በጎነት የሚታይ ፍሬ ነው። የሕይወትን ጎተራ የሚሞላ ለግለሰብና ለሀገር የሚተርፍ ተግባር፤ በጎነት ከማሰብ በዘለለ፤ አብዝቶ ከመልካም ሥራዎች ጎን መሰልፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማተኮርን ከሰው ምላሸ ሰይጠብቁ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን የሚጠይቅ የንፁህ ልብ ክዋኔ ነው።
በጎነት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸው ድልድይ፣ የትስስራቸው ገመድ ሆኖ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው ትልቅ እሴት ነው። በጎነት የአእምሮ እርካታ የምናገኝበት፣ ደስታን የምንፈጥርበት፣ ሃገር የምትለማበት በሰውነታችን የታደልነው ስጦታ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የሕሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው። ይህ እንቅስቃሴ ማኅበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው ፋይዳ ነው።
በኢትዮጵያ በጎነትን ኖረው ሰብዓዊነትን ተላብሰው ለሕዝባቸው የተቆረሱ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፤ ዘመናቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያውያን በጎ በማድረግ ያሳለፉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ከእነዚህ እንቁ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው።
አቶ ሽመልስ አዱኛ ከአባታቸው ከመቶ አለቃ አዱኛ ካሳ እና ከእናታቸው ከ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ኃይለሥላሴ ጥቅምት 2 ቀን 1928 ዓ.ም በጅጅጋ ከተማ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ላይ ሰፍሯል። ሐረር መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለው በኋላ ደግሞ ወደ ዊንጌት ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትለዋል።
የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሥነ ትምህርት ቢ ኤ ዲግሪያቸውን በ 1952 ዓ.ም አግኝተዋል። ከዚያም በሕንድ እና በእንግሊዝ ሀገራትን ተጨማሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በ1960ዎቹም ሆነ በ1970ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ደርሶ የነበረውንና የብዙዎች ሕይወትን የቀጠፈው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ ብዙኃኑን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከሞተ ሕይወት ለመታደግ ተቋቁሞ የነበረውን የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽንን ባጭሩ ዕማማኮን በዋና ኮሚሽነርነት የመሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ እርዳታ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በማሰባሰብ በረሃብ ያልቅ የነበረውን ወገናቸውን ለመታደግ ብርቱ ሥራ ስለማከናወናቸው ይነገራል።
ለ1966ቱ አብዮት መፈንዳት አንዱ መንሥኤ የነበረው በ1965 ዓ.ም. በወሎ ጠቅላይ ግዛት የደረሰው ድርቅና ረሃብ ለመግታት፣ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ ብሔራዊ የዕርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሲያቋቁም በመሪነት የተሰየሙት የአገር ግዛት ምክትል ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ ነበሩ። ድኅረ አብዮት ኮሚቴው ወደ ኮሚሽንነት ሲያድግ መሪነቱን ይዘው ቀጥለውበታል።
በኮሚሽነርነታቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች በየአገሮቹ እየዞሩ ዓለም ድጋፉን እንዲሰጥ በዕንባ ጭምር በመታጀብ የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸው ተቀባይነትም አግኝተው ለወገኖቻቸው ዕርዳታ እንዲደርስ ማድረጋቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል።
የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽንን ለ10 ዓመት ያህል እስከ 1975 ዓ.ም. የመሩትና በ1976 ለሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ያስረከቡት አቶ ሽመልስ ዳግም በወሎ፣ በትግራይ፣ በኦጋዴንና አፋር የተከሰተው ድርቅ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ መጋለጡንና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን በ1975 ዓ.ም. ይፋ አድርገው ነበር።
የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነርነታቸውን ካስረከቡ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል የሕፃናት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሠርተዋል። በዚህን ወቅት የሕፃናት አምባን በተደጋጋሚ በመጎብኘት ለሕጻናቱ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሟላ ጥረት ያደረጉ እንደነበር ይነገራል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በተመሠረተበት ዋዜማ በ1979 ዓ.ም. በዘውዳዊው ሥርዓት በመምሪያ ኃላፊነት በሠሩበት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር (በደርግ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባለው) ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።
‹‹በመልካም አስተዳደር ምስጉን ሰው›› እንደነበሩ፣ ‹‹ቢሯቸውን በዕለተ ረቡዕ ለሁሉም ክፍት አድርገው ችግር አለብኝ ለሚሉ የሚቀበሉ የሕዝብ አገልጋይ›› ነበሩ ብለው ምስክር የሰጡላቸው እንዳሉ በገጸ ታሪካቸው ተጠቅሷል።
ኢሕአዴግ በግንቦት 1983 ዓ.ም. መንበሩን ስልጣን ከመያዙ በፊት፣ ኢሕዲሪ ባደረገው ሹም ሽር ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረጉት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከሾሟቸው የካቢኔ አባላት መካከል አቶ ሽመልስ አዱኛን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረጋቸው ይታወሳል።
አቶ ሽመልስ ከመንግሥታዊ ከፍተኛ ኃላፊነት ጡረታ ከወጡ በኋላ ድሮም በነበሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት በልማትና በሰላም፣ በሰብዓዊነት መስኮች የላቀ አገልግሎት መስጠታቸው ይነገርላቸዋል።
በ1950ዎቹ መሥራች የነበሩት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመግታት የተቋቋመው ‹‹ኦሳ›› የተባለ አገር በቀል ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስጠበቅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር መሥራች ፕሬዚዳንት ነበሩ።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ አማካሪ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ያገለገሉ ባለውለታ ናቸው። በ2002 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫም በግል ተወዳዳሪ ነበሩ።
በ1950ዎቹ መጨረሻና 60ዎቹ መጀመሪያ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት በኃላፊነት የሠሩት አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊነትን ሲያስተጋቡ ኖረዋል። እሳቸውም በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም አሳይተውታል። ‹‹የገባነውን ቃልና መግለጫ በተግባር ካላሳየን፣ ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን የራሳችን ቃላት በእኛ ላይ ይፈርዱብናል፤›› ማለታቸውም ተመዝግቧል።
ከአቶ ሽመልስ አዱኛ ጋር በ1982 አብረው የሠሩት አቶ ተስፋዬ ድረሴ የተባሉ ሰው በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ አቶ ሽመልስ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በሳምንት አንድ ቀን ጽሕፈት ቤታቸውን ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት አድርገው በቅንነት ያገለግሉ የነበሩ ሰው እንደነበሩ መስክረዋል።
ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት “ቢሮ ውስጥ ረቡዕ ረቡዕ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባለ ጉዳይ ያነጋግረኝ ብለው ቢሯቸውን ከፍተው ይጠብቃሉ። በጣም ችግር ላይ ያሉ ሰዎች ረቡዕ ረቡዕ ይሰበሰቡ ነበር። ብዙ ዓመት ማመልከቻ አስገብተው ሳይሳካላቸው የቀሩ ግን ተስፋ ያልቆረጡ ሰዎች በየተራ ወደ ሚኒስትሩ ቢሮ እየገቡ ቆመው አነጋግረዋቸው ይመልሷቸው ነበር።
ብዙዎቹ እሳቸውን በማነጋገራቸው ብቻ ጉዳያቸውን የጨረሱ ያህል ተደስተው ነበር የሚመለሱት። ይህን ምሳሌነት የወሰድኩት ከእሳቸው ነው” በማለት አቶ ሽመልስ የነበራቸውን የአገልጋይነት በጎ ልማድ አስታውሰዋል።
ከ1977 እስከ 1979 በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ከ1979 እስከ 1983 የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፤ ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይም ስለመሳተፋቸው እና ልዩ ልዩ እውቅናዎችን ስለማግኘታቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
ስለ ደጉ የሕዝብ አገልጋይ ስለ አቶ ሽመልስ አብረዋቸው የሰሩና የሥራ ትጋት በቅርብ የሚያውቋቸው የሚናገሩት ሀቅ ነው። በድርቅ የተጎዱ ሚሊዮኖችን አብልተውና አጠጥተው ከሞት የታደጉት አቶ ሽመለስ አዱኛ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኃላፊ ሆነው ሲሰሩም በመልካም አስተዳደር ምስጉን ሰው ነበሩ።
አቶ ሽመልስ አዱኛ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በመሆን፣ የኢትዮጵያ የቤተሰብ መምሪያ መሥራች እና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን እንዲሁም በሌሎችም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ስለማገልገላቸው ልጃቸው አቶ ብሩክ ሽመልስ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አቶ ሽመልስ አዱኛ በኢትዮጲያ ቅርስ ባለአደራ ማሕበር ከ1989ዓ.ም ጀምሮ በአባልነት እና ለተከታታይ ዓመታት በሥራ አመራር ቦርድ ፕሬዚደንት በመሆን አገልግለው የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማሕበር በነበራቸው የአባልነት እና የኃላፊነት ቆይታ የማሕበሩን ዓላማ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ለአብነት ያህል ለማሕበሩ ከፍተኛ አባላትና ደጋፊዎች በማፍራት፣ በእንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ የመጀመሪያውን ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ለታለመለት ዓላማ ምቹ እንዲሆን የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲኖረው አድርገዋል።
የማሕበሩን ልዩ ልዩ ተግባራት ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር አዲስ የመስክ መኪና ማስገኘት ችለዋል። በተጨማሪም በሃገር ደረጃ የተለያዩ ታላላቅ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ታላቅ ሰው ነበሩ።
አቶ ሽመልስ በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት የላቀ አገልግሎት ከተበረከቱላቸው ሽልማቶችና ዕውቅናዎች መካከል ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር የሔንሪ ዱናንት የላቀ የሰብዓዊ አገልግሎት ሜዳሊያና የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ይገኙበታል።
ታህሣስ 15 2017 ዓ.ም በተወለዱ በ 89 ዓመታቸው ያረፉት አቶ ሽመልስ፤ ስርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ፀባዖት ቅድስተ ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል። በሀገር ባለውለታነታቸው በበጎ የሚጠቀሱት አቶ ሽመልስ አዱኛ የአራት ወንድ እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበሩ።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ በበጎ አድራጎት ሥራቸው የሚታወቁትን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ባለውለታ አቶ ሽመልስ አዱኛን ለነበራቸው ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም]