ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የሊቢያ ሚሲዮን በሆነው አባድር ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውን ደግሞ በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መዲና በመሄድ ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሸሪያ እና ዓለማዊ ሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወደ ተወለዱባት አገር ተመልሰውም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ቋንቋ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ለጥቂት ዓመታት በአወሊያ ኮሌጅ በመምህርነት ተቀጥረው አገለገሉ። በመቀጠልም በኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ የሃይማኖት ትምህርት ወኪል ሆነው ሰሩ።
ላለፉት ስምንት ዓመታት ኑሯቸውን አሜሪካ ካደረጉበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቨርጂኒያ የሰላም ፋውንዴሽን ኢማም፣ የኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ኪንግስ ኦፍ አባይ ሚዲያ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያና በአረቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የተጠነሰሱ ሴራዎችን በማጋለጥ ለአገራቸው ጥቅም እየተጉ የሚገኙ ሰው ናቸው። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኡስታዝ ጀማል በሽር በተለይም ግድቡን በሚመለከቱ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን የሚያወጡትን ሐሰተኛ መረጃ በማጋለጥ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ከዚህ አልፎ በአሜሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎች ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያቸው በተጨባጭ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ በማስተባበር ረገድ የአገራቸው ባለውለታ ስለመሆናቸው ይጠቀሳል። ይህ ሥራቸው ታዲያ ከግድቡ ባሻገር በአመለካከት ተራርቀው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በማቀራረብ ለአገራቸው ጥቅም አብረውን እንዲቆሙ ማድረግ አስችሏቸዋል። እኚሁ አገር ወዳድ ሰው ከሰሞኑ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተከትሎ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አነጋግሯቸዋል። በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኡስታዝ ጀማል በሽር ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች አገርን መውደድ እንደኡስታዝ ጀማል እያሉ ይናገራሉ። በተለይም ለአገርዎ እና ለወገንዎ ያለዎትን ፍቅር በተግባር ያረጋገጡ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተዋል። በዚህ ልክ አገርዎን ለመውደድዎ ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ያንሱልንና ውይይታችንን ብንቀጥል?
ኡስታዝ ጀማል፡– በእኔ እምነት ሁሉም ሰው አገሩን ይወዳል። ተፈጥሯዊም ነው። ነገር ግን የምንወድበት መንገድ ልዩ ምልከታ ይፈልጋል። እንዳልሽው አስተዳደግ፣ ትምህርትና ሌሎችም ነገሮች የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። እኔ አስተዳደጌ በሃይማኖት ቤት ውስጥ ነው። በተለይ አባድር ትምህርት ቤት መማሬና ያደኩበት ኳስ ሜዳ የተባለው ሰፈር ሶስት መስኪዶች ያሉበት መሆኑ ቅዱስ ቁርዓንን ጠንቅቄ እንድረዳ ብሎም በዚያ ውስጥ ያሉ ትምህርቶች ሰውንና አገርን እንዴት መውደድ እንዳለብኝ እንዳውቅ አድርጎኛል። አካባቢያችን ሙስሊም ክርስቲያኑ ተፋቅሮና ተከባብሮ የሚኖርበት መሆኑ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ብዬ አስባለሁ። በነገርሽ ላይ ኳስሜዳ ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በፍቅር የሚኖርበት ማኅበራዊ ግንኙነቱም ጠንካራ የሚባል ሰፈር ነው። የሃይማኖቱ አስተምሮት በራሱ የሚሰጠው የተለየ እይታ አለ። ከሁሉም በላይ ለሰው ልጅ ጥሩ ማሰብና መደጋገፉን ትማሪበታለሽ። በአጠቃላይ እነዚህ ሁለት ነገሮች አሁን ላለሁበት ማንነት መሰረት የጣሉልኝ ጉዳዮች ናቸው ብዬ አምናለሁ።
ሁልጊዜም እንደምናገረው ደግሞ በእስልምና እምነት ነብያዊ የሆነ አስተምህሮት አለ። ነብዩ መሐመድን እስኪሰደዱ ድረስ ያሰቃዩአቸው የነበሩ ‹‹ቁረሽ›› የሚባሉ ማኅበረሰቦች ነበሩ። ወደ መዲና እያባረሯቸውና ያሳድዷቸው ነበር። ነብዩ መሐመድን ገድሎ ላመጣ 100 ግመል እንደሚሰጥ ተነግሮም ነበር። በዚያ ወቅት ደግሞ ግመል በጣም ውዱ ነገር ነበር። በዚያ ውጥረት ውስጥ ሆነው እንኳ ነብዩ መሐመድ ‹‹ አንቺ መካ እኔ በጣም የምወድሽ አገሬ ነሽ፤ ሕዝቦችሽ ባያባርሩኝ ኖሮ አልወጣም ነበር›› እያሉ ይቆጩ ነበር። ይህም የሚያሳየው ነብዩ መሐመድ በችግር ውስጥም ሆነው ምን ያህል አገራቸውን ይወዱ እንደነበረ ነው። ይህ መልዕክት ሃይማኖታዊም ፤ ሰብዓዊም ነው።
ትልቁና እኛን እዚህ ያመጣን ነገር አገርን የምንወድበት ምስጢር ነው። አገርን ለመውደድ መስፈርት የምናስቀምጥ ሰዎች አለን። ሲመቸን ብቻ አገራችን የምንወድ አለን። ግን በከፋም ሆነ በደስታ ጊዜ አገር አገር ናት። ልክ እንደእናት ደሃ እናት አልያም ‹‹ባህሪዋ ጥሩ አይደለም›› ተብሎ እናትነቷን መካድ አንችልም። ለሚያልፍ ፖለቲካና አስተሳሰብ የማታልፈውን አገራችንን ለምንም ነገር አሳልፈን መስጠት የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶ የአገር መውደድ ዋነኛ መገለጫ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ነው። ለመሆኑ ለምንድነው ስለዓባይ ወንዝና ስለህዳሴ ግድቡ ብቻ አቋም ይዘው የአረቡ ዓለምን መሞገት የመረጡት?
