አቶ ኡሙድ ኡጁሉ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት ከህዳር 1ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ቀደም ሲል ክልሉን በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ የክልሉን አጠቃላይ ሁኔታ ፣ ለውጡንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ሰፊ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጋምቤላ አሁን ያለው የለውጥ ሂደት ምን ይመስላል?
አቶ ኡሙድ፡- ክልሉ ችግር ውስጥ ስለነበረ እኔ ኃላፊነቱን ከተቀበልኩ በኋላ ቀዳሚ ትኩረቴ የተበላሸውን የጸጥታ መደፍረስ ለማስተካከልና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ መስራት ነበር፡፡ ከሚመለከታቸው የክልል አመራሮችና የክልሉ ሕዝብ ጋር በመሆን በመረባረብ ከሰራን በኋላ ባለፈው ባካሄድነው ጉባኤያችን ውሳኔ መሰረት የአስፈጻሚ አካላት ላይ የአደረጃጀት ለውጥ አድርገናል፡፡
በ3 ወር ግዜ ውስጥ መሰረታዊ የአደረጃጀት ለውጥ አድርገናል፡፡ ለውጥን መጀመርና ማስቀጠል ውስብስብና ከባድ ስራ ነው፡፡ በሦስት ወር ውስጥ ግዙፍ ለውጥ ይመጣል፣ሁሉም ችግሮች በአንዴ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል፡፡ ለውጥ የሚመጣው በሂደት ነው፡፡ አደረጃጀቱን አስተካክለናል፡፡ቀደም ሲል 23 የነበረው የክልሉ አስፈጻሚ አካላት ቁጥር ወደ 18 ዝቅ ተደርጓል፡፡ በእነዚሁ ቢሮዎች ውስጥ ለሚሰሩት አዳዲስና ነባር ሰዎች ሹመት ሰጥተናል፡፡
ብዙ ሰዎች ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ‹‹ለውጥ የለም›› የሚል ጥያቄ ስለሚያነሱ ሁኔታውን እንዲረዱት ተገቢ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ክልላችን የተማረ የሰው ኃይል ችግር የለበትም፡፡ችግሩ ቁርጠኝነት አለመኖር ነው፡፡ ባደረግነው አደረጃጀት ድርጅቱ እንደ ድርጅት ያስቀመጣቸው መመዘኛዎች አሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ለውጥ ማካሄድና ለውጡን በአግባቡ መምራት ካለብን ጠንካራ በሆኑ አመራሮች መያዝ አለበት ብለን ወስነናል፡፡ የመጀመሪያ መመዘኛ የግለሰቡን የትምህርት ዝግጅትና ሙያውን ነው፡፡
በዚህ መሰረት አምስት አመራሮች ከነበሩበት አመራር ወደ ሌሎች ቢሮዎች እንዲሸጋሸጉ አድርገናል፡፡ አምስቱ አመራሮች ደግሞ አፈጻጸማቸው ጥሩ ስለነበረ ወደሌላ ቢሮ ሳይሄዱ የትምህርት ዝግጅታቸው ዲግሪ፣ ማስተርስና ፒኤችዲ ስለነበረ በነበሩበት ቀጥለዋል፡፡
በመጀመሪያ በካቢኔው ውስጥ ያልነበሩ አዲስ የመጡ 8 ሰዎች የትምህርት ዝግጅታቸው ጥሩና ጠንካራ የሆኑትን መልምለን ወደዚህ ሹመት አስገብተን እንዲሰሩ አድርገናል፡፡ ጉባኤውን ካጠናቀቅን በኋላ በተደረገው የመዋቅርና የአደረጃጀት ለውጥ በእኔ እምነት ከ95 በመቶ በላይ ሕዝቡ ደስተኛ ነው፡፡ ከዚህ የቀረውን በተመለከተ የሰውኛ ባህሪ ስለሚታወቅ ያልተደሰተ ሊኖር ይችላል፡፡ ለውጡ ግን በአግባቡ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በስነምግባራቸው ጭምር በአግባቡ የተፈተሹ ሰዎች ናቸው የተመደቡት፡፡ለውጥ ሲባል በአግባቡ ያለመረዳት ችግር አለ፡፡ ሰዎችን በአካል ከቦታው ማንሳት ወይም መቀየር ብቻ ለውጥ ነው ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ በእኔ እምነት ሰዎች ከነበሩበት ቦታ መነሳት ሳይሆን በመሰረታዊነት መለወጥና መቀየር ያለበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ቀደም ሲልም በኃላፊነት ነበርኩ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከነበርኩበት ኃላፊነት ወደሌላ ኃላፊነት ስዛወር በአካል ወደሌላ ቦታ መግባቴን ማየት ሳይሆን የኡሙድ አስተሳሰብ ከለውጡ ጋር ምን ያህል አብሮ ተቀይሯል፣ ተለውጧል የሚለው ነው መፈተሽ ያለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት በክልላችሁ ኃላፊነት የሚመደበው ለብሔሮች ኮታ በመስጠት ነበር፡፡ አሁንም በዛ መልኩ ነው ያለው ?
