ከአፍሪካ የሰው ኃይል መካከል መሥራት ከሚችለውና አምራች ከሆነው ከጠቅላላው ህዝቧ ውስጥ 58 በመቶው የሚሆነው የሚተዳደረው በግብርና ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የአህጉሪቱን ከፍተኛ ድርሻ የሚወስዱት ቡርኪናፋሶ፣ ኢትዮጵያ፣ ጊኒ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጀሪያና ሩዋንዳ መሆናቸውን የዓለም የምግብና እና እርሻ ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርገው የሚገልጹት በግብርና ሚኒስቴር የሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና አስተባባሪ አቶ ውብሸት ፍስሃ ናቸው፡፡
“ከበቂ በላይ የሆነ ራስን ለመመገብ የሚያስችል አቅም ያላት አህጉር እንዴት በምግብ ግዥና እርዳታ ላይ ጥገኛ ልትሆን ቻለች?” በማለት የሚጠይቁት አቶ ውብሸት፤ አህጉሪቱ በምግብ ራሷን እንዳትችል እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ዋነኛው ተግዳሮትም የአህጉሪቱ አርሶ አደሮች የሚከተሉት ታዳሽ ባልሆኑ ሰው ሰራሽ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ የሆነ ዘለቄታዊነት የሌለው የአመራረት ዘዴ መሆኑን ጉዳዩን አስመልክቶ ያደረጉት ጥናት ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም
በአመራረቱ ሂደት ከመጠን በላይ በግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውሉት እንደ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ መድሃኒት ዓይነት ኬሚካሎች የአፈር ለምነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዱ ከመሆናቸው ባሻገር በከባቢ አየር ላይ ብክለትን የሚያስከትሉና አጠቃላይ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን የሚያዛቡ ናቸው፡፡ ይህ ችግር ያሳሰባቸው የአፍሪካ መሪዎችም ህዝባቸውን በምግብ ራስ ለማስቻልና ድህነትን ለመቀነስ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት ማሻሻል እንደሚገባቸው ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ በመሆኑም እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2011 ሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴን በግብርና ሥርዓታቸው አካትተው ለመተግበር የሚያስችል ውሳኔ አሳለፉ፡፡
ከመደበኛው ግብርና በምን ይለያል?
የተፈጥሮ ግብርና ተፈጥሯዊ የሆኑ አፈር ለምነት መጠበቂያ ስልቶችንና ለተባይ መከላከያ የሚውሉ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀም የሚተገበር የአመራረት ዘዴ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የተፈጥሮ ግብርና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ ወርቁ እንደሚሉት የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ ከመደበኛው የግብርና ዘዴ የሚለይበት ዋነኛው ምክንያት ከአላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችና ኬሚካሎች ንክኪ የጸዳ መሆኑ ነው፡፡
ግብዓቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የግብርና ስራውን ለማከናወን ጥቅም ላይ የሚውሉት የመስሪያ ቁሳቁሶችም ከአላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችና ኬሚካሎች ንክኪ የፀዱ መሆን አለባቸው፡፡ ስለሆነም የአፈር ለምነት መጠበቂያና የተባይ መከላከያ ግብዓቶችን ለማግኘት አገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም ዋነኛ መለያው ነው፡፡ በተጨማሪም የአርሶ አደሩን ፈጠራዎች፣ ሳይንስ፣ የሥነ ምህዳር ሂደቶችንና የብዝሃ ህይወትን ጥምረትና መስተጋብር የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
አስፈላጊነቱና ፋይዳው
ሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና ዋነኛ ዓላማም የአፈር ለምነትን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችልና በአጠቃላይ አካባቢን ሥነ ምህዳር የማይጎዳ የግብርና ዘዴን በመከተል በአፍሪካ ግብርና ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ነው፡፡ በዚህም የአህጉሪቱ የግብርና ሥራ ዋና ተዋናይ የሆነውንና በአነስተኛ ማሳ ላይ የተሰማራውን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የአህጉሪቱን በምግብ ራስን የመቻል ዋስትና ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተፈጥሮ ግብርና አፈርን ከመሸርሸር በመከላከልና ለምነቱን በመጠበቅና የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ሥነ ምህዳርን ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
ለኢኮኖሚ ዕድገት
በሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ የሚመረቱ ምርቶች ከኬሚካል የጸዱና ተፈጥሯዊ ይዞታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊ ከመሆናቸውም ባሻገር በዋጋ ደረጃም ከመደበኛው ግብርና ምርቶች የበለጠ የሚያስገኙ መሆናቸውን የሚገልጹት ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ምንም እንኳን ዘርፉ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2015 ብቻ ወደ ውጭ ከተላኩ የተፈጥሮ ግብርና ምርቶች 181 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት አገሪቱ በተፈጥሮ ግብርና ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ዕምቅ ኃይል አላት፡፡ በዚህም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘውን የቡና ምርት ጨምሮ፣ ሰሊጥ፣ ማር፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም የተፈጥሮ የግብርና ዘዴን ተከትለው የሚመረቱ ናቸው፡፡ የዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ግብርና የ2018 መረጃም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡
በተገኘው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ግብርና ሊለማ የሚችል 161 ሺ 113 ሄክታር የቡናና 24 ሺ 936 ሄክታር በቅመማ ቅመም ሊለማ የሚችል የእርሻ መሬት አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሁለት መቶ ሺ በላይ አርሶ አደሮችና የግለሰብ አምራቾች፣ 23 አቀናባሪዎችና አርባ ላኪዎች በተፈጥሮ ግብርና ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ዘርፉ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራበት አጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አገሪቱ ካላት ግዙፍ ተፈጥሮ ግብርና ዕምቅ ሀብት አኳያ ማግኘት የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች አለመሆኗን በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወልደሃዋርያት አሰፋ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ ግብርና ሥርዓትን የሚመለከት አዋጅ 488/1998 ከ13 ዓመታት በፊት ጀምሮ የወጣ ቢሆንም አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች ባለመዘጋጀታቸው እስከአሁን ድረስ ወደ ተግባር አልተገባም፡፡ ስለሆነም ደንብና መመሪያዎችን ለማውጣትና አዋጁን ሥራ ላይ በማዋል አገሪቱን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርና ሚኒስቴርና በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር ከግብርና ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡ በዚህም ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት በማሳተፍ የተፈጥሮ ግብርናን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል በሚቻልበት መንገድ ላይ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ አዋጁን የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ በበርካታ ዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች እየተዘጋጁ በየጊዜው ውይይት እየተደረገባቸው ግብዓቶች በመሰብሰብ ላይ ናቸው፡፡
የተፈጥሮ ግብርና ያለበት ነባራዊ ሁኔታ
ሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ መጀመሪያ በስዊድን ማህበረሰብ ከተፈጥሮ ጥበቃ ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ አገሮች ማለትም በኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ናይጀሪያ ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ቀጥሎም በሌላኛው የልማት አጋር በስዊድን ልማት ድርጅት ድጋፍ በሌሎች ሦስት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማለትም ቤኒን፣ ማሊና ሴኔጋል ተተግብሯል፡፡
በኢትዮጵም የግብርና ዘዴው ያለበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ያሉበት ተግዳሮቶች፣ በአግባቡ ቢተገበር ለአገሪቱ የሚኖረው ፋይዳ፣ የዘርፉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች፣ ቀደም ሲል የወጣውን አዋጅ ተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችንና አጠቃላይ የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘጋጀት ሂደት ላይ በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ ጉባኤ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሁሉም በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ስለ ጉዳዩ በሚገባ እንዲያውቅና ህብረተሰቡንም እንዲያሳውቅ በማድረግ በተፈጥሮ ግብርና አተገባበር ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና ቀደም ሲል የወጣውን አዋጅ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡በመሆኑም አዋጁን ለማስተግበር የሚያስችሉ ዝርዝር የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን የማዘጋጀቱ ሂደት በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ አፍሪካ በተለይ በግብርናው ረገድ ታዳሽ ባልሆኑ ሰው ሰራሽ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ የሆነ እና ዘለቄታዊነት የሌለው የአመራረት ዘዴ መከተል ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ ይህ ቢሆንም አሁን አሁን ግን የግብርና ዘዴው ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ብቻ ሳይሆን የአፈር ለምነትን ክፉኛ ከመጉዳት አንፃር እየተኮነነ ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ ምህዳራዊ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴን በግብርና ሥርዓታቸውን አካትተው በመተግበር ውጤታማ የሆኑ አገራት ኢኮኖሚያቸውን በሚገባ ከመደጎም ባለፈ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህን በሚገባ በመተግበር ስኬታማ ስራዎችን ለመስራት በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በመሆኑም የተፈጥሮ ግብርናን የመጠቀም አዋጭነት ለሚመለከተው አርሶ አደር እና በየደረጃው ላሉ የግብርና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ መፍጠር፤ በስራውም ተሰማርቶ ገቢውን የሚያሻሽልበት እና የአፈር ለምነትን የሚጠብቅበትን ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት ስልጠና መስጠት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በይበል ካሳ