ኡስታዝ ጀማል፡– ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የሚገለፅለትና በዚህ ጉዳይ ላይ የተሻለ ነገር እሰራለሁ ብሎ የሚያስበው ነገር አለ። በአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ብዙ ነገሮችን ይነካካል። ዋናውና ትልቁ ነገር ይህንን የመሰለ ሀብት እያለን በድህነት መኖራችን ሁላችንንም የሚያስቆጭ መሆኑ ነው። ድህነታችንን መሰረት በማድረግ ደግሞ በኢኮኖሚ ያደጉት አገራት የፖለቲካ ጫና መላቀቅ ያለመቻላችን እንደማንኛውም ዜጋ ልብ የሚነካ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ድህነትን አሸነፍን ማለት በሁሉም ዘርፎች ላይ ያሉብንን ችግሮች መቋቋም እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዓባይን ጉዳይ ብናይ ብዙ በአዕምሮዬ ላይ የሚመጡና ለአገራችን ቢሆን ብዬ የማስባቸው ነገሮች አሉ። የዓባይ ውሃ ሥራ ላይ መዋል ብዙ ችግሮቻችንን ይፈታልናል ብዬ ስለማስብ ነው አቋም ይዤ በየዓለም አደባባይ የምሞግተው።
አዲስ ዘመን፡- ልክ እንደእርስዎ አረብኛ ቋንቋን የሚያውቁ አልፎ ተርፎ የአረቡን ዓለም ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚረዱ በርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን አሉ። ግን ደግሞ ብዙ ለአገራቸው ሲሞግቱ አናይም። ይህ የሆነው ለምን ይመስልዎታል?
ኡስታዝ ጀማል፡- እኔ እንደሚመስለኝ እራሴንም ጨምሮ በአገር ላይ ለመቆም ብዙ አጋዥ ነገሮች ያስፈልጋሉ። እውቀቱ አንዱ ጉዳይ ሆኖ እንደዚሁም ደግሞ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ያስፈልጋል። በሀሳብም ሆነ በገንዘብ መታገዝ የሚያሻው ሥራ ነው ባይ ነኝ። ያ ችግር እንዳለ ሆኖ ግን እኔ እንደማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር ፣ በሃይማኖትና በጎጥ ተከፋፍለን ፖለቲካውም በዚያ መንገድ ተከፋፍሎ በደል ይደርስበት የነበረ የኅብረተሰብ ክፍል ነበር። ከዚያ ውስጥ አንዱ ተጠቂ የሚባለው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ነው። ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሃይማኖቱ፤ በቋንቋው አልያም በአለባበሱ ሊሆን ይችላል በሥልጣን ላይ በነበሩ ሰዎች ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው ሲጨቁኑት ነው የኖሩት።
ስለዚህ እንደእኔ አይነቱ ብዙ ኅብረተሰብ የሚገባኝን ጥቅም ከሌላው እኩል ተረጋግጦልኛል፤ መብቴም ተከብሯል ብሎ የሚስብ የኅብረተሰብ ክፍል አለ። እስካሁን ድረስ ብዙ ወንድሞችና እህቶቻችን አገራዊ ስሜትን የሚፈጥር ሥራ ከመሥራት አኳያ የሚጎላቸው ነገሮች እንዳለ ይሰማኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የሙስሊም ኅብረተሰብ የሚነሳ ቅሬታ እንደነበር ይታወቃል። ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የሚባለው እንቅስቃሴም ከዚሁ ቅሬታ የመነጨ ነው። በነበረው አጠቃላይ አሠራር ጥቂት የማይባለው ሙስሊም ቅሬታ ነበረው።
ይህም ቢሆን ከአገር ጉዳይ ለድርድር የምናቀርበው ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም። አስቀድሜ እንዳልኩት ለአገር ስለአገር በሚመችም ሆነ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነን መሥራት ነው ያለብን ብዬ ነው የማስበው። ጉዳት የሚያደርሱብን ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንጂ የምንደግፈው አገራችንን እንዲሁ አንተዋትም። ሆኖም ሰዎች ደግሞ ደካሞች ነን፤ እንዲህና እንዲህ እያልን ስለአገራችን ዋጋ ላለመክፈል የቆረጥን ሰዎች አለን። አሁን ራሱ ‹‹እዚህ ሰው እየሞተ አንተ እንዴት ዓባይ ዓባይ ትላለህ?›› ብሎ የሚናገር አይጠፋም። በእኔ እምነት ግን ጦርነት ላይ እየተፋለመ ያለው ወታደር ነው ሊታደገው የሚችለው። ሌቦችንም የሚያድነው ፖሊስ ነው። ስለዚህ ሁላችንም በየዘርፋችን የምንችለውን ስናበረክት ነው ተደምሮ አገርን ጥሩ ቦታ ላይ ማስቀመጥ የምንችለው።
በአጠቃላይ ሥር የሰደደው የአመለካከት ችግርና የታሪክ ትርክት እንዲሁም በደል ተጠራቅሞ ነው ብዙዎቻችን ራሳቸውን እንዲያገሉ ያደረጋቸው። ይህም ማለት ሁሉም ሙስሊም የአገሩ ጉዳይ አያገባውም አያንገበግበውም ማለት አይደለም። በተለይ አሁን ላይ ቀድሞ ይፈፀሙ የነበሩ በደሎች በአንፃሩ የቀለሉ በመሆናቸው የብዙዎች አመለካከት ይለወጣል ብዬ አስባለሁ። በተለይ ፖለቲካውን የሚመሩት አካላት ሁሉንም ሰው አገር ወዳድ ለማድረግ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ደግሞ ከባድ ሥራ አይደለም። ኅብረተሰቡ በፍትሕና በሰላም ተጠቃሚ አድርጎ አገራዊ ስሜት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ በተለይ ግብፆች ዜጎቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ለዚያም ደግሞ እንዲታገሉ አድርገው ነው የቀረጿቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ግን ምንም እንኳን የወንዙ መመንጫና ባለቤት ብንሆንም በዚያ ልክ ትውልድ ስለሀብት ባለቤትነቱ እንዲያውቅ አልተደረገም። ለመሆኑ ይህ አለመሆኑ ያደረሰብን ጉዳት ምንድን ነው?
