መስሏቸው ለድርድር ሲመጡ አንድ በአንድ የጨረሰ አረመኔና ከሀዲ ስብስብ ነው። እነ ስሁልን ፣ ሙሴን፣ ሀይሎምንና ሌሎቹ በሃሳብ የተለዩትን እልፍ አእላፍ ታጋዮችንና ልጆቹን ፤ የዛሬ ዓመት በሰሜን ዕዝ ፣ በመከላከያ ሠራዊታችን ፣ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እንደፈጸመው ክህደት ከጀርባ ወግቶ ወይም በጥይት ደብድቦ የጨረሰ አሪዮስ ነው።
ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የሀውዜንን ሕዝብ በገብያ ቀን በአውሮፕላን አስፈጅቶ ሙሾ የሚያወርድና የአዞ እንባ የሚያነባ የሀፍረተቢሶች ስብስብ ነው። በ77 ድርቅ ለተግራይ ሕዝብ የተላከ እርዳታን ሽጦ የጦር መሳሪያ የገዛ የማፍያ ስብስብ ነው።
አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 የግፍና የዘረፋ ዓመታት በከፋፍለህ ግዛ መርሁ በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነትንና ጥላቻን ሲጎነቁል የኖረ ከፋፋይ ቡድን ነው። ከማዕከላዊ መንግሥት ስልጣን ከተነቀለ ወዲህም በተላላኪዎቹና ምንደኞቹ አማካኝነት እዚህም እዚያም ግጭትንና ሽብርን ስፖንሰር ሲያደርግና ስምሪት ሲሰጥ የባጀ እንዲሁም ደባን ሲጎነጉን ሴራን ሲሸርብ የመሽበት እኩይ ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ አንስቶ በመላ ሀገሪቱ ከተፈጸሙ የሽብር ወንጀሎች ጀርባ እጁ እንዳለበት የሚነገርለት ተስፋ የቆረጠ አጥፍቶ ጠፊ ነው። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የራሱን የሽብር ፣ የሴራ ፣ የደባ ፣ የዘረፋና የእብሪት ክብረ ወሰን ሲሰባብርና ሲያሻሽል ፤ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲያሸጋግር እና ልምድ ሲቀምር የኖረ መርገምት ፣ ባንዳና ከሀዲ ነው።
ታሪክም ትውልድም ዘላለም በማይረሷት በዚያች ጥቁር ቀን ማለትም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የፈጸመው ክህደት ፣ ዘግናኝ ሽብርና ጥቃት የዚህን አረመኔ ስብስብ ማንነት ገሀድ አውጥቶታል።
ላለፉት 21 ዓመታት የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር እየተፈራረቀበት ፤ በቀበሮ ጉድጓድ የዕድሜውን ሲሶ ገብሮ ሲጠብቀው ፤ በትግራይ ሕዝብ ደስታና ኀዘን ተካፋይ ፤ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ፤ በእርሻው በዘሩ በአረሙ በአጨዳውና በበራዩ እንዲሁም አንበጣን በመከላከል እንደ ቀንጃ(ረዳት ገበሬ) ተለይቶት በማያውቀው ፤ ከሬሽኑ እየቀነሰ ለልጆቹ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም ሲገነባ ፤ በኮቪድ 19 ለችግር ለተጋለጡ አሁንም ከእጅ ወዳፍ ከሆነች አበሉ ያካፈለ እሩህሩህና ለወገኑ ሟች የሆነ ሠራዊት በአረመኔውና ጉግማንጉጉ የትህነግ እፉኝት ቡድን ለማየት የሚዘገንንና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደትና ግፍ የተፈጸመበት በዛሬዋ ቀን 2013 ዓም ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፣ “ ለስግብግቡ ጁንታ ግፍ እስትንፋሱ ፤ ጭካኔ ነፍሱ ነው። “ ያሉትን እዚህ ላይ ያስታውሷል። ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በወልቃይት ማይካድራ ትህነግ በዘር ማጥፏት እና በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀውን 1600 ንጹሐንን በማንነታቸው የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሞል።
በወቅቱ የመንግሥታቱን ድርጅት የጦር ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ በመግለጽ ማጣራት እንደሚያደርግ ሲገልጽ፤ እንደ አመነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ጨምሮ እነ ሲኤንኤንና ቢቢሲም ይሄን ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተቀባበሉት ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና አለማድረጋቸው ሀገሪቱን ዛሬ ለምትገኝበት ውጥንቅጥ ዳርጓታል።
አሜሪካ ምዕራባውያንና ዓለምአቀፍ ተቋማት ሲጠቃ ጩኸቱን ሲያስተጋቡ ሲያጠቃ ግን ድምፃቸውን ከማጥፋት ባሻገር የሳታላይት ድጋፍ ይሰጡታል። የዚህ አረመኔ ግፍ መቼ በዚህ ይቆምና ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሽራሮን ሲቆጣጠር፣ እጅና እግራቸውን የፊጥኝ ታስረው የተረሸኑ የመከላከያ አባላትን ማግኘቱን ገልጸዋል። በየቦታው ከዚህ የከፋ ጭካኔና ግፍ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል።
