‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› የሚለው የሰርግ ዘፈን ጫና አሳድሮባቸው ይሁን ባይታወቅም ገበያ ላይ የሚገኙ አብዛኛው የሙሽራና የሚዜ አልባሳት ቀጭኗን፣ ወገበ ስምንት ቁጥሯን ያማከሉ ናቸው። በዚህም በርካታ ሙሽሮችና ሚዜዎች ያማራቸውን ሳይሆን ገበያ ላይ በልካቸው ያገኙትን ለመልበስ ሊገደዱ ይችላሉ። በዚህም ብዙ ጊዜ ያሰቡት የሰርጋቸው ቀሚስና የለበሱት አልገናኝ ብሎአቸው በርካቶች የሰርጌን ፎቶ ማየት አልፈልግም እስከማለት ሲደርሱ ታዝበናል። ይህን ችግር ለማቃለል ይመስላል በሀገራችን በኪራይና የተወሰኑ ሙሽሮች ደግሞ በግዢ ተገድቦ የነበረው የሙሽራ ልብስ ገበያ በትእዛዝና በምርጫቸው ማሰራት ጀምረዋል።
ሙሽሮች ቬሎአቸውን በምርጫቸው ከሚያሰ ሩበት ቤቶች አንዱ ቴድራ ዲዛይን ይሰኛል። የቤቱ ባለቤት ቴድራ የኋላሸት ትባላለች። እናቷ የቤት ውስጥ መገልገያ የሚሆኑ አልባሳትን ስትሰራ እያየች አድጋለች። ሆኖም መሞከርና እጇን ከሲንጀር ጋር ማስተዋወቅ ቢያምራትም ዋና ትኩረቷ ትምህርት ብቻ እንዲሆን በቤተሰቡ በመፈለጉ እድሉን አላገኘችም። በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተመርቃለች። ወዲያው ወደሥራ አለም ሳይሆን የልቧን መሻት ወደ መማር አተኮረች። ከምርቃት ማግስት የፋሽን ዲዛይን ተማሪ ሆነች። ቤተሰቦቿ የእነሱን መሻት ፈጽማለችና ተቃውሞ አልነበራቸውም፤ የልቧን ምርጫ እንድትከተል ፈቀዱላት።
ከምርቃት በኋላ የሀበሻ አልባሳትን መስራት ጀምራ ነበር። ‹‹ሳየው ገበያው ላይ ብዙ ጉድለት ያለው ዘመናዊ አልባሳት ነውና ወደ ዘመናዊ ገባሁ›› ትላለች።
የሰርግ አልባሳት መስራት ከመጀመሯ በፊት ብዙ ጊዜ ሚዜ ሆናለች። ያኔ ታዲያ ልብስ በልኳ ማግኘት ፈተና ነበር። ልብስ የሚመርጡት ቀጭኖቹ እንጂ ትንሽ ወፈር ያለ ሰው ገበያ ላይ ያገኘውን እንጂ እንደልቡ አማርጦ መልበስ ያስቸግራል ትላለች። ልብሱ ልክ አልሆን ሲል ከኋላ ማስፊያ ጨርቅ ገብቶ ተነካክቶ ይለበሳል። ስለዚህ መሰሎቿም ሆኑ ቀጭኖቹ አማርጠው ይለብሱ ዘንድ የሚዜ ልብስ መስራት ጀመረች። ገበያው ላይ የሙሽራ ቬሎም ክፍተት አለና የሙሽራ ቬሎም መስራት ጀመረች።
በአብዛኛው ደንበኞቿ መነሻ(ኢንስፓይሬሽን) የሚሆን ልብስ መርጠው ይዘው ይመጣሉ። በጋራ ከደንበኛዋ ጋር ተቀምጠው እየተወያዩ ከደንበኛዋ ሰውነት ጋር ይሆናል ወይስ አይሆንም የሚለውን ተመካክረው ይወስናሉ። በዚህ ሂደት ይሰራልን የሚሉት ልብስ ከእነርሱ ሰውነት ጋር የማይሄድበት ሁኔታ ያጋጥማል። ዲዛይነሯ ወፈር ያለች ሴት የልብሱ ሁኔታ ለቀጭን ሴት የሚሆን ልብስ መርጣ ይሰራልኝ የምትልበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ታነሳለች። ያኔ ከሰውነት ቅርጻቸው ጋር የመርጡት ልብስ እንደማይሆን ይነገራቸዋል። በአብዛኛው ምክር ይሰማሉ፤ የተወሰኑት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ በመግለጽ የመረጡት ዲዛይን እንዲሰራ የግድ ይላሉ። እንደሁኔታው የመረጡት ልብስ ከሰውነት ቅርጻቸው ጋር እንዲስማማ ተደርጎ ይሰራላቸዋል።
