አሌክስ ስኪል የ22 ዓመት እንግሊዛዊ ነው። ሴት ጓደኛው ለዓመታት የቤት ውስጥ ጥቃት ስታደርስበት ኖራለች። የስቃይ ታሪኩን ለቢቢሲ ተንፍሶታል። እንዲህም እንደወረደ ወደ አማርኛ አምጥተነዋል፡፡
ጆርዳና እና እኔ ኮሌጅ እያለን ነው የተዋወቅነው። ስተዋወቃት ሁለታችንም ገና 16 ዓመታችን ነበር። እሷ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ሰቃይ ተማሪ የምትባል ናት። ዩኒቨርሲቲም መግባት ችላ ነበር። እኔ ግን ደካማ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በሁለታችን መካከል ችግሮች እየከፉ የመጡት የኋላ ኋላ ነበር።
አብረን መኖር ስንጀምር ቀስ በቀስ ከሁሉም ጓደኞቼ ጋር እንዳልገናኝ ታስፈራራኝ ጀመር። ፌስቡክ እንዳልጠቀምም አስጠነቀቀችኝ። መጀመሪያ እሷን እንዳይከፋት እያልኩ እሺ ነበር የምላት። በኋላ ግን አእምሮዬን ተቆጣጠረችው።
ዘዴዋ ቀስ በቀስ ሠርቶላት የሷ ባሪያ አደረገችኝ። ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሯ ሥር አድርጋኝ የቤት ውስጥ ጥቃት ታደርስብኝ ጀመር። ታስርበኛለች፣ አስራ ትገርፈኛለች።
በርካታ ቀናት ምግብ ትከለክለኝ ጀመር። ራሴ አብስዬም መብላት አልቻልኩም። ከበላሁ አስራ ስለምትገርፈኝ ጾሜን መዋልና ማደር ጀመርኩ። በከፍተኛ ደረጃ ኪሎዬ ቀነሰ።
ባህሪዋን ተቋቁሜ ስጋፈጣት ደግሞ ጥፋቱን አዙራ እኔ ላይ መጠምጠም ጀመረች። ይበልጥ የራሷን ጥፋት በኔ እያላከከች ታሰቃየኝ ጀመር።
ለምሳሌ ያን ጫማህን አልወደድኩትም’ ወይም ደግሞ ‘ቡኒውን ሸሚዝህን እንዳትለብሰው’ ስትለኝ እሷን ደስ ይበላት እያልኩ የምትለኝን አደርጋለሁ። ትዕዛዟ ግን ማቆምያ አልነበረውም። ዓላማዋ እኔን የሷ ባሪያ ማድረግ ነበር።
አንድ ቀን በሻይ ማፍያው ውኃ አፈላች። ውኃው በደንብ ሲንተከተክ የፈላውን ውኃ በማንቆርቆርያ ይዛ ታስፈራራኝ ጀመር። መኝታ ቤት ጥግ ወስዳ ውኃውን ላዬ ላይ ለቀቀችው። ይህንን ቀን በፍጹም አልዘነጋውም።
ከጆርዳና ጋር ለሦስት ዓመታት አብረን ኖረናል። በመሀላችን ፍቅር አልነበረም ባልልም በትንሽ በትልቁ እንነታረክ ነበር። የሚገርመው ጠቡ የሚጀምረው ከትንንሽ ነገሮች መሆኑ ነው። የጸጉሬ ቁርጥ ወይም ደግሞ የለበስኩት ቲሸርት ለከባድ ንትርክ ሊዳርገን ይችላል።
የፈላ ውኃ ከደፋችብኝ በኋላ ሕመሙን መቋቋም አልቻልኩም። እያለቀስኩ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ እንድነከር ለመንኳት። ፈቀደችልኝ። የተሰማኝ እፎይታ ከቃላት በላይ ነበር።
የፈላ ውኃ እንደደፋችብኝ ለሰው ብናገር ቅጣቱ እንደሚበረታብኝ ነግራ አስፈራራችኝ። ዝም ጭጭ አልኩኝ። እስክንቀጠቀጥ ነው የምፈራት።
ልጆች ስንወልድ ነገሮች ይለወጣሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ መሳሳቴን የተረዳሁት በኋላ ነው። እኔ ላይ የምታደርሰው ጥቃት እየጨመረ ሲመጣ ከኔ ይልቅ ለልጆቼ መፍራት ጀመርኩ። ጥያት ብሄድ ልጆቻችን ላይ አደጋ ልታደርስ እንደምችል እርግጠኛ እየሆንኩ መጣሁ። ከዚህ በኋላ ሕይወቴ በጭንቀት የተሞላ ሆነ።
እርግጥ ነው የኔና የጆርዳና የፍቅር ሕይወት ጭቅጭቅና መከራ ብቻ አልነበረም። ደስ የሚሉ ጊዜም አሳልፈናል። በእነዚህ ጊዜያት ግንኙነታችን መልክ እንደሚይዝ በማሰብ ላነጋግራት እሞክራለሁ። ወዲያው ግን ታስፈራራኛለች። እንዳልለያት ደግሞ ከፍርሃቱም በላይ ፍቅሯ አስቀረኝ።