አቶ ኡሙድ፡- አዎን፡፡ ክልሉ የአምስት (አኝዋ፤ ኑዌር፤ መጃን፤ ኦፖ፤ ኮሞ) ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ነው፡፡ የሀብት ፍትሀዊ ክፍፍል ማድረግም ወሳኝ ነው፡፡ በክልሉ በስብጥር መስራት የግድ ነው፡፡ አንድ ብሔር ብቻ ሁሉንም ነገር ከያዘ ቀድሞ የነበሩት አዝማሚያዎች ይመለሳሉ፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡እኛ ያስተካከልነው እንዳለ ሆኖ በሚደረገው ስብጥር ውስጥ ማነው ብቃትና አቅም ያለው የሚለውን በሚገባ ፈትሸናል፡፡ በዚህ መልኩ የተስተካከለበት ሁኔታ አለ፡፡
የክልሉ ነባር ብሔረሰቦችን ብቻ አይደለም፡፡ከእኛ ጋር የሚሰሩ በአካባቢው የተወለዱም ያልተወለዱም እዛው የቆዩ ሰዎች ካቢኔ ውስጥ ባይገቡም በቢሮዎችና በኤጀንሲዎች በምክትልነት ተሹመዋል፡፡ አቅማቸውና ለክልሉ ያላቸው ቀና አመለካከት ታይቶ ተካተዋል፡፡ ስብጥር የመጠበቁ ጉዳይ ግድ ነው ፡፡ትላልቅ ብሔረሰቦች የሚባሉት አኝዋና ኑዌር በካቢኔ ውስጥ ሰባት ሰባት ወንበር አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎ መዠንገር ስለሆነ 3 የካቢኔ መስሪያ ቤት ይዘዋል፡፡የተቀረው ለኦፖ ለኮሞ አንድ አንድ የካቢኔ ወንበር የተሰጠበት ሁኔታም አለ፡፡ይሄ ተገቢ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት የጋምቤላ ክልል ጸጥታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
አቶ ኡሙድ፡- የክልሉ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ባለፉት ሶስት ወራት ከሌሎች ጋር ስናነጻጽረው ክልላችን በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ይህን ስል ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ከውጭ ጋር ካለው ሁኔታ አንጻር ክልሉ አሁን ስጋት ውስጥ ነው፡፡ አንደኛ ሙርሌ የሚባል ብሔረሰብ በየአመቱ በዚህ ወቅት ክልሉ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታም አለ፡፡ ልጆችና ከብቶች የመዝረፍ ሁኔታ አለ፡፡ የእነዚህ እንቅስቃሴ አሁን አለ፡፡ ባለፈው አንድ ወር ከእኛ ሚሊሻዎች ጋር ተጋጭተው ከእኛ አንድ ከእነሱ ወገን አምስት ሰው ሞቷል፡፡
ሌላውና ትልቁ ጉዳይ ከደቡብ ሱዳን ጋር የተያያዘው ሲሆን ክልሉ ድንበር አካባቢ በመሆኑ በቀላሉ የጦር መሳሪያ የሚገባበት ሁኔታም አለ፡፡ ይሄ አንዱ የእኛ ስጋት ነው፡፡ እነዚህ በዋነኛነት ክልሉ ላይ ችግር ያመጣሉ ተብሎ የሚገመት ስለሆነ ከሚመለከታቸው የጸጥታ ኃይሎች የፌዴራል ፖሊስ የሀገር መከላከያ የእኛም ልዩ ኃይልና ፖሊስ ጋር አብረን እቅድ አውጥተን በተጠንቀቅ ላይ(ስታንድ ባይ) ላይ እንገኛለን፡፡ በተረፈ ይሄ ነው የሚባል ችግር በክልሉ ውስጥ አልተከሰተም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጸጥታውን በተመለከተ በተጨባጭ የተሰራና እንደማሳያ የሚቀርብ ነገር አለ?