ኡስታዝ ጀማል፡- አስቀድሜ ከጠቀስኩልሽ ችግር ባሻገር ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለአረቦች ብሎም ለግብፆች ያለው መልካም የሚባል ነበር። ምክንያቱም ደግሞ ሁላችንም ክፋት ያለው አስተሳሰብ ይዘን እንድናድግ ባለመደረጉና በተለይ ግብፆች ያን ያህል ጉዳት ያደርሱብናል የሚል ስላልነበረን ነው። በእኔ እምነት ይሄ ያዘናጋን ይመስለኛል። እኔ አባቴ ጀማል ያሉኝ የግብፁን መሪ ጀማል አብዱልናስርን ስለሚወዱት ነው። የሚገርመው ግን ይህ የግብፅ መሪ ንጉሥ ኃይለሥላሴን ለመጣል የማይምሰው ጉድጓድ አልነበረም። ንጉሡ በተለይ በወንዙ ላይ ግድብ ለመሥራት ካሰቡበት ጊዜ ጀምሮ የግብፁ መሪ ከእነመንግሥቱ ንዋይ ጋር በማበር አገር ለማፍረስ ብዙ ጥረት ያደረገ ሰው ነበር። ጄኔራሎችን በሄሊኮፍተር ሳይቀር እዚህ ድረስ አምጥቶ መንግሥት ለመገልበጥ አሻጥር ሲሰራ የነበረውን ይህንን ሰው እንደእኔ አባት ያሉ የዋህ ኢትዮጵያውያን ይወዱት ነበር።
ስለዚህ ከአባቶቻችን ጀምሮ የግብፆችን ተንኮልና ትክክለኛ ማንነት እንድናውቅ ተደርገን አለማደጋችን ነው ዛሬ ላይ በዲፕሎማሲውም ሆነ በፕሮፖጋንዳ እንዲበልጡን የተደረገው። ሚዲያውም ቢሆን በዚህ መልኩ ትውልዱ ላይ አልሰራም። በትምህርትም ቢሆን ያለፍንበት ሁኔታ የዓባይን ባለቤትነት የሚያስታውሰን ነገር አልነበረም። ከዚያ ይልቅም አሉታዊ ትርክቶታችንን ነበር ጠንቅቀን እንድናውቅ የተደረግነው። ብዙዎቻችን ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለውም፤ ግንድ ይዞ ይዞራል፤ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› የሚሉ አሉታዊ የሆነ ሃሳብ ያላቸውን አባባሎችን ነው እየሰማን ያደግነው። የውኃና የውኃ ሀብት ዙሪያ ማጥናትም መመራመርም ጥቅም ያስገኛል ተብለን አላደግንም። ከዚህ በተጨማሪም ገበሬውም እንደዚያው የአስተራረስ ዘይቤው ዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው። ገበሬውን መሬት ቆፍሮ ውኃ ማግኘት እንደሚችል ያስተማረውም ሆነ ያሳየው የለም።
ወደ ግብፅ ስንመጣ ግን ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ የሆነ ነገር ነው የምናገኘው። ሁሉም ግብፃዊ እያንዳንዱ የውኃ ጠብታ ዋጋ እንዳለው ተምሮ ነው ያደገው። በጣም ብዙ ውኃ ከሚፈጀው የጥጥ ምርት ጀምሮ ፍራፍሬና የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አካባቢው ያለውን በፖለቲካም በጥቅምም ለመያዝ ያስቻለ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ተሰርቷል። ስለዚህ ያ ነው ሚዛኑን እንዲለያይ ያደረገው። የዓባይ ጉዳይ አሁን ፖለቲካ ሆኗል። የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። እኛም መነጋገር ጀምረናል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ሁሉም በሚችለው በአቅሙ መረባረብ ይጠበቅበታል። በተለይ መንግስት የዓባይን ጉዳይ ትውልዱ ከሥር መሠረቱ አውቆ እንዲያድግ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ማካተት እንደሚገባው ሊያስብበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማሲው ረገድስ ከግብፅ እኩል ወይም ፈጥነን መራመድ ባለመቻላችን ምን አሳጥቶናል ብለው ያምናሉ?
ኡስታዝ ጀማል፡– የዚህም ምክንያት ተመሳሳይ ነው። በዓባይ ጉዳይ ከንቃተ ሕሊና ጀምሮ ያለን ተነሳሽነት ይወስነዋል። ሌላው ግን ሆን ተብሎ በማንኛውም የውኃ ጉዳይ ላይ ሃሳብ እንዳይኖረን፤ ቢኖረንም እንኳን ያንን ሃሳብ ተግባራዊ እንዳናደርገው ከፍተኛ ሴራ ሲሰራብን ነው የቆየው። ግብፆች እንደሚታወቀው የአረብ ሊግ አባላት አገራትን ከመያዝ አልፈው ሱማሌን የአረብ ሊግ ውስጥ አስገብተዋል። በመሠረቱ በምንም ሂሳብ ሱማሌዎች አረብ ሊሆኑ አይችሉም። ቋንቋቸውም ሆነ ባህላቸው ከአረቦች ጋር አንድ ሊያደርገው የሚችል ነገር የለም። ግን ‹‹አረብ ሊግ ናችሁ›› ብለው አሳምነው አረብ ሊግ ውስጥ አስገብተዋቸዋል። ጅቡቲንም በተመሳሳይ ጎትተው አስገብተዋል። ጅቡቲ ግን እንደሚታወቀው የአፋርና የሱማሌ ስብስብ ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን ‹‹እናንተ አረቦች ናችሁ›› ብለው አስገብተዋቸዋል። ግብፆች እስከዚህ የሚደርስ ሴራ ነው የሚጠነስሱት።
ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውም ‹‹ተቃዋሚ ነኝ›› ብሎ የተነሳን አካል ሁሉ በመደገፍ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ ሆነው ነው ሁልጊዜ የሚቆሙት። እንደ ጣና በለስ ያለ ፕሮጀክት እንዲሁም ንጉስ ኃይለሥላሴ ያሰቡት ግድብ ሂደት ጨምሮ አረቦችና ተቃዋሚዎችን በማስተባበር፤ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ቀስቃሾችንና አፈቀላጤዎችን በመቅጠር የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ነው የኖሩት። የአረቡ ዓለም ደግሞ ውኃውን በደንብ ተጠቅሟል። ምክንያቱም የአስዋን ግድብ 162 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ነው የሚይዘው። ይህም ማለት ኢትዮጵያ የምትይዘው 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሜትር ጋር ሲነፃፀር ከሁለት ጊዜ እጥፍ በላይ ነው። በዚያ ላይ በጣም ብዙ እርሻዎች አሏቸው። ግብፅ በዓለም ከፍተኛ የብርቱካን ፤ የጥጥ አምራች አገር ናት። በሽንኩርትና በድንች ምርቶቻቸውም አውሮፓን አጥለቅልቀውታል። ስለዚህ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገራት ግብፅ ላይ ከፍተኛ እምነት አላቸው። ግብፅ ካላመረተች ችግር ይገጥመናል የሚል ስጋት አላቸው። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ተጠራቅሞ የምዕራባውያኑን ትኩረት ለመሳብ አስችሏቸዋል ብዬ አምናለሁ።
