በስፖርታዊ ውድድሮችና ስልጠናዎች ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን በተመለከተ ለስፖርት ክለብ የህክምና ባለሙያዎች(ወጌሻዎች) የተለያዩ የፊዚዮቴራፒ ስልጠናዎችን እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስፓይን የስፖርት አማካሪ ድርጅት(SSC) ከኢትዮጵያ ፊዚዮቴራፒ ማህበር(EPTA) ጋር በመተባበር በስፖርታዊ ውድድርና ስልጠና ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶች፣ የስፖርት ጉዳት ህክምና አሰጣጥ እና ጉዳት ከመከሰቱ በፊት የመከላከል ስልጠና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ሀኪሞች ሰሞኑን ለአምስት ቀናት የቆየ ስልጠና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መስጠት ችሏል፡፡
ስልጠናው ስፖርተኞች በውድድር ከጉዳት ውጪ ሊያደርጋቸው የሚችለውን የህክምና ክፍተት የሚሞላ ሲሆን ባለሙያዎች ጉዳት ሲከሰት አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት በመስጠት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሌላ የህክምና ማዕከል በማድረስ ትክክለኛ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ ስልጠናው በቂ የሆነ እውቀት፤ ክህሎት ብሎም ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚረዳ ስልጠናውን የሰጡት ዶክተር ዊንታና መኮንን ገልፀዋል፡፡
በስልጠናው ከኢትዮጵያ ቡና፤ ኤሌክትሪክ፤ንግድ ባንክ፤ሀዋሳ ከተማ፤መከላከያ፤ አዳማ ከተማ፤መቀለ 70 እንደርታ፤ትግራይ ፖሊስ ዋልታ፤ብሩህ ተስፋ ብስክሌት ክለብ ፤ወልዋሎ ብስክሌት ክለብ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፤ የካ ክፍለ ከተማ፤ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና በግል የመጡ በአጠቃላይ 34 ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ስፓይን የስፖርት አማካሪ ድርጅት በስፖርታዊ ውድድርና ስልጠና ወቅት አደጋዎች ሲከሰቱ በእርዳታ አሰጣጥ ስልጠና ላለፉት ጊዜያት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድንገተኛ ህክምና ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ሲሰራ እንደቆየ ስራ አስኪያጁ አቶ ዮናስ አለማየሁ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ስልጠናዎችም በስፖርት ክለቦችና ዩኒቨርሲቲዎች በመስራት ላይ ለሚገኙ አሰልጣኞች፤ቡድን መሪዎች ፤የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ለስምንት ዙር አሰልጥኗል፡፡
በእነዚህ ዙሮች ለመጀመሪያ ጊዜ “የስፖርት ህክምና አሰጣጥ እና ፊዚዮቴራፒ’’ የሚል ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስፖርታዊ ውድድር ወቅት ጉዳቶች እንዳይከሰቱ ቅድመ አካላዊ ዝግጅትን ማድረግ፤ጉዳቶች ሲከሰቱ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ መከላከል እና ቅድመ ሆስፒታል ህክምና መስጠት የስልጠናው አላማ ነው፡፡ እውቀትና ክህሎትን ለባለሙያዎች በተገቢው ሁኔታ በማስጨበጥ በስፖርታዊ ወድድርና ስልጠና ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ ስፖርታዊ ጉዳቶችን አስፈላጊውን የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥን የተመለከተ እስካሁን ከሁለት መቶ በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ችሏል፡፡
ስፓይን ስፖርት አማካሪ የስፖርት ህክምና ስልጠና ለሁሉም የክለብ የህክምና ባለሙያዎች ተደራሽ ማድረግና በስፖርታዊ ውድድርና ስልጠና ወቅት የሚከሰትን አደጋና ጉዳት አስፈላጊውን የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታና ህክምና የሚሰጡ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን ለማፍራት ቀጣይነት ባለው መልኩ ሌሎች ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅ የድርጅቱ የትምህርትና ስልጠና ሀላፊ አቶ ማቲያስ አስራት ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በቦጋለ አበበ