ክፉ አውሬ አይለምድ፤ ከለመደም አይወለድ፤
በዓለም ወታደራዊ የተጋድሎ ጥቁር ታሪክ ውስጥ በክፉ ምሳሌነታቸውና ትውስታዎች በሐዘንና በቁጭት ሲጠቀሱ ከሚኖሩት ክስተቶች መካከል፤ ምናልባትም በልዩ ባህርያቸው ልዩ የማስተማሪያ ስፍራ ከሚሰጣቸው ውስጥ፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በእኛዎቹ ሽብርተኛ ጉዶች የተፈጸመው ክህደት አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር እንገምታለን።
ከኢትዮ ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ለሠሜናዊው የሀገራችን ክፍል ጽኑ ዘብ ሆኖ ግዳጅ ላይ የነበረው የመከላከያ ሠራዊታችን በትግራይ ምድር የኖረው በወታደራዊ ዩኒፎርሙ (ፋቲግ) ብቻ ይለይ ካልሆነ በስተቀር በዕለት ተዕለት ኑሮውና እንቅስቃሴው እጅግም ከሕዝቡ አኗኗር ልዩነት አልነበረውም።በየትኛውም ሀገር ወታደራዊ ሕግ መሠረት አንድ የመከላከያ ሠራዊት ከመደበኛ ወታደራዊ ግዳጁ ጎን ለጎን ሕዝቡን እንዲታደግ ጥሪ የሚደርሰው ያልተጠበቀና ድንገተኛ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው በሕዝብ ላይ ጉዳታቸው የከፋ እንዳይሆን እርዳታና ድጋፍ እንዲያደርግ ሲታዘዝ ብቻ ነው።
እንጂማ ከወታደራዊ ካምፖቹና ከምሽጉ ውስጥ እየወጣ አለኝታ የሆነለትን ሕዝብ ከጓዳው እስከ ግብርና ማሳው፣ ከሀዘኑ እስከ ደስታው ባሉ የዕለት ተዕለት ጉዳዮቹ እየገባ “አለሁልህ” በማለት በዕዝ አመራሮቹ መመሪያ እየተሰጠው የሸሚዙን እጅጌ ጠቅልሎ በገበሬው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሳተፍ ግዴታ የለበትም።ከዘር እስከ አረም፣ ከኩትኳቶ እስከ ዐውድማ እየዘለቀም የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ማድረግም አይጠበቅበትም።መደበኛ ወታደራዊ ዲስፕሊንም ቢሆን ይህን መሰሉ ለሕዝብ የሚሰጥ ተጨማሪ አገልግሎት ምንም አንኳን ተግባሩ መልካም መስሎ ቢታይም በሠራዊቱ አባላት ዘንድ በስፋት እንዲለመድ አይበረታታም።ለምን ቢሉ ከዋናው መሠረታዊ ተልዕኮው እንዳያዘናጋው ስለማያስፈልግ።
እርግጥ ነው ተፈጥሮ ፊቷን አጨፍግጋና ባህርይዋን ለውጣ አደጋ ስታደርስ፤ ለምሳሌ፡- የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የሰደደ እሳት አደጋ፣ ጎርፍና ድርቅን የመሳሰሉ “በላዎች” በሀገር ላይ ሲከሰቱና ለሠራዊቱ የግዳጅ ጥሪ ሲደርሰው ምላሽ ለመስጠት መጣደፍ ውዴታው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ጭምር ሊሆን ይቻላል።
በመቀሌ ውስጥ የነበረውና ከሀገሪቱ የመከላከያ ኃይል ሰማኒያ ከመቶ በላይ ድርሻ የያዘው ሠራዊት ግን ግዳጁን ሲፈጽም የኖረው ከመሠረታዊው ተልዕኮው ባልተናነሰ ሁኔታ ሕዝቡን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይል በማገልገል ነበር።ት/ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች የመማሪያ ክፍሎችን ሲያንጽ፣ በግብርና ወቅትም ከዘር እስከ አዝመራ እኩል በመሳተፍና አንበጣ እስከ መከላከል ድረስ አያገባኝም ሳይል ጉልበቱንና ሀብቱን ሲገብር እና በልዩ ልዩ ልማቶች ሲሳተፍ መኖሩ የተገለጠ ተግባሩ ነበር።ውሎውና አምሽቶው በግዳጅ ቀጣና እንደተሰማራ የሉዓላዊነት የክብር ዘብ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የትግራይ ቤተሰብ እንደ አባል በመሆን ጭምር በአለኝታነት ሲደግፍ መኖሩ አይካድም።ይህንን እውነታ የሚከዱ ካሉም እነርሱ የከፉ ከዳተኞች ናቸው።