አቶ ኡሙድ፡- ብዙ ግዜ በጋምቤላ የሚታወቀው የሁለት ብሔረሰቦች ግጭት ነው፡፡ ባለፈው ሁለት አመት ግጭት ውስጥ አልገቡም፡፡ ሰላም ነው ፡፡በሀብት አጠቃቀም ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ግጭቶች አሉ፡፡ እኛ ይሄ ችግር እንዳይሆን ኃላፊነቱን እንደያዝን ከሁሉም ብሔረሰቦች ጋር ስፋት ያለው ውይይት አካሂደናል፡፡መጀመሪያ ከብሔር ብሔረሰብ ዞን ጀምረን ከዚያም ወደ አኝዋ ብሔረሰብ ዞን ቀጥሎ ወደ መዠንገር ብሔረሰብ ዞን እና ኢታንግ የምትባል ልዩ ወረዳ ብዙ ግዜ ችግሮች የሚከሰቱባት ወረዳ ነች፡፡የሕዝብ ውይይት አድርገናል፡፡ሕዝቡ በውይይቱ ደስተኛ ነው፡፡ እኛም ባደረግናቸው ውይይቶች የእርስ በእርስ ግጭቶች የሚያስነሱ ነገሮች ቢኖሩ በውይይት መፍታት አለብን እንጂ ወንድም ከወንድሙ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት የለበትም በሚለው ሀሳብ ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡
ከተማ ውስጥ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተዘጋጁ መድረኮችም ከአምስት በላይ ውይይቶች አድርገናል፡፡ መጀመሪያ የአለፈው ለውጥ መነሻው ምክንያት ወጣቶችና ሌሎች የክልሉ ሕዝቦች ጥያቄ ሲያቀርቡ ምላሽ በወቅቱ ስለማይሰጥ እስከ ብጥብጥ የተገባበት ሁኔታም ነበር፡፡ያ ምእራፍ ተዘግቷል፡፡ ወጣቱ አሁን በተገኘው ለውጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን በአሁኑ ወቅት በአንድ ግዜ ሁሉንም ነገር ማድረግ ስለማይቻል በእርጋታና በማስተዋል ሁኔታዎችን እንዲያይ በመግለጽ ከእነሱ ጋር ሰፊ ግዜ የወሰደ ውይይት አድርገናል፡፡በሁለተኛ ደረጃ በከተማዋ ከሚገኙት አምስቱ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ጋር በሰፊው ተወያይተናል፡፡ከነጋዴው ሕብረተሰብ፤ ከመንግስት ሠራተኛውና ከሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ብዙ ውይይቶች አካሂደናል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ተደጋጋሚ ሙርሊዎች ድንበራ ችንን ጥሰው የሚገቡት ሰፊ ስለሆነና መቆጣጠር ስለማይቻል ነው ? ልጆች ሰርቀው ከብቶችም እየነዱ ይወስዳሉ፡፡ ቀደም ሲል ተወስደው ከነበሩት ልጆች ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ናቸው የተመለሱት፡፡ አልተገኙም እስቲ ይግለጹልን ?
አቶ ኡሙድ፡- ይሄ በየአመቱ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ድንበር አጠቃላይ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ወደ ደቡብ ሱዳን በቀላሉ መግባትና መውጣት ይቻላል፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው አለመረጋጋትም አንድ ችግር ነው፡፡ ሙርሌ በተፈጥሮው ከቦታ ቦታ ውሃ ፍለጋ ከብቶቹን ይዞ የሚዞር እና ኑሮው በዚህ ላይ የተመሰረተ ማሕበረሰብ ነው፡፡ ከብቶቻቸውን ይዘው ድንበራችንን አልፈው ወደ እኛ ግዛት ይገባሉ፡፡ በተጨማሪም ከክልላችን ልጆችና ከብቶችን ለመውሰድ ይመጣሉ፡፡ ይሄን እንደ ባህልና ልማዳቸው አድርገው የሚወስዱት ስለሆነ ወደ እኛ ግዛት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ክልሉ በአጠቃላይ ድንበሩ ክፍት ስለሆነ ማንም ቢሆን ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በሙርሊዎች ከተወሰዱት ሕጻናት ውስጥ የተወሰኑት ተመልሰ ዋል፡፡ ያልተመለሱ ሕጻናት ጉዳይስ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ?
