እርስ በእርስ መፋቀርም ሆነ መተባበር የኢትዮጵያውያን መለያ ነው። ይህ አብሮ መኖርና መተሳሰብ የውጭ ወራሪ ሐይሎችን ለመመከትና ድል ለማደረግም ሲጠቅመን ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ ሲሆኑ የሚታዩት በዚህ ብቻ አይደለም፤የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖራቸው የውጭ ጠላቶች ሲመጡባቸው ሳይወዱ በግድ ይፋቀራሉ፣ ይተባበራሉ።
ዘንድሮ ግን የቀን ክፉ ገጥሞን የራሳችን ጠማሞች የጠላቶቻችን ፈረስ በመሆን ጥፋትና እልቂት ተሸክመው ደጃፋችን መጥተው ካልተላለቅን ካልተፋጀን እያሉ ነው ። ምክንያታቸው ደግሞ እንደ ጀብድ የሚናገሩት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ያልሆነው የብቻቸው ክብር፣ የብቻቸው ዝና፣ የብቻቸው ጥቅም መፈለጋቸው ነው። አሸባሪው ሕወሓት የዚህ ሙሾ አውራጅ ነው፡፡
ሕወሓቶች ራሳቸው ለጫሩት እሳት ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተሰጣቸውን የመልስ ምት መቋቋም ሲያቅታቸው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብና የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት ተማጸኑ። ሐሰተኛ መረጃ እየሠሩ የኢትዮጵያን መንግሥት እውነት ለመሸፈን ጣሩ፡፡ በዚህ የፕሮፓጋንዳ ሥራቸው ብዙ አልጎዱንም አይባልም፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ቢሆንም ይህን የቡድኑን መረጃ ግን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሰደር ውስጥ ገቡ፡፡ ይህ ሁኔታ ለአሸባሪው ቡድን ሰርግና ምላሽ ሆነለት፡፡ ከእነዚህ ኃይሎች ድጋፍ አስገኘለት፤ በዚህም በመጠቀም የጥፋት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡
ሐሰተኛ መረጃ በመፈብረክና በማሰራጨት ሐገርና ህዝብ እያመሰ ያለው ይህ ቡድን አሁንም የበሬ ወለደ መረጃ ማሰራጨቱን ቀጥሎበታል፡፡ በተለይ በጦር ሜዳ ውሎ ተስፋ እየቆረጠ ሲመጣ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ዋና ሥራ አርጎ ይቀጥላል፤ በዚህም ያልያዘውን ከተማ መያዙን፣ በቅርቡም የሚይዘውን አካባቢ ጭምር ይናገራል፡፡ ቀኑ ሲደርስ ትህነግ ከዋሸበት ስፍራም ንቅንቅ ሳይል ይገኛል፡፡
በዚህ ድርጊቱ የማያፍረው ቡድኑ አሁንም ሌላ ሐሰተኛ መረጃ ይሰራል፡፡ በሐሰተኛ መረጃው ያልያዘው ከተማ ፣ ያልደመሰሰው ክፍለ ጦር የለም፡፡ እንደሱ መረጃ ቢሆን በኢትዮጵያ አንድም ክፍለ ጦር ባልነበር፡፡ ሐሰተኛ መረጃው ግን በርካታ የዋሆችን ረብሿል፤ አተራምሷል፤ በዚህ መረጃ ላይ በመመስረት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ፣ ቤተሰባቸውን ይዘው የሸሹትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ቀንደኛ መሪዎቹ በፍልሚያው መድረክ እስከሚደመሰሱ ወይም እጃቸውን እስከሚሰጡ ይህ ሐሰተኛ መረጃቸው የማይቀር ስለመሆኑ የመጡበት ታሪክ ያስገነዝባል፡፡ ህዝብ የእነሱን መረጃ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ማስገንዘቢያ ቢሰጥም፣ መረጃዎቹ መሬት ላይ የሌለ እውነታ እንደማያመለክቱ ሰዎች ራሳቸው ተረድተውም መረጃውን ከመጠቀም ሲቆጠቡ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ይህ ደግሞ ለቡድኑ ጥሩ ገበያ ሆኖለታል፡ ፡ለኅብረተሰቡ ደግሞ ስቃይ አምጥተውበታል፡፡
