የአሜሪካ ግምጃ ቤት በቻይና ኮምፒውተር ጠላፊዎች “ጥቃት ደርሶብኛል” ሲል ገለጸ

ለቻይና መንግሥት የሚሠራ አንድ የኮምፒውተር ሰርሳሪ የአሜሪካ ግምጃ ቤትን ጠልፎ የሠራተኞችን ኮምፒውተር እና ምስጢራዊ መረጃዎችን እንደተመለከተ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ። ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ገደማ መሆኑን ግምጃ ቤቱ ለሕግ አውጭዎች በላከው ደብዳቤ አስታውቋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “በቀላሉ የማናየው” ያለው ጠለፋ ያስከተለውን ጥፋት ለመመርመር ከኤፍቢአይ ጋር እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።

በዋሽንግተን የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ወቀሳው “በሐቅ ላይ ያልተመሠረተ” እና “ተራ ጥቃት” ነው። ግምጃ ቤቱ ፊርማው ያረፈበትን ደብዳቤ ለሕግ አውጭዎች የላከ ሲሆን በደብዳቤው መቀመጫውን ቻይና ያደረገ አካል ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች እርዳታ የሚያደርግ ሦስተኛ ወገን ድርጅትን ‘ሲስተም’ ጥሶ መግባት ችሏል ሲል ወቅሷል።

ሦስተኛ ወገን የተባለው ቢዮንድትረስት የተባለ ድርጅት ከኮምፒውተር ጠለፋው በኋላ ‘ኦፍላይን’ እንዲሆን መደረጉንም ባለሥልጣናቱ ገልፀዋል። እንዲሁም የኮምፒውተር ጠላፊው አሁንም የግምጃ ቤቱን መረጃዎች ማግኘት ይችል እንደሁ የሚያሳይ መረጃ የለም ብለዋል። ግምጃ ቤቱ ከኤፍቢአይ እና ሲአይኤስኤ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኮምፒውተር ጠለፋው ምክንያት የተከሰተውን ጉዳይ እየመረመረ ይገኛል ተብሏል።

እስካሁን በተሰበሰቡ ማስረጃዎች መሠረት ጠላፊው “መቀመጫውን ቻይና ያደረገ እና ‘አድቫንስድ ፐርሲስተንት ትሬት (ኤፒቲ)’ የተባለ መንገድ የተጠቀመ” ነው። “በግምጃ ቤት ፖሊሲ መሠረት በኤፒቲ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም” ይላል ደብዳቤው። ቢዮንድትረስት የተባለው ለግምጃ ቤት ተቀጥሮ የሚሠራው ድርጅት በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2 ቢጠለፍም፤ ተጠልፎ እንደሆነ ለማጣራት ሦስት ቀናት እንደወሰደበት አንድ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ጠላፊው የሠራተኞችን ኮምፒውተር እንዲሁም አንዳንድ ምስጢራዊ የሚባሉ መረጃዎችን መበርበር ችሏል። ግምጃ ቤቱ ምስጢራዊ የተባሉት መረጃዎች ምን አይነት ናቸው የሚለውን ከማሳወቅ ተቆጥቧል። የኮምፒውተር ጠለፋው ለምን ያክል ጊዜ እንደቆየም ይፋ አላደረገም። የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ የግምጃ ቤቱን ወቀሳ አስተባብለው ጠላፊዎቹ ከየት መሆናቸውን ለማወቅ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል በመግለጫ አሳውቀዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ በሳይበር ደኅንነት ጉዳይ ቻይና ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ማቆም አለባት። ከቻይና የሚመነጩ ስለሚሏቸው ጠለፋዎች የሚያስተላልፉትን የተሳሳተ መረጃም መግታት አለባቸው። “ዩናይትድ ስቴትስ በኮምፒውተር ጠለፋ ጉዳይ የቻይና መንግሥት ላይ ወቀሳ ስትሰነዝር ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You