ከዚህም ባሻገር በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ፖለቲካ በማረጋጋትም ይሁን በማባባስ ብሎ በማናወጥ ረገድ ግብፅ ከፍተኛ ሚና አላት። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን ሚና መፈተሽ ያስፈልጋል። እርግጥነው ኢትዮጵያም ለዓለም የምታበረክታቸው አስተዋፅዖዎች አሉ። በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላት ይታወቃል ። ስለዚህ ይህንን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። የድሮውን ታሪክ እንደመመሪያ ልናደርገው ነው የሚገባን እንጂ ሁልጊዜ እሱን እያወሳንና እያነሳን መቆዘም አይገባንም። ከዚህ በኋላ ያንን የግብፅን በሴራ የተሞላ አካሄድ የሚያስቆም ሥራ መሥራት መቻል አለብን። ይህንን ማድረግ ከቻልን ጥሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል። በተለይም ግብፅ ለዓለም የምታቀርበውን ምርት እኛ እያመረትን መተካት እና የዓለምን ትኩረት መሳብ እንችላለን። እኛም ሰፊ መሬትና ብዙ ሕዝብ አለን። ስለዚህ ከግብፅ የሚያገኙትን ነገር ከእኛ ማግኘት እንደሚችሉ ልናረጋግጥላቸው ይገባል።
ሌላውና ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ የግብፆችን የውሸት ትርክቶችን ለማስወገድ ሰፊ ሥራ ይጠበቅብናል። ለምሳሌ የውኃውን ትክክለኛ መነሻ ኢትዮጵያ መሆንዋን ለአረቡ ዓለም በስፋት ማሳወቅ ይገባናል። ምክንያቱም በግብፅ ለዘመናት የተነዛው ሐሰተኛ ትርክት የዓባይ ውኃ መነሻ ቪክቶሪያ ሐይቅ መሆኑና ኢትዮጵያ ልትገድብ ነው የሚለውን ሐሰተኛ ወሬ ቀድመን ማፍረስና እውነታውን ማሳወቅ ይገባናል። እኛ የምናበረከተውን መጠን እንዲያውቁ ማድረግ መቻል አለብን። እነሱ ከዓባይ ባሻገር ባሉን ወንዞችም ጥያቄ ያነሳሉ። ይሁንና ዓለም አቀፍ ሕጉ የሚመለከተው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ብቻ ነው። የሚገርመው ግን እነሱም የከርሰምድር ውሃ አላቸው። እኛ በዚያ ሀብት እንካፈላችሁ አላልንም ምክንያቱም ያ ውኃ የእነሱ ነው። ቀይባህርንና ሜዲትራኒያን ባህርን ይጠቀማሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የዓባይን ውሃ ያለገደብ ሲጠቀሙ ነው የኖሩት። ሱዳንና ግብፅ ላይ በስፋት ጥጥ የሚያመርቱት እንግሊዞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያ ከዚህ ውኃ እንዳትጠቀም ውል አስፈርመዋል። ያንን ውል ግን ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ሽሮታል። እኛ ይህንን ማሳወቅ ይገባናል። ምክንያቱም እነሱ የሚሞግቱት ሕዝብ ያልቃል ብለው ነው አይደለ? የእኛም ሕዝብ ያልቃል። እነሱ ስደት ነው የሚፈሩት ፤ እኛም ዋነኛ ችግራችን ስደት ነው። ይህንን እውነታ ለዓለም ማሳየት ግዴታችን ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ እንቅልፍ በቃ ብለን አረብኛ የሚችለው አረብኛ ፤ እንግሊዝኛ የሚችለው በእንግሊዝኛ ፤ ፈረንሳይኛ የሚችል እንዲሁ የዓለም ሕዝብ ዘንድ በመድረስ የራሱን ጥረት ማድረግ አለበት። ሃይማኖትና ብሔር ሳይገድቡን በኅብረት መታገል አለብን። ደግሞም ድህነት የሚባለው የጋራ ጠላት ስላለን ይህንን ማሸነፍ የምንችለው በሀብታችን መጠቀም ስንችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከግድቡም ሆነ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን አቋም እንዴት ያዩታል?
ኡስታዝ ጀማል፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ እየተቀያየረ መጥቶ አሁን ያለንበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። አንዱ አንዱን እየጠቀመ የሚቀጥልበት ዓለም ላይ ነው ያለነው። ግብፆችን ለተለያዩ ጥቅሞች የሚፈልግ እንዳለ ሁሉ ኢትዮጵያንም በተመሳሳይ መንገድ ለጥቅሙ የሚፈልጋት አለ። እርግጥ የተባበሩት መንግሥታት ከአንድ ወገን የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ በጣም እንጎዳ ነበር። ለምሳሌ የአሜሪካና የአውሮፓውያን አቋም ወደ ግብፆቹ ያደላ ነው። አስቀድመን እንዳነሳነው አውሮፓውያን ከግብፅ ጋር ብዙ የጥቅም ትስስር አላቸው። ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋርም ከባድ የፖለቲካ ግንኙነት አላቸው። ምክንያቱም ግብፅ ከመከለኛው ምስራቅ ጋር በተያያዘ ምዕራባውያኑን የምታገለግልበት ሁኔታ በመኖሩ ነው። ከዚያ አንፃር ግብፅን ማጣት አይፈልጉም። ስለዚህ የሆነ ነገር ፈጥረው ግብፅን ማስደሰት ይፈልጋሉ። በአንፃሩ ደግሞ ቻይና ፤ ራሺያና ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት አላቸው። ስለዚህ በዚያ ትግል መሐል አይን ያወጣ ስህተት መስራት አይችሉም።
ለዚህም በተባበሩት መንግሥታት በዚያ ሁሉ ጫና መሐል ኢትዮጵያ ድል አድርጋ ነው የወጣችው ማለት ይቻላል። በተለይም ኢትዮጵያ የያዘችው የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ ኅብረት መፈታት አለበት ማለቷ ጥቂት በማይባሉት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። አሳማኝም በመሆኑ ነው ውይይታቸው ፍሬ አልባ የሆነው። ግብፆችም በበኩላቸው ውሳኔ ላይ አለመደረሱ ድል ነው ይላሉ። ግን ውጤቱና መጨረሻው ላይ የሚደረገው ስምምነት ነው። ልክ ሱዳን እንደተሰራባት አይነት ስህተት እንዳንሰራ መጠንቀቅ ይገባናል። ሱዳንን እንደሚታወቀው የማታርስበትን ውል አስፈርመዋት ዛሬም ድረስ ጠፍንገው ይዘዋታል። ስለዚህ እኛም ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት ውል አንገባም። ጉዳዩን በጥንቃቄ ካስኬድነው በጣም ጥሩ ነገር ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ በተጨባጭ ማዕቀብ ትጥላለች ብለው ያምናሉ?
