አዲስ አበባ፡- ኖርዌያዊቷ የ2018 ባሎንዶር አሸናፊ የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ኮከብ አዳ ሄገንበርግ ራሷን ከሃገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ለማግለል መወሰኗና በሚቀጥለው ክረምት ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 7 በፈረንሳይ በሚካሄደው የዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ እንደማትሳተፍ መግለጿ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማርቲን ሲዮግረን ለቢቢሲ ስፖርት እንደተናገሩት ተጫዋቿ በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ የመጫወት ፍላጎቷ እየቀዘቀዘ የመጣው በ2017 ኖርዌይ አንድም ጎል ሳታስቆጥር ከአውሮፓ የሴቶች ሻምፒዮና መውጣቷን ተከትሎ ነው፡፡ በ2018 በሴቶች እግር ኳስ የባሎን ዶር አሸናፊዋና የ2017 የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋጭነትን ክብር የተጎናጸፈችው የ23 ዓመቷ አጥቂ ኖርዌያዊቷ አዳ ሄገንበርግ ሰሞኑን ደግሞ በዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ እንደማትሳተፍ አቋሟን ግልጽ አድርጋለች፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረሷም “ኖርዌይ ውስጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ክብር የላቸውም” የሚል ቅሬታን በምክንያትነት አቅርባለች፡፡
የተጫዋቿ ራሷን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሏንና በቀጣይ ክረምት በፈረንሳይ በሚካሄደው የዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ እንደማትሳተፍ ማሳወቋን ተከትሎ አሰልጣኙ የዓለም ኮከቧን ብቃት ለቡድናቸው ስኬት የመጠቀምን ትልቅ ዕድል አጥተዋል፡፡ በመሆኑም አሰልጣኝ ማርቲን ሲዮግረን፤ “ከአዳ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የምንችለውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ ተከታታይ ስብሰባዎችን አድርገን ነበር፤ ሆኖም ላለመጫወት ለራሷ ውሳኔ ላይ ደርሳለች” ብለዋል፡፡
ብርግጥም የተጫዋቿ ውሳኔ በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም “እንደ አሰልጣኝ ትኩረት ማድረግ ያለብህ ቡድኑ ውስጥ መሳተፍ በሚፈልጉ ተጫዋቾች ላይ ነው፤ አዳ ደግሞ አትፈልግም” ያሉት አሰልጣኝ ሲዮግረን፤ ፍላጎቷ ከሆነ ውሳኔያዋን እንደሚያከብሩላትና ቡድኑን ስኬታማ ለማድረግ ከሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሦስት ጊዜ ሻምፒዮንስ ሊግ ባለድሏና የ2018 ባሎን ዶር አሸናፊዋ የሊዮኗ አጥቂ ኖርዌያዊቷ ኢንተርናሽናል አዳ ሄገንበርግ ራሷን ከአገሪቱ ብሔራዊ ቡድንና ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ መድረክ ለማግለል መወሰኗ ለኖርዌያውን ያልተጠበቀ መጥፎ ዜና ሆኗል፡፡ ተጫዋቿ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በኖርዌይ እግር ኳስ ማህበርና በሃገሪቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ታሪካዊ የእኩል ክፍያ ስምምነት ከመፈረሙ ጥቂት ወራት በፊት መሆኑ ደግሞ የበለጠ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በይበል ካሳ