ይህ ጸሐፊና አራት ወንድምና እህቶቹ ተወልደው ያደጉትና የልጅነታቸውን ዕድሜ ያጣጣሙት በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ነበር።ጸሐፊው የወላጅ አባቱን በርካታ ወታደራዊ ሰነዶችና ታሪኮች በቅርበት ይከታተል ስለነበረ ለአጠቃላይ ወታደራዊ እውቀቶች እንግዳ አይደለም።ከዚህ በላይ የዘረዘራቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች ለመዳሰስ የሞከረውም ከዚሁ የቤተሰባዊ የዕውቀት ውርስና የንባብ ተሞክሮው በመነሳት መሆኑን ልብ ይሏል።
የጥቅምት 24 ቀን 2013 መሪር ትውስታ፤
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጠላቶቹ የተከዳውና የተወጋው በግዳጅ ቀጣና ሲያከናውናቸው በኖረው ወታደራዊ ግዳጆችና ማኅበራዊ ተሳትፎዎች “አመድ አፋሽ” ሆኖ ውለታው በመዘንጋቱ ብቻ አልነበረም።እንደ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር በምሽትና በእረፍት ሰዓታት የሠራዊቱ አባላት የየግል ታሪካቸውን በቤተሰባዊ ፍቅር ይጋሩ ነበር።
ገመናቸውንም እየተገላለጡና በሚያስቀው እየሳቁ በሚያሳዝነውም አብሮ ስሜትን እየተጋሩ “አንተ ትብስ እሷ ትብስ” በመባባል ሲደጋገፉ ማስተዋል የወታደራዊ ሌላው ውሎ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም።“ባለቤቴ ወለደች፣ ከቤተሰቤ ይህ ስጦታ ስለመጣልኝ ደስ ብሎኛል፣ እንዲህ ዓይነት ሐዘን ሰምቼ ተረብሻለሁ ወዘተ.” እየተባባሉ አንጽናኝና ተጽናኝ ሆነው አብረው “በፍቅር” እየኖሩ ብዙ የሥነ ልቦና መደጋገፎችን ተጋርተዋል።ህሊናቸው የሞተው አሸባሪዎች የካዱትና ጦር የሰበቁት በዚህ መሰሉ ማኅበራዊ ትዝታም ላይ ነው።
ይህ ሰብዓዊና ጤናማ ግንኙነት ለጨካኞቹ ጠላቶች ቁብ ሳይሰጣቸው ቀርቶ የአውሬነት ባህርይ በማሳየት እንደምን ጀግናውን ሠራዊት እንደከዱት ለመገመትና ለማሳብ በእጅጉ ይከብዳል።የሠራዊቱን አባላት ደስታና ሀዘን በአንድ ጆሯቸው እያዳመጡ ሲቀምሩ የኖሩት ለካንስ ከአንድ ኮዳ ውሃ የተጋሩትንና ከአንድ የሬሽን ማዕድ አብረው የተቋደሱትን ያን “የትግራዋይ ደም” የለበትም ብለው ያሰቡትን ጀግና ሠራዊት እንዴት እንደሚጨፈጭፉና እንደሚያዋርዱ ነበር።“የዋህ ርግብ በእባብ አፍ እንቁላሏን ትጥላለች” ብሂል ጉዳዩን በሚገባ ይገልጠዋል።
በሠይጣናዊ ክፋት የተሞሉት ጠላቶቹ የዕዝ ማዕከላቱን ወረውና የተከበሩ አዛዦችን፣ የወታደራዊ ትጥቅና ስንቁን በቁጥጥር ስር አዋልን በማለት የግፋቸውን ጥግ በሌሊት ሊፈጽሙ እንደምን እንደጨከኑ ማሰላሰሉ አንኳንስ የተጠቃውን ሠራዊት ቀርቶ ጤናማ አእምሮ ላለው ሰውም ቢሆን ጉዳዩ ውስብስብ እንቆቅልሽ መሆኑ አይቀርም።ከገደሉም በኋላ ቢሆን በወንድም እህቶቻቸው በድን እየተሳለቁ “በመብረቃዊ ጥቃት ድል አደረግን” በማለት በለመዱት የከበሮ ድለቃ ወራሪ ጠላትን እንደቀጣ “ጀግና” ጮክ እያሉ ከሙታኑ ጋር የሙት ህሊናቸውን እስትንፋስ አፈር እያለበሱ መሆናቸው አልገባቸውም።በባህላዊ ጭፈራቸው ክብ ሠርተው አቧራውን እያጨሱ ሲፈነጥዙም ታሪክ የማይረሳውን የከፋ አሻራቸውን በራሳቸው ምድር ላይ እያተሙ እንደሆነም አልተረዱም።