ጭካኔው ልብ የሚሰብር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገልጸው ዓላማውም ኢትዮጵያን መስበር ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን ከአልማዝ የጠነከረች መሆኗንም አመልክተዋል። ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት ይሄን ሃሳባቸውን ደግመውታል።
የጁንታው ዓላማ ሠራዊቱንና ሕዝቡን አስቆጥቶ ለበቀል እርምጃ ማነሳሳት እንደሆነም ጠቁመው ፤ ኢትዮጵያም ልበ ሰፊ ሕዝብና ሠራዊት እንዳላት አስታውቀዋል። ሠራዊቱ ለሰብዓዊነት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ሰብአዊ እርዳታና አገልግሎት እየሰጠ እንደነበር አስታውሰው ፤ ነፃ ባወጣቸው አካባቢዎች ሕዝቡን እየመገበ ፣ እያከመና እየተንከባከበ ነበር ብለዋል ።
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ የዛሬ ዓመት በጥቃቱ ሰሞን የሰሜን ዕዝን ጎብኘተው ሲመለሱ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የትህነግ እፉኝት ስብስብ ምን ያህል ከትግራዋይና ከኢትዮጵያ የስነ ልቦና ውቅር ፣ ሃይማኖትና ወግ ያፈነገጠ መደዴና ወፍ ዘራሽ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ስግብግብና አረመኔ ቡድን እውን ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የተገኘ ነው ? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል። አረመኔው ስግብግብ ጁንታ ሠራዊቱ በተኛበት በውድቅ ሌሊት በማረድ ፣ በቦንብና አውቶማቲክ በማርከፍከፍ የአውሬነት ጥጉን አሳይቶናል።
አስከሬን ከሙሽራ ባልተናነሰ ክብር በሚሰጥበት ሀገር አስከሬን ገፎ ከማዋረድ ባሻገር የአውሬ ሲሳይ እንዲሆን አድርጓል። ለስልጣንና የሸረበውን ሴራ ለማስፈጸም ሲል ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ አረጋግጧል። ከዚያ በኋላ በማይካድራ ጋሊ ኮማ አጋምሳ ጭና ሰሞኑን ደግሞ በሀይቅ በኮምቦልቻና በውጫሌ ይሄን አብሮ አደግ አረመኔነቱን በአደባባይ አስመስክሯል ።
ይሁንና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ዕዝ ጥቃት ወቅት እንዳሉት ፣ ዛሬም ሕልውናችን በሉዓላዊነታችን በግዛት አንድነታችን ላይ ጦርነት ተከፍቶብናል። ይህ የጡት ነካሽ ፣ የከሃዲና የባንዳ ስብስብ የተናጠል የተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በአማራና በአፋር ክልሎች በሕዝባዊ ማዕበል የውጭ ሀገር ቅጥረኛ ወታደሮችን (መርሲናሪስ) ሳይቀር በማሳተፍ ወረራውንና ጥቃቱን እያስፋፋ ይገኛል። ሕወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ ሀገር እና ህዝብ ለማዳን ሲባል መከላከያ ሠራዊቱ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ እንደታዘዘው ሁሉ ዛሬም ሁሉንም ክልሎች ያሳተፈ ክተት ታውጇል።
ሀገር እና ህዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል። ለዚህ ነው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ” ሳንወድ ተገደን አሳፋሪ ጦርነት ውስጥ ገብተናል” ያሉት፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅና አገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል ሀገራዊ ተልዕኮ ተቀብሎ በግዳጅ ላይ የነበረን የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተከፈተው ጥቃት “ የአገር ክህደት” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በሌላ በኩል ብልጽግና ፓርቲ የተከሰተውን ጦርነት አስመልክቶ በወቅቱ አውጥቶት የነበረው መግለጫ ዛሬም ወቅታዊ ሆኖ ስላገኘሁት እንዳለ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ። የትግራይ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን በአገር ላይ ክህደት ፈጽሟል ያለውን የሕወሓት ኃይል እንዲታገል ጥሪ አቅርቦ። “የትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ጠንካራ
ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው ፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ ጭቆና ትግል ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የአገረ መንግሥት ምሥረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ሕዝቦች ናቸው ፤ “ ያለው መግለጫው ፣ በማስከተል “ የሕወሓት አጥፊ ቡድን የሀገርንና የሕዝብን ሰላም፣ አደጋ