ኡስታዝ ጀማል፡- እኔ የፖለቲካ ሰው ባለመሆኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ማብራሪያ መስጠት አልችል ይሆናል፤ ሆኖም ካለው ሁኔታ አንፃር ብዙ ጊዜ ማዕቀብ ላይ የተሳካላቸው አገራት የሚንተራሱባቸው መሠረቶች አሉ። ከዚያ ውስጥ የሕዝብ አመፅ ነው። ሌላው ተገዳዳሪ ኃይል የመኖር ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን የሚደግፉ ከአሜሪካ ጋር የሚገዳደሩ ኃይሎች በመኖራቸው ማዕቀቡ ያን ያህል ያሰጋታል ብዬ አላስብም። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በመሆኑ ይህ በራሱ ማዕቀብ ለመጣል አያደፋፍራቸውም። ከዚህ ቀደም ኤምባሲ በመሄድ የበሰበሰ እንቁላል ሲወረውር የነበረውና ለምን ለግድቡ ብር ተጠየቅን ብሎ አምባሳደሩን ሲቃወም የነበረው የዲያስፖራ ኅብረተሰብ አሁን ግን ተገልብጦ ‹‹ኢትዮጵያን አትንኩብኝ›› ብሎ ነው ቀን ከሌሊት እየተቃወመ ያለው። መንግሥትም ተጨባጭ የሆነ ለውጦችን አሳይቶናል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ አስችሏል ባይ ነኝ።
በመሆኑም ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚፈልገው አካል ስጋት እንዲገባው አድርጓል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩል መሰደዳችን ስቃይ ቢሆንም በጣም ደግሞ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችልና ብዛት ያለው ኃይል አለ። አሜሪካ ውስጥ ያለው ዲያስፖራ በሙሉ የሥራ ማቆም አድማ ቢያደርግ አሜሪካን አደጋ ውስጥ ሊከሰት የሚችል ኃይል አለ። ስለዚህ እንደሕዝብ አሁንም በጣም ጠንክረን ከቆምን አሁንም ያሰቡትን ማዕቀብም ሆነ ጫና ማስቆም እንችላለን። በነገራችን ላይ እነሱ ማንኛውንም ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት የሕዝቡንና የአገሪቱን ሁኔታ ይሰልላሉ። ስለዚህ የሕዝቡ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር መቆም ጫናውን እንዳያደርጉ ያግዳቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
ሌላኛው ጉዳይ የኃይል ሚዛኑ ተመጣጣኝ መሆኑ በራሱ የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ አለው። ቻይና ፤ ሩሲያ፤ ህንድና ቱርክ የመሳሰሉት አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ትስስር ያላቸው በመሆኑ እነሱም ሂሳብ ውስጥ ስለሚገቡ ዝም ብሎ መተናኮስ የሚቻልበት እድል የለም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ሲሰበሰብ ለ11ኛ ጊዜ ቢሆንም አንድም ጊዜ ስምምነት ላይ ሳይደርስ መበተኑም አሁን በጠቀስነው ምክንያት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እኛ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚፈልጉ ሰዎች ስብስብ ብቻ አይደለም። ሌሎች ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየት የሚችሉ ግን ትልቅ ሚዛን ያላቸው አገራትም አሉበት። ስለዚህ ዝም ብሎ እንደፈለጉ መፍረድ አልቻሉም።
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን ማባረሯ ይታወሳል፤ ይህ ምን ተጽዕኖ አለው ይላሉ?
ኡስታዝ ጀማል፡– በእኔ በኩል እንደመርሕ ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች እዚህ አገር በሚገቡበት ወቅት ሕጋዊውን መስመር መከተል አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። እርዳታ ስለሰጡን ብቻ እርዳታውን አስታከው የፈለጉትን ሊያደርጉ አይችሉም። እኔ እንደሃይማኖት ተማሪ አንድ ሰው ፅድቅ ሲያደርግ መመፃደቅ ተገቢ እንዳልሆነ ነው የማምነው። ስለዚህ እኔ እንዲህ አይነቱን ነገር እንደመመፃደቅ ነው የምቆጥረው። እንዳውም ከመመፃደቅም ያለፈ ነው። ቅዱስ ቁርዓን ፅድቅ ብላችሁ የሰጣችሁትን ወይም ያደረጋችሁትን መልካምነት በሰዎች ላይ መመፃደቅና ተንኮል መስራት እንደማይገባ ነው የሚያዘው። እነሱ የዚህ አይነት ሃሳብ ያላቸው ነው የሚመስሉት። እንደሰማነው ከ600 የድርጅቱ ሰራተኞች ውስጥ ሰባት ብቻ ናቸው በሕግ ጥሰት የተባረሩት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ችግሯ ከእርዳታው ጋር እንዳልሆነ በጣም ግልፅ ነው ማለት ነው። ከዚያ ውጭ እንዲህ በጣም ችግር ውስጥ ያለችን አገር ፈፅሞ እርዳታ ልትገፋ አትችልም። ስለዚህ እኛ የደህንነት ሠራተኞች ባንሆንም የተረጋገጠ ማስረጃ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ በጣም የሚደገፍ ነው። ደግሞም በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚሰሩ የእርዳታ ድርጅቶች ብዙ ጥፋቶች እንደሚሰሩ በግል ተሞክሮዬ ለማረጋገጥ ችያለሁ። ለምሳሌ ሴት እና ህፃናትን ደፍረው የሚያዙ ከፍተኛ የሚባሉ የድርጅቱ ሠራተኞች አሉ። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ወንጀል ሲሰሩ አንጠየቅም እኛ ስለምንረዳ ብለው የሚያስቡ ከሆነ የተሳሳተ እሳቤ ነው። ጥፋት በሠሩ ቁጥር ሊጋለጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የምዕራቡም ሆነ የምስራቁ ዓለም የሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ ፍፁም የሆነ ወገንተኝነት ያለው ዘገባን ማስቆምም ሆነ ያንን የሚመጥን የሚዲያ ሥራ መሥራት ያልተቻለው ለምን ይመስልዎታል?
ኡስታዝ ጀማል፡– አሁንም የፊትና የኋላ አካሄድ ነው የሚመስለኝ። እነሱ ብዙ ቀድመው ሄደዋል። ከኋላ የሚመጣው ሰው ከእነሱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መልፋት ይጠበቅበታል። የቢቢሲ እና የአልጀዚራ ዘጋቢዎች ሌላው ቀርቶ የአሜሪካው አልጀዚራን እንዲተካ የተሰራው አልሁራ የተባለው ሚዲያ ዘጋቢዎችና በአጠቃላይ ፕሮግራሙን የሚሰሩት ሰዎች ወይ ግብፃዊ ናቸው፤ አልያም የግብፅ ተፅዕኖ ያደረባቸው አረቦች ናቸው። በነገራችን ላይ አሜሪካ ከአገሯ አልጀዚራን አስወጥታዋለች። ለእሱ ግኑ መተኪያ ብላ አረቦች ቀጥራ ነው የምታሠራው። የአልሁራ ጋዜጠኞች ይዋሻሉ፤ ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ዘገባ ያሰራጫሉ፤ ለአገራቸው ፖለቲካ ይበጃል የሚሉትን ሁሉ በመሥራት ይታወቃሉ። አልጀዚራም የተወረረው በግብፃውያን ነው። እንደ ሙስጠፋ አሹር የተባሉ ሰዎች ከጋዜጠኝነትም በላይ አክቲቪስት ሆነዋል። ይህ ግለሰብ
ኢትዮጵያን ሲሳደብ ነው የሚውለው ፤ የሚያድረው። ይህ ሰውዬ ደግሞ አልጀዚራ ላይ የኳታር ነፃ ፕሬስ ነው ተብሎ አወያይ ሆኖ ይቀርባል። ገና ተወያዮቹን ከሚጠራበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የቢሮክራሲው አካሄድ ለእሱ እሳቤ ሁሉም ነገር የሚበጅ አድርጎ ነው የሚያስተካክለው። ብዙ ፕሮግራሞችን አይቻለሁ እሱ ይሁን እንግዶቹ ተከራካሪ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በሚታይ ሁኔታ ወገንተኝነቱን ያንፀባርቃል።
ሌላው አሁንም ከድህነታችን ጋር የተያያዘ ያለው ችግር ነው። ለምሳሌ ግብፆች ከአሜሪካ የሚያገኙት በጣም ብዙ ሀብት እንዳለ ሆኖ ግን እነሱ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ለአፈቀላጤዎቻቸው የሚከፍሉት ገንዘብ አለ። ከ80 ቢሊዮን በላይ አውጥተው ብዙ ደላሎችን አስቀምጠው፤ የኮንግረስ አባላትን ለማሳመን የሚሄዱበት መንገድ በጣም ከእኛ የተለየ ነው። ስለዚህ ይህና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው የእነሱ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው። እንኳን የእነሱን ይቅርና ከሕወሓት ጋር ተያይዞ የገባንበትን ችግር የገንዘብ ሚዛን ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ አይተነዋል። በአጠቃላይ በዚህ ላይ በልጦ ለመገኘት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሕወሓት መራሹን መንግሥት ሲቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ነዎት። በዚያም ምክንያት ብዙ ችግር የደረሰብዎት እንደመሆኑ ያ ሥርዓት መወገድ ምን መልካም ነገር ይዞ መጥቷል ብለው ያምናሉ ?
ኡስታዝ ጀማል፡– በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፤ ግን ለውጥ እንዳለ ይታየኛል። ለምሳሌ በሕወሓት ሥርዓት የታሰሩ፣ እኔንም ጨምሮ ከአገር የወጡ ዜጎች በአገራቸው ላይ በሰላም መኖር ችለዋል። ከዚህ ቀደም ግን እንደሚታወቀው አክራሪ ወይም ፅንፈኛ አልያም ደግሞ አገር ሊያፈርስ ተብሎ 21 ዓመት የተፈረደበት እንደአቡበከር አይነቱ አሁን ላይ የሰላም አምባሳደር ተብለው ተሹመዋል። ስለዚህ ይህና ሌሎችም በጣም ብዙ ነገሮችን ስናይ ጥሩ መንገድ ላይ እንዳለን ይሰማኛል። እናም ለውጡ ከተሰራበት የበለጠ የሚያድግ ይሆናል። አሁን ለውጥ ውስጥ ነው ያለነው። ምርጫውም ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚዎቹ እንኳን ምን እንከን ሊያወጡለት ያልቻሉት በጣም ጥሩ በሆነ መንገድ ነው የተከናወነው። ግን ልክ በሰሜኑ ላይ ያለው አይነት ችግር አሁንም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ደግሞ በአስተሳሰብ ፤ የበፊቱን አመለካከት እንደያዙ ተሰግስገው ያሉ ኃይሎች አሉ።
በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም ሳይቀር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ነው ያለው። ስለዚህ የለውጡ ሂደትን ስናስብ በጣም በጥልቀት ማየት አለብን። ሁሉም እንደእኛ ጥሩ አሳቢ ነው፤ ስለዚህ ይቅር ብሎ ነገሮችን አሳልፎ ይሄዳል ማለት አይደለም። አንዳንዱ ይቅርታው ራሱ ይቅርታ የሚያስፈልገው ነው። የውሸት ይቅርታ ጠይቆ ያችኑ በፊት ይፈፅማት የነበረችውን በደል ፤ በፊት የነበረውን ሙስና እና ስግብግብነት ማስኬድ የሚፈልግ አለ። በለውጡ ልብስ ውስጥ ሆኖ የቀድሞውን ሥርዓት የሚያራምድ አለ። ለምሳሌ በሙስሊም ተቋማት ውስጥ እስካሁን ያልተፈታ ችግር አለ። ሕወሓት ሰርቶት የሄደው የሁለትዮሽ መጓተት እስከአሁን ድረስ አለ። እና መንግሥት ይህንን ነገር ከመፍታት አንፃር የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህንን ስል ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ይግባ ማለቴ አይደለም። ነገር ግን እንደ ድርጅት ፤ ትክክለኛ የሆነ አቋም ያለው ተቋም እንዲሆን ግን ማገዝ መቻል አለበት።
በዚህ ተቋም ምክንያት አኩርፈው አሁንም መንግሥት እጁ አለበት ብለው የሚፈሩ አሉ። እንደአገር ለውጥ ቢመጣ ለእኛ ለሙስሊሞቹ ለውጥ አልመጣም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። ስለዚህ እነዚያ ሰዎች ተደራሽ ያደረገ ሥራ መሥራት መቻል አለበት። ምክንያቱም የመፍትሔው አካል አድርገሽ የምታቀርቢው ሰው ዋናው የችግሩ አካል ራሱ ሊሆን እንደሚችል መጠራጠር ይገባል። ለምሳሌ የራሳችን ሰዎች ናቸው መከላከያውን ከኋላው የመቱት። አሁንም የለውጡ አካል ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ከበስተጀርባ ተቃራኒ ሥራ የሚሠሩ እንዳሉ ነው እኔ የማምነው። እነዚህን መንጥሮ የማውጣት እና የእውነት ንስሐ የገቡትን ፤ የእውነት ለውጥ የሚፈልጉትን አከላት በትክክል አቅፎ የሚሄደውን ዓይነት ለውጥ እንዲሆን ሥራ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ ”የዓባይ ንጉሦች” በሚል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እየሰሩ ስላሉት ሥራ ያብራሩልን?