ሰብዓዊ ባህል በሚጠየፈው ድርጊት የጨፈጨፉትን የጀግናውን ሠራዊት ኩሩ አባላት በድን ፀሐይ ላይ በማስጣት ለአራዊትና ለአሞራ ቀለብ እንዲሆን መፍረዳቸው ምን ያህል በግፍ ተግባር እንደታወሩ የሚያሳይ ነው።በሲኖ ትራክ መኪና ሳይቀር እየደፈጠጡ በጀግናው ሠራዊት ላይ የግፋቸውን እልቂት ሲከውኑበት ፈጣሪ የሚባል ፈራጅ እስከ መኖሩም ዘንግተዋል።እነዚህ እኩይ የሠራዊቱ አራጅ መኮንኖችና አልባሌ ወታደሮች ይህንን መሰል ግፍ በጀግኖቹ ኩራቶቻችን ላይ በመፈጸም በዓለም ታሪክ ተፈጽሞ የማያውቅ “ዲያቢሎሰው ገድል” ማስመዝገባቸውን የሚደሰኩሩት እንደ ጀብድ ነው።“ደስ ብሏቸው” የሰከሩበት ይህ የከረፋ ታሪካቸውም በጥቋቁር የዓለማችን የታሪክ መዛግብት ውስጥ አዲስ “ታሪክ” ሆኖ ስለተመዘገበ “ጅጋኑ” እየተባባሉ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ቢያቅራሩ አይገርምም።
የክፋት ድርጊታቸው በዚህ ብቻ ሳይገታም ንፁሐን ዜጎችን በመጨፍጨፍ የደም ጥማት ሀራራቸውን አረኩ።የማይካድራ፣ የጋሊኮማና የሌሎች አካባቢዎች መስዋዕቶች “ፈጣሪ ሆይ ፍረድልን!” በማለት ንፁሑ ደማቸው ከፀባዖት ፍትሕን እየተማጠነ እንደሚጮኽ እንኳን የጠረጠሩ አይመስልም።“የተፈጠርነው በሃይማኖት በከበረ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው” የሚለው ትምክህታቸውንና የእምነት ውርሳቸውን ጊዜ ሲገልጠው አየንላቸው፤ ሰማንላቸውም።በደም የጨቀየው እጃቸውና በግፍ የታወረው ህሊናቸው እያንቀዠቀዠ እነሆ ዛሬም ድረስ ሀገሪቱን “ለማፍረስ” የሚያቅበዘብዛቸው የዚሁ የቃዬላዊ መርገምት ውጤት ነው።
ዓለም ከተፈጠረ፤ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ በሌሎች ሀገራት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ክህደት ተፈጽሞ ስለመሆኑ የዘርፉ ጠበብት ቢያሳውቁን አይከፋም።መሠረታዊው እውነታ ግን በፍጹም ሊዘነጋ አይገባም።በረሃ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በደም መሃላ የተሻረኩት ዲያቢሎስ ራሱ እንዲህ ዓይነቱን ክህደትና ክፋት ፈጽሞት ስለመሆኑ ያጠራጥራል።
ይሄ ሁሉ የክህደት ማዕበል ቢፈታተነውም መከላከያ ሠራዊታችን እጥፍ ድርብ ጀግና ነው ብለን የምንመሰክረው አለምክንያት አይደለም።የመከራው ዶፍ የወረደበት ሠራዊታችን በሞት ሽረት ተጋድሎ ከጠላት ምርኮ ያስተረፋቸውን መሳሪያዎች አቀባብሎ በአባሪ ተባባሪዎቹ ላይ በቀል ለመፈጸም አልጨከነም።የክህደቱን ብርታት መቋቋም ተስኖትም “ገበርኩ” ብሎ ለኢትዮጵያ እናቱ የገባውን የመሃላ ኪዳን አላፈረሰም።መበተኑና መዋረዱ ተስፋ አስቆርጦትም ፊቱንና ልቡን ከሙያው አላዞረም።ይልቁንስ “ኢትዮጵያ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ!” በማለት በግፍ በተሰውት ጀግና ጓዶቹ እየማለ ራሱን በፍጥነት አደራጅቶ ለተጋድሎው ተጋ እንጂ ተስፋ አልቆረጠም።ለዚህም ነው ይህንን ክፉ ቡድን ከነክንፉ ለመንቀል ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆኖ መዝመት አለበት የሚባለው።