ላይ ለመጣል የሚያደርገው ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ የትግራይን ሕዝብ የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እያቀረብን በዚህ አሸባሪ ቡድን ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል ውስጥ ከጎናችን እንድትሆኑ፤ “ ሲል ጥሪውን አቅርቧል። የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአገሪቱ ከሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ሕዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉአላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን ብልጽግና ፓርቲ ከልብ እንደሚገነዘብ ገልጿል።
“ምንም እንኳ በክልሉ አምባገነን የሆነው የሕወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን እንግልትና ስቃይ የታዘባችሁ ቢሆንም ባለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ምክንያት ለውጡን ከሕዝባችሁ ጋር ሆናችሁ ማጣጣም ሳትችሉ ቀርታችኋል፤”ያለው መግለጫው፣” ሆኖም ለረዥም ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ሰላም ደኅንነት በኃላፊነት መንፈስ ወስዳችሁ ስትጠብቁ የቆያችሁ የክልሉ ፖሊስ ፣ ልዩ ኃይል አባላትና ሌሎችም በሕዝብ ትክሻ ላይ ሆኖ እየቀለደ ባለው ዘራፊና አጥፊ የሕወሓት ቡድን ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለውን ትግል በመቀላቀል ሕዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ “
እንደማውጫ
መንግሥት ስግብግቡን የትህነግ ጁንታ ቡድን ከሁለት ዓመት በላይ የለውጡ አካል እንዲሆን በአደባባይም በጓዳም ለምኖታል። ከሰማይ በታች ያሉ የሰላም አማራጮቹን ሁሉ አሟጦ ተጠቅሟል። በሰሜን እዝ ላይ ጥቃቱን ለመሰንዘር ጥቂት ሰዓታት ቀርተውት እያለ እንኳ አይተ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ጋር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ስለክልሉ ኢኮኖሚና እና ስለአዲሱ የብር ለውጥ ተነጋግረዋል።
በዚህ አላበቃም በዚያው ምሽት አዲሱ የብር ኖቱም ወደ መቀሌ ተልኳል። ይህ መንግሥት እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለሰላምና ለፖለቲካዊ መፍትሔ የነበረውን ቁርጠኝነት ያሳያል። ክህደትና አረመኔነት ምሱ የሆነው እፉኝቱ የትህነግ ጁንታ ግን ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይለውን ክህደት ፈፅሟል። በዚህም ቀዩን መስመር አልፏል።
የኢፌዴሪ መንግሥትም በሚገባው ቋንቋ ለማነጋገር ተገዷል። ስግብግቡና ከሀዲው የትህነግ ጁንታ የሰሜን ዕዝን በውድቅት ሌሊት ካጠቃ ፤ በዚህም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከተዳፈረና ቀዩን መስመር ካለፈ በኋላ የኢፌዴሪ መንግሥት ሕግን ለማስከበር ሲንቀሳቀስ ጁንታው ተወረርሁ ፤ ጦርነት ተከፈተብኝ እያለ በተለመደው ቅጥፈቱ ዓለምን እንዳዳረሰው ሁሉ ሰሞኑን እያስፋፋው ያለውን ወረራ ለመቀልበስና ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ሲነሳ ደግሞ ተመሳሳይ እያየውን ያቀልጠዋል። ከሰሞነኛው የደሴና የኮምቦልቻ ጊዜያዊ የድል ስካር ነቅቶ በአሜሪካና በአውሮፓ ደጋፊዎቹ በየጎዳናው እንዲንከባለሉ ያደርጋል።
የተወሰነውን ዓለምአቀፍ ማህበረሰብና ሚዲያም ማደናገሩን ካቆመበት ይቀጥላል። ይሄን ሸሩን ቀድሞ ማምከንና ማጋለጥ ፤ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራውን ማጠናከር ከመልሶ ማጥቃቱ እኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ለሀገራችን ሁላችንም ቃል አቀባይ ፣ አፈ ቀላጤ መሆንን የሚጠይቅ ስለሆነ ከዲያስፖራው ጋር ተናቦ መሥራት ይጠበቅብናል።
ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ “ ይህን ሕዝብ ማገልገል በራሱ ክብር ነው !” ያሉትም ሆነ ፤ መከላከያ ሠራዊታችን “ ለዚህ ሕዝብ መሞት ክብር ነው !” ያለለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን ወደ ጎን ብሎ ከመንግሥት እና ከመሪው ጎን ከመሰለፍ አልፎ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ደጀን ያደረገ ጀግና ሠራዊት ባጠረ ጊዜና መስዋዕትነት እጅን በአፍ የሚያስጭን ድል በማስመዝገብ ያንዣበበውን የህልውና ስጋት እንደሚገፍ ቅንጣት ታክል አንጠራጠርም ።
ኢትዮጵያ ትቅደም ! እናሸንፋለን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014