ግብዓት የማንበብ ችግር

ስንፍና እየያዘኝ ከሰፈር ርቆ ላለመሄድ በር አካባቢ ከሚገኝ ሱቅ ውሃ እጠይቃለሁ። ሁልጊዜም የሚሰጡኝ አንድ የሶዲየም መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ውሃ ነው። ይህ ውሃ በጥራት መለኪያዎች ችግሩ ስለታወቀ ይመስላል ታግዶ እንደነበር አስታውሳለሁ። ድጋሚ ተፈቅዶለት ይሁን ወይስ በሕገ ወጥ መንገድ እያከፋፈለ ባላውቅም ከዚህ ከሰፈሬ ሱቅ ግን አይጠፋም። መቼም የዚህ አካባቢ ሰው አይገባውም ነው ወይስ ምን አይነት ንቀትና ድፍረት ነው እያልኩ እየተነጫነጭኩ ወደ ሌላ ሱቅ ሄድኩ።

ከብዙ ጊዜ በኋላ እስካሁን ይቀይሩት ይሆናል ብዬ ጠየቅኩ፤ ያው ውሃ ነው ያለው። ቆጣ ብዬ ‹‹ይሄ ውሃ እኮ የተከለከለ ውሃ ነው፣ የሶዲየም መጠኑን አይተሽዋል?›› ብዬ አሳየኋት። ውሃ ሲገዟት የታሸገ መሆኑን እንጂ ማንም እንደዚህ ብሎ እንደማያውቅ እየነገረችኝ ‹‹ደግሞ የውሃ ልዩነት አለው እንዴ?›› አለችኝ። ውሃው በራሱ ሳይሆን የሚዘጋጅበት ግብዓት ልዩነት እንደሚኖረው አታውቅም ማለት ነው። የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት በውሃ ውስጥ የሶዲየም መጠን ከፍተኛ ሲሆን ለኩላሊት መጥፎ ነው። ኩላሊትን ያህል ነገር እንደዋዛ እያየነው ነው ማለት ነው።

ይህን እንደ ማሳያ አነሳሁት እንጂ እንዲህ አይነት ችግር የዚች ባለሱቅ ችግር ብቻ አይደለም፤ የብዙዎቻችን ችግር ነው። በአንድ ምርት ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን አናነብም፤ የአንድን ምርት ግብዓት አላየንም ማለት ከምን እንደተሠራ እንኳን አናውቅም ማለት ነው።

ብዙዎቻችን አንድን ምርት የምናውቀው በሚጠራበት የምርቱ ስም ብቻ ነው። የምግብ ወይም የመጠጥ አይነት ሆኖ በአንድ ጥቅል ስም ይጠራል። ያ ምርት ግን በውስጡ የያዛቸው ግብዓቶች አሉት። ለምሳሌ፤ የብስኩት አይነት ቢሆን ‹‹ብስኩት›› በሚለው ብቻ ነው የምናውቀው። በውስጥ ያሉት ግብዓቶች ግን ‹‹የትኛው ብስኩት?›› እንድንል ያደርጉናል ማለት ነው። የጾም የፍስክ የሚባለውም ለዚያ ነው፤ የተዘጋጀበት ግብዓት ስለሚወስነው ማለት ነው።

በምርቶች ውስጥ ግብዓት ባለማወቃችን ዋናውን ግብዓት ልንንቀው እንችላለን፤ ከእሱ እንደተዘጋጀ ባለማወቃችን ማለት ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ፈረንጅ ያዘጋጃቸው ስለሚሆኑ በምን ተዓምር እንዳዘጋጁት መገረም ብቻ እንጂ ግብዓቶቹ እኛው ጋ ያሉ፤ ከጓሯችን ያሉ መሆናቸውንም አናውቅም።

በቅርቡ ቲክቶክ ላይ አንዲት ልጅ አንድ የሀገር ውስጥ ምርት ስም እየጠራች ፊት ያፀዳል እያለች አስተዋወቀች። አብዛኞቹ ሰደቧት፤ እንዴት እንዲህ አይነት ኋላቀር ነገር ተጠቀሙ ትያለሽ ብለው ማለት ነው። በድጋሚ በሠራችው ቪዲዮ ተሳዳቢዎቿን እየወቀሰች ‹‹እናንተ በውድ ዋጋ የምትገዙት ይህ ሳሙና፣ ይህ ቅባት ከዚህ እንደሚዘጋጅ እንኳን አታውቁም›› እያለች የዘመናዊ ቅባቶችንና ሳሙናዎችን ግብዓት መመሪያ እያሳየች መዘርዘር ጀመረች።

በእርግጥ እዚህ ላይ ልጅቷም ትክክል ናት ማለት አይደለም። ምንም እንኳን የዘመናዊ ቅባቶች፣ ሳሙናዎች፣ የመድኃኒቶች ግብዓት በዙሪያችን ያለ ነገር ቢሆንም በዘፈቀደ መጠቀም ግን አግባብ አይደለም። ልኬታው እና መጠኑ ተመዛዝኖ ነው የሚዘጋጀው፤ ጥሬ ምርቱን ብቻውን መጠቀም አግባብ ላይሆን ይችላል።