ስቃዩን እየለመድኩት መጣሁ፡፡ የሆነ ወቅት ድንገት ተነስታ “ለሴቶች የስልክ መልዕክት ትልካለህ’’ ብላ ከሰሰችኝ። በፍጹም ያን እኔ አላደረኩም። ግን አስፈራርታ ይቅርታ እንድጠይቃት አደረገች። ያንን ማድረግ ነበር ደስታ የሚሰጣት። እኔን ማንበርከክ፣ መግረፍ፣ ማሸማቀቅ ነበር የደስታዋ ምንጭ። ሁልጊዜም ስትተኛ የቢራ ጠርሙስ ከጎኗ አድርጋ ነው። ከተነሳባት አናቴን በጠርሙስ ትበረቅሰዋለች። ስቃዩ ሲበዛብኝ መቻልና መላመድ ጀመርኩ። ይህ ይበልጥ አናደዳት።
ጠርሙሱን ትታ በመዶሻ ጀርባዬን ትወግረኝ ጀመር። ከዚያ ደግሞ ቢላ ይዛ በስለቱ ታስፈራራኛለች። በርካታ ጊዜያት ከሞት አፋፍ ነው የተመለስኩት። በፈላ ውኃ ሦስተኛ ደረጃ ቃጠሎ አድርሳብኝ ታውቃለች። ከዚህ ቀጥሎ ልትገድለኝ እንደምትችል እርግጠኛ እየሆንኩ መጣሁ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ለፖሊስ ሪፖርት አላደረኩም። ልጆቼ ላይ የከፋ አደጋ ታደርሳለች ወይም ትበቀለኛለች ብዬ ፈራሁ፡፡ አደጋ አድርሳብኝ ሆስፒታል በወሰደችኝ ቁጥር አደጋውን ራሴ ላይ እንዳደረስኩ እንድናገር ታስፈራራኝ ነበር።
ጎረቤቶቻችን የድረሱልኝ ጥሪዬን ሰምተው መጥተው ያውቃሉ። ሆኖም ፖሊስ ጋር እንዳይደውሉ እየዋሸሁ አሳስታቸው ነበር። በቡጢ ነርታኝ ፊቴ ሲበልዝ ሜካፕ ቀባብታ ታጠፋዋለች።
ከሷ ጋ በነበርኩበት ወቅት በፍርሃትና በምታደርስብኝ የምግብ ቅጣት የተነሳ በድምሩ 30 ኪሎ ቀነስኩ። ሆስፒታል ወሰደችኝ። ከዚህ በኋላ ምግብ ለ10 ቀናት እንኳ በተገቢው ሁኔታ ባልመገብ ልሞት እንደምችል ነገሩኝ።
በ2018 ነገሮች መቋጫ አገኙ። ቤታችን ውስጥ ወለል ላይ አስተኝታ እየደበደበችኝ ነበር። ፖሊስ የደረሰው። የመጣው ይምጣ ብዬ ያደረገችኝን ዘከዘኩ። ፊቴ በላልዞና አባብጦ ነበር።
በዚያ ወቅት ፖሊስ ባይደርስልኝ ኖሮ የሕይወቴ ፍጻሜ ሊሆን ይችል ነበር።ፖሊሱ የሚያየውን ማመን አቃተው።
ያን ሁሉ ታደርግ የነበረው በቅናት ተነሳስታ እንደሆነ ነው የገባኝ። እኔ ከቤተሰቤ ጋር ቅርብ ነበርኩ። ጓደኞቼም ጋር ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ከሁሉም ነገር ቀስ እያለች ነጠለችኝ። የሷ ብቻ አደረገችኝ።
ለነገሩ በአንድ ወቅት አፍ አውጥታ “ሕይወትህን ገሀነም ማድረግ ነው ፍላጎቴ’’ ብላኝ ነበር።
ብዙ ወንዶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሲደርስባቸው ለመናገር አይደፍሩም። ያሳፍራቸዋል። እኔም እንደዚያ ነበርኩ። በየቀኑ “አንተ ደደብ፣ አንተ ደንቆሮ፣ አንተ ፈሪ፣ አንተ ልክስክስ…’’ እያለች ትሰድበኝ ነበር።
ጆርዳና ባደረሰችብኝ ነገር አንድም ጊዜ ተጸጽታ አታውቅም። በጣም ያናደዳት እኔ ለፖሊስ መናገሬና እሷ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ነው። ለፍርድ ቤት ጥፋተኛ እንደሆነች አምናለች። ያን ያደረገችው ግን ፍርድ እንዲቀልላት ብቻ ነው።
የቤት ውስጥ ጥቃት የሚያደርሱ ሴቶች ያን ለምን እንደሚያደርጉ ሳስበው ሱስ መሰለኝ የሚሆንባቸው። ወንድ ጓደኛቸውን ሲያሰቃዩ ልዩ ደስታን ይጎናጸፋሉ። ነገሩ ልክ እንደ ሲጋራ፣ እንደ ኮኬይን ሱስ ነው…
ትልቁ ጥፋት የቤት ውስጥ ጥቃት ከዛሬ ነገ ይቆማል ብሎ ማሰብ ነው። ያ ነው ትልቁ ስህተት። ጆርዳና በመጨረሻ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ፍርድ ቤት ወስኖባታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በሙሀመድ ሁሴን