ሰሜን ኮሪያ ትዳራቸውን የሚፈቱ ሰዎች እንዲቀጡ የሚደነግግ አዲስ ሕግ አፀደቀች

እስያዊቷ ሀገር ሰሜን ኮሪያ ትዳራቸውን በሚፈቱ ጥንዶች ላይ በሌላ የዓለም ክፍል የማይገኝ አዲስ ሕግ ማፅደቋ ተገልጿል፡፡ አዲሱ ሕግ ባለትዳሮቹ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ አካላዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች በደሎችን ቢያደርሱም ለመፍታት እስከወሰኑ ድረስ ቅጣቱ እንደሚተላለፍባቸው ይደነግጋል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን “ባለትዳሮች አጋርነታቸውን ለመበተን በመወሰን ለሠሩት ወንጀል ከፍተኛ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች እንዲላኩ ወስነዋል” ብሏል፡፡ የሰሜን ኮሪያው መሪ ፍቺ እንደ “ፀረ-ሶሻሊስት” ድርጊት ስለሚቆጠር ጥንዶቹ እስከ ስድስት ወር ድረስ በጉልበት ካምፖች ውስጥ እንዲቆዩ ወስነዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው ሕግ በመጀመሪያ ፍቺ የጠየቀው አካል ብቻ እንዲቀጣ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በአዲሱ ሕግ መሠረት የፍቺ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ሁለቱም ተጋቢዎች እንዲታሠሩ ደንግጓል፡፡ በባለፈው ዓመት መንግሥት በብዛት የትዳር ፍቺ ጥያቄ የሚያቀርቡት ሴቶች መሆናቸውን ተከትሎ የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘመቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል አድርጓል፡፡

በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በምታስተናግደው ሀገር የትዳር ፍቺ ምጣኔን ለመቀነስ የተለያዩ ጠንካራ ሕጎችን ተግባራዊ ብታደርግም እኤአ ከ2020 ወዲህ የፍቺ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ እንደሚገኝ የዘገበው አል ዐይን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You