ሌላው ችግራችን ደግሞ መመሪያ አለማንበብ ነው። ብዙዎቻችን የፋብሪካ ዕቃዎችን እንገዛለን። በተለይም ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ዝርዝር መመሪያ ይኖራቸዋል። እዚህ ላይ ታዲያ የብዙዎቻችን ችግር መመሪያውን ገንጥሎ መጣል ነው። ለብቻው የተዘጋጀውን ወረቀትም ገሸላልጦ መጣል ነው። ያ ወረቀት የተዘጋጀው ግን ስለዕቃው አጠቃቀምና አጠቃላይ ባሕሪያት ለመግለጽ ነው። ከአከፋፈቱ ጀምሮ አሠራሩ እንዴት መጀመር እንዳለበት፣ መሐል ላይ የሚያስፈልግ ነገር ካለ፣ መጨረሻ ላይ የሚያስፈልግ ነገር ካለ… ይነግረናል ማለት ነው። አንዲት ቀላል ምሳሌ እንውሰድ!

ለምሳሌ የውሃ ማሞቂያ (ቦይለር) ገዛን እንበል። በእርግጥ ብዙ ጊዜ በልማድ በምናውቀው ስለምንጠቀም ቤት ውስጥ ሲያደርጉ በምናየው ብቻ ልንጀምረው እንችላለን። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ዕቃ በተደጋጋሚ የሚበላሽብን።

መመሪያው እንደሚለው ዝቅተኛ መጠን (Minimum) እና ከፍተኛ መጠን (Maximum) የሚባል አለው። የውሃ መጠኑ ከዝቅተኛው መጠን በታች ከሆነ አይሠራም፤ ከከፍተኛው መጠን በላይ ከሆነም አይሠራም፤ ወይም የመበላሸት ዕድሉ ሰፊ ነው። እየፈላ መከፈት የለበትም ይላል፤ ወይም እየፈላ ከላዩ ላይ ሌላ ቀዝቃዛ ውሃ መጨመር የለበትም ይላል። ውሃው ከውስጥ ሲገለበጥ ውስጡ መፅዳት እንዳለበት፣ ካልተፀዳ በእርጥበት ሊበላሽ እንደሚችል መመሪያው ይዘረዝራል።

ብዙዎቻችን ግን እነዚህ ነገሮች ልብ አንላቸውም፤ በዘፈደቀ ወይም በልማድ በምናውቀው መጠቀም ነው። ተፈጥሮ ይሁን የልማድ ልዩነት ባላውቅም በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ወንዶች የባሰ ግዴለሽ ነን። ሴቶች በጥንቃቄ ይይዛሉ። የታሸገ ነገር እንኳን ስንፈታ፤ ሴቶች እሽጉ የሚፈታበት ቦታ ላይ ነው የሚፈቱት፤ ወንዶች ግን በመመሪያው መሠረት ከመክፈት ይልቅ በኃይል ለመቅደድ ይታገላሉ። የተቋጠረ ነገር እንኳን ለመፍታት ውሉን ከመፈለግ ይልቅ ለመቅደድ መታገል ይቀለናል።

ከላይ የተጠቀምኩት የውሃ ማሞቂያው በጣም ቀላል ምሳሌ ነው፤ ያን ያህል ውስብስብ አሠራር ያለው ሆኖ አይደለም። በነገራችን ላይ መመሪያውን ያነበብኩት ለሦስተኛ ጊዜ ተበላሽቶብኝ ‹‹ምን አድርጌው ነው›› የሚል ስሜት ስለተፈጠረብኝ ነው። ለካ ያለአጠቃቀሙ እየተጠቀምኩበት ነበር። ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች አደርግበት ነበር ማለት ነው። ከዚያ በፊት ስገዛ መመሪያውን አውጥቼ የቆሻሻ ማጠራቂሚያ ውስጥ መጣል ነበር። መመሪያውን ሳነበው ግን ብዙ ስህተት ስሠራ ነበር የቆየሁት።

እንዲህ ተራ እና ትንንሽ ዕቃዎችን እንዲህ ካበላሸን የትልልቆቹን ዕቃዎች ኪሳራ ደግሞ አስቡት! መመሪያ ባለማንበብ የገንዘብ ኪሳራ እየደረሰብን ነው ማለት ነው።

ይባስ ብሎ ደግሞ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶችንም ግብዓቶቻቸውን የማወቅ ፍላጎት የለንም፤ ልምዱም የለንም። በዚህ ምክንያት ለሕመም እንዳረጋለን ማለት ነው። በመሆኑም የገንዘብም ሆነ የጤና ኪሳራ እንዳይደርስብን መመሪያ እናንብብ፣ ግብዓቶችን እንወቅ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You