በክፋት ተጸንሰው በክፋታቸው ተጠልፈው የሚወድቁ ከንቱዎች፤
የሕወሓትን ጭካኔ ለመግለጽ ቋንቋችን አቅም ያነሰው ይመስላል።“ኔፊሊም” (ዘፍጥረት ምዕራፍ 6) የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ስያሜ ይበልጥ ሊገልጻቸው እንደሚችል ባለፈው ረቡዕ ጽሑፌ ላይ ጠቅሼ ማለፌ ይታወሳል።ጥቂት ማብራሪያ ማከል ካስፈለገ “ኔፊሊሞች” ከአጋንንቶች ጋር የተዳቀሉ ግማሽ የሰው ፍጡራን መሆናቸውንና የእርኩሰት ተግባራቸውንም በተመለከተ የተፈጠሩት እልቂት ለማድረስና ለማውደም እንደሆነ የእምነቱ የትርጓሜ መጻሕፍት (Commentaries) ማብራሪያውን በዝርዝር ያስነብባሉ።ተጨማሪ መግለጫ ካስፈለገም “ሲፊኒክስ” (ግማሽ ሰው ግማሽ አውሬ) የሚለው ስያሜ ሊወክላቸው ይችላል።ከእነዚህ ሁለቱ ሌላ ተጨማሪ ገላጭ ቃል ለመፈለግ መሞከሩ ከማድከም ውጭ ብዙ ርቀት አያስኬደንም።
ለምን በእነዚህ ቃላት ይህንን አረመኔ ጨካኝ ቡድን ለመግለጽ እንደተፈለገ የተወሰኑ የቅርብ ጊዜ ታሪኮችን ማስታወሱ ብቻ በቂ ይሆናል።ቡድኑ ሥልጣን በያዘ ማግሥት ከፈጸማቸው የከፉ ድርጊቶች መካከል ቀዳሚው የሀገሪቱን የጦር ኃይል “የደርግ ሠራዊት” በማለት መዋቅሩን ሙሉ ለሙሉ በማፈራረስ በራሱ ጀሌዎች መተካቱ አንዱ ነበር።ያዋረደው ተቋሙን፣ ሠራዊቱንና ሀገርንም ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል።
በሁለተኛነት የምናስታውሰው “በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ የከፋ ደም አፋሽ” እየተባለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀሰውና ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም ተጀምሮ ለዓመታት የቀጠለው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ሌላው አብነት ነው።በዚህ ከሃዲ ቡድን አስተውሎት በጎደለው ጭፍን ውሳኔ በተካሄደው በዚያ ጦርነት የተሰዋው የሰው ኃይልና የባከነው የሀገር ሀብት ምን ያህል እንደነበር ዛሬም ድረስ ተጣርቶ ለሕዝብ በይፋ አልተገለጸም።ክህደት ባህርይው የሆነው ይሀ አሸባሪ ቡድን “ወዳጄ” ሲባባሉ ከኖሩት ከሻዕቢያ ጋር ተነጋግሮ ችግሩን በሰላም ከመፍታት ይልቅ ምርጫ ያደረገው ጦርነትን ነበር።ጦርነቱ ከቆመም በኋላ በአደራዳሪ የውጭ መንግሥታት የተወሰነውን ውሳኔ በጭፍን ውሸት ሕዝቡን አታሎ የሀሰት ብስራት በማሰማት መሳለቁ የሚዘነጋ አይደለም።
በጥቅምት 24 ዕለታት የተፈጸሙ ሌሎች ክስተቶች፤
የ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ ይሄው እኩይ ቡድን ከቅንጅት ፓርቲ ጋር የተጋባው እልህ እያንተከተከው ምን ያህል ንፁሐን ዜጎችን ለሞትና ለእስር እንደዳረገ ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው።የመንግሥትን ሥልጣን በምልዑ በኩለሄ ብርታቱ ጨብጦ የነበረው ይሄው ቡድን አሰቃቂ የግፍ ተግባር በቃሊቲ የሕግ ታራሚዎች ላይ የፈጸመው ጥቅምት 24 ቀን 1998 ዓ.ም ነበር።በዚያ እልቂት ከመቶ ሃምሳ በላይ ንፁሐን የሕግ ታራሚዎች እንደተገደሉ የዓይን ምስክር የሆኑ ጸሐፍት ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ውስጥ ለማሳየት ሞክረዋል።የዚሁ ክስተት ሙሉ ሪፖርት በገለልተኛ ወገን በግልጽነት ባለመቅረቡ ቁጥሩ እየተዛባ ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዓመታት አስቆጥሯል።
