በአብዛኛው መፀው የእረኛ ወራት በመባል ይታወቃል፤ ከላይ እንደገለጽነው ለእረኛ የጥጋብ የደስታ የእርካታ የጨዋታ ወቅት ነው። የበቆሎ ፣ የባቄላ፣የአተር፣ የስንዴ፣ የማሽላ እሸት እንደልቡ ይበላል፤ የማሽላና የስንዴ እሸት እየጠበሰ (በኦሮምኛ ወጠላ ይባላል) የሚበላበት ነው። የቤቱ ምግብ ብዙም አይታሰበው፤ በክረምት ቆፈን ተቆራምዶ ተጨማዶ የከረመ ገላው ፈታ ፈካ የሚለው በዚሁ ወቅት ነው። እረኛ ሁሉ ሆዱ ሞልቶ፣ ደረቱ ቀልቶ የሚታይበት ወቅት፤ መፀው።
ወደ ኅዳርም ሲገባ ወሩ የራሱ መለያ አለው። «በኅዳር አትበል ዳርዳር» የሚለው አገርኛ ብሂል አትግደርደር የሚል አንድምታ አለው።ጊዜው የበረከትና የጥጋብ ስለሆነ እንደ ልብህ ብላ ለማለት ፈልገው ነው።
በመፀው አብዛኛው አርሶ አደር የእህል አጨዳ፣ የባቄላ ሰበራ፣ የአተራ ነቀላ ያከናውናል። እረኞች ከወፍ ቀድመው ማልደው በመነሳት የደረሰ ሰብላቸውን በወንጭፍ ከአዕዋፍ ይከላከላሉ። ሰብሉ ታጭዶ ቃርሚያውም ከተነሳ በሁዋላ ከብቶቻቸውን በማሳው ላይ እንደልባቸው አሰማርተው ይጫወታሉ። በእዚህ ወቅት ከብቶች ወደ ክምር እንዳይደርሱ መጠበቅ ብቻ ይበቃል፤ በተረፈ ሰብል ያጠፋሉ የሚል ስጋት ስሌለ በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ።
እረኝነትን የሚያውቁ እንደሚናገሩት፣ የእሸት ወቅት ሲያልፍ የእንኩቶው ይከተላል። እንኩቶው የሚዘጋጀው አዝመራው ደርሶ ከታጨደ የደረቀ ሰብል ነዶ ነው።/ ነዶ የደረቀ የስንዴ ወይም የገብስ ሰብል ሰብሰብ እየተደረገ እየታሰረ የሚያዝበት መንገድ ነው።/ እንኩቶ እየታሸ የሚበላ ሲሆን፣ ቆሎ እንደ ማለት ነው። የደረሰ ሰብል ተጠብሶ ሲበላ ምን ያህል ልዩ ጣዕም ያለው ስለመሆኑ የበቆሎ እሸትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
በዚህ ወቅት ነዶ ሰርቆ እንኩቶ መብላት የተለመደ ነው። በተለይ እረኞች በእዚህ ይታወቃሉ። ገለባ በእሳት እያቀጣጠሉ የስንዴ ነዶውን ይጨምሩትና እያገላበጡ እንዲበስል ያደርጉታል። በሚፈለገው ልክ ሲበስል በሁለት እጃቸው እያሹ ይበሉታል። ባቄላና አተር የሚያነኩቱም አሉ።
ለእረኛው የጥቅምትና የኅዳር ወራት ረሀብ ማስታገሻ፣ ብርድ መከላከያ እና መጫወቻው እሸት ፣የእሸት ጥብስና እንኩቶ ናቸው። በመፀው እንኩቶና ጥብስ በሁሉም አካባቢ የሚዘወተሩ ቢሆንም፣ እንኩቶ በይበልጥ በደጋማ አካባቢ፣ ጥብስ ደግሞ በቆላማ አካባቢዎች ይዘወተራሉ። በተለይ ለእረኛው የኅዳርና የጥቅምት ወራት ብርድ መከላከያዎቹ እሸት እንኩቶና ጥብስ ናቸው።
በዚህ ወቅት የሚደርሰው የማሽላ እሸት ከማርና ወተት ያስንቃል የሚሉ አሉ። በወርሐ ኅዳር እረኛ ከአዕዋፍ አፍ ጠብቆ ለፍሬ ከደረሰው የማሽላ እሸት መቅመስ ሲጀምር ወዘናው ሁሉ ይለወጣል፤ ፊቱ ያበራል፤ ድምጹ ያምራል ፤ ደረቱ ይሰፋል ፤ሆዱ ይሞላል ይባላል።
በእዚህ ወቅት የጉብሎችና ኮረዶች ጠረንም መልካም መዓዛ ይላበሳል ይባላል። ይህም የማሽላ እሸት ውጤት ነው። ጉብሉ ለከጀላት ኮረዳ መውደዱን ለመግለጽ የጥንቅሽ አገዳና ምርጥ የማሽላ እሸት በገጸ በረከትነት መስጠት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተለመደ ነው። ይህም በመጸው የሚደርሰው የማሽላ እሸትና ጥንቅሽ ከመብል አልፎ ለወጣቶች እንደ ፍቅር መግለጫ እንደሚያገለግል ያሳየናል። የማሽላ እሸት ሰውነት ገንቢ ውበት አሳማሪ ስለመሆኑ ጋዜጠኛና ደራሲ ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት አንድ መጽሐፍ ጠቅሰዋል።
በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የኦሮሞ ተወላጆች «ሸጎዬ» የሚባለውን ተወዳጅ ውዝዋዜና ዘፈን እያቀነቀኑና እየተወዛወዙ የማሽላ እሸት ያለከልካይ ውለው ያድሩበታል። በዚሁ በመፀው ወቅት እረኞች በትግራይና በጎንደር ቆላ አካባቢዎች ከብቶቻቸውን ይዘው ውጭ የሚያድሩበት ወቅት ነው።ቀን ቀን በየአውድማው ዙሪያ በተከመረው ገለባ ትግል እየገጠሙ ጡንቻቸውን ይፈትናሉ ።
አንዳንዴ አጨዳው በደቦ ወይም በወንፈል ይደረጋል። ይሄኔ ለደቦተኞቹ የሚሆን ምሳ ከቤት እንዲመጣ ይደረጋል። ገበሬው በደቦ አጨዳው ረሀብ ረሀብ ሲለው ከመጣለት ምግብ እየተመገበ ከመጠጡ እየተጎነጨ ደከም ሲለው ዳቦውን እየገመጠ በዚያ ላይ እየተጫወተ እየዘፈነ ያጭዳል።ከዘፈኖቹ መካከል አንዱም፡-
ይበላሃል ጅቦ
ይበላሃል ጅቦ
የማይበላ መስሎሃል
ይጎረድምሃል
የእነገሌን እርሻ
እናድርገው ቅምሻ
እረኞች እህል ሲወቃ ደግሞ ቀን በማበራየቱ ላይ ከመዋላቸው ባሻገር የተወቃው እህል ከገለባው ያልተለየ ከሆነ ውድማ ማደር ይኖራል። ውድማ ማደር በጉጉት ይጠበቃል። ጨዋታው ልዩ ነው። በጋቢና መሰል ልብስ ተሸፋፍኖ ገለባ ውስጥ ሰርስሮ በመግባት ውስጡ ይታደራል። ገለባው በጣም ይሞቃል።
በገጠር በክረምት ወቅት የተሰበሰበ አረም ተከምሮና ደርቆ በየማሳው ዳር ስለሚገኝ የማለዳ ብርድና ውርጭ የማይለየው ጥቅምትና ኅዳር ወራት ከሰውም አልፎ የደረሰውን እህል የሚጎዳበት ጊዜ ያጋጥማል። ገበሬው ከብርዱ ራሱን ለመከላከል አካባቢውን ለማሞቅ ማለዳ ተነስቶ በማሳው ዙሪያ የተከመረውን ደረቅ አረም ያቀጣጥላል ። ሂደቱ እስከ ኅዳር መጨረሻ ይቀጥላል።
በታኅሳስ ወር ሁለት ሳምንት በአንዳንድ አካባቢዎች የእሸት በዓል በሚል ይከበራል ።ገብስ ወይም ስንዴ ታጭዶ ከመከመሩ በፊት አፍርቶ በቁሙ ዘመም ሲል በዓሉ ይከበራል። በወፍራሙ የተጠመቀ ጠላ ጉሽ በትልቅ እንስራ ተሞልቶ ይቀርባል፣ ትኩስ ዳቦ / በኦሮምኛ ገረገልቻ/ ይባላል። በቅቤ በተለወሰ ድልህ ተቀብቶ ፣ እርጎም በጮጮ ተደርጎ ይቀርባል ። ገበሬዎች በዛፍ ጥላ ሥር ተሰብስበው ድግሱን ይቋደሳሉ። በዝግጅቱ መጨረሻ የአገር ሽማግሌዎች እህሉ እንዲበረክት ከብቱ እንዲሰባና እንዲራባ ሰው ጤናማ እንዲሆን ይመርቃሉ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014