ኡስታዝ ጀማል፡-መነሻዬ ላይ እንዳልኩት ግብፆች በዚህ ውኃ ላይ ያላቸው አቋም ሕይወታችን ነው እስከማለት ይደርሳል። የዓባይ ውኃ ከሌለ እኛ የለንም ነው ብለው የሚናገሩት። ግብፅን ራሱ የሚጠሯት ‹‹የአዱኛ እናት›› ብለው ነው። የትም ቦታ ግብፃዊ ስንተዋወቅ የመጀመሪያ የሚናገሩት ነገር ‹‹ እኔ የዓባይ ልጅ ነኝ›› የሚል ነው። ከዚህ አንፃር እኛስ ለምን ባለቤትነታችን የሚያረጋግጥ ሥራ አንሠራም የሚል ጥያቄ ነበረኝ። በተለይ በየመገናኛ ብዙኃኑ ብዙ የምሞግት እንደመሆኔና በራሴም ዩቲዩብ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስለምሠራ ለሚዲያው ስም እንስጠው ብለን ስንጨነቅ ግብጾች የዓባይ ልጅ ነኝ ካሉ። እኛ የዓባይ ማመንጫ ሆነን ሳለ ጠቅልለው ውኃውን ብቻቸውን ሲጠቀሙበት ከመኖራቸው አንፃር ያንን ሁሉ በደል የሚያካክስ ስም ማውጣት አለብን ብለን ነው ‹‹የዓባይ ንጉሦች›› የሚል መጠሪያ ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለነው።
ግብፆች ይህንን ጥቅም ለማስቀጠል ሲሉ አገራችን ላይ የፈጠሩት ቀውስ እስከአሁን ድረስ የተለያየ ኃይሎችን በማነሳሳት በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። እንዳው በጥቂቱ ብገልፅልሽ በሕወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የሕወሓት አባል እስከሚመስሉ ድረስ ሲሞግቱ ይታያሉ። ለምሳሌ ‹‹ትልቂቱ ትግራይ እንዴት ትፈጠር?›› የሚል ካርታ ዘርግቶ የሚያስረዳበት ሁኔታ አለ። አንድ የአልሲሲ ቀኝ እጅ የሚባል የግብፅ ጋዜጠኛ ‹‹ትልቋን ትግራይን የሚመሰርቱ ሰዎች›› እያለ ልክ ራሱ የሕወሓት አባል በሚመስል መልኩ ነው የሚዘግበው። በአጠቃላይ በፊት እንደሚያደርጉት ተቃዋሚዎችን በመደገፍ እና የኢትዮጵያን የልማት ሥራ እያደናቀፉ ነው የኖሩት። በልማት ላይ የሚያተኩር መንግሥት እንዳይፈጠርም ሁሉንም ዓይነት አሻጥር ይከተሉ ነበር። ከዚህ በኋላ ይህ ነገር እንዲቆም ብዙ መሥራት አለብን። በእርግጥ አሁን ላይ ሕዝቡ ነቅቷል። ብዙ ሰው አሁን ላይ ስለግድቡም ሆነ ስለአገሩ እየሞገተ ነው ያለው።
እኔ መጀመሪያ ላይ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ብለን አሜሪካ ላይ ሰልፍ ስንወጣም ግድቡ መገደቡ ችግር የለውም የሚል አቋም ነበረኝ፤ ግን ደግሞ በደላችሁን ገድቡልን ነበር ስንል የነበረው። ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ወንድሜ መሐመድ አልአሩሲ ከግብጾች ጋር ሲወያይ ስመለከት በግሌ በጣም ትልቅ ተሐድሶ ነው የፈጠረብኝ። እሱን ሳየው የሆነ ነገር ነው የኮረኮረኝ። እና እንድነቃ አድርጎኛል። ስለዚህ እስካሁን ያላየነውን ነገር እንዳይ አድርጎኛል። በተለይ በሃይማኖት ስለተሳሰርን ብቻ ለግብፅ ያለን ጭፍን ፍቅር ተገቢ እንዳልሆነ መገንዘብ ቻልኩ። እኛ እኮ በአጠቃላይ ለአረቡ ዓለም ካለን ጭፍን ፍቅር የተነሳ ከስማችን ጀምሮ አለባበሳችንና አመጋገባችንን እነሱን ለመምሰል ነው ጥረት የምናደርገው። ይህንን የምናደርገው እኛ ጥሩ ሰዎች ስለሆንን ነው። ይሄም መልካም ባህላችን ነው ብዬ አምናሁ። የነብዩ መሐመድም ተከታዮቻቸውን ኢትዮጵያ ሄደው እንዲያርፉ ነው ትዕዛዝ ያስተላለፉት። ይህንን ያህል ሥር የሰደደና የከፋ ጥላቻና ስግብግብነት ‹‹እኔ ብቻ ተጠቅሜ ሌላው በችግር ይኑር›› የሚል፤ እነሱ የፈሩትን ስደት እኛ እያፈስነው እንድንኖር በችግር እንድንማቅቅ የመፈለጋቸው ሁኔታ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ቁጭት ይፈጥራል።
በዚህ ላይ ንቀታቸውና ስድባቸው ይበልጥ ያማል። ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት አባቶቻቸው ሳይቀር በጣም በሚያሳፍር ቋንቋ ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ ስትሰሚ በጣም ነው የሚጎዳሽ። በጣም ፍርደ ገምድል የሆነ ብይን ሲሰጡ ስትመለከቺ ታዝኚኛለሽ። የሚገርመው ደግሞ በቅዱስ ቁርዓን ግብፆች እየተከተሉት ያሉት መንገድ ፍፁም ትክክል አለመሆንና ፍርደ ገምድል መሆኑን የሚሳይ በምሳሌ የተቀመጠ ታሪክ አለ። ይህንን ደግሞ ማንም ሙስሊም የሆነ ወይም አረብኛ የሚያነብ ሁሉ ሊያገኘው የሚችል ነው። ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ በቁርዓን ላይ መኖሩ በራሱ ለእኛ እንደእድል ነው። የተረጋገጠለት ነብያዊ የሆነ ቱፊት ነው።
ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ መልሶች ያለን ሰዎች ሃይማኖቱን ሁሉ ችላ ብለው ‹‹ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ነው የቆመችው›› ይላሉ። አንዴ ደግሞ ሙስሊም የሚባል ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ አድርገው ወይም ካለም አስቀድሜ የገለፅኩልሽ አይነት ትርክት በመንዛት ሙስሊሙን የዓለም ክፍል ቀልብ ለመግዛት ጥረት ያደርጋሉ። በመሆኑም ከግብፅ የሚላከውን አፍራሽ አመለካከት ለመስበር ጠንካራ ሚዲያ ያስፈልጋል ብለን ጀምረን ውጤት ማምጣት ችለናል። እኛ ከጀመርን በኋላ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በአረብኛ ቋንቋ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ጀምረዋል። ይህም በጣም የሚያስደስት ነው። ግን ማደግ አለበት። ስለዚህ ከዚህ መነሻ ነው የዓባይ ንጉሦች የሚለው ሃሳብ የመነጨው።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሰፊ እቅስቃሴ ሲጀምሩ የሚያግዝዎት አካል ካለ ቢጠቅሱልን?