አሸባሪው ሕወሓት ጠላትነቱ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ጎላ አድርገው በሚያቀነቅኑ ዜጎች ላይ ጭምር እንደነበር አንድ ተጨማሪ ክስተት ማስታወስ ይቻላል።አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በሙዚቃው ጉልበት የሚሊዮኖችን ልብ የማረከ የጥበብ ሰው መሆኑ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው።ስለ ኢትዮጵያ ያቀነቀናቸው ሙዚቃዎቹም ከሺህ ቃላት የሚበልጥ አቅም እንዳላቸው ይታወቃል።ይህ የጥበብ ሰው ምክንያት ተፈልጎለት ወደ ወህኒ እንዲወረወር የተደረገው “ሰው በመኪና ገጭተህ ገድለሃል” የሚል ሰበብ ተፈጥሮ ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም እንደነበር አይዘነጋም።“የፍትሕ አካሄዱን” ጉዳይ በሆድ ይፍጀው እንለፈውና የአርቲስቱ መታሰር ምን ያህሉን ዜጋ ለቁጣ ቀስቅሶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የሀገርንና የሕዝብን ሀብት ግጦ ማራቆቱ፣ በቋንቋና በብሔር አደናቁሮ የኢትዮጵያዊነትን መሠረት ማናጋቱ፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በአጎብዳጅነት ቼ እየተባለ “ታላላቅ ነን” ለሚሉ ሀገራት መሪዎች የዲፕሎማሲ መጋለቢያ ፈረስ መሆኑ፣ ፖለቲካውን “የአባት ርስት አድርጎ” በፈላጭ ቆራጭነት መፏለሉ፣ ሥልጣን ከእጁ ከወጣ በኋላም በእብሪትና በትዕቢት ተነሳስቶ ለወረራ መሰለፉ፣ ከሌሎች መሰል የጥፋት ኃይላት ጋር ኪዳን በመግባትም ሀገርን ለማፈራረስ ምሎ መገዘቱ ወዘተ. የአሸባሪ ቡድኑ የባህርይ መገለጫዎች ናቸው።
የእነዚህ ወንጀሎች ከፍታ የሚደመደመውና ከፋሽስቶችና ከናዚዎች ድርጊት ልቆ በዓለም የወታደራዊ ታሪኮች ውስጥ እየተረገመና እየተዘበተበት በስፋትና በቀዳሚነት ሲጠቀስ የሚኖረው መሪ ክስተት ግን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በጀግናው የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ነው።በዛሬው ዕለት በሀዘን ውስጥ ሆነን የምናስታውሰው ያ አሰቃቂ ግፍ ሳይውልና ሳያድር በአደባባዮቻችን ላይ ልዩ ልዩ መታሰቢያዎች ቆመውለት መፃኢው ትውልድ የቡድኑን የክህደት ጥግ በሚገባ እንዲገነዘብ ቢደረግ መልካም ይመስለናል።
መሰል ታሪኮች እንዳይፈጸሙም ማስተማሪያ ስለሚሆን የሚመለከተው ክፍል በሚገባ አስቦበት የተግባር እርምጃ እንዲወስድ በዜጎች ድምጽ እንጠይቃለን።“ለማይታወቅ ወታደር” ሳይሆን በግፍ ለወደቀው ጀግናችንና በፍልሚያው ጎራ ላይ ተሰልፎ ለሚዋደቀው በሚገባ ለምናውቀውና ለሚያውቀን ሳተና ክብር ይሁን።ኢትዮጵያ በልጆቿ ደምቃና ተውባ ከፍ ትበል!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014