ይህን አንደ ጦር መሣሪያቸው የሚጠቀሙበት ፕሮፓጋንዳ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚያከናወን አይደለም፤ ዋናው ፋብሪካ አውሮፓና አሜሪካ ይመስለኛል፡፡ ሕወሓት ህልውናው የተመሠረተው በምዕራባውያኑ ላይ አንደመሆኑ ምዕራባውያን ሀገሮች ያሉ የቡድኑ አባሎች የቡድናቸውን ህልውና ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ህልውና ለማረጋገጥ በዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ሠራዊቱ የትግራይ ክልልን ለቆ እንዲወጣ ሲያደርግ እነሱ ይህን ታላቅ የመንግሥት ቅንነት እንደ ሽንፈት ቆጥረው አሁንም በሐሰተኛ መረጃቸው ከበረሃ በድል ከተማ እንደገቡ አርገው ማውራት ጀመሩ፤ ዘፈኑ ፤አዘፈኑ፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ጀግና አሏቸው፡፡
አጋጣሚውን ለመልካም ተግባር ማዋል ሲገባቸው በብርሃን ፍጥነት ከድረሱልን ጥሪ ወደ በቀል በመግባት ወረራውንና ዘረፋውን ገቡበት። መዳረሻቸውን የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት በማድረግ ተከታያቸውን ተስፋ ይመግቡት ጀመር፤ በጦርነቱ ገፉበት፡፡ የትግራይን ወጣቶች ሴት ወንድ ሳይሉ መገበሩን ቀጠሉበት። አንዳንዶቹን ከድል በኋላ ስለሚሰጣቸው ሥራ እየዋሹ ፣አንዳንዶቹንም እያፈሱ በጦርነቱ ማገዷቸው፡፡ አማራጭ የሌለው የትግራይ ህዝብም በምንም ስሌት ቡድኑ በአሸናፊነት በማይጠናቀቀው ጦርነት ውስጥ እየገባ የሳት ራት እየሆነ ይገኛል።
በአንጻሩ ፊትም በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸው ብርታት እየሰጧቸው መጡ፡፡ ዛሬ ላይ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለተመለከተ የአሸባሪው ትህነግ እድሜ አጭር መሆኑን ይመሰክራል፤ ትህነጎች ጉድጓዳቸውን እየማሱ ናቸው፤ ለዚያውም አርቀው፡፡ የሳት እራት ለመሆን መጥተዋል፡፡ ይህ ድፍረታቸው ግን ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ አንድ እያረጋቸው ነው፡፡ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል በውጤትም መታጀብ ይኖርበታል፡፡
የወያኔ ባለሥልጣናት ይህን አሳምረው ያውቃሉ፤ እድሜያቸውን ለማራዘም ግን የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። የሰሞኑን አያያዛቸውንና እንቅስቃሴያቸውን ያስተዋለ ደግሞ ትግራይን ትውልድ አልባ እስከማድረግ ከመሄድ የሚመለሱ አለመሆናቸውን ይገነዘባል። ወገኔ ለሚሉት ያልተመለሱ ወገኔ ለማይሉት እንደማይመለሱ ሰሞኑን በገቡባቸው ከተሞች ከፈጸሙት ጭፍጨፋና አስገድዶ መድፈር እንዲሁም ዘረፋና ውድመት መረዳት አያዳግትም፡፡
ሕወሓት ይዞት የሚመጣው የጥፋት እሳት ቤት የሚዘል፣ ሰውና ንብረት የሚለይ አይደለም። በመሆኑም ጠንከር ብለን የእነዚህን ቡድኖች ህልም በማምከን የዜጎችን ሰቆቃና ስጋት አስቀድሞ ማስወገድ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ ኅብረታችን ብቸኛው መንገዳችንም ጉልበታቸንም ነው።