አቶ ኡሙድ፡- ባለፈው በተፈጠረው ችግር የፌዴራል መንግስት ገብቶበት የመከላከያ ሠራዊታችን በዋናነት እነሱ ግዛት ውስጥ ገብቶ በእነሱው መሪነት የተወሰዱት ልጆች ያመጡበት ሁኔታም አለ፡፡ በእኛ ግምት የቀሩትን ልጆች ወደ ሌላ ቦታ አዛውረው ደብቀዋቸዋል የሚል እምነት አለን፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ቀደም ሲል የሱዳን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ዴቪጆዮ በአሁኑ ሰአት የእዛ ግዛት አስተዳዳሪ ሆኖ ተሹሞ መጥቷል፡፡፡ ያኔ እሱ ነው ከፌዴራል መንግስታችን ጋር ተባብሮ የተወሰዱት ልጆች እንዲመለሱልን ያደረገው፡፡ ከፍተኛ ስራ ነው የሰራው፡፡ አሁን የእሱ ወደዚያ ቦታ በአስተዳዳሪነት መሾም ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በእርግጥ በእዚህ ሶስት ወር ውስጥ ከእሱ ጋር አልተገናኘሁም፡፡ ለመገናኘት ግን ቀጠሮ ይዘናል፡፡ እነዛ የቀሩ ልጆች በመሉ መመለስ አለባቸው፡፡ ይሄ የመንግሰት አቋም ነው፡፡ እሱን ካገኘን በኋላ ይመለሳሉ የሚል እምነት አለን፡፡ በሙርሊዎች ከተወሰዱት ውስጥ በራሳቸው ግዜም ቢሆን ትንሽ በእድሜ የገፉት በዲማ በኩል አድርገው በአለፈው አመት ሰባት ሰዎች ወደ እኛ ገብተዋል፡፡ በቅርብ ቀን እኔ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቴ በፊት አንድ የአስራ አራት አመት ልጅ ተመልሶ ከቤተሰቦቹ ጋር አገናኝተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የክልሉ ሕገ መንግስት ክልሉ የነባሮቹ አምስት ብሔረሰቦች ነው ይላል፡፡ ከዚህ አንጻር ሌሎች በዜግነታቸው በኢትዮጵያዊነታቸው በእዛው ክልል የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተመጣጠነ እኩል አገልግሎት እንዲያገኙ ምን እየተሰራ ነው ? ነባርና መጤ በሚባሉት ብሔረ ሰቦች መካከል ለሚፈጠረው ግጭት መንስኤው ምንድነው ብለው ያምናሉ መፍትሄውስ ?
አቶ ኡሙድ፡- እስከ አሁን በነባርና መጤ መካከል የተፈጠረ ችግር አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምናልባት የዛሬ አስራ ምናምን አመት በ1996 አ/ም አካባቢ የሚታወቀው ተፈጥሮ የነበረው ችግር እሱ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ መጤና ነባሩ ብሔረሰብ የተጋጨበት ግዜ የለም፡፡ 2008 ዓ.ም አካባቢ ስደተኞች ካምፕ የሚሰሩት ሌሎች ብሔረሰቦች ከስደተኞች ጋር ተጋጭተው የሰው ሕይወት ያለፈበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ነባሩና ሌላው ወደ ግጭት ውስጥ የገቡበት ሁኔታ የለም፡፡
ሕገ መንግስቱ የፖለቲካ ስልጣንን በዋናነት ቢያስቀምጥም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለምሳሌ በፐብሊክ ሰርቪሱ አብዛኛው ወይንም ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ በሌሎች ብሔረሰቦች ነው የተያዘው፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦችም እንደ የትምህርት ዝግጅታቸው አብረው ነው የሚሰሩት፡፡ቀደም ሲል የነበረው ተወላጁ ትንሽ ነበር፡፡ አሁን በእኩልነት ሰው በሙያው ስራ እየሰራ ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው በፓርላማ ከጸደቀው የስደተኞች አዋጅ ጋር ተያይዞ የጋምቤላ ነዋሪዎች የዜግነት መብታችንን የሚጋፋና ስደተኞችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤ በአሁኑ ወቅት ከ300 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በጋምቤላ ሰፍረዋል በሚል ቅሬታቸውን ለመንግስት ለማሰማት ሰልፍ እንወጣለን ብለው ነበር፡፡ይሄንን ጉዳይ እንዴት ነው የምታዩት ?
አቶ ኡሙድ፡- ሰልፍ አልተወጣም፡፡ ጥያቄ ግን ቀርቧል፡፡ የስደተኛ ጉዳይን በተመለከተ አንደኛ እንደ ሀገር ስደተኞችን የመቀበል ግዴታ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ የስደተኞችን ህግ ፈራሚ ከሚባሉ ሀገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ጋምቤላ ደግሞ ስደተኞችን ማስተናገድ የጀመረችው ዛሬ አይደለም፡፡ ከደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ የአኛኝያ ትግል ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ሕዝቦች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲያደርሱ እንደነበረ ማንም ያውቃል፡፡ አሁንም ቢሆን በደቡብ ሱዳን ባለው ችግር በአሁኑ ሰዓት በጋምቤላ ሰፍረው የሚገኙት ወደ 420 ሺህ ስደተኞች ናቸው፡፡ የክልሉ ሕዝብ እንግዲህ የአሁን የህዝብ ቆጠራ ባይታወቅም የዛሬ አስር አመት የነበረውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ከወሰድነው ወደ 319 ሺህ ነው፡፡ ይሄ ሲታይ በጣም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የስደተኛው ቁጥር ከክልሉ ሕዝብ በላይ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ምን ሊያስከትል እንደሚችል በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ ከትናንሽ የገበያ ጉዳዮች ጀምሮ እስከ ሌሎች አለመረጋጋት ድረስ በክልሉ ላይ ችግር እንደሚያስከትል ማንም ያውቀዋል፡፡
ባለፈው ስደተኞችን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ በተለይ ክልል ላይ ያለው ወጣት ሲሰማ ተቃውሞ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን በማለት ከተማ አስተዳደሩን ጠይቀው ጉዳዩ እኔም ድረስ ቀርቦ ነበር፡፡ ከእነሱ ጋር ተነጋግረን እንደ ክልል ፌዴራል መንግስት ያወጣውን አዋጅ መሻር አንችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ተቃውሞውን ሆነ ድጋፉን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ መብቱ ነው፡፡ ሆኖም ጥሩ የሚሆነው ይህን ጉዳይ የሚመለከተው አዋጁን ያወጣው የተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ፣ በሁለተኛ ደረጃ ስደተኛውን የሚያስተዳድረው ከስደት ተመላሾች ድርጅት ስለሆነ ፕሮግራም ይዘን ውይይት ብናደርግ ይሻላል የሚል ሀሳብ አቅርበን ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
አዲስ አበባ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን ተብሎ የተሞከረበትም ሁኔታ አለ፡፡ አልተሳካም፡፡ ከተወካዮች ምክር ቤት ሰዎች ወደ እኛ መጥተው መጀመሪያ ከሁሉም አመራር ሁለተኛ ከወጣቱና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአዋጁ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ፕሮግራም ከያዝን በኋላ የማዕከላዊ ኮሚቴና የሰሞኑ የአዲስ አበባው ስብሰባም ስለነበር በእነዚህ ምክንያቶች ነው ውይይቱ ላልተወሰነ ግዜ የተራዘመው፡፡ ከሕዝብ ግን ጥያቄ ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጋምቤላ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር 420 ሺህ ነው፡፡ በቀደመው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት የክልሉ ነዋሪ 320 ሺህ ነው፡፡ከክልሉ ነዋሪ ቁጥር በላይ እጅግ የገዘፈ የስደተኞች ብዛት ስለሆነ በብዙ መልኩ የዜጎችን መብት ይጋፋል፤ያሳጣል የሚሉ አስተያየቶች በርክተዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ ለግዜያዊ ጥቅም ሲባል ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅምንና ግዛትን ጭምር በግዜ ሂደት ታሳቢ ያላደረገ ነው የሚል ብርቱ ትችት በሰፊው ይደመጣል፡፡ ውሎ አድሮ የማንወጣው ትልቅ ሀገራዊ ችግር አይፈጥርም፤ቀውስስ አያስከትልም ይሄን እንዴት ያዩታል?
አቶ ኡሙድ፡- ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ቅድም ያልኩት አንድ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ስደተኛን የማስተናገድ ግዴታ አለባት፡፡ ጋምቤላ የኢትዮጵያ አካል ነው፡፡ እንደ መንግስት ጥሩ የሚሆነው ስደተኞች በጋምቤላ ብቻ አይደለም መስፈር ያለባቸው፡፡ በምናደርገው ውይይት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የተወሰነው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍር መንግስት አቅጣጫ ቢያስቀምጥ ጥሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን የስደተኞቹ የሕዝብ ቁጥር ከክልሉ የሕዝብ ቁጥር ስለሚበዛ ችግር እንደሚመጣ ማንም በቀላሉ የሚገምተው ይሆናል፡፡ የመንግስት ውሳኔ ስለሆነ በመወያየት በመነጋገር በተለይ ወደ አፈጻጸም በምንገባበት ግዜ ሌላ አቅጣጫ ይሰጣል የሚል እምነትም አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ስደተኞቹን እንዴት ነው የምታደራጁዋቸው ?
አቶ ኡሙድ፡- አምስት በጣም ትልልቅ የሆኑ የስደተኞች ካምፖች አሉን፡፡ ከጋምቤላ ከተማ የፉኚዶ ካምፕ በጣም ቅርብ ነው፡፡ወደ አስራ ምናምን ኪሎ ሜትር ጀቤ የሚባል አንድ ካምፕ አለ፡፡ ወደ ኢታንግ መስመር ስንሄድ ኢታንግና አላሬ ኩታ ገጠም የሆኑ ወረዳዎች ናቸው፡፡እዛ መካከል ሁለት ትላልቅ ካምፖች አሉ፡፡ የተርኪዲና ኩሌ ካማፖች ለኢታንግ ከተማ በጣም ቅርብ ነው፡፡ ባለፈው በትንሹ ስደተኛው በራሱ ግዜ ወደ ውጭ ወጥቶ ከማህበረሰቡ ጋር የተጋጨበት ከእኛ ወገን የሰው ሕይወት ያለፈበትም ሁኔታም አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስደተኞች ለምንድነው የጦር መሳሪያ ሳይፈቱ የሚገቡት ፤እንዲህ አይነት ሕግ በአለም ደረጃ የለም፡፡ ከደቡብ ሱዳን የሚመጡት ስደተኞች ከነመሳሪያቸው ነው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚገቡት ነው የሚባለው፡፡ ይሄ እንዴት ይደረጋል ? የእርስዎ መልስ ምንድነው?
አቶ ኡሙድ፡-በእርግጥ ስደተኞች ካምፕ ሲገቡ ያለመሳሪያ መሆኑ ነው የሚታወቀው፡፡ ግን ወታደር የሆኑት መሳሪያቸውን ይዘው ሲገቡ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እነሱ እጅ ሊገባ ይችላል፡፡አብዛኛዎቹ በስደት የሚገቡት ወንዶች ሠራዊት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የኢኮኖሚ ስደተኞች የሆኑት በብዛት ሴቶች ሕጻናት ወጣቶችና ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ከእዛም ሲመጡ እርስ በእርሳቸው ጭምር ስለሚገናኙ አሁን ያለኝ መረጃ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ባልገባም የጦር መሳሪያ በካምፕ ውስጥ አለ ነው የሚባለው፡፡
አዲስ ዘመን ፡-የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞቹን መሳሪያ በተመለከተ በራሱ ግዛት ውስጥ ያለ እስከሆነ ድረስ ለአካባቢው ለዜጎችም ሰላምና ደህንነት ሲል ካምፑን መፈተሽ ትጥቃቸውንስ ማስፈታት አይችልም ?
አቶ ኡሙድ፡-ይሄ የመንግስት ውሳኔ ነው የሚያስፈልገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነዎት፡፡ ክልሉ ራሱ የጸጥታ ኃይል አለው፡፡ የትም አለም ላይ ስደተኛም ሆነ ሌላ ሰው ወደ ሌላ ሀገር ሲገባ በመጀመሪያ መሳሪያ አይይዝም፡፡ አይፈቀድም፡፡ ከያዘም መሳሪያውን ያስረክባል፡፡ ይዞ መቀመጥም ሆነ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ መሳሪያቸውን ልታስፈቱ ለምን አልቻላችሁም ?
አቶ ኡሙድ፡- ስደተኛን ማስፈታት አትችልም፡፡ እንዴት ትችላለህ ? መሳሪያ ሌላ ነዋሪ እጅ ከገባ ወስነን ትጥቁን ማስፈታት እንችላለን፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ትጥቅ ማስፈታት በክልላችን አካሂደናል፡፡ አሁንም የሚደረግ አለ፡፡ በሕገወጥ መንገድ መሳሪያ ስለሚገባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ስደተኞች የተወሰነ ቦታ ተከልሎላቸው ሕጋዊ ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው፡፡በስደተኛ በመርህ ደረጃ በአንድ ሀገር ውስጥ ገብቶ መሳሪያውን እንደያዘ እንደታጠቀ ሊቀመጥ አይችልም፡፡የሀገራችን ሕግም አይፈቅድም፡፡ሕገ ወጥ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?
አቶ ኡሙድ፡- ልክ ነው፡፡ ግን በእኛ ክልል ውስጥ ቢገኙም የስደተኞቹን ጉዳይ በቀጥታ ይዞ የሚከታተለው ቁጥጥር የሚያደርገው የፌዴራል መንግስት ስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ኮሚሽን ስላለ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ትጥቅ የያዙ ስደተኞችን ትጥቅ የማስፈታቱን ጉዳይ ከመከላከያ ጋር ተነጋግሮ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለሁሉም በእኛ በኩል ጥያቄ አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጋምቤላ ክልል ሰፊ ለም መሬት አለው፡፡ ለኢንቨስትመንት የሰጠና የተመቸ ነው፡፡ በብዛት የመሬት ዘረፋና ቅርምት እንደተካሄደ ይታወቃል፡፡ቢገልጹልን ?
አቶ ኡሙድ፡- ቀደም ሲል እኔ በኃላፊነት ከመምጣቴ በፊት የተደረገ ጥናት አለ፡፡ በክልሉ ለኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱትን በተመለከተ፡፡ ሶስት ምድብ አለው፡፡ በአግባቡ ስራ እየሰሩ ያሉ ስራቸውን እንዲቀጥሉ፤ መሀል ላይ የሆኑትና አፈጻጸማቸው በ‹‹ቢ›› ደረጃ በ‹‹ሲ›› ደረጃ ላይ ያሉትን ድጋፍ በመስጠት ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ማበረታታት ከዛ በታች የሆኑት ደግሞ ተለይተው መንግስት የራሱን ውሳኔ ይሰጥበታል ማለት ነው፡፡ያ ውሳኔ ማለት መሬት መንጠቅ ነው፡፡ ሌላ ነገር የለም፡፡ በዚያ ጥናት ውጤት መሰረት እስከአሁን በአግባቡ ወደ ስራ የተመለሱ አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ጋምቤላ ከተማ ላይ ውይይት አድርጌአለሁ፡፡ሙሉ በሙሉ ባይገኙም፡፡ ጠርተናቸው የመጡ ወደ ስራ የገቡ አሉ፡፡ ያደረግነውን ውይይት ሲሰሙ ወደ ስራ እንገባለን ብለው ያሉም አሉ፡፡ በአጠቃላይ የጠፉም አሉ፡፡ የእነሱ መሬት ይነጠቅ አይነጠቅ የሚል ገና ውሳኔ አልወሰንንም፡፡ ግን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ያንን መሬት ለሌላ ባለሀብት ወይንም ኢንቨስትመንት ስለምንፈልገው ነው፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው ይሄንን ይመስላል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ሙስና ምዝበራ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ችግር በጋምቤላ ክልል የተንሰራፋ እንደነበረ ይገለጻል፡፡አመራር ላይ ከመጡ ሦስት ወር ብቻ ያስቆጠሩ ቢሆንም አጠቃላይ ሁኔታውን እንዴት ያዩታል ?
አቶ ኡሙድ፡- የብልሹ አሰራርና የሙስና ጉዳይ አይደለም በጋምቤላ በአለም ላይ አለ፡፡ ችግሩ ይሄንን ለመቆጣጠር የሚዘረጋው አሰራር ጠንካራ ከሆነ ይቀንሳል ወይንም ሊጠፋ ይችላል፡፡ጠንካራ ካልሆነ በከፋ ሁኔታ ይንሰራፋል፡፡ በክልሉ በዋናነት የኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጡ ከዚህ ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ ያለ ነው፡፡ አንዱ ክልሉ የሚታወቀው በእሱ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደር ውስጥ ያለው የመሬት አስተዳደርና አሰጣጥ በተመሳሳይ ችግር እንደነበረበት የሚታወቅ ነው፡፡፡ በክልሉ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል እንደሚታየው ብልሹ አሰራሮች ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አመራር ከመጡ ወዲህ ምን እርምጃ ወሰዳችሁ ?
አቶ ኡሙድ፡- እኔ ወደ አመራር ከመጣሁ ወዲህ የወሰድኩት እርምጃ የለም፡፡ በፈት ተከሰው የተፈረደባቸው፤ የተባረሩም ፤የተለያየ እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ፡፡ ይሄ ከእኔ በፊት ነው፡፡ በዚህ ሶስት ወር ግዜ ውስጥ ዋነኛ ስራችን አድርገን የወሰድነው የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማረጋጋት ስራ ነው፡፡ ትልቁን የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ ወደ ጎን አድርገህ የማረጋጋት ስራ ሳትሰራ ወደሌላ ስራ መግባት የበለጠ ውስብስብ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ ችግሩ ስለሚታወቅ መጀመሪያ ይሄንን አስተካክለን ሌላውን በሂደት የምንገባበት ስራ ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መነሻቸውን ደቡብ ሱዳን ያደረጉ ታጣቂዎች ጋምቤላ ውስጥ በስውር ይንቀሳቀሳሉ የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን ሀሳብ ቢገልጹልን ?
አቶ ኡሙድ፡- ቀድም ብዬ ተናግሬአለሁ፡፡ ሙርሌ የሚባል በቀላሉ ይገባል፡፡ ሕዝባችንንም ድንበራችንንም የመከላከል ኃላፊነት ስላለብን ሰሞኑን በአዲስ መልኩ ከመከላከያ ሠራዊት የተመደቡ አሉ፡፡ እነሱም የጸጥታ ቀጣናዎቹን እንዲጎበኙ አድርገናል፡፡ ሌላው ወታደሩ ሁሉም ቦታ ላይ መድረስ ስለማይችል እኛም በራሳችን ያሰለጠንናቸው የክልሉ ሚሊሺያዎች፤ የክልሉ የፖሊስ ኃይልም አለ፡፡ መደበኛ ፖሊስ ድንበር መጠበቅ ባይችልም በእነዚህ አማካኝነት እንደገናም ችግሩ የሚከሰት ከሆነ በምናቀርበው ጥያቄ ሁሉም አካባቢ በተጠንቀቅ (ስታንድባይ) ጥበቃ እያደረገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን አጋር ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጋችሁት ውይይት የተገለጸ ነገር አለ፡፡ ወደ አንድ ፓርቲነት የመምጣቱን ነገር እንዴት ነው የምታዩት ?
አቶ ኡሙድ፡- ቀደም ሲል ስናቀርበው የነበረ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ምላሽ ሲያገኝ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሰማችሁት በአንድ ሀገር ውስጥ ሆነን የተናጠል ውሳኔ ሲወሰንብን ነበር፡፡ ለምሳሌ አጋር ተብለው የሚታወቁ አራት ድርጅቶች አሉ፡፡ ኢህአዴግ የሚባሉ አራት አሉ፡፡ በአብዛኛው የሀገሪቱን ጉዳዮች ኢሕአዴግ ነበር የሚወስነው፡፡ አጋር ድርጅቶች በክልላቸው ጉዳይ የሚወስኑበት ሁኔታ አለ፡፡ በእርግጥ ኢሕአዴግ በሁሉም መልኩ ለእኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ አሁን የክልል ፓርቲ አይኖርም ተብሎ ሲወሰን አንደኛ የእኛ ጥያቄ መልስ ያገኘበት ሁኔታም አለ፡፡ ሁለተኛው ዋናውና ትልቁ ነገር እንደ ሀገር ልጆች በሀገራዊ ጉዳይ የመወሰን እድል የምናገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ሲታይ በጣም የሚያስደስት ውሳኔ እንደሆነ ነው እኔ የምወስደው፡፡
አዲስ ዘመን ፡-ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን
አቶ ኡሙድ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በወንድወሰን መኮንን