ኡስታዝ ጀማል፡– ማንም ድጋፍ አያደርግልኝም፤ በግሌ ነው የምሠራው። የራሴ የሆኑ ሥራዎች አሉኝ። ግን ብዙ ሰዓቴን የማሳልፈው በዚህ ሥራ ላይ ነው። አሁን ላይ ግን ብዙ አባላት እየመጡ ነው። በዩቲዩብ በኩል ወርሐዊ ከፋይ የሆኑ ጥቂት ሰዎች አሉ። አሁን ላይ የበለጠ እንዳይደክመን ወደኋላ እንዳንቀር ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት የበለጠ መጠናከር አለባቸው። በመንግሥትም ደረጃ ቅርንጫፋችንን ሰፋ አድርገን ያንኑ ሥራ እዚህም ለማስቀጠል ድጋፍ ያስፈልገናል። በነገራችን ላይ በዚህ ሚዲያ የምናደርገው ትግል የዓባይን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፈታው ክርስቲያኑና ሙስሊሙ መካከል የነበረውን ችግር ነው። የዚህ ፕሮግራም መጀመር በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ላይ መሥራት እንዲችል እድል ፈጥሯል። ለምሳሌ ለዓባይ ግድብ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ስንሰበስብ ቄሱም፤ ሼሁም፤ ኡስታዙም ፤ ዲያቆኑም በሁሉም ተባብሮ ነው ድጋፍ ያደረገው። ስለዚህ በጋራ ጉዳይ ላይ ሙስሊም ክርስቲያን ሳንል ተባብረን መስራት እንደምንችል አስመስክረናል።
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚውል ድጋፍ የአንድ ወር ጊዜ ገደብ ሰጥተን አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አሥር ሺህ ዶላር ነው የሰበሰብነው። ይህንን ያሰባሰብነው አምስት ሺ ከማይሞላ ሰው ነው። ስለዚህ ይህም ደግም የሚሳየን ስደተኛውን ሁሉ ማስተባበር ከተቻለ ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደምችል ነው። ለምሳሌ አንዲት ሰላም አስመላሽ የተባለች ኤርትራዊት እህት በየቀኑ አንድ አንድ ሺ ብር እየላከች በድምሩ 30 ሺ ብር ነው የሰጠችን ። ሌላው ደስታ ገላጋይ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ከ300 ሺ ብር በላይ አሰባስበው ነው የሰጡን። እኛ በምንኖርባት አካባቢ ያለውን ሁሉ ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንኳን ማስተባበር ቢቻል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። በዓለም ያሉትን ዲያስፖራዎች ሁሉ በነቂስ ማስተባበር ቢቻል አንድ ግድብ ብቻ ሳይሆን በርካታ ግድቦች መስራት አያቅተንም።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው መግባታቸው ይታወቃል። እነዚህ ዲያስፖራዎች በማስተባበር ውጤታማ ሥራ ከመሥራት አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል?
ኡስታዝ ጀማል፡– ይሄ ጉዳይ አሁንም የሚመልሰው አገር የሚመራው አካል ነው። ሰዎችን ‹‹አገር አለኝ፣ አገራችን ላይ ብንሰራ እናድጋለን፣ አገራችንን መለወጥ እንችላለን፤ ገንዘባችንን አገራችን ላይ ብናወጣ አንከስርም›› የሚል ስሜት እንዲፈጠርባቸው እስከገነባን ድረስ ሰዎቹን መሳብም ሆነ ብዙ መሥራት እንችላለን። የራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መሳብ እንችላለን። ደግሞም በሃይማኖትና በባህል የምንተሳሰራቸው አገራት በመኖራቸው እነዚህን አገራት መሳብ ይገባናል። በዘርና በጎሳ ከመጥበብ በላይ በዓለም ላይ ያለውን ሕዝብ መድረስ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- እኔ ጥያቄዎቼን ጨርሻለሁ፤ እርስዎ ግን ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ኡስታዝ ጀማል፡– የመጨረሻ ልናገር የምችለው kings of abai.com ወይም kings of abai. org ብለን በሁለቱም አቅጣጫ አንደኛው ሰብዓዊ እርዳታዎችን ከዚህ በኋላ ሥርዓት አስይዘን የምንሄድበት አደረጃጀት ውስጥ ገብተናል። በአሜሪካ መንግሥት ፈቃድ ተሰጥቶናል። በተጨማሪም የተለያዩ እዚህ አገር ላይ ሊሠሩ የሚችሉ የእርዳታ ሥራዎች ሕጋዊ በሆነ መልኩ በደንብ ለመሥራት ዝግጁ ነን። እዚህ ላይ ተባባሪ መሆንም ሆነ ማገዝ ለሚፈልግ በእኛ በኩል በራችን ክፍት መሆኑን ማሳወቅ እወዳለሁ። ሌላው kings of abai.com ብለን ደግሞ ሚዲያችን የሚደገፍ እንዲሁም ለሌላው ዓለም የምናሳይበት ሥርዓት ዘርግተናል። በዚህም ‹‹የዓባይ ንጉሶች፤ ዓባያችን አድዋችን፤ በፍፁም በቅኝ ግዛት ያልተገዛች፤ ሰላም›› የሚሉ ቃሎች የታተሙባቸው ቲሸርቶችን በማሳተም በኦን ላይን እንሸጣለን። ስለዚህ ይህን ቲሸርት በመግዛት የእውነት የዓባይ ንጉሶች መሆናችንን እናውጅ ነው የምለው። ሌላው አሁንም ዩቲዩባችንን ያልተቀላቀሉ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ማስተላፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኡስታአዝ ጀማል፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014