ጠላቶቻችንንም የመጨረሻ መውደቂያቸው የእኛ ኅብረት መጠናከር መሆኑን የተገነዘቡ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ አጠንክረው ሲሠሩ የኖሩትና አሁንም እየሠሩ ያሉት እኛን በመከፋፈሉ ላይ መሆኑም ከዚህ የመነጨ ነው። እነዚህ አጥፊ ቡድኖች በቀጥታ ጦርነት ከከፈቱባቸውና የጦር አውድማ ካደረጓቸው አካባቢዎች አላማቸውን ሊያሳካ የሚያስችል ሁኔታ እንደማያገኙ ሲረዱ በየቦታው የሚጭሩት እሳት መኖሩ ያደባባይ ሚስጥር ነው።
ሠላሳ ዓመት ተሞክሮ የከሸፈው የመጣብህ የወረረህ አካሄድን ዛሬም በተለይ በአሜሪካና አውሮፓ ባሉ ሚዲያዎቻቸው እያስተጋቡት ይገኛል። አሁንም የተከፈተብንን ይህን የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመመከት ጠንከር ያለ ምላሽ ለመስጠት በህብረት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
በእኔ እይታ የውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነት እንዲኖርና ጫና ለማስፈጠር ወያኔ ከምትሄድበት ርቀት አብልጣ እየሠራች ያለችው የራሳችንን ስነልቦና በመፈረካከሱ ላይ ነው። በዚህ በኩል የተጋነነ ባይሆንም በሀገር ውስጥ ዘመቻቸው እያስመዘገቡት ያለ ውጤት መኖሩን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። በዚህ በኩል በልጠውናል፤ በየደቂቃው በስውር አካውንት እንዲሁም በታዋቂ ሰዎችና ባለሥልጣናት ስም በሀሰት በተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶች የሚለቀቁት የፎቶ ሾፕ ቅንብር ዜናዎች እየፈጠሩ ያሉት ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።
ከእዚህ ሐሰተኛ መረጃቸው በቅድሚያ ራሳችንን እንጠብቅ ፡፡ እያንዳንዳችን እንደ ግለሰብ የሐሰት ማደናገሪያው ሰለባ እንዳንሆን የምናገኘውን መረጃ ሁሉ ከመቀበል ይልቅ ግራ ቀኙን አይተን እናረጋግጥ። ለዚህ ደግሞ ቢያንስ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም ያለባቸውን ሚዲያዎች አንድም ለመረጃ ምንጭነት አልያም ላገኘነው መረጃ እውነታነት ማረጋገጫ መጠቀም አለብን።
በሁለተኛ ደረጃ በአቅራቢያችን ያሉ የምናቃቸው ሁሉ በትንሽ በትልቁ እንዳይሸበሩ ያገኘነውንና ፈትሸን ያጣራነውን መረጃ ልናካፍላቸው፣ ያገኙትን መረጃ ሳያጣሩ ለሌሎች እንዳያስተላልፉ የማድረግ ኃላፊነትም አለብን። ይህን ማድረጋችን በቀዳሚነት የሀገራችንን ህልውናና የህዝባችንን ደህንነት ለማስጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ያስችለናል። እንደ ግለሰብም የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጣር በወጣው አዋጅ የህግ ተጠያቂ ከመሆን የሚታደገንም ይሆናል። በመሆኑም ለአውደ ውጊያውና በጦርነት ለተፈናቀሉ ድጋፍ ለማድረግ የጀመርነውን የህብረት አካሄድ በፕሮፓጋንዳ ዘመቻችንም ልንቀጥልበት ይገባል እላለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014