የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የጥምር ድል ባለቤቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቶኪዮ ማራቶን እንደሚወዳደር ቢጠበቅም ከሳምንት በፊት ለውድድሩ ብቁ ባለመሆኑ እንደማይሳተፍ አረጋግጧል፡፡ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው ውድድር ቀነኒሳ ራሱን ቢያገልም በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ለአሸናፊነት ታጭተዋል፡፡
በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች ሁሉ ፈጣን ሰዓት በመያዝ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቀነኒሳ 2016 በርሊን ማራቶን ላይ 2፡03፡03 የሆነ የዓለም ሁለተኛ ፈጣንና የኢትዮጵያ ክብረወሰን ሰዓት አስመዝግቦ ካሸነፈ ወዲህ ወጥ የሆነ አቀም ማሳየት አልቻለም፡፡ ይህም በተደጋጋሚ በታላላቅ ውድድሮች አቋርጦ እንዲወጣ አስገድዶታል፡፡ በ2017 የዱባይ ማራቶን ለአሸናፊነት ሲጠበቅ የነበረው ቀነኒሳ ውድድሩን አቀርጦ የወጣ ሲሆን ከሦስት ወራት በኋላ በፍጥነት አገግሞ በለንደን ማራቶን 2፡05፡57በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ ድሉን ያጣጥማል ተብሎ ሲጠበቅም ውድድሩን መፈፀም አልቻለም፡፡ የ2018 የውድድር ዓመትም ቢሆን ለቀነኒሳ ጥሩ የሚባል አልነበረም፡፡ ወደ ለንደን ማራቶን ተመልሶ 2፡፡08፡፡53 በሆነ ሰዓት ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ከአራት ወራት በፊትም በአምስተርዳም ማራቶን ውድድሩን ማጠናቀቅ እንዳልቻለ ይታወሳል፡፡
ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዞ ከቀነኒሳ ጋር የሚፎካከረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ለገሰ ሲሆን 2፡04፡15 የሆነ የራሱን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበው ባለፈው 2018 የዱባይ ማራቶን በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት ወቅት ነው፡፡ በቶኪዮ ማራቶን ሲወዳደርም በርቀቱ ሦስተኛ ተሳትፎው ይሆናል፡፡ የ2014 እና 2018 የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊ አትሌት ዲክሰን ቹምባ ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን በውድድሩ ተካቷል፡፡ ይህ ኬንያዊ አትሌት 2፡04፡32 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ሲሆን በቶኪዮ ማራቶን ሁለት ጊዜም ሲያሸንፍ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን ማጠናቀቅ የቻለው ከ2፡05 በታች ነው፡፡ በዘንድሮ ውድድርም ከቀነኒሳና ብርሃኑ ቀጥሎ የሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ነው፡፡ ቹምባ በ2015፣2016 እና 2017 የቶኪዮ ማራቶን ውድድሮች ሦስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅም ሌላ ታሪክ አለው፡፡ እነዚህ ሁለት አትሌቶች ለውድድሩ አሸናፊነት ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ቢሆንም ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያን ና ጃፓናውያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር የተሻለ ፈጣን ሰዓት እንዲመዘገብ ሁለት አሯሯጮች የተዘጋጁ ሲሆን የመጀመሪያው እስከ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ከ2 ነጥብ 57 እስከ 2 ነጥብ 58 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት እንዲያሯሩጥ ታስባል፡፡ ይህም ውድድሩን ከ2፡04፡30 እስከ 2፡05፡10 ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነው፡፡ ሁለተኛው እቅድ ደግሞ ሦስት ኪሎ ሜትሮችን የሚያራሩጥ ሲሆን ውድድሩን እስከ 2፡06፡35 ባለው ሰዓት ውስጥ ለማጠናቀቅ ያለመ ነው፡፡
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር በቅርብ ጊዜ በርቀቱ ትልቅ ስም ማኖር የቻለችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ሩቲ አጋ በአሁኑ ወቅት ፈጣን ከሚባሉት የማራቶን አትሌቶች ግንባር ቀደም እንደመሆና የአሸናፊነት ሚዛኑን ደፍታለች፡፡ ባለፉት ሦስት የበርሊን ማራቶን ውድድሮች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዛ መፈፀም የቻለችው ሩቲ አጋ በተለይም ባለፈው የበርሊን ማራቶን 2፤18፤34 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቧ በርቀቱ ታሪክ ስድስተኛዋ ፈጣን አትሌት እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይህም ዘንድሮ በቶኪዮ ማራቶን ለአሸናፊነት እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡ ከሩቲ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት አትሌቶች ማራቶንን ከ2፡20 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ተካተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ፈይሴ ታደሰና የብርጓል መለሰ እንዲሁም ኬንያዊታ የቀድሞ የዓለም ግማሽ ማራቶን ባለ ክብረወሰን ፍሎረንስ ኪፕላጋት አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን ከ2፤20 በታች በማጠናቀቅ የተካኑ አትሌቶች በመሆናቸው ዘንድሮ ቶኪዮ በጠንካራ ፉክክር ትደምቃለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 2፡22፡51 በመያዝ በውድድሩ ዘጠነኛ ፈጣን ሠዓት ባለቤት የሆነችው የዓለም ቻምፒዮኗ ሮዝ ቺሊሞ በውድድሩ መካተቷም ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖር ማሳያ ነው፡፡
በዓለማችን በየዓመቱ ከሚካሄዱ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነውና የወርቅ ደረጃ ያለው የቶኪዮ ማራቶን (world marathon majors) ከሚባሉት አምስት ታላላቅ ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ በአምስቱ ታላላቅ ውድድሮች በሰበሰቡት ነጥብ መሰረት ወንድና ሴት አትሌቶች በጋራ አንድ ሚሊየን ዶላር የሚሸለሙበት የውድድር አካል እንደመሆኑ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ቶኪዮ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2020 ላይ ኦሊምፒክን የምታስተናግድ ከተማ እንደመሆኗ የዓለማችን ድንቅ ድንቅ አትሌቶች ትኩረታቸውን ወደ ሩቅ ምስራቅ አገር አድርገዋል፡፡ የውድድሩ ዳይሬክተር ታድ ሃያኖ ኦሊምፒክ እየተቃረበ መሆኑን በመግለፅ በርካታ ኮከብ አትሌቶች በቶኪዮ ማራቶን ልምድ ለመቅሰም ወደ ውድድሩ እንደሚመጡ ለአይ ኤ.ኤ.ኤፍ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በቦጋለ አበበ