የሰርግ ቬሎ ለሴት ልጅ ትርጉሙ ብዙ ነው። አብዛኛው ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰርጋቸው ቀን የሚለብሱትን ቬሎ እየመረጡና በህሊናቸው እየሳሉ ያንን ቬሎ ለመልበስ ዓመታትን በጉጉት ጠብቀዋል። ለዛም ይመስላል የሚፈልገውን ወስኖ የሚመጣ ሙሽራ አለ የምትለው ዲዛይነሯ፤ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያስበው የሰርግ ቀሚስ ስለሚኖር አንዳንድ ሰዎች ያሰቡት እንዲሰራላቸው ብቻ የሚጠይቁ አሉ ትላለች። ያሰቡትን ቬሎ መልበስ መቻላቸው ደስታን እንደሚሰጣቸው ትገልጻለች።
የሙሽራ ልብስ፣ የሚዜ ልብስ፣ የፕሮቶኮል ልብስ፣ የልደት ልብሶች፣ ለፎቶ ፕሮግራም የሚሆኑ ልብሶች፣ የራት ልብስ፣ አጠቃላይ የፕሮግራም ልብስ በእያንዳንዱ ደንበኛ ምርጫ ይሰራል። የሙሽራ ቬሎ ትእዛዝ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚደርስ የምትናገረው ዲዛይነሯ፤ የራት ልብስ ከአስር ቀን እስከ ሁለት ሳምንት ባለው እናደርሳለን ትላለች። የሚዜ ልብስ ብዛት ስለሆነና ሌላ ትእዛዝም ሊኖር ስለሚችል ከሦስት ሳምንት እስከ አንድ ወር ይፈልጋል። ሥራውን እንደጀመረች ገበያ ላይ ለልብስ ሥራው የሚሆን ግብአት እጥረት ነበር የምተለው ዲዛይነር ቴድራ፤ የልብሱን ዲዛይን ለማምጣት ጨርቅ በመደራረብና በመሰል ቴክኒኮች ትጠቀም እንደነበር ትገልጻለች። አሁን ግን ገበያው ላይ የሚፈለገው ግብአት የሚገኝ መሆኑን ትጠቅሳለች።
በተሻለ ግብአት ገበያው ላይ ይገኛል ትላለች። ያኔ ስጀምር እንደዚህ አይነት ሥራ የምንሰራ ማንም የለም ነበር፤ አሁን መሰል ልብሶች የሚሰሩ ሰዎች ስለበረከትንም ገበያው ላይ ይገኛል ብላለች።
እንደ ዲዛይነሯ ማብራሪያ፤ ብዙ ጊዜ ሰርጎች ላይ ቬሎው የኪራይ ሲሆን ሙሽሮች እየተቀያሩ ቬሎው ተቀራራቢ ሲሆን ይታያል። ቬሎ የሚያሰሩት ተመሳሳይ መልበስ የማይፈልጉ ሙሽሮች ናቸው። ዋጋውም ከኪራዩ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ አንድ ቀን ተለብሶ ለሚመለስ ከመክፈል ቬሎአቸው የታሪካቸው አካል ሆኖ ከእነሱ ጋር መቅረቱን ይመርጣሉ። በተለይ በልካቸው የሚፈልጉትን ማግኘት የሚቸገሩ ሴቶች፤ የራሳቸውን ማሰራት ምርጫቸው እየሆነ ነው።
ሥራዋን በማህበራዊ ሚድያዎች ታስተዋውቃለች። በፊት በፌስቡክ ከዛ ዘመኑ የኢንስታግራም ሲሆን ወደዛ ጎራ አለች። አሁን ዋናው መገኛዋ ቲክቶክ ሆኗል። ያም ቢሆን በብዛት ገበያ የሚያመጣልን የሰው ምስክርነት ነው ትላለች። አንድ ሙሽራ የለበሰችውን ልብስ የወደደ ለራሱ ለማሰራት ይመጣል። ሥራው የሰርግ ወቅት ላይ ይበዛል። ከዛ ውጭ ለልደት፣ ለጋብቻ በዓል ቀን ማስታወሻ (አኒቨርሰሪ)፣ ለፎቶ ፕሮግራምና ለተለያዩ ፕሮግራሞች ሰዎች በትእዛዝ የመረጡትን ልብስ ያሰራሉ። ብዙ ሰዎች ለፕሮግራም የሚሆኑ ልብሶችን አሰራር እንድናስተምራቸው ይጠይቁናል የምትለው ዲዛይነሯ፤ ለዛ የሚሆን ዝግጅት እያደረገች መሆኑንና በቅርብ የዲዛይን ትምህርት ቤት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑን ትናገራለች።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም