ተቋማት በሠራተኛው የበጋ ውድድሮች ተፎካካሪ ለመሆን ተዘጋጅተዋል

የ2017 የሠራተኞች የበጋ ወራት ስፖርታዊ ውድድሮች ከመጪው እሁድ ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚከናወኑ የተለያዩ መርሐ-ግብሮች ይጀመራሉ። ለረጅም ወራት በሚካሄደው የበጋ ወራት ውድድሮች ለመሳተፍ ሠላሳ አምስት የሠራተኛ ስፖርት ማኅበራት መመዝገባቸው ታውቋል። የተለያዩ የሠራተኛ ስፖርት ማኅበራትም በበርካታ ስፖርቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁም ገልጸዋል።

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቦል፣ ዳማ፣ ቼስ፣ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታና ሌሎችም የስፖርት አይነቶች ሠራተኛው ለረጅም ወራት ፉክክር የሚያደርግባቸው ስፖርቶች ሲሆኑ፣ ‹‹ስፖርት ለሠላም፣ ለጤናና ለምርታማነት›› በሚል መሪ ቃል የዘንድሮው ውድድር እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍስሐጽዮን ቢያድግልኝ እንደተናገሩት፣ በሠራተኛው ውድድሮች የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር ከኢሠማኮ ቅርናጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ጀምሮ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

እንደ አቶ ፍስሐጽዮን ገለፃ፣ በሠራተኛው ውድድሮች አሠሪዎች ስፖርት ወዳድ ሲሆኑ ለተሳትፎ ጥሩ መነሳሳት ይታያል፣ አሠሪዎች ለስፖርት ጥሩ ግንዛቤ ከሌላቸው ደግሞ በተቃራኒው የሠራተኛው ተሳትፎም ይቀንሳል። የሠራተኛው ስፖርት ላይ የሚስተዋለው አንዱ ችግርም ይሄ ነው። ያም ሆኖ በዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድሮች የተለያዩ አዳዲስ ተቋማት ተሳታፊ ለመሆን መጥተዋል። ይህም ወደ ስፖርቱ ያልመጡት ላይ ጥሩ መነሳሳት ስለሚፈጥር መቀጠል አለበት። የሠራተኛው በስፖርቱ መሳተፍ ጥቅሙ በዋናነት ለአሠሪው ነውና ሊደግፉትም ይገባል።

በሠራተኛው የስፖርት መድረኮች ለረጅም ዓመታት በመሳተፍና በተለያዩ ስፖርቶች አሸናፊ በመሆን ከሚታወቁ ተቋማት አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም ነው። የኢትዮ ቴሌኮም የሠራተኞች የእግር ካስ ቡድን አሠልጣኝ አሥራት ሰይፉ እንደሚናገሩት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሠራተኛው ውድድሮች ከሃያ ዓመታት በላይ የተሳትፎ ታሪክ አለው። በዚህም ሠራተኛው የውስጥ ውድድሮችን ከማድረግ ጀምሮ በስፖርት ጤናውን እንዲጠብቅ ትልቅ ሚና አለው። በዘንድሮው ውድድር ውጤታማ ለመሆንም በተለያዩ ስፖርቶች የውስጥ ውድድሮችን በማድረግ ተሳታፊዎች ተመርጠው ዝግጅት አድርገዋል። ‹‹ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነት የምናደርግበትና በጉጉት የምንጠብቀው ነው፣ ሥራ እንዲሳለጥም ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው መድረክ ነው፣ ሌሎችም ሊጠቀሙበት ይገባል›› በማለትም አሠልጣኝ አሥራት ስለ ሠራተኛው የስፖርት መድረክ አስተያየት ሰጥተዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የቮሊቦል አሠልጣኝ ሲሳይ ታደሰ በበኩላቸው፣ የሠራተኛውን አንድነት ለመጠበቅና ቤተሰባዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ስፖርታዊ መድረኩ ትልቅ ጥቅም ስላለው ሠራተኛው በደስታ ተዘጋጅቶ እንደሚመጣ ይናገራሉ። እንደ አሠልጣኛ ገለፃ፣ በአንዳንድ ስፖርቶች የሚሳተፉ ተቋማት ብዛት አጭር በመሆናቸው ውድድሮች ውስን ናቸው። ስለዚህም ሌሎች ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ወደ ስፖርቱ ማምጣትና መደገፍ ይገባቸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሠራተኛው የስፖርት መድረኮች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ይጠቀሳል። የተቋሙ የእግር ኳስ ቡድን መሪ ከበደ ደበሌ እንደሚናገሩት፣ በሠራተኛው ስፖርት መሳተፍ ከጀመሩ ከአራት ዓመታት በላይ ይሆናል። ጤና ከመጠበቅ፣ ማኅበራዊ ግንኙነትና ወዳጅነትን ከማጠናከር አንፃር የሠራተኛው የስፖርት መድረኮች ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው በአጭር ዓመታት ተሳትፏቸው ማረጋገጣቸውን ቡድን መሪው ያስረዳሉ። ዘንድሮም በበጋ ወራት ውድድሮች የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየዓመቱ ሦስት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ያከናውናል። ለረጅም ጊዜ የሚካሄደውና በርካታ ሠራተኞችን የሚያሳትፈው የበጋ ወራት ውድድር አንዱና ዋነኛው ሲሆን፣ ዓለም አቀፉን የሠራተኛ ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ የሚካሄደው ውድድር ሁለተኛው ነው። ሌላው በክረምት ወራት በተለይም በወንጂ ስታድየም የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና ሠራተኛውም በጉጉት የሚጠብቀው መድረክ ነው።

እነዚህ ውድድሮች ሠራተኞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለማፍራት፣ የሠራተኞችን አንድነት ለማጠናከር፣ የልማት ተቋሞቻቸውን ማስተዋወቅና የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጠናከር ዓላማ በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው።

በኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ የስፖርት መድረኮች አንዱ የሆነው ይህ የሠራተኞች ውድድር በዚህ ዘመን ሠራተኛው በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ለሚሠራበት ድርጅት ውጤታማነት የሚኖረውን አስተዋፅዖ የጎላ እንደሆነ አሠሪዎች እንደሚረዱት ይታመናል። በመሆኑም ስፖርቱ የሠራተኛውን አንድነትና ለጋራ ጉዳይ አብሮ የመቆም ባሕሉን ያጠናክርበታል። በሀገሪቱ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ጤናማ፣ ንቁና አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ውድድሮችን ማሰናዳት ውጤታማ ሠራተኛ ማፍራት እንደሚያስችል ይታመናል።

በአሠሪና ሠራተኛው መካከልም ጥሩ ግንኙነት እንዲዳብር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለኢንዱስትሪ ሠላም መስፈን የላቀ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ይጠበቃል። የሠራተኛ ማኅበር ዓመታዊ ውድድሮችን ማዘጋጀት ሠራተኛውን እርስ በርስ ከማቀራረብ አንፃር የጎላ ሚና እንዳለውም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተካሄዱ ውድድሮች ለመታዘብ ተችሏል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You